Post date: Jan 19, 2016 11:40:17 AM
በዓለ ልደት ትኤምሐክሙ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት…(1ኛጴጥ5፤14)…
የለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስቲያን እንኳን ለጌታችን ለመድኅኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ በማለት ለመላው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታዮች ምዕመናን የምስራች ታበስራለች፤ ነአምን ክልዔተ ልደታተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ልደትን ታምናለች፡ ታስተምራለች፡፡ቀዳማዊ ልደት ተአውቀ በደሃራዊ ልደት ቀዳማዊ ልደት ማለት ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ከአብ ያለ እናት መወለዱን፤ ደኃራዊ ልደት ማለት ደግሞ አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ከቅደስት ድንግል ማርያም ያለ አባት መወለዱን የሚያስረዳ ምሥጢር ነው።
ወለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመዝ ውእቱ ልደቱ.(.ማቴ 1፤18 ) ወንጌላዊ የጌታ ልደቱ እንዲህ ነው አለ….ብዙ ልደት አለና ከዚያ ለይቶ፤ልደተ አዳም እምድር ማለት የአዳም ልደት ከመሬት፤ ልደተ-ሔዋን እምገቦ የሔዋን ልደት ከአዳም ጎን ሲሆን የጌታ ልደት ግን ከነዚህ ሁሉ የተለየ መርግርመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ፤ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን የሚያድል፤የሰው ልጆች ተስፋ የተፈጸመበት፤የኃጢአት ማሰሪያ የተቆረጠበት፤ጨለማ የተገፈፈበት ብርሃን የሰረቀበት፤እርቅ ሰላም የሰፈነበት ሰውና መላእክት በአንድነት በቤተ ልሔም አውራጃ ያመሰገኑበት በመሆኑ የጌታ ልደቱ እንዲህ ነው አለ።ኢነሥኦ ለዘነሥኦ እመላእክት አላ እምዘርዓ--የተዋኃደውን ሥጋ ከመላእክት አላደረገውም ከአብርሃም ዘር አደረገው እንጂ፡ የመጀመሪያው ፍጥረት አዳም የፈጣሪውን ትእዛዝ በማፍረሱ ምክንያት የዲያብሎስ ተገዢ ሆኖ፤ በመንጸፈ ደይን ወድቆ፤ በእግረ አጋንንት እየተጠቀጥቀ አዝኖ ተክዞ ሲኖር አይቶ መሐሪ ይቅር ባይ ነውና እርሱን ነጻ ለማውጣት በኃሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ፤ ወእድኅክ ወስተ መርሕብከ፡ ወእከውን ሕጻነ በእንቲአከ፡ እትቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየ አምስት ሽህ ከአምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀል ተሰቅየ አድንኃለሁ የሚል ቃል ኪዳን ገብቶለት ነበርና የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ቀነ-ቀጠሮው ሲደርስ ሳይውል ሳያድር ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁንና ዛሬ በዓለም ዙሪያ ለፍጥረቱ ሁሉ የታሪክ ማኅደር በሆነችው ባታናሿ በቤተ ልሔም ዋሻ በግርግም ተወለደ፡፡
ቤተ ልሔምና ክብሯ
ልደቱ በቤተ ልሔም የሆነበት ምክንያት ከነቢያት አንዱ የሆነው ነቢዩ ሚክያስ ጌታ ኢየሱስ ከርስቶስ በውስጧ እንደሚወለድ አስቀድሞ ተገልጾለት እንዲህ ሲል ትንቢት ተነበየላት”ወአንቲኒ ብቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴኃቲ እምነገሥተ ይሁዳ..” የኤፍራታ ክፍል የምትሆኝ እንቺ ቤተ ልሔም ሆይ የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው አህጉሮች ብትበልጭ እንጂ አታንሽም ፡የሰው ሁሉ አዳኝ ንጉሥ ክርስቶስ ባንቺ ይወለዳልና ብሎ፡ ተናገረላት .ሌሎችን የእስራኤል አህጉሮች ሲያስተምር ሰንብቶ ከእርሷ ደረሰ፡ ምድረ በዳ፤ጫካ ሆና አራዊት እንስሳት ሰልጥነውባት አይቶ በቃለ አክብሮ፤ በቃለ አጋኖ፡ አንቺ ቤተ ልሔም ሆይ እንዲህ ምድረ በዳ ሆነች አትቀሪም። ድንኳን ይተከልብሻል፤ የነጋሪት ድምጽ ይሰማብሻል፤ አህዛብ ይገብሩብሻል፤እስራኤል ደጅ ይጸኑብቻል በማለት ትንቢቱን ተናገረላት፡ይህውም አልቀረም ሁሉም ተፈጽሟል ዘሩባቤል እንደነሠባት እነሆ ጌታ ተወልዶባታል፡ድንኳን እንደተተከለባት የብርሃን ድንኳን ተተክሎባታል፡ የነጋሪት ድምጽ እንደተሰማባት ዝማሬ መላእክት ተሰምቶባታል አህዛብ እንደገበሩባት ሰብአ ሰገል ገብረውባታል፡ እስራኤል ደጅ እንደጸኑባት መቶው ነገደ መላእክት አንድ ሆነው ደጅ ጸንተውባታል፡፡
የቤተ ልሔም ትርጉም
ቤተ ልሔም ማለት ቤተ ኅብስት ማለት ነው፡ ቤተ ኅብስት ማለት ደግሞ የእንጀራ ቤት ማለት ነው።ወአምጽኡ ልሔሞሙ ውስተ አፉሆሙ እንዲል ኅብስቶሙ ሲል ምሳሌ ነው፡ ቤት እመቤታችን፡ ኅብስት ጌታ ነው፡፡አነ ው እቱ ኅብስተ ህይወት የህይወት እንጀራ እኔ ነኝ (ዮሐ 6፤35) የህይወት እንጀራ ጌታ በታናሿ ክፍል በቤተ ልሔም ዋሻ ተወለደ፡ ረሀበ ሥጋ ረሀበ ነፍስ ተወገደ፡ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ተትረፈረፈ፡ የኃጢአት ሰንሰለት ተቆረጠ፡ ኃብተ ጸጋ ኃብተ ሥርየት ለሰው ልጆች ሁሉ ታደለ፡፡
ኤፍራታና ትርጉሟ
ከሚጠተ እስራኤል በኋላ ማለትም እስራኤል ከግብጽ ተመልስው ኢያሱ ሰጢን በምትባል ቦታ ሳለ ካሌብ የሚባል ሰው ኬብሮንን አሻግሮ አይቶ ይቺ ቦታ ቀደም ሲል በሙሴ ጊዜ የኔ ነበረች ያን ጊዜ አርባ አመት ሆኖኝ ነበር አሁን ሰማኒያ ዓመት ሆኖኛል ለኔ ስጠኝ አለው፡ኢያሱም ጉዳዩን ለእስራኤል ልጆች አማክሮ በጠየቀው መሥረት ሰጠው፡ኬብሮንን እጅ ካደረገ በኋላ ኤፍራታ የምትባል ሴት አገባና ልጅ ወለደ ስሙንም ልሔም አለው በዚያ ወራት እንጀራ ገባ ገባ ብሎለት ነበርና እንጀራዬ ሲል ነው፡ በኤፍራታ ኤፍራታ ተብላለች ኤፍራታ ማላት ጸዋሪተ ፍሬ ማለት ነው፡ ምሳሌ ነው ጸዋሪት እመቤታችን፤ ፍሬ ጌታ ነው፡ በልሔም ቤተ ልሔም ተብላለች፡፡
ሰብአ ሰገል
ወናሁ መጽኡ መሰግላን እነሆ ሰብአ ሰግል የተወለደው የእስራኤል ንጉሥ ወደየት ነው በምሥራቅ ኮከቡን አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናል አሉ።(ማቴ2፤ቁ1)።ይህውም ኮከብ ይሰርቅ እምያዕቆብ ወየአትት ኃጢአተ እም እስራኤል.. ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል የእስራኤልንም ኃጢአት ይመረምራል ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ግድ ስለነበር ነው፡ እሊህ ሶስቱ የምሥራቅ ነገሥታት ከፋርስ ባቢሎን ተነስተው ሶስቱን ንዋያት ማለትም ወርቁን፤ ዕጣኑን፤ከርቤውን ይዘው ሊገብሩለት መጥተዋል።ይህ የከበረ ንዋይ በቀላሉ ከምድራዊ ገበያ ወይም ሱፐር ማርኬት የተገዛ አይደለም ራሱ ባለቤቱ በማይመረመር ጥበቡ ያዘጋጀው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
የሶስቱ ንዋያት አመጣጥ
የዚህ የከበረ ገጸ በረከት አመጣጥ ቅድመ ታሪክ እንደዚህ ነው፡ ሥላሴ ለሶስቱ መላእክት ሰጡ ሶስቱ መላእክት ለአዳም አበረከቱለት አዳም ደግሞ“ንሥኢ እፄኪ ብሎ ለሔዋን ማጫ ይሆናት ዘንድ ሰጣት፡ ሔዋን ለሴት ሰጠችዉ ከሴት ሲወርድ ሲዋረድ የነዚህ የሰብአ ሰግል አባት ዘረደሽት ይባላል ከእርሱ ደርሷል። እርሱም ከዕለታት አንድ ቀን አመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሰሌዳ ኮከብ ተቀርጻ ህጻኗን ታቅፋ አየ ፡ መልካም ነገር ነው ብሎ በሰሌዳ ብርት ቀርጾ አስቀመጠው ለልጆቹ ለሰብአ ሰገል ይህ ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ወስዳችሁ ገብሩለት ብሏቸው ስለነበር ያንን ይዘው መጥተዋል፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ነገሥተ ተርሴስ ወደስያት አምሐ ያበዉዑ-----የተርሴስና የአረብ ነገሥታት እጅ መንሻ ያመጣሉ ብሎ የተነበየው እንደደረሰና እንደተፈጸመ ለማጠየቅ ነው፡፡ ይህ የከበረ ወርቅና ከርቤ ለሔዋን በማጫነት እንደተበረከተ ከላይ ገልጸናል፡፡ ይህንን ቅድመ ትውፊት ተከትሎ የአብርሃም ሎሌ ኢያቡር ለይስሃቅ ሚስት ትሆነው ዘንድ ርብቃን በሚለምንበት ጊዜ”ወእምዘ ረወዩ አግማሊሁ ኢያውብር ነሥአ አእኑገ ዘወርቅ ይላል” ለእግሮቿ ወርቁን፤ ለእጆቿ አምባሩንና ቀለበቱን ዘጋጅቶ ማጫዋን እንዳበረከተላት ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳናል፡፡ ( ዘፍ 29 6-28 ) ኢትዮጵያውያንም ይሁን ትውፊታዊ የታሪክ ቅብብሎሽ ይዘው እስከ እሁን ድረስ ለሴት ልጅ ማጫ የሚያበረክቱት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ በመሆኑ ነው፡፡ ሰብአ ሰገልም ወርቁን፤ ዕጣኑን፤ከርቤውን አበርክተው የልደቱ በረከት ባለቤት ሆነዋል የሶስቱን ዓመት መንገድ በአርብዓ ቀን ተጉዘዋል፡፡
ንጉሥ ነውና ወርቅ አመጡለት ወርቅ ያስገብሩ የነበሩ ነገሥታት ጥንትም ፍጡራን፤ ኋላም ኃላፍያን ጠፋዕያን ናቸው፤ አንተ ግን ጥንትም ያልትተፈጠርክ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ፤ ዕጣን አመጡለት ዕጣን እናጥናቸው የነበሩ ጣዖታት ጥንትም ፍጡራን፤ ኋላም ኃላፍያን ጠፋዕያን ናቸው፤ አንተ ግን ጥንትም ያልተፈጠርክ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ፤ የሞቱ ምሳሌ የሚሆን ከርቤ አመጡለት ምንም እንኳ ጥንትም ያልተፈጠርክ፤ ኋላም የማታልፍ ብትሆን በለበስከው ሥጋ መራራ ሞትን ትቀበላለህ ሲሉ፤ከርቤ የተለያየውን አንድ ያደርጋል አንተም ከባህርይ አባትህ የተለየውን አዳምን በልደትህ በጥምቀትህ አንድ ታደርገዋለህ ሲሉ ነው፡፡የአዳም ተስፋ በልደቱ ብቻ አልተካተተም “ወሰጠጠ መጽሐፈ እዳሆሙ ለአዳም ወለሔዋን--- የአዳምና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤያቸውን ደመሰሰ ማለትም ሰይጣን አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፤ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ ----አዳም የዲያብሎስ ተገዢ ነው፤ ሔዋን የዲያብሎስ ተገዢ ናት የሚል ደብዳቤ ጽፎ በዕብነ በረድ አትሞ አንዱን በዮርዳኖስ፤ አንዱን በሲዖል ጥሎት ነበርና በዕደ ዮሐንስ በተጠመቀ ጊዜ በዮርዳኖስ የጣለውን እንደ ሰውነቱ ተርግጦ፤ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶላቸዋል ፡በሲዖል የጣለውን ደግሞ በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ ደምስሶላቸዋል፡፡
በዓለ ጥምቀት
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በክርስቲያኖች ደሴት በዓለም ዙሪያ ባታላቅ ሁኔታ ተከብሮ ይውላል፡ ጥምቀት ማለት በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋንያ ፤በግዕዝ አስተርእዮ ሲሆን መገለጥ፤ መታየት ማለት ነው፡ቀጥተኛ ትርጉሙ ውሃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ነው፡ምሥጢሩ ጥምቀት ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በዮ፣ወን በም(3፤ቁ35) ላይ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም ብሎ አንዳስተማረው ሥርየተ ኃጢአት የምናገኝበት፤ መንግሥተ ሰማያት የምንወርስበት ዐቢይ ምስጢር ነው፡የምሥጢረ ጥምቀት መሥራቹ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆንም ቀደም ሲል ከጌታ ጥምቀት በፊት የአይሁድ ጥምቀት እንደነበረ ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ነገር ግን ከልዩ ልዩ ደዌ ሥጋ የሚፈውስ፤ ለንስሐ የሚያቀርብ ጥምቀት እንጂ ፍጹም ስርየተ ኃጢአት የሚገኝበት አልነበረም፡፡
ጥምቀት በዘመነ ኦሪት
አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከ ጼዴቅ መሄዱ የጥምቀት ምሳሌ ነበር አብርሃም የምዕመናን፤ መልከ ጼዴቅ የ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡(ዘፍ14፤17) ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጥምቆ ከደዌው ተፈውሷል፤ምዕመናን ተጠምቀው ከድዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ለመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡ ንዕማን ሶርያዊ በዮርዳኖስ ውሃ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያለ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፤ምዕመናን ተጠምቀው ከድዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ለመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡(ነገ፤2፤ቁ5-14) የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነበረች ይህንንም ቅዱስ ጴጥሮስ ይህ ውኃ የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ አሁን ያድነናል የሰውነትን እድፍ ማስወገጃ አይደለም ለእግዚአብሔር የበጎ ህሊና ልመና ነው እንጂ ሲል ተርጉሞታል (1ኛ ጴጥ 3-20)እስራኤል በደመና ተጋርደው ቀይ ባሕርን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው(፡ዘፍ 14፤15)ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ አባቶቻችሁ ሁሉ በባሕር መካከል ተሻገሩ በደመናና በባሕር ተጠመቁ ሲል ተርጉሞታል (1ኛ ቆሮ 10፤2) የአብርሃም ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ሲሆን ልጆቹም በስምንት ቅን እንዲገረዙ በእግዚአብሔር ታዞ ነበር ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ በመሆኑ በዘመነ ኦሪት ቀን ተወስኖ ሕጻናቱ ይገረዙ እንደነበር በዘመነ-ሐድስም ቀን ተወስኖ ወንዶች በተወለዱ በአርብዓ፤ ሴቶች በሰማኒያ ቀን ይጠመቃሉ።(ቆላ1፤11)
ጌታ የተጠመቀበት ዘመን
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ5531 ዓ.ም በዘመነ ሉቃስ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ መጠመቁን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡(ፍት.ነገ አን.19 ድስቅ፤29) በተጠመቀም ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት ነበር። (ሉቃ. 3፤23) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደዮርዳኖስ መጣ፤ይህውም ጥምቀትን ለእኛ ባርኮ ለመስጠት፤የአዳምን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስሕተት ያስወሰደውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው እንጂ ለእርሱ ክብር የሚያገኝበት ሆኖ አይደለም፡፡ ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ማድረጉ ለምንድነው ቢሉ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው “ባሕር አይታ ደነገጠች፤ዮርዳኖስም ወደኋላ ተመለሰ፡ አቤቱ ውኆች አይተው ፈሩህ፡ (መዝ 113/114)
ከዚህ ጋራ ዮርዳኖስ ካላይ ምንጩ አንድ ነው፤ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና ዝቅ ብሎ እንደሚገናኝ ከ አግዚአብሔር ጋራ ተለያይተው የነበሩ የአዳም ልጆች ሁሉ በጌታ ልደትና ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚያስረዳ ዓቢይ ምስጢር ነው፡፡
ታቦታቱ ወደባሕር መውረድ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልጋዩ በዮሐንስ ዕጅ ሊጠመቅ በወደደ ጊዜ ሁለቱም በአድነት ወደዮርዳኖስ ወንዝ ወረዱ፡ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ዓቢይ ምስጢርና ሥርዓት ተከትላ ታቦታቱን ከመንበራቸው አውጥታ፤ የውሃ ምንጭ፤ ወዳለበት ወንዝ በመውረድ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥርዓት በዓሉን ታከብራለች፡ ተከታዮቿ ምዕመናንም ታቦታቱን አጅበው አብረው በመውረድ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ እያከበሩ የበረክቱ ተሳታፊ ይሆናሉ፡ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቀጣዩ ዓመት በሰላም ያድርሰን አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ሎንዶን ብሪታንያ
ጥር 9 ቀን 2008 ዓም.
ከመ/ር ሄኖክ ቸሩ