የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያን ከመመስረት ጀምሮ ሉአላዊነቷ የተጠበቀች አገር ሆና እንድትቆይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካበረከቱት መካከል በግንባር ቀደምነት ሊጠቀስ የሚችል ነው። በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ ወራሪ ሃይላት የተቃጣባትን ጥቃት በመከላከል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ጉልህ ሚና ተጫውቷል። የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያን ለመገንባት በፖለቲካው፤ በኢኮኖሚው፤ በማህበራዊ ዘርፎች ሁሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ ህዝብ ነው። በታሪክም ስንመለከት ኢትዮጵያ በአለም ዙሪያ ከምትታወቅባቸው በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች አብዛኞቹ የሚገኙት በአማራ ክልል ነው። በዚህ ዙሪያ በ12ኛው ክ/ዘመን የተሰሩትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ቢተክርስቲያናትን፤ በ16ኛው ክ/ዘመን የተሰራውን የጎንደርን አጼ ፋሲል ግንብ መጥቀስ ይቻላል። የአገራችን ብሄራዊ ቋንቋም ከዚሁ ማህበረሰብ የወጣ ነው።

የአማራን ህዝብ አሰፋፈርም ስንመለከት በአብዛኛው የሚኖረው በአራቱ ክ/ሀገራት (ጎንደር፤ ጎጃም፤ ወሎ፤ ሸዋ) እና በአዲስ አበባ ይሁን እንጂ በሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶች ሁሉ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር አብሮ ሲኖር የቆየ ህዝብ ነው።አሁንም እየኖረ ይገኛል። የአማራ ህዝብ የትኛውም የኢትዮጵያ ክልል አገሬ ነው፤ ህዝቡም ህዝቤ ነው ብሎ በጽኑ በማመን በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል የሚኖር ህዝብ ነው። የአማራ ህዝብ ራሱን እንደ አማራም እንደ ኢትዮጵያዊም የሚመለከት ህዝብ ነው። አማራነትና ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ብለን እናምናለን።

ይህ ይሁን እንጂ በስልጣን ላይ የነበረው የወያኔ ሃርነት ትግራይ አገዛዝ ለአገራችን ችግሮች በሙሉ ተጠያቂ የአማራ ህዝብ ነው ብሎ በጅምላ በመፈረጅ ከፍተኛ ግፍ ሲፈፀምበት ቆይቷል። በዚህም መሰረት በአገራችን በሚደረጉ ማንኛውም ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውጭ እንዲሆን ሆኗል። በመሆኑም የአማራ ህዝብ ደሙን አፍሥሶ ሉአላዊነቷ የተጠበቀች አገር ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላበረከተ ሁሉ በገነባት አገሩ ላይ ባይተዋር እንዲሆን፤ እንዲታሳር፤ እንዲገደል፡ እንዲፈናቀልና በአጠቃላይ የህልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ ተደርጓል። በዚህ ረገድ እየተፈጸሙ ካሉ ግፎች ውስጥ የአማራ ህዝብ ነባር ይዞታዎቹ በጉልበት እየተቀሙ ወደ ሌሎች ክልሎች በተለይም ወደ ትግራይ እንዲሆን የተደረገበት ይገኝበታል። በዚህ ረገድ እነ ሁመራን፤ ወልቃይትን፤ ጠገዴን፤ ጸለምትን፤ ራያን መተክልን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

በመሆኑም በአትላንታና አካባቢው የምንኖር አማራዎችን የሚያሰባስብ፤ የሚያደራጅ፤ በማህበረሰባችን ችግሮች ላይ በጋራ ለመምከርና የበኩላችንን አስተዋጻኦ ለማድረግ ፤ እርስ በርሳችንም ለመረዳዳት፤ ጠቃሚ የሆኑ ባህሎቻችንንም ለመጠበቅ፤ በሁለንተናዊ መልኩ የሚያግዘን ማህበር ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ማህበር መስረተናል።