Post date: Nov 2, 2013 12:06:15 AM
“ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኃበ እግዚአብሔር፤
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። መዝ67፤31
ኢትዮጵያ በጥንት የግብጻውያን ቋንቋ ጱንጥ፤ “ቶ” ኔቶር፤ ኩሽ፤ እየተባለች ትጠራ ነበር። ጱንጥ የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ካለው ፉጥ ከሚለው ስም ጋራ ይመሳሰላል።ዘፍ 10፤7 “ቶ”ኔቶር ማለትም ሀገረ እግዚአብሔር ማለት ነው ይላሉ የቋንቋው ባለቤቶች፤
ሙሴ ብሉይ ኪዳንን ሲጽፍ ይህችን ቅድስት ሀገር የኩሽ ምድር እያለ የጻፈው በግብጽ ተወልዶ ያደገ እንደመሆኑ መጠን የግብጻውያንን ቋንቋ ያውቅ ስለነበር ነው፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኩሽ የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የካምየመጀመሪያው ልጅ እንደሆነ ነው። ዘፍ 10፤1-7 1ኛ ዜና 1፤810
ኩሽ የሚለው ቃል ሀገርን ሲያመለክት ኢትዮጵያ ተብሎ ተተርጉሟል። ዘፍ 2፤13
ኢትዮጵያ የሚለው የቃሉ ትርጉም የሕብር፤ የመልክ፤ የሀገር ስም ሲሆን የትውልዱ ማንነት ሲመዘን ቁመቱ እንደአዛሄል ቀውላላ፤ እንደድንክም በጣም አጭር ያልሆነ መጠነኛ ቁመት ያለው ዜጋ ነው፡፡ በጣምም ነጭ ያልሆነ ከመጠን በላይም እንደቁራ ያልጠቆረ፤ እንደለምጻምም ያልተንቦገቦገ፤ዓሣ የሚመስል ጠይም መልክ ያለው ነው፡
ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ40 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ ዘፍ 2፤13 ኤር 12፤23፤ ኢሳ 18፤1 ሶፎ3፤102፤12 2ኛ ዜና 14፤9-45 2ኛ ነገ 19፤9፤ ናሆ 3፤8-10 .........................ወ.ዘ.ተ
ኢትዮጵያ የኩሽ ምድር ለመባል የበቃችበት ዋናው ታሪካዊ ምክንያት ቀደም ሲል ከላይ እንደተገለጸው የካም የመጀመሪያ ልጅ የኩሽ ዘሮች ስለሰፈሩባት ነው የካምልጆች ኩሽ ምጽራይ ፉጣ እና ከነዓን ናቸው። ዘፍ10፤1-8
According to African history, the first to arrive were Cushitic-peaking farmers and cattle herders who made their way to the region from present-day “Ethiopia” and settled in land and along the coast. They moved mostly in small family groups and brought with them traditions that are still practiced by their descendents.......
የኩሽ ልጆችም ሳባና አቢሳ(ሰብታ) ይባሉ ነበር ዘፍ 107-8 ይህችው ሀገር በሌላ አጠራር የሳባ ምድር በተለይም በምዕራባውያን ዘንድ አቢሲኒያ እየተባለች ስትጠራ ቆይታለች ምናልባትም ይህን ስያሜ ያገኘችው እነዚህ የኩሽ ልጆች ሳባና አቢሳ( ሰብታ) ስለሰፈሩባት በስማቸው አስጠርተዋታል ማለት ነው ብለው ምሁራን አባቶቻችን ይተርካሉ፡ ያስተምራሉ፡፡
According to ancient Roman history, Rome was founded in 753 B.C by the twins brothers Romulus and Remus ....But they quarrelled, and one killed the other. The survivor became king of the new city, which he named after himself. He was Romulus, the city was Rome--------
According to Ancient Greece history 323-356 BC, Alexander the great created the city of Alexandria in Egypt .Which became a world centre of knowledge for hundreds of years.
ለምሳሌ ያህል ከላይ የጠቀስናቸው ሁለቱ ታላላቅ የታሪክ ባለቤቶች ሮምንና አሌክሳንደርያን ከመሰረቱ በኋላ በራሳቸው ስም እንዳስጠሯቸው ኢትዮጵያም በአቅኒዎቿ ስም ማለትም በሳባ የሳባ ምድር፤ በአቢሳ አቢሲኒያ እየተባለች ለብዙ ዘመናት ስትጠራ ቆይታለች አሁንም ትጠራለች።ሆኖም ግን የእኛ አላማ ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ ከየት እንደመጣና አቕኒዎቿም እነማን እንደነበሩ በመጠኑ ለትውልዱ ለመግለጽና ለማስተዋወቅ ያህል እንጂ ስለሮምና ስለአሌክሳንደርያ አመሰራረት ግድ ብሎን አይደለም አቢሲኒያ የሚለውን ቃል ዐረቦች ብዙ ጊዜ ሀበሽ በማለት ይጠቀሙበታል፡ ይህውም ድብልቅልቅ፤ ውጥንቅጥ ለማለት ነው፡ ነገር ግን የታሪክ ተመራማሪዎች በቂ መረጃ የለውም ይላሉ፡፡
በ3600 ዘመን አካባቢ ከጌታ ልደት በፊት (B.C)በየመን ይኖሩ የነበሩ ከነገደ ሴም የተከፈሉ ነገደ ዮቅጣን በባብ አልመንድብ(የመከራ በር ማለት ነው)አካባቢ ገብተው ሰፈሩባት: በዚህች ሀገር ከሚኖሩ የኩሽ ማለትም ከኗሪዎቹ ጋራ ተጋብተው እየተበራከቱ ሄዱ ሀገሪቱንም ምድረ አግዓዚት: ምድረ አግዐዝያን፤ ትርጉም ነጻ ሀገር፤ ነጻነት ያላቸው ስዎች ፤መኖሪያ ብለው ጠሯት:: በመጨረሻም ለዚች ሀገር የተሰጣት ስያሜ ኢትዮጵያ የሚል ነው፡፡
በሀገራችን እንደሚተረከው “ኩሽ” ሁለት ስም ነበረው።ሁለተኛው ስሙ “ኢትዮጲስ” ይባል ነበር በዚህ መነሻነት አቅኒዎቹ ባባታቸው ስም ሀገሪቷን ኢትዮጵያ ብለዋታል።እነርሱም ኢትዮጵያውያን ይባላሉ እየተባለ ይተረካል።ነገር ግን በጽርዕ(ግሪክ) ቋንቋ “ኢትዮጲስ” የተባለው በዕብራይስጥ “ኩሽ” የተባለው የመጀመሪያው የካም ልጅ ነው። ኪዳነ-ወልድ ክፍሌ ገጽ 248”ኢትዎፕስ” ማለት በጽርዕ (ግሪክ) ሁለት ዓይነት ትርጉምን ያሳያል።
የስው ስም ሲሆን ጥቁር፤ የሀገር ስም ሲሆን ደግሞ ቆላ በረሃ፤ ምድረ-በዳ ማለት ነው፡፡ስምነቱም ኩሽ ከሞተ በኋላ በ2450 ዓመት ሰብዓ ሊቃናት ያወጡት ስም ሲሆን በሱዳን ዙሪያ ያለችውን ክፍል የኩሽ ልጆች የሚኖሩባት ሀገር ስለሆነች በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም መሰረት ኢትዮጵያ ተብላለች፡፡ ዘፍ 2፤13 በብሉይ ኪዳን እና በሐዲስ ኪዳን የተጻፈው መደበኛው ኢትዮጵያ ግን ታላቁን የሳራን በረሃ ጨምሮ ያለው ክፍል ነው። 2ኛ ዜና 14፤9 12፤13 16፤8.....ኪዳነ-ወልድ ክፍሌ ገጽ 248 “ይዌልጥኑ ኢትዮጵያዊ ማዕሶ ወነምር ሕንብርብሬሁ” በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? ኤር 13፤23
አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከግሪኮች የተወረሰ ነው “ኢቶስ” ዋዕይ(ሙቀት) “ኦፕ” “ሲስ” ገጽ አርአያ ማለት ነው እነዚህ ሁለቱ ቃላት ሲጣመሩ“ኢቲኦፕያ”ወይም“ኢቲኦፕስ” የሚል ይወጣል፡ ይህም እንደመጀመሪያው “ኤቴኦፕያ” ቢል የሀገሪቱን ቆላነት ያመለክታል “ኢቲኦፕስ” ቢል የሕዝቧን ምንነት የሚገልጽ ይሆናል፡
የግሪኮች የቅኔ ገጣሚ በሆነው በሆሜር መጽሐፍ ደግሞ ቀዩንም ኢትዮጵያ ብሎት ስለሚገኝ ኢትዮጵያ ማለት ጥቁር ብቻ ሳይሆን ቀይ ፤የቀይ ዳማ ቀለም ያለው ሕዝብ ማለት ነው፡የኢትዮጵያውያን ቅድመ አያት ኩሽ የነበረው በ2734 አካባቢ ሲሆን እርሱ በሞተ በ2450 ማለት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ284 መሆኑ ነው መጻሕፍተ ብሉያትን ከዕብራይስጥ ወደ ጽርዕ(ግሪክ) የመለሱ(የተረጎሙ) ሰብዓ ሊቃናት ነቢዩ ሙሴ ኩሽ እያለ በብሉይ ኪዳን የጻፈውን ኢትዮጵያ በሚል ቃል ለውጠውታል። ባለቅኔው ሆሜርም ስለኢትዮጵያ ሲናገር ኢትዮጵያውያን በጉልበት ኃያላን፤ በውበት የተደነቁ፤ የዋሆች በጠባይ ጭምቶች፤ ትህትናን ፍቅርን የተመሉ ናቸው ብሏል።
ከዚህ የተነሳ ከግሪኮች 12 አማልክት አንዱ የመጀመሪያ ታላቁ እንደ-አባት የሚቆጠረው ዜውስ የተባለው ኢትዮጵያውያንን ለማየት፤ ከእነርሱ ጋራ ለመብላት ወደውቅያኖስ ወረደ ብሏል። ኢትዮጵያ በላስፎችና በታሪክ ሰዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ የታወቀች ሀገር፤ የሕዝቧ ማንነት በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸ፤ የጂኦግራፊ አቀማመጧ እና ከባቢ አየሯ ለፍጥረታት ሁሉ ተስማሚ የሆነ ነው፡፡ ሙሴ የስነ-ፍጥረትን ዝርዝር ሲጽፍ በአባይና በተከዜ የተከለለች መሆኗን ያወሳት በኢትዮጵያና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ፍቅር አስመልክቶ ነቢዩ ዳዊት ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ሲል በግልጽ የተነበየላት ቅድስትና ውብ ሀገር ናት። መዝ 67፤31
ስለ ኢትዮጵያ የሃይማኖትና የሞራል ክብር የተናገረ ሶፎንያስ ኢትዮጵያ በአንድ አምላክ የምታምን ሀገር መሆኗን ሲገልጽ “እምነ ማዕዶተ አፍላገ ኢትዮጵያ ያመጽኡ ሊተ መሥዋዕተ ከኢትዮጵያ ወንዝ ማዶ የሚሰግዱልኝ የተበተኑት ልጆቼ መባዬን ይዘው ወደኔ ይመጣሉ” ብሏል ሶፎ 3፤10
ሃይማኖቷም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ትባላለች ኦርቶዶክስ ቃሉ የጽርዕ(ግሪክ) ሲሆን ጥምር ቃል ነው”ኦርቶስ” ቅጽል፤ (adjective) ርትዕት ቀጥተኛ ማለት ነው። “ዶክስ” ማለት ደግሞ “ዶኮ” ካለው ግስ (verb) የወጣ ሲሆን ትርጉሙ ማሰብ: መገመት: ማመን ማለት ነው “ኦርቶዶክስ” እንደ አንድ ስም ሆኖ ተጠቃሎ ሲፈታ ቀጥተኛ ሃሳብ፤ በሃይማኖትም የቀናች ቀጥተኛ ሃይማኖት ማለት ነው
ምንጭ
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ 1974 ዓ.ም
መጽሐፈ ግሥ ወሰዋስው በኪዳነ-ወልድ ክፍሌ ገጽ 248
Roman World Ancient history ISBN9-780746042045
Ancient Greek history-------- ISBNO-86318-909-1
African history..........................ISBN 1-74104-286-0
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መ/ር ሔኖክ ቸሩ
ሎንዶን ብሪታንያ