ጌታ ሆይ፥ ከአንተ የሆነውን ሰማያዊ ደስታ አትንፈገኝ።
ጌታ ሆይ፥ ከዘላለም ፍርድ አድነኝ።
ጌታ ሆይ፥ በአሳብም ሆነ በአእምሮ፥ በቃልም ሆነ በሥራ ብበድል ይቅር በለኝ።
ጌታ ሆይ፥ ከአላዋቂነት፥ ከዝንጉነት፥ ከፈሪነት፥ ከልብ ጥንካሬ አድነኝ።
ጌታ ሆይ፥ከማናቸውም ፈተና አድነኝ።
ጌታ ሆይ፥ ክፉ ምኞት ያጨለመውን ልቤን አብራልኝ።
ጌታ ሆይ፥ ሰው የሆንኩት እኔ በድያለሁ፥ ነገር ግን አንተ ባለጸጋው አምላክ፥ ምሕረት አድርግልኝ፤ የነፍሴን በሽታ ታውቃለህና።
ጌታ ሆይ፥ ቅዱሱ ስምህን አክብር ዘንድ ጸጋህ እንዲያግዘኝ ላክልኝ።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ እኔን ባሪያህን በሕይወት መጽሐፍ ጻፈኝ፤ መልካም ፍጻሜ ስጠኝ።
ጌታዬ አምላኬ፥ በፊትህ ምንም መልካም ሥራ ባይኖረኝም፥ ከጸጋህ የተነሣ መልካም ጅማሬ አድለኝ።
ጌታ ሆይ፥ የጸጋህን ጠል በልቤ ላይ እርጨው፤ የሰማይና የምድር ጌታ፥ እኔን ኃጢአተኛውን አገልጋይህን በመንግሥትህ አስበኝ። አሜን
ምጽዋት በአበው አንደበት
"አንተ ልትበላው ያልፈለግኸው እንጀራ የተራቡት ሰዎች እንጀራ ነው። በቁም ሳጥንህ ውስጥ ሰቅለህ የተውከው ልብስ ዕርቃኑን የሆነው ሰው ልብስ ነው። የማታደርጋቸው ጫማዎችህ ባዶ እግሩን የሚሔድ ሰው ጫማዎች ናቸው። የቆለፍክበት ገንዘብ የደሃው ገንዘብ ነው። የማትፈጽማቸው የቸርነት ሥራዎች ሁሉ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችህ ናቸው።"
#ቅዱስ_ባስልዮስ
"አንድ ነዳይ አጥብቆ እየለመነህ በቸልታ ትተኸው ስትሔድ እግዚአብሔርን አጥብቀህ በምትለምን ጊዜ ቢተውህ የሚሰማህን አስብ።"
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
"ክርስቶስን በቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ወድቆ በሚለምነው ነዳይ ውስጥ ካላገኘኸው ውስጥ ገብተህ በመንበሩ ላይ ባለው ጽዋ ላይ አታገኘውም።"
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
"ወንድምህ ዕርቃኑን ወድቆ እያለቀሰ ነው ፣ አንተ ግን የሚያምር የወለል ንጣፍ ለመምረጥ ተቸግረህ ቆመሃል።"
#ቅዱስ_አምብሮስ
"አባት ሆይ ወጪውን ሳናሰላ እንድንመጸውት አስተምረን።"
#ቅዱስ_አግናጥዮስ
በረከታቸው ይደርብን አሜን!
ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ህንጸተ ቤተክርስቲያን ይባላል። የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የታነጸው በዛሬዋ ቀን ነው አናጺውም እራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗየተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው። ጴጥሮስ፤ ዮሐንስ በርናባስና ሌሎችም ሐዋርያት በፊልጰስዩስ ተሰብስበው ሳለ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች፤ 3 ድንጋዮችን አንስቶ ጎተታቸው እንደ ሰም ተለጠጡ እንደ ግድግዳም ሆኑ ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ በሰማያዊቷ እየሩሳሌም አምሳያ አድረጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ፤ ዳግመኛ በበነጋው ሰኔ 21 ቀን እመቤታችንን እና ቅዱሳን መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል ቅዳሴ ቀድሶ ለሐዋርያቱ አቆረባቸው ፍጹም ደስታም ሆነ። ከዚህ በኃላ ሐዋርያት ከጌታ እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተክርስቲያን አንጸዋል። ከዚያ በፊት የነበረው የነሶሎሞን ቤተመቅደስ የአይሁድ ምኩራብ የአይሁድ ስርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ስርዓት መፈጸሚያ አልነበረም፤ ታዲያ ሐዋርያት የት ነበር ህዝቡን የሚያጠምቁት የሚያቆርቡት ካሉ በየሰው ቤት ነበር። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ታላቁ ነብይ ኤልሳዕ አረፈ። ይህ ነብይ በ 12 ጥማድ በሬ ሲያርስ ቴስቢያዊው ነብዩ ኤልያስ ተከተለኝ አለው ምንም ሳያቅማማ ሀብት ንብረቱን ትቶ ተከተለው፤ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ከማረጉ በፊት ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ ይለዋል ባንተ ላይ ያደረ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ድርብ ሆኖ ይደርቢኝ ይለዋል፤ እንደ ቃሉ ሆነለት ተደረገለት፤ ኤልያስ አንድ ሙት ሲያስነሳ ኤልሳዕ ሁለት ሙት አስነስቷል፤ ኤልያስ አንድ ጊዜ ባህር ሲከፍል ኤልሳዕ ሁለት ጊዜ ባህር ከፍሏል። እምቤታችንን የኤልሳዕ ጋን ይላታል ኤልሳ የመረረውን ውኃ እንዳጣፈጠ እመቤታችንም ይህን መራራ ዓለም ጌታን በመውለዷ አጣፍጣዋለች፤ የዚህ ነብይ ድንቅ ታሪኩ 2ኛ ነገስት ላይ በስፋት ተጽፏል ሰኔ 20 ቀን እረፍቱ ነው ቤተክርስቲያን የዛሬውን ቀን እመቤታችንን እና ነብዩን አስባ ትውላለች። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።
በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ውስጥ "ዝክር" ማለት ዝም ብሎ የምግብና የመጠጥ ድግስ ማለት አይደለም። ዝክር ማለት ማሰብ፣ መዘከር፣ ማስታወስ ማለት ነው። እግዚአብሔር አምላክ በቅዱሳኑ ላይ ያደረገውን ድንቅ ሥራ እያሰብን፣ የቅዱሳኑን ገድልና ትሕትና አርአያ አድርገን፣ በስማቸው ለነዳያን የምንመጸውትበትና የበረከታቸው ተሳታፊ የምንሆንበት መንፈሳዊ ሥርዓት ነው።
እግዚአብሔር አምላክ የወዳጆቹን የቅዱሳንን ስም እንድናነሳና እንድንዘክራቸው ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚናገረው፦
"ጻድቅ ለዘላለም መታሰቢያ ይኖራል።" (መዝሙር 112፥6)
"የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፤ የኃጥአን ስም ግን ይጠፋል።" (ምሳሌ 10፥7)
ስለዚህ የቅዱሳንን ስም ጠርተን ዝክር ስናዘጋጅ እግዚአብሔር ያከበራቸውን ማክበራችንና ቃሉን መፈጸማችን ነው።
በቅዱሳን ስም የሚደረግን አነስተኛም ቢሆን ዝክር ወይም ምጽዋት እግዚአብሔር ታላቅ ዋጋ እንዳለው አስተምሮናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ላይ እንዲህ ብሏል፦
"ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።" (ማቴዎስ 10፥41-42)
ይህ ጥቅስ ዝክርን ለምን እንደምንዘክር ትልቁ ማረጋገጫ ነው። በአቅማችን ልክ በጻድቃን ስም ለነዳያን የምንሰጠው ቅምሻ የጻድቁን በረከትና ዋጋ እንድንካፈል ያደርገናል።
ብዙዎቻችን ዝክርን ወደ ይውጣንና ወደ ትዕቢት የምንቀይርበት ጊዜ አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚቀበለው ዝክር የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት አለበት፦
ዝክር የእግዚአብሔርን ስም የምናመሰግንበት እንጂ የሀብት ማሳያ ወይም የፉክክር መድረክ መሆን የለበትም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦
"ነገር ግን የምታደርጉትን ሁሉ በፍቅር አድርጉ።" (1ኛ ቆሮንቶስ 16፥14)
የዝክር ዋናው ትርጉም ለሌላቸው ማካፈል ነው። ዘመዶቻችንንና ባለጠጎችን ብቻ ጠርተን የምንደግሰው ድግስ ዝክር ሳይሆን ግብዣ ነው። ጌታችን በሉቃስ ወንጌል ላይ የመከረንን ማስታወስ ይገባል፦
"ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ፤ ምናልባት እነርሱ ደግሞ መልሰው ይጠሩሃልና ፍዳም ይሆንልሃል። ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጉደኞችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ...።" (ሉቃስ 14፥12-14)
ስለዚህ እውነተኛ የዝክር መባ በመጀመሪያ ወደ ቤተክርስቲያን ደጃፍ፣ ወደ ማኅበር፣ ወደ ታመሙና ወደ ተራቡ ወገኖች መሄድ አለበት።
አንዳንዶች "ዝክር አልዘከርኩም" ብለው በመጨነቅ ተበድረው ወይም አቅማቸው የማይፈቅደውን ትልቅ ድግስ ደግሰው ቤተሰባቸውን ችግር ላይ ይጥላሉ። ይህ ስሕተት ነው። እግዚአብሔር የሚፈልገው ልብን እንጂ የደግሱን ታላቅነት አይደለም።
የወන්දማችን የደሀዋን መበለት ታሪክ እናስታውስ፤ ያበረከተችው ሁለት ሳንቲም ብቻ ቢሆንም ጌታችን ከባለጠጎቹ ሁሉ አብልጦ አድንቆላታል። (ሉቃስ 21፥1-4)። የኢሊያስን ታሪክ ብናይም፣ የሰራፕታዋ መበለት በነቢዩ ስም ያዘጋጀችው ቅንጣት ዱቄትና ዘይት ቤቷን በረከት ሞልቶታል። (1ኛ ነገሥት 17)። ስለዚህ በአንድ ኩባያ ቆሎም ቢሆን ንጹሕ ልብ ካለ እውነተኛ ዝክር ነው።
ውድ ምዕመናን ሆይ! ዝክር በረከት የምናፍስበት፣ የቅዱሳንን አማላጅነትና ተራዳኢነት የምናገኝበት መለኮታዊ ምስጢር ነው። ዝክር ስንዘክር፦
በንስሐ ሕይወት ሆነን እንዘክር፦ የምናቀርበው መባ የተቀደሰ ይሆን ዘንድ እኛ ራሳችን ከኃጢአት የራቅን መሆን አለብን። "የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች" (ያዕቆብ 5፥16) እንደተባለ፣ በንጽሕና የቀረበ መባ ፈጣንን ቁጣ ያበርዳል።
ካህናትን እናስባርክ፦ መባችን በቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በካህናት ጸሎትና ቡራኬ ሊታገዝ ይገባል።
ትውልድን እናስተምርበት፦ ልጆቻችን የቅዱሳንን በረከት እንዲለምዱ፣ ዝክር ስንዘክር ለምን እንደምናደርገውና የቅዱሳኑን ታሪክ እያነበብንላቸው ልናሳድጋቸው ይገባል።
እግዚአብሔር አምላክ የሁላችንንም ዝክር፣ መባና ጸሎት ይቀበልልን፤ የቅዱሳኑ በረከትና አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።
ከመጥምቁ ዮሐንስ ተማሪዎች መካከል ሁለቱ "የእግዚአብሔር በግ እነሆ" የሚለውን የመምህራቸውን ስብከት ሰምተው ጌታን ተከተሉት::
"ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ፦ ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ" ዮሐ. 1:37-39
ጌታን ተከትለው የሚኖርበትን ካዩት ደቀ መዛሙርት አንደኛው ስም እንድርያስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የራሱን ስም በወንጌሉ ላይ እኔ የማይጽፈውና ቤተ ክርስቲያን ግን የራሱን ነገር ሲገልፅ በሚጠቀመው ቋንቋ የምታውቀው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነበረ::
"ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ" የሚለው ቃል በእርግጥ በጣም አስገራሚ ነው:: የክርስቶስን መኖሪያ ማየት መፈለጋቸው ፈልገው እንዳያጡት አድራሻውን ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ነበረ::
ሆኖም ክርስቶስ በምድር ላይ ሲኖር ቋሚ አድራሻ አልነበረውም:: ራሱ እንደተናገረ :-ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም" (ማቴ. 8:20)
እነዚህ ሁለት ደቀ መዛሙርት የጠየቁት "ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ?" የሚለው ጥያቄ አድራሻ ከመጠየቅ ከፍ ያለ ጥልቅ ጥያቄ ነው:: ነቢያቱ "የጥበብ ሀገርዋ ወዴት ነው? ማደሪያዋስ ወዴት ነው?" ብለው የተጨነቁለት የጥበብ ክርስቶስ ማደሪያ የት እንደሆነ ማወቅ የነፍስ ዕረፍት ነውና ተራ ጥያቄ አይደለም?
ይህ ጥያቄ ዳዊት ለዓይኖቹ እንቅልፍ ለሽፋሽፍቶቹ ዕረፍት ያልሠጠበት "የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስኪያገኝ ድረስ" የለመነበት ጥያቄ ነው::
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? የሚለው ጥያቄ እንድርያስና ዮሐንስ በአንድ ቀን ብቻ የሚመለስ ጥያቄ መስሎአቸው አብረውት ሔደው አብረውት ዋሉ እንጂ የጌታ መኖሪያ ግን ያን ቀን የዋለበት ብቻ አይደለም::
ረቢ ወዴት ትኖራለህ?
"ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ" መዝ. 43:3
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? "ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች" መዝ. 139:8 ለአድራሻ የሚያስቸግረው የረቢ መኖሪያው ብዙ ስለሆነ የት ትኖራለህ ለሚለው ጥያቄ መልሱ "መጥታችሁ እዩ" ብቻ ነው::
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ብለው ለጠየቁት ደቀ መዛሙርቱ ቦታውን ከመናገር ይልቅ "መጥታችሁ እዩ" ያለው ጌታ እርሱን ጸንተው እስከተከተሉ ድረስ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ አልፎም ከሞቱ በኋላ የሚያዩት ብዙ መኖሪያ ስላለው ነበር::
የረቢ መኖሪያው ብዙ ነው:: "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፡ ወደ እርሱም እንመጣለን፡ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን" እንዳለ ቃሉን የሚጠብቅ ሰው ሰውነትም የእርሱ ማደሪያ ነው:: (ዮሐ. 14:23)
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? " በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና" ስትል ሰምተንህ ነበር:: (ዮሐ. 14:2) የአንተ መኖሪያ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን? ቅዱስ ጳውሎስ "ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" ሲል እንደሰማነው እስከ ዐሥር ሰዓት ድረስ እንደመዋል ዐሥሩ መዓርጋት ላይ የደረሱ በጽድቅ መንገድ የሔዱ የሚያዩት ማደሪያህ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን? መጥተን ለማየት "እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ" እስክትለን በተስፋ እየጠበቅን አይደለምን?
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ካሉት ጠያቂዎች መካከል አንዱ ዮሐንስ መሆኑን ሳስብ ደግሞ ዮሐንስ ያያቸው የረቢ መኖሪያዎች ከገሊላ እስከ ታቦር ተራራ ፣ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ ፣ ከወንጌል እስከ ራእይ እጅግ ብዙ እንደነበሩ ታየኝ::
"ወዴት ትኖራለህ?" ብሎ ጠይቆ ጌታን የተከተለው ዮሐንስ "መጥተህ እይ" በተባለው መሠረት የጌታን መኖሪያ የእርሱን ያህል ያየም ሰው የለም::
ዮሐንስ "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" ለሚል ጥያቄው ግን አንጀት የሚያርስ ልብ የሚያሳርፍ መልስ ያገኘው አርብ ዕለት መስቀሉ ሥር ነበር:: ወዴት ትኖራለህ? ላለው ዮሐንስ የዘጠኝ ወር ከተማውን የዘላለም ማረፊያውን "እነኋት እናትህ" ብሎ ሲሠጠው መጥቶ ካያቸው የረቢ መኖሪያዎች ሁሉ የምትበልጠውን መኖሪያ አየ:: "እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ፦ ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ" ብሎ የመረጣትን ማደሪያ ከማየት በላይ ምን ክብር አለ? (መዝ. 132:13)
ዮሐንስ ይህችን የረቢ መኖሪያ ወዲያው ወደ ቤቱ ወሰዳት:: ዮሴፍ ሊወስዳት ስላልፈራ ምን እንዳገኘ ያውቃልና እርሱም ይህችን የዕንቁ ሳጥን ወደ ቤቱ ወስዶ ቢዝቁት የማያልቅ ጸጋን ተጎናጸፈ::
ጌታ እናቱን ለዮሐንስ መሥጠቱ የሁለት ድንግልናዎች ማስረጃ ሆነ:: የድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልናም የዮሐንስ ድንግልናም በጌታ ንግግር ታወቀ::
አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ድንግል ማርያም ከጌታ ሌላ ልጆች ቢኖሩአት ኖሮ "እናቴን ከልጆችዋ ነጥለህ ወደ ቤትህ ውሰዳት" "አንቺም ልጆችሽን ይዘሽ ወደ ሰው ቤት ሒጂ" ብሎ ለዮሐንስ አይሠጣትም ነበር:: ድንግል ማርያም የአብን አንድያ ልጅ አንድያ ልጅዋ አድርጋለችና አምላክ ባደረበት ዙፋን ሌላ ፍጡር ያላስቀመጠች የአምላክ ብቸኛ ዙፋን ፣ እግዚአብሔርን አስገብታ በርዋን የዘጋች ዘላለማዊት ድንግል መሆንዋ ለዮሐንስ በመሠጠትዋ ታወቀ:: ዮሐንስም ቤት ንብረት የሌለው መናኝ ባይሆንና ሚስት ድስት ያለው ሰው ቢሆን ድንገት ወደ ቤቱ ይዞአት እንዲሔድ እናቱን ባልሠጠው ነበር::
የሰው ልጅ ድኅነት ታሪክ በሁለት "እነሆ"ዎች መሃል መከናወኑ እጅግ ይደንቃል:: የሰው መዳን የተጀመረው "እነሆኝ የጌታ ባሪያ" ብላ ራስዋን ለፈጣሪ በሠጠችው ድንግል ቃል ሲሆን የተጠናቀቀው ደግሞ "እነኋት እናትህ" ብሎ በደም በታጠበ አንደበቱ በነገረን የኑዛዜ ቃል ነው::
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ለእኛም አታሳየን ይሆን? እስከ ዐሥር ሰዓት መዋል ፣ ዐሠርቱን ትእዛዛትህን ፣ ዐሥሩን የቅድስና ደረጃዎችን መውጣት ላቃተን ለእኛስ መኖሪያህን ታሳየን ይሆን? መጥታችሁ እዩ የሚለውን ጥሪ ሰምተን ለማምጣት አቅም ላነሰን መጻጉዕዎች ፣ ዓይን ላጣን በርጤሜዎሶች ተነሡ እዩ ብለህ መኖሪያህን አታሳየን ይሆን? መቅደስህን እንመለከት ዘንድ ፣ መኖሪያህን መንግሥትህን እናያት ዘንድ ፣ ዮሐንስ ያያትን መኖሪያህ እናትህን እናይ ዘንድ እንመኛለን::
ረቢ ወዴት ትኖራለህ?
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መስከረም 21 2016 ዓ.ም. ተጻፈ
"ማርያም ገጸኪ እፈቱ ርእየ
ድንግል ድንግል ንዒ ኀቤየ
እስመ ኪያኪ ጸምአት ነፍስየ"
ወተዘከርኒ ለኃጥእ ገብርኪ ተክለ ማርያምመ