Post date: Oct 28, 2013 2:49:39 PM
ቃለ ዓዋዲ ምንድን ነው?
ቃለ ዓዋዲ የሚለው ቃል በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደና በአብዛኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከ1965 ዓመተ ምሕረት ጀምሮ ላለፉት አርባ አመታት የቤተክርስቲያናችን ሃይማኖታዊ፣ መንፍሳዊ አስተዳደርን፣ የሰበካ ጉባኤ አደረጃጀት መሠረት ቤተክርስቲያናችን በበላይነት እየመራ የሚገኝ የቤተክርስቲያንችን ዐቢይ መመሪያ ነው።
ቃለ ዓዋዲ በሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ወሳኔና ፈቃድ ብቻ እንደ ወቅቱ ሁኔታ እየታየ ተሻሽሏል። ይሁንእንጂ አንዳንድ ካህናት በአብዛኛው ምዕመናን የቃለ አዋዲን ትርጉም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለው ተግባቢነት፣ ወደ ሀገራችን እንዴት እንደመጣ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ስያሜው ምን እንደሆነ ባለመረዳት በቃለ ዓዋዲው መሠረት ለቤተክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ አስተደር የሚመረትጡ ምዕመናን ቃለ ዓዋዲ ምንድን ነው? በማለት ይጠይቃሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በቤተክርስቲያን ውስጥ በመቆየትና በመኖር በመቀራረብ በሚፈጠር ያወኩሽ ናኩሽ፣ የብልጣ ብልጥነትና ጥቅመኝነት በስደት የሚኖሩበትን ሀገር እንደምክንያት በማቅረብ ቃለ ዓዋዲውን በግላችን እናሻሽላለን፣ እንተርጉማለን ወይም የተሻለ ሕግ እንሰራለን የሚሉም በመፈጥራቸው ፤በተለይም በውጭ ሀገር የሚገኙ ካህናት ክህነቱን ከያዝኩት ቃለ ዓዋዲ ምን ያደርግልኛል ብለው በሚያስቡ የጠባብነት ስሜት ለራሳቸውን ብቻ የራሳቸውን ተከታይና ጄሌ ወይም የጎሳ መለያና «ገለልተኛ» መሆንን የመረጡ የጮሌዎች ጥቅም ማስከበሪያ እየሆነ በመምጣቱ ነው።
ይህን የቤተክርስቲያን የበላይ ሕግ ላላወቁም ሆነ እያወቁ ለሚያጠፉ ማብራራቱ ተገቢ ከመሆኑም በላይ በተለይም በሎንደን ደብረ ጽዮን ቅደስት ማርያም ቤተክርስቲያን ጥቂት ምዕመናን የቤተክርስቲያን ውስጥ መተዳደሪያ ቃለ ዓዋዲውን መሠረት ያደረገና የማይቃረን የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ አርቅቁ ተብለው በሰበካ ጉባዔ ቢመደቡ፤ በረቀቀ ስልት ከነባር የቻሪቲ ኮሚሽን የአደራ ጠባቂነት አስተዳደር አስወጥተው ቃለ ዓዲውን የሚቃረን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሕግ በማርቀቅ፤ ይህ ተግባራዊ እንዲሆንላቸው በማስገደዳቸው ምክንያት በቤተክርስቲያን ላይ የተፈጸመውን ግፍና በደል በአካል ተገኝቼ በአይኔ ተመልክቼ የተርዳሁ በመሆኔ ይህን ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪነት ለእምነታቸው ቅናት ላላቸው ታማኝ ባላደራዎች ካህናትና ክርስቲይኖች ሁሉ ሕጉን በተቻለ መጠን ቃለ አዋዲ የሚለው ሃይማኖታዊና ታሪካዊ መንፈሳዊ የሕግ ሰነድ ምን እንደሆነ ማብራራት ጠቀሜታ ይኖራዋል በሚል የቀረበ ነው።
ምክንያቱም ይህን የመሳሰሉ ችግሮች በየጊዜው እያደጉ በመምጣታቸው በተለይም በውጭው ዓለም ያለውን የዲሞክራሲዊ አስተዳደር ብሂል እንደ ደጀን በመቁጠር ማን ይነካኛል! በሚል እብሪት የሚደረገው አመጽና «ገለልተኛ»ነኝ ባይነት የቤተክርስቲያናችን ተጨማሪ ችግርና ውዝግብ ፈጣሪ በመሆን ቤተክርስቲያን ሕንጻና ሌሎች ንብረቶችና በገቢ ምንጮች ሁሉ ያነጣጠረ የይገባኛል ጥያቄ እያስነሳ ቤተክርስቲያንን በኃይል እስከ ማዘጋት ደረጃ በመደረሱ ነው።
ጥንታዊት፣ሐዋርያዊት እና ብሔራዊት በሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በብሉይና በሐዲስ ኪዳን የተዘገቡትን የእግዚአብሔር ቃል በአንድነት የምትቀበልና በአንድምታ ትርጉም አብራርታ የምታስተምር ቀደምት ቤተክርስቲያን ከመሆንዋም በላይ የምትተዳደርባቸው ሕግጋት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በሚያዘው መሠረት ተጣጥመው የተቀመሩ በመሆናቸው በጥንቃቄ ለመረመራቸውና ጥናት ላደረገባቸው በቀኖና ድንጋጌያቸው፣በሥርዓት አፈጻጸማቸው እና በመንፈሳዊ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ሃማኖታዊ ትምህርት ሰጭነታቸው፣ በታሪክ አስተዋሽና ነጋሪነታቸው እጅግ የሚያስደንቁ እና የተዋቡ ናቸው።
የአዋጂ ነጋሪ ቃል የእግዚአብሔርን መንገድ በምደረበዳ ጥረጉ የአምላካችንም ጎዳና በበርሀ አስተካክሉ ፣ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይበል፤ኮረብታው ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ጠማማው ሁሉ ይቅና፤ስርጓጉጡም ሜዳ ይሁን፤ሥጋ ለባሹ ሁሉ በአንድነት ያየዋል። የእግዚአብ ሔር ቃል ይህን ተናሮአልና። ትንቢተ ኢሳያስ 40፡3
ይህ የነብዩ ቃል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ ከስምንት መቶ ዓመት በፊት የተነገረ ነው። የዚህ ጥቅስ ዋና ዓላማ ቃለ ዓዋዲን ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት ነው። ቃሉ በግዕዝ ቃለ ዓዋዲ በአማርኛ የአዋጂ ነጋሪ ቃል ነው። አዋጂ ነጋሪ ማለት አዲስ መመሪያ፣ አዲስ ትእዛዝ አዲስ ብሥራት ወይም አዲስ አዋጂ መናገር…. ማለት ነው፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን አዋጂ ነጋሪ ቃል ተብሎ የሚጠራው በሐዲስ ከዳን ክርስቶስ በማሕጸነ ድንግል ሲያድር ስድስት ወራት አስቀደሞ ከቅድስት ኤልሳቤጥ የተጸነሰውን አዋጂ ተናጋሪውን መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዩሐንስን ነው።
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በድሜ ከሸመገሉት ከቅድስት ኤልሳቤጥና ከካህኑ ዘካርያስ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ተጸንሶ የተወለደ ነው። አረጋዊና ካህኑ ዘካርያስ ብስራቱን የተቀበለው በአይሁድ ቤተ መቅደስ በአገልግሎት እንዳለ ነበር፤ ነገርግን እኔ ሸምግያለሁ የሕወቴ ጓደኛ ኤልሳቤጥም ሸምግላለች በስተርጂና ይህ ከቶ እንዴት ይሆናል ብሎ መልአከ ብሥራቱን በመጠራጠሩ በአይሁድ ወገኖቹ ዘንድ አስቀደሞ ማንም ያልተጠራበትን ስም ልጁ አዋጂ ነጋሪው ተወልዶ «ዮሐናስ» ብሎ እስኪጠራ ድረስ በጀሮው የሚሰማ ሲሆን በአፉ ግን ያማይናገር ዱዳ ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ የልጁን ስም «ዮሐንስ» ብሎ በጠራ ጊዜ የካህኑ ዘካርያስ አንደበት ተፈታ። ቅዱስ ዮሐንስ ኢየሱስ ከርስቶስ ገና በማህጸነ ድንግል ሲያድር ኤልሳቤጥ አዋጂ ነጋሪውን/ዮሐንስን አርግዛ ስድስት ወራት ተቆጥሮ ነበርና ድንግል ማርያም ዘመድዋን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በሔደችበት ወቅት በእናቱ በኤልሳቤጥ ማህጸን እንዳለ በደስታ ያመሰገነና ለጌታው የሰገደ ቅዱስ ነው። ቅዱስ ዩሐንስ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋ ዘመዱ ነው።… ወአዝማዱ በሥጋ።
ቅዱስ ዩሐንስ በብሉይ ኪዳን የመጨረሻው ነብይ ተፈጻሜተ ነብያት በሐዲስ ከዳን የመጀመሪያው ሐዋርያ መጥምቀ መለኮት ነው። አዋጂ ነጋሪ ወይም ጋዜጠኛ ነው። መናኝ በበርሃ የሚኖር ባህታዊ ነው። ፍጹም ድንግል ነው። ሰማዕት ነው። የብሉይ ኪዳንን ወደ ሐዲስ ኪዳን ያሸጋገረ ወይም የሽግግር መተላለፊያ ድልድይ አዋጂ ነጋሪ/ቃለ ዓዋዲ ነው። አዋጁም መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ! ማቴዎስ 3፤2 እኔ በውሃ አጠምቃችኋአለሁ ከእኔ በኃላ የሚመጣው በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋአል! ማቴዎስ3፤10 በማለት ድምጹን ከፍ አድርጎ ያወጀ ነው። መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በኢሱስ ክርስቶስ ላይ ሲወረድና ሲያርፍ ያየ ነው። ዩሐንስ 1፤32 ናሁ ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም (እነሆ የአዋጂ ነጋሪ ቃል በምድረበዳ የሚጮህ) ተብሎ አስቀደሞ በነብይ እንደተነገረ ይህው ይፈጽም ዘንድ አዋጂ ተናገረ።
ከላይ ያነበብነውን በጥንቃቄ ከተረዳን አብዛኛወቹ የዓለም ሀገሮች መንግሥታት ለሕጋቸው መሠረትና ዋና መነሻ የሚያደርጉት መጽሐፍ ቅዱስን ነው። ለምሳሌ አንድ መንግሥት ወርዶ ሌላ መንግስት እስኪ መረጥ ድረስ የሚቋቋም የሽግግር መንግሥት ዓላማ በጊዚያዊነት መንግስት ሆኖ ከአሮጌው መንግሥት ማለቂያ ላይ በአዲሱ መንግስሥት ምሥረታ ወቅት በመካከል የሚሠራ ከአሮጌው ተንስቶ ስለ አዲሱ መንግሥት መቋቋምና ዓላማ የሚያስተምር፣ አዲስ አዋጂ የሚያወጣ፣ መመሪያዎችን የሚያዘጋጂ የአስታዳደር ጎዳና ፣ የምርጫ አፈጻጽም የሚያወጣና ለአዲሱ መንግስት መንገድ ጠራጊ ነው።
ይህ የሚያሳየው ከላይ በስፋት እንደ ተገለጸው አዋጂ ነጋሪው ቅዱስ ዩሐንስ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን መካከል ተወልዶ ጠማማው እንዲቀና፤ጎድጓዳው እንዲ ሞላ፤ ያበጠው ዝቅ እንዲል፣ ሸካራው እንዲለሰልስ ለምደራዊና ሰማያዊ ንጉስ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት መንገድ ያዘጋጀ ቃለ ዓዋዲ/ አዋጂ ነጋሪ ቅዱስ ዩሐንስ ሲሆን ምደራዊ ሰው የተናገርውና ያደርገው መለኮታዊ ከዊን ያስተማረውንና ያወጀውን ከመጽሐፍ ቅዱስ በመውሰድ በምድራዊ አስተሳሰብ የምንጠቀምበት የሕግ ምንጭ ሆኖ እናገኘዋለን። ብዙ በዓለም ላይ የሚገኙ ሀገሮች መንግሥታት ሕግጋት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕያው ቃል መነሻ በማድረግ ሕጋቸውን እንደሚቀርጹ እና ሕዛባቸውን በሰላም እንደሚያስተዳድሩ እንረዳለን፤ በተለይም የምንኖርባት ታላቋ እንግሊዝ መጽሐፍ ቅዱስን መነሻ በማድረግ የተቀረጹ ሕግጋትና የአስተዳደር መመሪያዎች እንዳሉ በተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል።
በመሆኑም ቃል በቃል ምራፍና ቁጥር ብቻ ሸምድዶ ደረትን ነፍቶ እንዳንበሳ ማግሳት ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ መረርምሮ የተረዳ ሰው ብልህ፣ አስተዋይና ሚዛናዊ፣ ከሁሉም በፊት ለሕግ ተገዥና ሕግ ከሁሉ በላይ መሆኑን የሚረዳና ትክክለኛ ፈትህ የሚሰጥ፣ ሰውን ኣክባሪ እግዚኣብሔርን ፈሪ፣ለቤተክርስቲያንና ለመንጋውን፣ አክባሪ ሀገሩንና ወገኑን አፍቃሪ፣ ሰላም አብሳሪ፤ ፍቅር ነጋሪ ይሆናል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለረጅም ዘመናት በቆየችበት አስተዳደር ከሀገሪቱ ጠቅላላ ገቢ አንድ ሦስተኛው በጀት ማለትም የቀዳሺ በጀት ባለሙሉ መብት ሆና በንጉሱ የበላይ ጠባቂነት ለረጂም ጊዜ ከቆየች በኃላ ወጣቱ ያቀጣጠለው የለውጥ ንቅናቄ ተከትሎ አሮጌው የዘውድ አገዛዝ እየተፈረካከሰ በሄደበትና የአሮጌው በአዲሱ የመተካት የነውጥ ዘመን እየሰፋና እየተቀጣጠለ መጣ።
ቤተክርስቲያን ከአሮጌው ዘውዳዊ ንጉሰ ነገሥት አስተዳደር ታገኘው የነበረው አንድ ሶስተኛው በጀት አደጋ ላይ መውደቁ ብሎም ሊቋረጥ እንደሚችል ሥጋት የፈጠረባቸው አርቆ አስተዋዩ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ከሮማንያ ቤተክርስቲአያን ባገኙት ያስተዳደር ልምድ መሠረት አሮጌው የዘውዳዊ አገዛዝ ማብቅያ አዲሱ የለውጥ ማዕበል በሚፍገመገምበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዋጂ ቁጥር 83/65 ጥቅምት 15 ቀን 1965ዓ.ም የቤተክርስቲያን ሕልውና ለመጠበቅ አንድነቷንና አስተዳደርዋን ለማጠናከር ከንጉሳዊ ዘመን የሲሶ መንገሥት አስተዳደር ወደ አዲሱ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ አስተዳደር የሚያሸጋግር ቃለ ዓዋዲ/አዋጂ ነጋሪ በሚል ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ስያሜ ይዞ የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ሕግ ሆኖ ወጣ።
ቀጥሎም ለለውጥ ያጎፈረው ነውጥ አሮጌውን ንጉሳዊ አስተዳደር አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ለውጦ ሲተካ የቤተክርስቲያንን አንድ ሦስተኛ በጀት አከተመ። ቅዱስ ፓትርያርኩ አስቀድመው የሰጉበት ነገር ተፈጸመ።ቅዱስነታቸውም የለውጡ ሰልባ ሆነው በደርግ ተገድለው ሰማዕት ሆነው አለፉ።ቤተክርስቲያን በከተማ ያሰራቻቸው ሕንጻውችና በበጎ አደራጎት በስጦታ የተሰጡት ንብረቶችና የእርሻ መሬቶች ሁሉ ተወርሱ ልክ እንደ ብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን መሸጋገሪያ ዘመን ቃለ ዓዋዲ/ አዋጂ ነጋሪ ቃል በአሮጌው መንግሥት ማለቂያና በአዲሱ የለውጥ መንግሥት መተካት መካከል እንደ መጥምቁ ዩሐንስ ለቤክርስቲያን ብርሃን ሆኖ ተወለደ አዲሱን የቤተክርስቲያን ሕግ ዜና ታወጀ። ስሙንም ቃለ ዓዋዲ ብለው ጠሩት።
ቃለ አዋዲ የአጥቢያ ሰበካ መንፈስዊ ጉባዔን በማጠናከር ከካህናት ከምዕመናንና ከወጣቶች ተዋጽዖ በአጥቢያው ምዕመናን ምርጫ የሚሰየሙ ሥራ አስፈጻሚዎች አስተዳደርና አመራር ቤተ ክርስቲያንን የታደገና ከዚህ ያደረሰ፣ የካህናትን ኑሮ በማሻሻል፣ አብያተክርስቲያናትን በማስፋፋት፣የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልዕኮ፣ የመንፈሳዊና ዘመናዊ ተምህርትን በማጠናከር፣ የሰንበት ትምሀርት ቤቶችን በማደራጀት፣ የልማት ሥራውችን በማከናወን፣ ውላጅ አልባ ሕጻናትን በማሳደግና የመሳሰሉት አብይ መንፈሳዊ ተግባራትን እየመራ ከላይ በስፋት እንደተገለጽው የአሮጌው ንጉሳዊ አስተዳደር ለውጥ በአዲሱ መንግሥት መግቢያ አጥቢያ በቤተክርስትያን ውስጥ የተወለደ መሪ መንገድ ጠራጊ፣ ድልድይ አሸጋገሪ በመሆን ከአርባ ዓመታት በላይ ያገለገለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ባለውለታ ሃማኖታዊ ሕግና ታሪካዊ ቅርስ ነው።
ቃለ ዓዋዲ/አዋጂ ነጋሪ ቃል በቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ አርቆ አስተዋይነት በአዋጂ ጸድቆ እንዲወጣ የተደረገ ቢሆንም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እስከ 1991 ዓ.ም ድረስ ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሏል። በአርባ ዓመት እደሜው ውስጥ የበለጠ እንዲጠናከር እነ ዶክተር ብጹዕ አቡነ ገሪማ፣ክቡር ሊቀ ጉባዔ አባ አበራ በቀለ ክቡር ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው የመሳሰሉ የቤተክርስቲያን ልጆች ከፈተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በአሁኑ ወቅት ቃለ ዓዋዲ/አዋጂ ነጋሪ ቃል ከሠላሳ ስምንት ሺህ በላይ አጥቢያ አብያተ ክርስትያናትን፣አምስት መቶ ሺህ ካህናትን፣ አርባ ሰባት ሚሊዮን ምዕመናንን በቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሰጭነት በአንዲት ቤተክርስቲያን ጥላ ሥር የሚያሰተዳደር በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ብቻ ሊቀነስ፣ ሊጨመርና ሊሻሻል የሚችል የቤተክርስቲያን የበላይ መተዳደሪያ ነው።የቃለ ዓዋዲ ሃይማኖታዊ ስያሜው፣ ታሪካዊ ገጽታውና ሕጋዊ መንፈሳዊ አገልግሎቱ ባጭሩ ይህን ሲመስል የዘመንና የታሪክ አጋጣሚ ሆነና ዛሬ በመንግስት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የሀገር ውስትጥ ሲኖዶስ እና የሰደተኛው ሲኖዶስ ተብሎ የቤተክርስርቲያን መከፋፈል እጂግ በጣም የሚያሳዝን የቤተክርስቲያናችን ትልቅ የታሪክ በሽታ ሆኖ ሳለ በታሪክ አጋጣሚ በሁለቱም በኩል የተሰየሙ የሃይማኖት አባቶች ይህን በሽታ ለማከምና ለማዳን አንድነትና ወደ አንድ የቃለ ዓዋዲ/አዋጂ ነጋሪ ቃል አመራር ሊያመጣ የሚችል መደኅኒት መፍጠር አልቻሉም።
ይህ በሽታ ቤተክርስቲያኗን እያንገላታትና እያሰቃያት ያለ በመሆኑ ምዕምናን የኣንድነቱንና የእርቁን ቀን በጉጉት እየናፈቁ በሚገኙበት በአሁኑ ስዓት መከፋፈሉ ሠርግና ምላሽ የሆነላቸው ምንደኛ ደንታቢስ ካህናት ከወደቁበት ትቢያ አንስቶ ደመወዝ እየከፈለ አንቀባሮ ያሳደጋቸውን እየጦራቸው የሚገኘውን ቃለ ዓዋዲን እያፈረሱ «በገለልተኝነት» እና በማህበራት ስም እየተዋቀሩ የራሳቸው ተከታይና ጄሌ አመጸኞችን በመፍጠር የቡደን መሪ አደርገው ራሳቸውን ሹመው በተለይም በስደት ሀገር በአሜሪካና እንዲሁም በአውሮጳ የሚገኙት የምዕራቡን ዓለም የነጻነውን አስተዳደር ብሂል ምሽግ አደርገው ማን ይነካኛል! በማለት ወነአምን በሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት (ቅድስት በምትሆን ሐዋርያት በሰርዋት በአንዲት ቤተክርስቲያን እናምናለን) የሚለውን የሃይማኖት ጽሎት የሃይማኖተ የአበው ድንጋጌ በደፍረት ያለሐፍረት እያጠፉ ፈረጂያ እያጠለቁ፣ ሳይገባቸው ካባ እየደረቡ፣ ጥምጥም እያሳመሩ፣ ወገባቸውን እየሰበቁና ዘንጋቸውን የሚነቀንቁ አስመሳይ ከዳተኖችና ዋሾዎች መሳሪያ በማደረግ ጥቅም ዓይናቸውን ያወራቸው ጠባብነት ያሽመደመዳቸው ግልሰቦችን በቡደን ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያን የግል ንብረታቸው፣ የጎሳና የዘር መለያ መታውቂያቸው፣ በእግዚያብሔር ቤት የወደዱትን የሚጠቅሙበት የጠሉትን የሚያሳድዱበት ሾተላቸው፣ ከሕጉ በላይ እራሳቸውን የሚሾሙበት ጣዖታቸው፣ በአለባበስ ከብረው የሚመጻጸቁባት የጮሌዎች ሰገነታቸው እየሆነች ከመጣች ዓመታት እየተቆጠሩ ነው። ከዚም ዓልፎ በፓለቲካው መስክ ወጤት ያላመጡት ገና ዳዴ የሚሉ ነብስ ያላወቁ ፓለቲከኞች እርጦ መቋሚያና አፋቸው እንዳመጣ የፈለጋቸውን የሚናገሩበት፣ በጡረታ የተገለሉት ወደ ንስሐ ከመግባት የቤተክርስቲንዋ አንድነት ለሀገራችን ነጻነት ያደረገችወን ታሪካዊ ተግባራት ከመስበክ ይልቅ የጭቅጭቅና የንትርክ ጊዜ ማሳለፍያ አውድማ በማድረግ፣ ምዕመናን በመከፋፈል ችግሩ ከኛ ከቤተ ክርስቲኗ ባለቤት አልፎ በስደት ተጠግተን የምንገኝበትን ሀገር ፍርድ ቤቶችና የህግ አስከባሪ ፓሊሶችን እያሰቸግረንና ገንዘብን፣ ጊዜን፣የሰው ኃይልን እያባከንን፣ የካባቢ ኑዋሪዎችን ሰላም እያደፈረስን፣ እርስበርሳቸን እየትጨቃጨቅን፣ በርሳችን ላይ ድራማ እየሰራን መንገደኞች ሁሉ እየሳቁብን እንገኛለን።የዚህ ሁሉ ጥፋት የሕገ ቤተክርስቲያን ተገዥ ሆነን አለመገኘታችን በገንዘብና በሚያለፍ ቁሳዊ ነገር ሁሉ ሃይማኖትንና ታሪከን አሳፈፎ የመስጠት፤ ማንነትን አለመራዳትና እራስን የማወቅ መሠረታዊ የግንዛቤ እጦት ነው።
ቤተክርስቲያን ከራስዋ አለፋ መንግስትን እንዳላማከረች፣ በአስታራቂነትና በሸምጋይነት ከፍተኛ ጥራት ያለው አኩሪ ታሪክን ደምስሠን በአንደነት የሚያሰተዳደረንን ቃለ ዓዋዲን ባለማክበር ቤተክርስትያንን በግል ባለቤትንነት ለመያዝ በተፈጠረው ጭቅጭቅ ገላጋይ ሽማግሌ ጠፍቶ በርዋ ተዘግቶ ምእመናን ተከፋፍለው እየባዘኑ ማየት እጂግ ለህሌና የሚከብድ ጉዳይ ነው። ሁሉንም መዳኘት ማስታረቅና ማስማት የሚችል የቤተክርስቲያን ሕግጋት ብርሃን ሳለ ብርሃንነቱን አምነን ያልተቀበልን ሰዎች በጨለማ ውስጥ እየተመላለስን በርሳችን ስሜት ተነሳስተንና የቀቢጸ ተስፋ ፈረስ በምናባችን እየጋለብን በስደት ሀገር የፓለቲካ አጥቂና ባለጀብዱ መስሎ ለመታየት ምናደረገው ሙከራ የትም አያደርስም።
ከይትም የምጣ ከየት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ቤተክርስቲያን ባርኮ የከፈተና የሚከፍት፣ ከህነት የሚሰጥ፣ ወንጌል የሚያስተምር ቀድሶ የሚያቆርብ የሚመክር፣የሚገስጽ ወደሰላም የሚጠራ የሚያሰታርቅ በእጁ መስቀል የያዘ ቃለ አዲን/የአዋጂ ነጋሪ ቃል የሚያስከብር ከሃምሳ ዓመት በላይ ያገለገሉ ኢትዮጵያዊን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ኢትዩጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ አናስገባም ብሎ መንገድ መዝጋት መጮህና አመጽኝነትን ማሳየት ከየት የመጣ ሃይማኖት ነው? ከየት የመጣ ሥርዓት ነው? ከየትኛው ታሪክ የተገኘ ኢትዮጵያዊነትና ባለ ሰንደቅዓላማ ነው? መልሱን በሌላ ጊዜ በስፋት እመለስበታለሁ።
ፓለቲካውን በቤተክርስቲያን ውስጥ አስገብተን አማኙን በጎሳ እየለየን፤ በሚናገረው የካባቢ ቋንቋ እየከፋፈልን፣ በሚጠራበት ስም በጥላቻ የጎሪጥ እያየን፣ የቤተክርስቲያን ሕግ እየደመሰስን፣ የባቶችን ስም እያጠፋን ታሪክ እያበላሸን፣ ከሊቃነ ጳጳሳቱ በላይ ርሳችን ቤተክርስቲያን ጉልላት ላይ ሹመን ሕጓን ሥርዓቷን እያፈረሰን የጥፋት አዋጂ እያወጅን የሀገር ተረካቢ፣ ትኩስ ኃይል፣ የለውጥ ምንጭ፣ የነቃ የተጋ አዕምሮ፣ ቢታገል የሚጥል፣ ቢሮጥ ሊቀደም በሚችለው በአዲሱ ትውልዱ መካከል መለያየት ወይም ቅራኔ እየፈጠርንና እያደባደብን ያቀድነውን ለውጥ ከግብ እናደርሳለን ብሎ ማሰብ ገና አለመብሰልና ሊጥነት ነው።
በመሆኑም በተለይም ወጣቱ ትውልድ የተወለደበት አካባቢ፣ የሚናገርው ጎሳዊ ቋንቋ፣ ጠባብ አስተሳሰብ ሳይበግረው በኢትዮጵያዊነቱና በአምልኮቱ ብቻ ተወስኖ እጂ በአንደነት በሕብረት በመደራጀት ይችን የአንድነት ሰገነት፣የምህረት አውደምህረት፣ የማንነታችንና የታሪካችን ባለቤት፣ የሃይማኖት እመቤት፣የነጻነት ተምሳሌት፣የዕውቀት ፍኖት፣የሰላም ቤት፣ጥንታዊት ሐዋርያዊት አርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከነ ሙሉ ሥርዓቷና ሕግጋቷ ጠብቆ እንዳለች እንደነበረች ለተተኪው ትውለድ የማሰተለፍ ግዴታ የኛ ድርሻ ነው።
የአባቶቻን አምላክ ቤተ ክርስቲያንን በአንደነት ይጠብቅልን!!
መጋቤ ጥበብ መንገሻ መልኬ
ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓመተ ምሕረት
ዘመነ ማርቆስ ወንጌላዊ