.
1. የአርሲ-ሥሬና አካባቢው ተወላጆችና ወዳጆችን መረጃ /database/ በማጠናቀር ባላቸው ፍላጎትና ችሎታ ለወረዳው ልማት በግልም ሆነ በቡድን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማስተባበር፣
2. የአካባቢው ማህበረሰብ በንቃት የሚሳተፍበት በገሀር ውስጥና በውጭ በስራ፣ በትምህርት፣ በምርምር በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ እንዲሁም በንግድ የራሳቸውን ተቋም የሚመሩ የአርሲ - ሥሬ ወረዳ ተወላጆችና ወዳጆች የሚገናኙበትን መድረክ /platform/ በመፍጠር ለወረዳው ሕዝብ ልማትና እድገት አስተዋፅኦ ሊያደርጉ የሚችሉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት፣
3. በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ የወረዳው ተወላጆች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብና ታዳጊ ወጣቶች የበጎ ስራ አገልግሎት የሚሰጡበትን ስርዓት በመዘርጋት ቋሚ የበጎ ስራ አገልግሎት ባህል እንዲሰርፅ ማድረግ፣
4. የአርሲ - ሥሬና የአካባቢው ህብረተሰብ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ መልክአምድራዊና ማኅበራዊ ሃብቶችና ችግሮችን በስፋትና በጥልቀት በማጥናት እንደየ ችግሩ አሳሳቢነት በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ለፕሮጀክት የጥናትና ትግበራ /Project Study and Implementation/ ማመቻቸት፣
5. በጥናት በተለዩ ችግሮችና የተጠቆሙ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ በመመርኮዝ በተለይ የሚከተሉት የልማት ዘርፎች ላይ በማተኮር ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ እገዛ በመስጠት፡
በመንገድ፣ በከተማና የገጠር ትስስርና ልማት፣ በውሃ አቅርቦትና የኤሌክትሪክ ሀይል መሰረተ ልማት፤
በትምህርት፣ በጤና ፤ በማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት ተደራሽነት ማስፋት፤
ስነ-ምህዳር እና ተፈጥሮ ሃብት እንዲያገግም እና በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የአካባቢ ልማትና ዕፅዋት እንክብካቤ ስራዎችን ማከናወን፤
የወጣቶችን የዕውቀት፣ የስራ ፈጠራና የሙያ ክህሎት የሚያጎለብቱ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት፤
በፕብሊክ ሲክተር የሚያገለግሉ የስራ ሀላፊዎችና ሰራተኞች፣ በወረዳው የማኅበረሰብ ድርጅቶች ተጠሪዎችና ባጠቃላይ ለሕብረተሰቡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ማቀድና መተግበር፤
ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጧሪና ደጋፊ ያጡ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናት፣ በከፋ ድህነት ውስጥ ለሚገኙ ሴቶችና ወጣቶች ድጋፍ ማድረግ፤ ዘለቄታዊ መፍትሄ መስጠት፣
የማኅበረሰቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማበራዊና ትውፊታዊ ዕሴቶች ተለይተው የሚመዘገቡበትና የወረዳው ሕብረተሰብ ለረዥም ዘመን ያዳበረው በወንድማማችነት/በህትማማችነት አብሮ የመኖር ፀጋ የሚጎለብትበትና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉበት ሁኔታ ማመቻቸት፣
ትምህርት በቴክኖሎጂ የታገዘና ንቁ ትምህርት የሚሰጥበትን፣ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት የሚያመጡ ወጣቶች የሚበረታቱበትንና ከአለምአቀፍና ሃገር አቀፍ የውድድር፣ የሽልማት እና የስፖንሰርሺፕ መዋቅር ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስርዓት ዘርግቶ ድጋፍ ማድረግ፤ በተለይ ወጣት ሴቶች በትምህርት፤ በስራ አመራርና በልማት የሚኖራቸው ተሳትፎ እንዲጎለብት ልዩ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣
በኢኮኖሚ አቅም ማሽቆልቆልና በድህነት ምክንያት የሃገር መሰረት የሆነው የቤተሰብ ሚና እንዳይዳከም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች የኢኮኖሚ አቅም የሚያጎለብቱ ፕሮግራሞችን መንደፍ፣ ጠንካራ ቤተሰብ (resilient family) እንዲሆኑ ማገዝ፣
ተከታታይ የማኅበረሰብ ውይይቶችን /Community Conversation or dialogue/ በማዘጋጀት መንግስት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት የህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲዳብር፣ ለልማት እንዲነሳሳ፣ በራሱ ሀብት ተጠቅሞ መለወጥ እንደሚችል አውቆ በራስ መተማመን እንዲያዳብር ማስተማርና ድጋፍ ማድረግ፤
እነዚህን የልማት ስራዎች ለማከናወንና የሕብረተሰቡን ችግሮች ለማስወገድ እንዲቻል ከመንግስታዊ ተቋማት፣ ከሁለትዮሽና በርካታ ሀገራትን ከሚያካትቱ የልማት ተራድኦ ድረጅቶች (bilateral and multilateral development agencies) ፣ መንግስታዊ ካልሆኑ የሀገር ውስጥና የውጪ ድርጅቶች፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከአረሲ-ሥሬ ወረዳ ተወላጆችና ወዳጆች ጋር አጋርነት መመስረትና ልዩ ልዩ ስልቶችን ቀይሶ ሀብት በማሰባሰብ ፕሮጀክቶችን መተግበር፡፡