ቤተ ክርስቲያንን ወደ ግል ካምፓኒ የመቀየር አመጽ (ይጫኑ)

Post date: Nov 5, 2013 3:45:08 PM

ቤተ ክርስቲያንን ወደ ግል ካምፓኒ የመቀየር አመጽ

በለንደንና አካባቢው ለምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህናት መእመናንና ወጣት የሰ/ት/ቤት አባላት በሙሉ

«እነሱ ሰውን የሚለያዩ የሥጋን ምኞት የሚከተሉ መንፈስ ቅዱስ የተለያቸው ሰዎች ናቸው» ይሁዳ. 1፤19

ይህ ቃል የተነገረው በዘመን ሰማዕታት ወሐዋርያት ሐሰተኞች በሐሰት በሰው ልጆች መካከል አንዱን ከአንዱ በማጋጨት ያልሆነውን ሆነ እያሉ ስም በማጥፋት፣ በመለያየት በሠይጣናዊ ተልኮ ሁከት፣ ንትርክና መከፋፈልን ጭቅጭቅን የባሕሪያቸው ዋና መግለጫ የዕውቀታቸው መቋጫ አድርገው ቀጥተኛውንና መልካሙን ነገር ሁሉ በማጣመም በነገር ሱሰኝነት የተለክፉ እምነት የጎደላቸው የመንፈስ ቅዱስ ሀብት ለተለያቸው ዘወተር ንብረትና የገንዘብ ፍቅር አእምሯቸውን ረፍት ለሚነሳቸው የመንፈስ ድሆች ማስተማሪያና ማስጠንቀቂያ ይሆን ዘንድ ለእሥራኤል ወገን ለሆነው ለይሁዳ የተጻፈ ሕያው መልዕክት ሕያው ቃል ነው።

የተከበራችሁ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ሁላችሁ፦

ርዕሰ አድባራ ለንደን ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጨረሻ ዘመነ ንግሥና አካባቢ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርትርያርክ ዘኢትዮጵያ መልካም ፈቃድ በአባ አረጋዊ(ቆሞስ) በኋላ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ባለ አደራነት በሕገ ቤተክርስቲያን ተመሥርታ አርባ ዓመት ሐዋርያዊ ጉዞዋ ሳይቋረጥ በስደት ሀገር እምነትን፣ መንፈሳዊ አስተዳደርን ፣ሀገርና ታሪክን ጠብቃ በማስጠበቅ ከፍተኛ መንፈሳዊ አስተዋጾ አድርጋለች በማድረግም ላይ ትገኛለች።

ዘመን በዘመን እየተተካ መሄዱ ተፈጥሯዊ ግዴታ ነውና ከብዙ ድካም በኋላ በካህናት ሰባኪነት በመእመናን ተሰባኪነት ሁለቱም በአንድነትና በኅብረት የእራሷ ሕንጻ ቤተከርስቲያን ገዝታ ወንጌልን በማጠናከር ደቀ መዛሙርትን በማብዛት የጉባኤ ትምህርትን በማስፋት ቀሳውስትንና ዲያቆናትን በማሰልጠን መንፈሳዊ አገልግሎቱ በተሟላ ሁኔታ በማከናወን እጅግ በጣም የሚያስደስት መንፈሳዊ ፍሬ የታየባት ታላቅ ቦታ ርዕሰ አድባራት ናት።

ይሁን እንጅ መንፈስ ቅዱስ ባለበት ሁሉ ሰይጣን የራሱን ፈተና ማምጣቱ የባሕሪው ነውና ከላይ የተጠቀሰው የወንጌል ቃል እንደሚያስተምረን የሥጋ ፍላጎትና ምኞት ያሰከራቸው ጥቂት ግለሰቦች ሕንጻ ቤተክርስቲያን በግል ባለቤትነት ለመቆጣጠር በተወጠነ የካምፓኒ ሕግ ረቂቅ ውስጠ ደንብ ምክንያት ማኅበረ ካህናቱና ማኅበረ ምእመናኑን በመለያየት ጎራ ለይተው አዳራሽ ተከራየት መንፈስ ቅዱስ የተለየው፣ ምክረ ካህን የጎደለው፣ ሥጋዊ ምኞት ያደነዘዘው፣ የግል ፍላጎታቸውን ብቻ እያስፋፉ ‘’ቤተክርስቲያን ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ኩባንያ ካልተመዘገበች፣ በዳይሬክተሮች የበላይነት ካልተመራች ሀብትና ንብረቷ አይጠበቅም፤ በእንግሊዝ ሀገር ሕግ ሥር አትታወቅም” በሚል የሐሰት ፍልስፍና የቤተክርስቲያን ሕንጻ በካህናትና በምእመናን አንድነት ባለአደራ ተጠብቆ የቆየውን በተጭበረበረ ሁኔታ በኃይል ፈልቅቆ የግል ኩባንያ (Private Campany)፣ በግል ይዞታ ቁጥጥር ውስጥ ለማስገባት ያልተቆፈረ ጉድጓድ የለም።

ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በጨለማ የተሥራው በብርህን እየታየ፣ የተሰወረው ሁሉ እየተገለጠ መንፈስ ቅዱስ የተለየው የሥጋ ፍላጎት ሁሉ በአደባባይ ሲከሽፍ ታይቷል፤ሃይማኖት ያለው ሰው ሁሉ ከዚህ ብዙ ማወቅና መረዳት ይችላል።

የተገዛውን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ከካህናት ከመእመናንና ከወጣት የሰ/ት/ቤት አባላት ጥምር ባለአደራነት ፈልቅቆ በኃይል በማስለቀቅ በግል ኩባንያ አስመዝግቦ በግል ንብረትነት ለመያዝ በመንፈሳዊ አስተዳደር ምትክ የዴሬክተሮች ካምፓኒ አመራር ለመተካት በካምፓኒ ሕግ (Campanies law) ማርቀቅ ስራ የተሰማሩ ጥቂት ግለሰቦች በዋናነት ጌታቸው በሻህውረድና ሻለቃ ማሞ ለማ ታሪክ ሊታገሰው የማይችል፣ ቤተክርስቲያን የማትረሳውና ትውልድ የሚዘክረው በመንፈስ ቅዱስ ሀብት ላይ የአመጽ ዱላ ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል።

ለእርቀ ሰላም፣ ለምክክር ፣ሕገ ቤተክርስቲያንን መሠረት ላደረገ መንፈሳዊ የመፍትሔ ሀሳቦች የተዘጋጁ ሁነው አላገኘናቸውም፤ይልቁንም በህንጻ ቤተክርስቲያን ባለቤትነት የራሳቸውን ወይም ተላላኪዎቻቸውን ለማስቀመጥ የሚያደርጉትን የመከፋፈል ተግባር አጠናክረው ቀጥለውበታል።

ካምፓኒ ረቂቅ ውስጠ ደንቡ ባስከተለው ከፍተኛ የመከፋፈል ችግር ከባህል፣ ከታሪክና ከሁሉም በላይ ከእምነታችን አንጻር በሰበካ ጉባኤ ውሳኔ፤ ከካህናት፣ ከመእመናን፣ ከሰ/ት/ቤት ወጣቶች እና ከካፕፓኒ ሕግ አርቃቂዎች በተውጣጣ ኮሚቴ ችግሩ በሽምግልና እየታየ ባለበት ወቅት ፤በአርቃቂዎች በኩል ይታይ የነበረው የቃላት ማጭበርበር፣ ሸፍጠኝነትና ሀሰት እጅግ በጣም የሚያሳዝን ክስተት ከመሆኑም በላይ ገና ባልጸደቀ የካምፓኒ ሕግ (Campanies law) ስም ሁለት ምእመናንን እንደመጠቀሚያ ግዑዝ ነገር በመቁጠር ከሕገ ቤተክርስቲያን ውጪ ከካህናትና ከምእመናን ጋር በአንድነት ሳይመክሩበት ከሁሉም በላይ የሆነችውን ሕዝባዊቷን እናት ቤተክርስቲያን ከሶስት ወራት በፊት ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ኩባንያ በማስመዝገብ በሁለት ግለሰቦች የበላይነትና ባለንብረትነት በግል አድራሻቸው አስመዝግበው በመያዝ በመንፈስ ቅዱስ ሀብት አመጽና የማጭበርበር ወንጀል ፈጽመዋል።

እውነቱና ሀቁ ይህ ሁኖ ሳለ “የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ” እንደሚባለው ሁሉ፤ በፈጸሙት አመጽ በመጸጸት፣ ንስሀከመግባት፣ ቤተክርስቲያንን ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ ስለጸሎት ፍትሀትና ስለፓትርያርኩ ስም አለመጠራት ስለ ትምህርተ ወንጌል ጠቅላላ መንፈሳዊ አገልግሎት፤ እንዲሁም በዋልድባ ገዳም መደፈር ምክንያት የተሰማቸውን

ከፍተኛ ቅሬታ በሰላማዊ ሰልፍ የገለጹት የደብሩ ካህናት ምእመናን በማስተባበር ሆኖ ሳለ፤ ከሁሉም በላይ የካህናት ተቀዳሚ የሥራ ድርሻ መሆኑን በግልጽ እየታወቀ፤ ይህ አገልግሎት የካምፓኒ ሕግ አርቃቂዎች የእነ ሻለቃ ማሞ የሥራ ድርሻና የሥራ ውጤት አስመስሎ ማውራት ከታሪክ ፍርድ እና ከትውልድ ትዝብት አለማምለጥ ነው። “ላም ባልዋለበት ኩብት ለቀማ ማለት ይኽ ነው”።

ስለ እምነታቸው ቢጠየቁ መልስ መስጠት የማይችሉ በመንፈሳዊ እውቀት ያልቃኑ በተለይም እግዚአብሔር የለም በሚል ርዮተ ዓለም ውስጥ የነበሩ የቤተክርስቲያን በር ሲዘጋ ድምጻቸውን ያላሰሙ፤ ወጣቱን የሀገራችን ዜጋ በጆሮ ጠቢነት እየወነጀሉ ያስፈጁ የመንፈስ ደሆች ዛሬም ከቆየው የሥራ ልምዳቸው በመነሳት ንጹሐን የዋህ ምእመናንን እንደመሣሪያ በመጠቀም ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የካምፓኒ (Company) ባለቤት እንዲሆኑ፤ ሕገ ወጥ ሥልጣን እንዲኖራቸው አድርገዋቸዋል። እራሳቸው በእጣታቸው ሊነኩት የፈሩትን በሌሎች ወንድሞቻችን ትከሻ ላይ በማሸከም አሳዛኝ ሸፍጥ ፈጽመዋል።

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን

“ቤተክርስቲያን በካምፓኒ አስተዳደር ውስጥ ገብታ ቀኝ ተገዥ ካልሆነች፤ የግል ኩባንያ (Private Limited Company) ሆና ካልተመዘገበች፤ በሁለት ምእመናን ዲይሬክተርነት የበላይነት ካልተምራች፤ ካህናቱና ደገኛው ምእመናን የሀገር ጠላቶች ናቸው”። የሚለው የጌታቸው በሻህውረድ ስብከት በእምነት ያልጸኑትንና በምግባር ያልታሹትን ጀሌዎች በማስከተል በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አስተዳደር እና መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ የሚፈጽሙት አመጽ መቆም አለበት።

የክርስቶስ ተከታዮችን በአንድነት እና በእምነት አስተባብራ የምትጠብቀውን የሀገር፤ የሕዝብና የታሪክ ባላደራ(Trustee) የሆነችውን ቅድስት ቤተክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተለየው የግል ኩባንያ (Private Limited Company) ውስጥ ለማስገባት ለማፈራረስ በጨቅላ የፖለቲካ አስተሳሰብ የደረሰባቸውን ኪሣራ እንዲሁ በቤተክርስቲያን ላይ ለመድገም የሚያደርጉት የመለያየት፤ የመበታተንና የአድመኝነት ሴራ ጊዜ ሳይሰጠው መገታት አለበት።

ይህ ካልሆነ ዛሬ በስደት ሀገር ትውልዱን በመከፋፈል በቤተክርስቲያን ስም እነ ሻለቃ ማሞ የሚፈጽሙት መድኃኒት የሌለው በሽታ በቅጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ደርግና ወያኔ የሠሩት ወንጀል እየተደገመ መሆኑን መረዳት ይኖብናል።

ቤተክርስቲያን ከማንኛውም ሰው ሠራሽ ፖለቲካ ጥገኝነት ነፃ የሆነች፤ በአንድነቷና በነፃነቷ ፀንታ የኖረች፤ ወንጌልን ለሁሉም በእኩልነት ከጠፈር እስከ ጠፈር ለማዳረስ የምትንቀሳቀስ፤ ለሀገራችን ኢትዮጵያ አንድነት፤ ለሕዝቦችዋ ፍቅር እና በጠቅላላው ለዓለም ሁሉ ሰላም በማወጅ በየዕለቱ የምትጸልይ እንጂ በጌታቸው በሻውረድ ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ኩባንያ(Private Limited Company) የግለሰቦች ንብረት ሆና ባንክ የሚበደሩባት፤ ሽርክና የሚገቡባት፤ በዋስትና የሚያሲዙዋት፤ የፈለጋቸውን የሚሾሙባት፤ የሚቀጥሩባትንና የሚያባርሩባት፤ መቀለጃ መድረክ አይደለችም።

ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ መሠረቷን ኢትዮጵያ ባደረገ መንፈሳዊ አስተዳደር መዋቅርዋን ጠብቃ፤ ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን ለመወጣት በሕገ ቤተክርስቲያን እየተመራች የቤተ ክርስቲያን አንድነት እስኪ መለስ በካህናትና በምእመን አንድነት እየተመራች ባለችበት ሁኔታ ጸንታ ትኖራለች። ከዚህ ውጪ በሥጋዊ ፍላጎት ተነሳስቶ የሚከፋፍል እና መንፈስ ቅዱስ የተለየው ተግባር ሁሉ ተቀባይነት የለውም።

በሀገራችን የታሪክ ገጽታም እንደምንረዳው እምነት የሌላቸው አመጸኞች በሙሉ የመጀመሪያውን የጥፋት ዱላ የሚያሳርፉት በዚች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ነው -

  1. የእምነታችን መሠረት ጌታ የተወለደበት ቤተ ልሔምና ኢየሩሳሌም የፈረሱት በኢአማኒያን ነው።

  1. በዮዲት በጉዲት እና በግራኝ መሐመድ ወረራ ዘመን የተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት እንደበግ የታረዱት ካህናትና ምእመናን ባላደራዎች በመሆናቸው እንጂ የካምፓኒ ዳይረክተር በመሆናቸው አይደለም።

  1. በጣልያን ወረራም በአደባባይ የተረሸኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያንና የሀገራችን ባላደራ በመሆናቸው እንጂ የካምፓኒ ዳይረክተር በመሆናቸው አይደለም።

  1. ደርግም የብዙ አብያተ ክርስቲያንን በር የዘጋው እና ፓትርያርኩን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን የረሸነው ሃይማኖት ስለሌለው ነው።

  1. ወያኔም ብፁዕ ወቅድስ አቡነ መርቆርዮስን አሳዶ ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት የከፈለው ሃይማኖት ስለሌለው ነው።

  1. በወያኔ የዋልድባ መነኮሳት የሚደርስባቸውን መከራ ሁሉ በፀጋ የሚቀበሉት የገዳሙ አጽመ ዕርስት ባላደራዎች በመሆናቸው እንጂ የስኳር ፋብሪካ (የካምፓንይ ዳይሬክተሮች በመሆናቸው አይደለም)

  1. አሁንም ሃይማኖት እንደሌላቸው የሚጠረጠሩ የቀድሞ የደርግ አባላት እነ ሻለቃ ማሞ(የካምፓኒ ሰዎች) በካምፓኒ ስም ቤተ ክርስቲያንን ወደ ካምፓንይ ለመቀየር ምእመናንን ለሁለት ለመክፈል ካህናትን በማሳደድ ከመንፈስ ቅዱስ አስተዳደር የተለየና ሥጋዊ ፍላጎት ብቻ ያደነዘዘው ተግባር እየፈጸሙ ይገኛሉ።

ስለዚህ በለንደን አካባቢው የምትኖሩ ካህናት፤ ምእመናንና ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በአንድነት ሐዋርያዊት፤ ጥንታዊትና ታሪካዊት እናት ቤተ ክርስቲያናችንን ከካምፓኒ ሰዎች አመጽ የመጠበቅና የመከላከል የእምነት ባላደራነታችንን እንድንወጣ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን።

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠበቅ

ከተቆርቋሪ ካህናትና ምእመናን

ግልባጭ፤ በሀገር ውስጥ ለሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፤

ለመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት፤ አዲስ አበባ:: ኢትዮጵያ፤

በስደት ሀገር ለሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፤ ዋሺንግቶን ዲ ሲ:: አሜሪካ (Washington DC America)፤

ለመላው አህጉረ ስብከት ጽ/ቤት፤ በያሉበት፤

ማሳሰቢያ -

ቤተ ክርስቲያናችን በተጭበረበረ ሁኔታ ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ኩባንያ (Private Limited Company) የተመዘገበችበትን ማስረጃ ከዚህ ቀጥሎ ይመልከቱ በተጨማሪም የካምፓኒ ሃውስን (Companies house) ድህረ ገጽ(web site) በመጎብኘትና የካምፓኒውን ቁጥሩን (Companies No.) በመጥቀስ የበለጠ ማስረጃ ማግኘት ይችላሉ። "Evidential Documents" የሚለውን ክፍል በማየት ዝርዝሩን ይመልከቱ.