አርሴማ ሰመዐት አርሜንያ (ይጫኑ)

Post date: Oct 28, 2013 1:53:15 PM

መቅድም ዘተነግረ በእንተ አርሴማ ቅድስት፤

ስለቅድስት አርሴማ አስቀድሞ የተነገረ ነው።

አባቶችና ወንድሞች ሆይ ስለ ቅድስትና ስለብጽዕት ክብርና ልዕልና፤ መልካም ዜናን አንነግራችሁ ዘንድ በጸጥታ ስሙን በማስተዋልም አድምጡን፤ ይህችውም ብጽዕት ሰማዕት አርሴማ ናት፡

ለቅድስት አርሴማ ክብር ይገባታል። ትውልድና ፍጥረት ሁሉ ያደንቋታል ስለመከራዋ ስለሥቃይዋ ብዛት በሰማያት ያለች እህታችን ይሏታል።ይህችዉም ብጽዕት አርሴማ እግዚአብሔርን የምትፈራ ናት፡ በቅዱሳን ሰማዕት ማህበርና በገነት ባሉ ፍጥረታት ሁሉ ዘንድ ፈጽማ ትመሰገናለች፡፡ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን እግዚአብሔር ወዳጆቹን በችግር ይፈትናቸዋል፡ ይህንንም ቃል ለመፈጸም ቅድስት አርሴማ የመከራውን ሸክምና የእሳቱን ዋዕይ ታገሰች። ሰለዚህም መንግግሥተ ሰማያትን ወረሰች። ስለቅድስት አርሴማ ብሎ ቁራሽ እንጀራና ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ የሚሰጥ ብጹዕ ነው ዋጋው አይጠፋበትም። (ማቴ 10፤42)

አርሴማ ማለት ምን ማለት ነው?አርሴማ ማናት?

አርሴማ ማለት በወርቅ ልብሶች የተጎናጸፈችና የተሸለመች፤ መልከመልካም፤ ዉብ ማለት ነው፡፡

አርሴማ ማናት?

እንኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሌን ተሸክሞ ይከተለኝ፤...ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ፍሱንም ቢያጎድል ምን ይተቅመዋል?ተብሎ የተነገረውን የክርስቶስ ወንጌል ተከትላ፡ ዘመድ አዝማዶቿን ትታ፤ጌታን የተከተለች፤

በሮምና በአርማንያ ገዥዎች የነበሩ ሁለት ከህዲያን ነገሥታት ዲዮቅልጥያኖስንና ድርጣድስን፤ በሃይማኖቷ ጸንታ ድል ያደረግች፤የሮም ወታደሮች የሚያደርሱባት መከራና ግፍ፤ አስራትና ግርፋት ያልበገራት መላ ሕይወታቸውን ለእሳትና ለስለት ከሰጡት ከ27ቱ ቅዱሳት ደናግል አንዷ ሰማዕት ናት።

ዜና ልደታ ለቅድስት አርሴማ፤

ዜና ሕይወታ ለቅድስት አርሴማ፤

ዜና ሞታ ለቅድስት አርሴማ፡

ዜና ልደታ ለቅድስት አርሴማ፤

የቅድስት አርሴማ የትውልድ ሀረግ እንደሚከተለው ነው፡ አባቷ ከነገሥታት ወገን የሆነ ስሙ ቴዎድሮስ ይባል ነበር፡ አናቷ ደግሞ ከቤተ ክህነት ከካህናት ወገን የምትሆን ልዕልትና ክብርት የሆነች አትኖስያና ትባል ነበር፡እነርሱም እግዚአብሐርን የሚፈሩ ደጋግና ጻድቃን ነበሩ፡፡ (ሉቃ1፤6) ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም፤ አስከ እርጅናቸውም ድረስ መካን ነበሩ። (1ኛ ሳሙ1፤3)

ሰለዚህ አትኖስያና በብዙ ታለቅስ ነበር፤ ክርስቶስ ሆይ መልካም ፍሬ፤ ወንድ ልጅ ወይም ሴት ልጅ ስጠኝ፤ እያለች ዘወትር ወደግዚአብሔር ትጸልይ ነበር፡ እግዚአብሔርም የቅድስት አትኖስያናን ብዙ ልቅሶዋንና ኃዘኗን ሰምቶ መልኳ ያማረ፤ ግርምዋ የምታስፈራ፤ ልጅን ሰጣት፡ እርሷም ቅድስት አርሴማ ናት፡፤ሦስት ዓመት አስከሚሆናት ድረስ ከቤቷ አሳደገቻት፡ ከዚያ በኋላም በሃይማኖት ጸንታ፤ በሥነ-ምግባር ታንጻ ታድግ ዘንድ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም ለተሰራች ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንድትሆን ሰጠቻት።

ዜና ሕይወታ ለቅድስት አርሴማ፤

ይህንን ዓለም በመናቅ ክርስቶስን ከተከትሉት ቅዱሳት ደናግል አንዷ ቅድስት አርሴማ ናት፡ ይቺ ያማረችና የተወደደች ብላቴና አሥራ አምስት ዓመት ሲሆናት እናት አባቷ ለትዳር አጯት፡ አርሷ ግን ይህንን ዓለም ንቃ ክርስቶስን በድንግልና ታከተለች፡ በዚያን ጊዜ ከሀዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በሰይጣን አነሳሽነት ተገፋፍቶ በሀገሩ ላይ በመልኳና በደም ግባቷ እጅግ ያማረች ሴት እንድፈልጉለት፤አዋጅ ነገረ።በሰሌዳም መልኳንና ቅርጿን ሁሉ ስለው ያመጡለት ዘንድ ሠዐሊዎችን አዘዘ፡ ሰዐሊዎችም ሀገር ለሀገር እየተዘዋወሩ ሲፈልጉ በሮሜ ሀገር የደናግል ገዳም በመልኳ እጅግ የተዋበችቅድስት አርሴማን አግኝተው ሥዕሏን ስለው ለንጉሡ ሰደዱለት፡ እርሷን ለማግባት የሚፈለገውን ሁሉ አደረገ።

“በአንዲቱ ከተማ መከራ ቢያጸኑባችሁ ወደሌላይቱ ሽሹ”(ማቴ10፤23)

ቅድስት አርሴማም “በአንዲቱ ከተማ መከራ ቢያጸኑባችሁ ወደሌላይቱ ከተማ ሽሹ” ተብሎ የተጻፈውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ከዚህ ሰይጣናዊ ድርጊት ለመዳን ትችል ዘንድ ወደንጉሥ ድርጣድስ የግዛት አገር ወደአርማንያ ሄደች ከሰባ አምስት ወንዶችና ከሠላሳ ዘጠኝ ደናግል ሴቶች ጋር በምድረ በዳ ዋሻ ፈጣሪዋን እየለመነች ተቀመጡ፡ንጉሡም ብዙዎችንም ክርስቲያኖች ለጣዖት ካልሰገዳችሁ ጣዖት ካላመለካችሁ አያለ ይገርፋቸው ወደእስርቤት እያስገባ ያስራቸው፤ ብዙ መከራና ሥቃይ ያደርስባቸው ነበር። (ዳን 3፡1-12) ቅድስት አርሴማ ግን ከሀዲው ንጉሥ ድርጣድስ በሚፈጽመው ግፍ እያዘነች ያለምንም ፍርሀት ትገሥጸው ነበር ቅዱሳን ሰማዕትንም ከገድላችሁ ብዛት የተነሳ የማይጠፋ የብርሃን አክሊል ተዘጋግቶላችኋልና ሰላም ለእናንተ ይሁን እያለች ታጽናናቸው ነበር::

ከሀገረ አርማንያ ጋራ ያለን የሃይማኖት ግንኙነት

አምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት /Orental Churches/ማለትም ኢትዮጵያ፤ ግብጽ፤ ህንድ፤በአሁኑ ሰዓት የሰው ልጅ ደም እንደ በረዶ የሚወርድባት ሶርያ፤ ሲሆኑ አምስተኛዋ የሰማዕቷየቅድስት አርሴማ ሀገር አርማንያ ናት።

ሁለተኛ

ያንጊዜ ካቶሊኮችና ሌሎች የመሳሰሉት የኃይማኖት ልዩነት ፈጥረው ተገንጥለው ሰሄዱ አንድ ወልድ ዋህድ፤ አንዲት ሃይማኖት ብላ በማመን በ318 ሊቃውንት ጉባዔና ድንጋጌ የጸናች አንዷ የክርስትና ሀገር ናት፡ ጆግራፋዊ አቀማመጧን በተመለከተ በመካከለኛው ምስራቅ በእስያ ውስጥ የምትገኝ ትንሽ ሀገር ናት።

በሌላ መልኩ ሁለተኛው ቀስት እንደሚያመለክተው በኖኅ ዘመን የጥፋት ውሃ መሬትን ባጥለቀለቃት ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን አምሳልና መርገፍ የሆነችው የኖህ መርከብ በሰባተኛው ወር ያረፈችበት ታሪካዊና አስደናቂው /mount Ararat /አራራት የሚባለው ተራራ በዚሁ በአርማንያ ይገኛል።(ዘፍ 8፤5)

ቅድስት አርሴማ መንግሥተ ሰማያትን መረጠች

ቅድስት አርሴማ ቀደም ሲል ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስን አላገባም ብላ ወደአርማንያ ከተሰደደችም በኋላ ተመሳሳይ ፈተና አልቀረላትም ጣዖት አምላኪው ንጉሥ ድርጣድስን እንድታገባ ብዙ የፈተና ጥያቄ ቀረበላት፡ ነግር ግን ቅድስት አርሴማ ከዚህ ዓለም ብልጭልጭነት የማያልፈውን ዓለም መረጠች። ይህም ብቻ አይደለም ብጽዕትና ቅድስት አርሴማ ከርጉም ከድርጣድስ ጠላት እጅና ከወንጀለኞች፤ከመናፍቃን ያድናት ዘንድ በስግደት፤ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር እንባዋን ታፈስ ነበር።ለዘላለሙ በመንግሥተ ሰማያት እኖር ዘንድ አቤቱ አንተ በመስቀልህ ርዳኝ፡ በሰይፍና በቢለዋ የሥጋዬ መለያያ በየክፍሉ ቢቆረጥ ሥጋዬ አያሳዝነኝምና የዚህን አላፊና ጠፊ ዓለም፤ ንብረትም ንቄ ትቸዋለሁ ትል ነበር (ማቴ 16፤24-27)

ሥጋችሁን የሚገሏችሁን አትፍሯቸው

በሰማያት ያለውን ሞት እንጂ በምድር ያለውን ሞት አልፈራም እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ ሥጋችሁን የሚገሏችሁን አትፍሯቸው ነፍስን ከሥጋ ለይቶ በገሃነም የሚቀጣውን ፍሩ እንጅ (ማቴ10፤28) ያንጊዜም ንጉሥ ድርጣድስ በአደባባዩ የቆሙትን ወታደሮች በኃይላቸው የብጽዕት አርሴማን እጆች ስበው ወደአዳራሹ እንዲያስገቧት አዘዘ፡ ቅድስት አርሴማም ወደነገሥታትና ወደመኳንንት አደባባይ በሚወስዷችሁ ጊዜ ምን እንናገራለን ብላችሁ እትጨነቁ ብለህ በወንጌል ለቅዱሳኖችህ የገባህውን ቃል አስብ፡ ከነዚህ ኃይለኞች ከሃዲዎች እጅ አድነኝ በመስቀልህ አጥር እጠረኝ፤እያለች በራሷ አመድ ነስንሳ ብዙ ስግደቶችን ሰገደች። ምድርም እስከምትንቀጠቐጥ ድረስ ንጉሡንና ወታደሮችን ያጠፏቸው ዘንድ በታላቅ ግርማ የእግዚአብሔር መላእክት ሚካኤልና ገብርኤል ወርዱላት እርሷ ግን ነፍስ እንዳይጠፋ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች።

አንበሶቹና ጅቦቹ ከሰማዕት እግር በታች ሰገዱ

ንጉሥ ድርጣድስም አርሴማን ባያት ጊዜ በመዓትና በቁጣ ዛሬ ያሸነፍሽን አይምሰልሽ ነገ ብዙ በሆኑ አማልክቶቼ ድል አደርግሻለሁ አላት።የንጉሥ ድርጣድስ ወታድሮች ቅዱሳን ክርስቲያኖችን የኋሊት አስረው ወደአውሬዎች ጉድጓድ ጣሏቸው፡

ቅድስት አርሴማን ግን በጠንካራ ማሰሪያ አስረው በረጅም ተራራ ላይ ሁንኔታውን ታይ ዘንድ አስቀመጧት አንብሶቹና ጅቦቹ ግን ከቅዱሳን ሰማዕት እግር በታች ይሰግዱ የእግራቸውን ትቢያ ይልሱ፤ከጫማቸው ሥር ይተኙ፤ የቅዱሳኑን መዓዛም ያሸቱ ነበር። (ዳን 3፤19-28) ያን ጊዜም ቅድስት አርሴማን አፏን ይጸፏት ዘንድ አዘዘ ከወታደሮቹ አንዱ ተንስቶ አፏን መታት ከከንፈሮቿና ከአፍንጫዋ ብዙ ደም ፈሰሰ፡ የፈሰሰው ደምም ከራሷ እስከ እግር ጠጉሯ ድረስ ተንጠባጠበ። ከዚህም የተነሳ ቅዱሳን ሰማዕታት በኪዳንሽ የተማሰጸነ፤ ገድልሽን ያጻፈያናበበ፤ በስም ሽችግረኞችን ያጠገበ፤የተራቆቱትን ያለበሰ፤ የተጠሙትን ያጠጣ፤በጸሎትና በስግደት ራሱን ያዘነበለ፤ካንቺ ጋራ ወደመንግሥተ ሰማያት ይገባል። (ማቴ 10፤42) እያሉ የቅድስት አርሴማን ክብር ይመሰክሩ ነበር።

ንጉሥ ድርጣድስ የእሳት ነበልባል አስነደደ፡

በዚህም አላቆመም ንጉሥ ድርጣድስ ድምጹ እንደ ክረምት ነጎድጓድ እንደ መብረቅ የሚሰማ የእሳት ነበልባል አስነድዶ ቅዱሳን ሰማዕታትንና ቅድስት አርሴማን ወደ እሳቱ እንዲጥሏቸው ወታደሮቹን አዘዘ፡፡ነገር ግን ቅድስት አርሴማ በሰማዕትነት ለመሞት ቆርጣ የተነሳችበት ዓላማ ነውና ገና ጭፍሮቹ ሳይነኳት ከሌሎቹ ሰማዕታት አስቀድማ እጆቿን ዘርግታ ወደሚነደው እሳት ሮጣ ራሷን ወረወረች እንደ እቶን የሚነደውን እሳት ክብር ይግባውና አምላክ እንደ ውኃ አቀዘቀዘው (ዳን 3፤23-26) ንጉሥ ድርጣድስ በዚህ አልተመለሰም ከእሳት የወጡትን ሰማዕታት እንደገና ወደእሥር ቤት አስገባቸው፡ በእሥር ቤት እየተጋደሉ ሳሉ ለ27ቱ ሰማዕታት 27 አክሊሎች ወረዱላቸው (1ኛጢሞ 4፤8) እነዚህን የብርሃን አክልሎችን ያየ ጣዖት አምላኪ የነበረ የእሥር ቤቱ ጠባቂ የተደረገውን ተአምር አይቶ በክርስቶስ አመነ ክብር ምስጋና ለፈጣሪ ይሁን።ዳግመናም ንጉሡ ቅድስት አርሴማን የትዳር ጓደኛ ብትሆኝኝ መንግሥስቴንና ግዛቴን አሰጥሻለሁ አላት (ማቴ14፤7) እርሷ ግን ይህን ሁሉ አልወደደችም ነገር ግን ወርቅን እንደአመድ፤በንጉሡ ቤት መብላት መጠጣትን እንደ እሬት ቆጠረች እንጅ፤

27 የሚሆኑ ክርስቲያኖች ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡

አያይዘውም በሀገረ አርማንያ ከቅድስት አርሴማ ጋራ በእሥር ቤት በመታሠር፤ ወደ እሳት በመጣል ለብዙ ጊዜያት ሲሰቃዩ የነበሩትን ቁጥራቸው 27 የሚሆኑ ሰማዕታት በንጉሥ ድርጣድስ ትእዛዝ የሮማ ወታድሮች አስረው በአለንጋ እየገረፉ በሰይፍ አንገታቸውን እየቀሉ ገደሏቸው፡ እነርሱም እንደነቅዱስ ጊዮርጊስ እንደነቅዱስ ቂርቆስ በተጋድሎ በክብር፤ በጸጋ ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡በሃይማኖት በተጋድሎ ስታጽናናቸው የነበረች ቅድስት አርሴማም የእምነት ጋደኞቿ መራራ ሞትን ከተቀበሉ በኋላ እርሷም የሰማዕትነትን ጽዋ ትቀምስ ዘንድ ወደምስራቅ ፊቷን ዞራ በትዕምርተ መስቀል ፊቷን እያማተበች ጸሎት ጀመረች፡ የሞት ጽዋን በእጆቿ ይዛ በዓይኖቿ የተከፈተ ሰማይን እያየች አብዝታ ጸለየች።

ቅድስት አርሴማም ቃል ኪዳንን ተቀበለች

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋራ ወርዶ ቅድስት አርሴማ ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ስለኔ ፍቅር ይህንን ዓለምና ከሀዲውን ንጉሥ ድል ነስተሽዋልና ምን አደርግልሽ ዘንድ ትወጃለሽ አላት።ቅድስት አርሴማም መታሰቢያየን ያደረገውን፤ ስሜን የጠራውን፤ ቤተ ክርስቲያን በስሜ ያሰራውን፤ ሁሉ መልካም ዋጋውን ክፈልልኝ አለችው ጌታም ይህንን ሁሉ ያደረገውን በመንግሥተ ሰማያት ዋጋውን እከፍለዋለሁ ብሎ ቃል ኪዳኑን አጸናላት። (ማቴ10፤42)

ዜና ሞታ ለቅድስት አርሴማ

ይህ ሁሉ ገድልና ተአምራት ከተፈጸመ በኋላ ቅድስት አርሴማ እነዚያን የሮማ ወታደሮች እንግዲህ የታዘዛችሁትን ፈጽሙ አለቻቸው ወገቧን ታጥቃ፤ ልብሷን በትእምርተ መስቀል አምሳል ለብሳ፤ እንገቷን ከፍ አድርጋ ለሰይፍ አመቻቸች። እነርሱም ወዳንቺ መቅረብና አንገትሽን መቁረጥ አልቻልንም፡ በግንባርሽ ላይ ያለው የተሳለው ትዕምርተ መስቀል አስፈርቶናልና ግንባርሽን ሸፍኝልን አሏት፡ የምሸፈንበት ቁራጭ ልብስ ስጡኝ አለችና ወታደሮቹ በሰጧት ቁራጭ ልብስ ራሷን ተሸፈነች፡

ቅድስት አርሴማ የክብር አክሊልን ከፈጣሪዋ ተቀበለች

ከአንገቷ ደም፤ውኃ; ወተት; እንደክረምት ውኃ መነጨ ይህውም መስከረም 29 ቀን ሰማዕትነትን የተቀብለችበት በዓለ ዕረፍቷ ነው፡፡

በዚያ ንጉሡ ድርጣድስና ሰራዊቱ እየተመለከቱ የቅድስት አርሴማ አንገት ለሁለት ተቆረጠ ከዚያ ያሉ ሕዝቦች አስከሚያደንቁ ድረስ ራሷም ለብቻው ሦስት ሰዓት ያህል ቆመ ክብር ለፈጣሪ ይሁን።ከአንገቷ ደም፤ውሃ፤ ወተት፤ እንደክረምት ውሃ መነጨ ከዚያም በኋላ ብሩህ ደመና ወርዶ ጋረዳት ወደሰማይ እንደመብረቅ ሳባት፤ንጽሕት ነፍስ ሆይ ደስ ይበልሽ እያሉ የመላእክት ማህበር ሁሉ ነፍሷን በክብር፤በእልልታ በዝማሬ አሳረጉ፡ ሃሌ ሉያ እያሉ ወደሰማያዊት ኢየሩሳሌም አስገቧት። በመንግሥተ ሰማያትም የክብር አክሊልን ተቀበለች፡፡ይህውም በታኅሣሥ ስድስት ቀን የቅድስት አርሴማ ቅዳሴ ቤቷ የሚከበርበት፤ የሃያ ሰባቱ ቅዱሳን ሰማዕት መታሰቢያቸው ነው፡፡

የቅድስቲቱ የአርሴማን ስም በከንቱ አትጥራ

በመጽሐፍ የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ ተብሎ እንደተጻፈ እንደዚሁም የቅዱሳንንም ስም በከንቱ ማጉደፍ ፈጽሞ ትልቅ ኃጢአት

ነው፡ በተለይም በለንደን ከተማ የሚኖሩ አንዳንድ ተመጻዳቂዎች ሳይበቁ በቅተናል፤ ሕልም አየን፤ ቅድስት አርሴማ ተገልጻ አነጋግራናለች፤ ከእከሌ ጋራ የትዳር ጓደኛ መስርቺ መስርት ብላናለች እያሉ መማለጃ እየተቀበሉ፤እያቀበሉ እግዚአብሔር በመልኩና በአርአያው የፈጠረውን ሰው መሸንገል፤ የሰማዕቷንም ስም መመጻደቂያ ማድረግ ፍጹም ክህደት ነው፡ ለመሆኑ እርሷ ራሷ ከላይ የታሪኳን አመጣጥ እንደተመለከትነው ሁለት ነገሥታት ለጋብቻ ቢለምኗት ዓለም በቃኝ ብላ በስማዕትነት ያረፈች ቅድስት እናት ናት። እንዴት ስለጋብቻ በሕልም እየተገለጸች ከለንደን ድረስ ሰውን ለትዳር ትጋብዛለች? ይህ ፍጹም ሐሰት ነው።

ማጠቃለያ

v የድኅነትና የበረከት ልጅ ብጽዕት አርሴማ ሆይ፤

v የይቅርታ የምሕረት ልጅ ብጽዕት አርሴማ ሆይ፤

v የክብርና የልዕልና ልጅ ብጽዕት አርሴማ ሆይ፤

v የጽድቅና የሕይወት ልጅ ብጽዕት አርሴማ ሆይ፤

v የክብርና የምስጋና ልጅ ብጽዕት አርሴማ ሆይ፤

v የደስታና የኃሴት ልጅ ብጽዕት አርሴማ ሆይ፤

v የፆምና የጸሎት ልጅ ብጽዕት አርሴማ ሆይ፤

ዛሬ በዚች ቦታ የተሰበሰብነውን ዘወትር ጠብቂን የሞት መቅሰፍትን ከኛ ላይ አርቂልን፤ የበደልና የኃጢአት ጨለማ ከእኛ ይወገድ።የቅድስትና የብጽዕት አርሴማ በረከት በዚህ ከተሰበሰብነው ከሁላችን ክርስቲያኖች ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መስከረም 26 ቀን 2006 ዓ.ም

መ/ር ሔኖክ ቸሩ

ምንጭ

1.የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ፤

2.የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ን መጽሐፈ ስንክሳር ግዕዝ፤

3.ገድለ-ቅድስት አርሴማ ግዕዝና አማርኛ

1985 ዓ.ም አዲስ አበባ፤