Post date: Oct 28, 2013 2:37:50 PM
“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት
ሞኝነት፤ ለእኛ ለምንድን
ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና”
(1ኛ ቆሮ1፤18)
የተወደዳችሁ ክርስቲያኖች መስቀል በሐድስ ዘመን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከመዋሉም በፊት የድህነት ምሳሌ ሆኖ በዘመነ ኦሪት የመስቀሉን ምልክት አምነው ለተከተሉት ሁሉ ጠላትን ድል በመንሳት፤ ሕሙማንን በመፈወስ፤ ብዙ ገቢረ ተአምራት ሲያደርግ እንደነበረ ቅዱሳት መሳሕፍት ያስረዱናል፡፡
መስቀል በዘመነ ኦሪት
“ነሥአ ሙሴ በትረ ጸለየ ወአማዕተበ ውእቱኬ በአርአያ መስቀል ሙሴ በትሩን አንስቶ በመስቀል ምልክት አማተበ” የመስቀል ምልክት በሆነችው በትር የኤርትራን(ቀይ) ባሕር ሲመታው ለሁለት ተከፈሎ እንደምሰሶ ቆመ፤ ጠላት ድል ተነሣ፤ የመስቀሉን ምልክት አምነው የተከተሉት የእግዚአብሔር ሕዝቦች በየብስ በደረቅ ተሻገሩ፡፡(ዘጸ14፤15-31) ይህውም ትውፊት ለዛሬው አማናዊው የድኅነት መስቀል አርአያና ምሳሌ ነበር።ምንም እንኳ ከእግዚአብሔር ቸርነት፤ከእስራኤላውያን ጥፋት ባይታጣም የመስቀል ምልክት በመላ ህይወታቸው እየተከተለ ሲረዳቸው እንደነበረ እንመለክታለን፡“ዕብራውያን ሙሴን እግዚአብሔርና አንተን በድለናል፤ ከተቃጣብን መቅሰፍት እንድን ዘንድ ወደእግዚአብሔር ጸልይልን አሉት፡ ሙሴም ስለሕዝቡ ጸለየ፡እግዚአብሔርም ሙሴን የእባብ ናስ ሰርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፡ የተነደፈው ሁሉ ሲያያት በህይወት ይኖራል አለው፡ ሙሴም የእባቡን ናስ ሰርቶ በአላማ ላይ ሰቀለው”(ዘኍል 21፤ 8) ሕመሙ ያልጸናበት ሰው በአላማ ላይ የተሰቀለውን የመስቀል ምልክት ቀርቦ በማየት፤ ሕመሙ የበረታበት ለመቅረብ ያልቻለው ደግሞ የምልክቱን ድምጽ በመስማት ፍጹም ድኅነት አግኝቶ እንደዳነ ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል፡ በመሁኑም መስቀል አሁን ባለንበት ዘመን ብቻ ሳይሆን ሃይማኖት ባልተስፋፋበት ወንጌል ባልተሰበከበት ሳይቀር በምሳሌነቱ ድኅነትን ሲያደርግ እንደነበረ፤ ያም ትውፊት ለዛሬው ለክርስቶስ አማናዊ መስቀል ፍጹም ምሳሌ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡ የቀድሞዎቹ ዕብራውያን ሕመሙ ያልጸናባቸው ቀርበው፤ በደዌያቸው ምክንያት መቅረብ ያልቻሉት ሰዎች ደግሞ ድምጹን ሰምተው ከያዛቸው በሽታ እንደተፈወሱ ሁሉ የአሁን ዘመን ክርስቲያኖችም ደግሞ በሕመም ያልተያዙት ወደመስቀሉ በመቅረብ ተባርከው ተቀድሰው፤ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው በቤት የዋሉት በመስቀሉ ታሽተው፤ ድምጹን ሰምተው፤ መስቀሉን ዳሰው፤ ከደዌ ሥጃ ከደዌ ነፍስ የሚድኑ ለመሆናቸው ፍጹም ምሳሌ ነበር።
ለሰው ልጆች ፍጹም ድኅነት የሆነው የክርስቶስ ነገረ መስቀል በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾለት ከአንድ ሽህ ዓመት አስቀድሞ ነቢዩ ዳዊትም “ወንሰግድ ውስተ መካን ኃበ ቆመ እግረ እግዚእነ የጌታ እግሮቹ በቆሙበት ቦታ እንሰግዳለን” (መዝ131፤7) ብሎ ማመስገኑ ጌታ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ውሎ የአዳምን ልዶች ከአባቱ ጋራ አንድ ማድረጉን፤ እንዲሁም አንዳንድ የዘመኑ ተፈላሳፊዎችና የመስቀል ጠላቶች በራሳቸው ፍልስፍና ለመስቀል ስግደት አያስፈልግም እንደሚሉት ሳይሆን ለመስቀል የጸጋ ስግደት መስገድ እንደሚገባን የሚያጠይቅና የሚገልጽ ምስጢር ነበር፡፡ የንጉሥ ዳዊት ልጅ ብላቴናው ንጉሥ ሰሎሞንም እንዳባቱ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ከዘመናት በፊት “ሐረገ ወይን ኮነ መድኃኒትየ ዘእምኃሢሦን ይትገዘም ወበጎልጎታ ይተከል፣ ተቆርጦ በጎልጎታ የሚተከለው የወይን ግንድ መድኃኒትን ሆነኝ” በማለት መስቀል በኋለኛው ዘመን ለሰው ልጆች ሁሉ ድኅነትን የሚሰጥና ፈውስን የሚያድል መሆኑን የሚገልጽ ምሳሌያዊ ምስጢር ነበር፡፡
መስቀል በዘመነ ሐድስ
የተነገረው ትንቢት፤ የተቆተረው ሱባዔ ሲፈጸም ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወለደ ....”እትቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየ” ተብሎ እንደተጻፈው ለሰው ልጆች ሁሉ የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ የምድር መካከል፤ የዓለም ውበት የታሪክ ማዕከል በሆነችው በኢየሩሳለም በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ዋለ፡ ነፍሳትን ሁሉ በደሙ ነጻ አወጣ፡ እነሆ ክብር ይግባውና ዛሬ በዓለም ዙሪያ በክርስቲያኖች ዘንድ የሚከበረው መስቀልም ሕሙማንን ፈወሰ፤ ዕውራንን አበራ፡ለምጻሙን አነጻ፡ጎባጣውን አቀና፤ ዱዳዎችን አናገረ፡ ክርስቶስን የገደሉት አይሁድ በመስቀል የሚታየውንና የሚሰራውን ተአምራት ሁሉ እንደጥቃት በመቁጠር ከዚህ አስደናቂ ተአምራት ያመለጥን መስሏቸው በመሬት ዉስጥ ቀብረው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ አደረጉት፡ የከተማው ህዝብ ሁሉ የሚጥለው ቆሻሻ ከጊዜ ብዛት የተነሣ እንደኮረብታ ሆኖ ለ300 ዓመት ቆየ መስቀሉ ከተቀበረበት ጀምሮ ለመውጣት 15 ዓመት ሲቀረው ማለትም በ312 ዓ.ም ታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የሮማው ማክሲንድዮስን ለመውጋት ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት ብሎ አዋጅ ነግሮ በዘመተበት ወቅት በዚህ ድል ታደርጋለህ የሚል በጠፈረ ሰማይ ላይ የብርሃን መስቀል ተቀርፆ በዙሪያው በዮናኒ(ጥንታዊ ግሪክ) ቋንቋ “ኒቁስጣኑ፤ ኒቁስጣጣኑ” የሚል ተጽፎ አየ፤ ትርጉሙ በዝትእምርተ መስቀል ትመውዕ ጸረከ ወጸላዕተከ በዚህ የመስቀል ቅርጽ ጠላትህን ፍጹም ድል ታደርጋለህ የሚል ነበር፡ በፈረሱ አንገት በጦሩ አንደበት፤በጋሻው እምብርት መስቀላዊ ቅርጽ አድርጎ የመስቀል ቅርጽ ያላደረገ በሞት ይቀጣል ብሎ አዋጅ ነግሮ ዘመተበት የመክስምያኖስ (ማክሲንድዮስ) ሠራዊት በመስቀል ፊት መቆም አልቻለምና ድል ተነስቷል፡ የመስቀል ኃይል በዚሀ ታውቋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነገሥታቱ ሳይቀሩ መስቀልን በታላቅ ክብር ያከብራሉ። ታዲያ ክርስቲያኖች እየተጠናከሩ በሄዱበት ሰዓት ስለጌታ አየሱስ ክርስቶስ መስቀል ማንሳታቸው እልቀረም በዚህም ምክንያት በዘመኑ ከነበሩት ክርስቲያኖች አንጋፋዋ የንጉስ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ስትሆን በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ከቁስጥንጥንያ ወደኢየሩሳለም ተሻግራ በ(327) ዓ.ም “ዕሌኒ ንግሥት ኃሠሠት መስቀሎ” መስቀሉ የተቀበርበትን ፍለጋ ጀመረች ትክክለኛ ቦታውን ለማወቅ ትችል ዘንድ በዚያ የሚኖሩትን ሰዎች ስታጠያይቅ ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ እንደሚባለው ኪራቆስ የሚባል የአይሁድ ሽማግሌ ምዕመን የተቀበረበትን ቦታ ጠቆሟታል፡ደመራ አስደምራ ዕጣንም አስጭሳ ጉዳዩን ስትከታተል የዕጣኑ ጭስ ወደሰማይ ወጥቶ እንደገና ወደመሬት መስቀሉ የተቀበረበትን አመልክቷታል፡ ይህንንም እትዮጵያዊዉ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ሰገደ ጢስ በጎልጎታ መካን ዘደፈኑ አይሁድ ዮም ተረክበ ዕጸ መሰቀል ጎልጎታ በሚባለው ቦታ ጭስ /ጢስ ሰገደ፤ እነሆ አይሁድ የቀበሩት ዕጸ መስቀል ዛሬ ተገኘ ብሎ ገልጾታል፡(በ327)ዓ.ም መስቀሉን አስቆፍራ ከተቀበረበት አውጥታለች፡ በዚያን ጊዜም በሀገሩ ዙሪያ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁሉ ችቦ እያበሩ በእልልታና በዝማሬ ተቀብለዋታል፡፡
ሁለቱ ወንበዴዎችም የተሰቀሉበት አብሮ ተቀብሮ ሰለነበር መስቀሉ ተቆፍሮ ሲወጣ ለመለየት የተቻለው የጌታ መስቀል፤ሙታንን በማስነሳቱ፤ ዕውራንን በማብራቱ፤ጎባጣን በማቅናቱ፤ ድውያንን በመፈወሱ ነበር። ለዚህም ነው በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን መስቀል ኃይላችን ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፡ መስቀል የነፍሳችን መዳና ነው፤ አይሁድ ይክዱታል አኛ ግን አናምነዋለን፤ በመስቀሉ ኃይልም ድነናል፤እያልን እንሰግድለታለን እናከብረዋለን፡ ከመስቀሉ ፍቅር የተነሳ እናቶቻችን በአንገታቸው ያስሩታል በግንባራቸው፤ በጉንጫቸው፤ በእጃቸው ቅርጹን አድርገው ይታያሉ፡ ይህ ሁሉ የመስቀሉ ፍቅር አገብሯቸው የሃይማኖታቸው መገለጫ፤የባሕላቸው መታወቂያ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡
መስቀሉ ወደሀገራችን እንዴት መጣ?
መስቀሉ ከተቀበረበት ተቆፍሮ ከወጣ ካንድ ሺህ ዓመት በኋላ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ጌታ የተሰቅለበት ግማደ መስቀሉ ወደኢትዮጵያ መምጣቱን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይመሰክራል”ግማድ” ማለት ክፋይ ማለት ነው ዐፄ ዳዊት ከነበራቸው መንፈሳዊ ቅንዓት የተነሣ ንግሥት ዕሌኒ አስቆፍራ ካስወጣችው የጌታ ግማደ መስቀል ከፍለው እንዲልኩላቸው ለገጸ በረከት የሚሆን ብዙ ወርቅ አስጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ላኩ በወቅቱ የነበሩት ፓትርያርክም የመስቀሉን ክፋይ፤ አክሊለ ሶኩንም፤ ቅዱስ ሉቃስ የሳለውንም ምስለ ፍቁር ወልዳ ጨምረው ላኩላቸው፡ መልእክተኞቹም ይህንን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡ ግማደ-መስቀሉም ወደ ኢትዮጵያ የገባው መስከረም 10 ቀን ሲሆን የተቀጸል-ጽጌ አከባበርም የተጀመረው ያንጊዜ ነው ይባላል፡አሁን ግማደ-መስቀሉ የሚገኘው በግሸን አምባ ማርያም ደብረ ከርቤ ነው።
ደ መ ራ
ደመረ ጨመረ፤ አንድ አደረገ፡ ከሚለው የግእዝ ቋንቋ የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም ትርጉም አንድነት ህብረት ማለት ነው፡ የበዓሉን አከባበር በተመለከተ መስቀል ተይዞ ችቦ እየተበራ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በአንድነት ይከበራል ከላይ እንደተገለሰው ንግሥት ዕሌኒ ደመራ አስደምራ፤ ዕጣን አጭሳ፤ መስቀሉን ቆፍራ፤ ባወጣታች ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ችቦ እያበሩ ተቀብለዋት ስለነበር ችቦውም ሆነ የደመራው ጭስ ከዚያ ተያይዞ የመጣ ነው።
የመስቀሉ በረከት ከሁላችን ክርስቲያኖች ጋራ ይሁን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መ/ር ሔኖክ ቸሩ
ለንደን ብሪታንያ