ህይወት አጭር ነች።
ሰዓታት እያለፉ ነው። ቀናት እያለፉ ነው። ወራት እያለፉ ነው። ዓመታት እያለፉ ነው።
ለ 100 ዓመታት ትኖራለህ እንበል። እድለኛ ከሆንህ በዓለም ላይ ያለው ሰው የሚኖረው አማካይ ዕድሜ 72 ዓመት ብቻ ነው (3,700 ሳምንታት አካባቢ)።
ረጅም ጊዜ ሊመስል ይችላል ግን አይደለም። 30 ዓመት ከሆንህ 1,500ውን ሳምንት ጨርሰሃል። ይህን የምላችሁ ላሳዝናችሁ ወይም የማንነት ቀውስ ውስጥ እንድትገቡ አይደለም ፥ ግን እንደምናስበው ብዙ ጊዜ እንደሌለን እንድታውቁ ነው።
የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። አስቀድመን እንደምናውቀው እና ሺ ጊዜ እንደተነገረን ያለንን ጊዜ በደንብ እየተጠቀምንበት ነውን? የምታደርጋቸውን ነገሮች ትወዳለህ? ከምትወዳቸው ሰዎች ጋር ነህ? የምትጠላውን ነገር ለማድረግ ወይም ማድረግ የምትፈልገውን ነገር ላለማድረግ ህይወት አጭር ናት። ስታረጅ ጸጸቱ የከፋ ይሆናል።
ዕድሜህ ወደ ሰማንያ እንደተቃረበ አስብ ፥ ወደኋላ መለስ ብለህ ስታስብ ወይኔ እነዚህን ነገሮች እንደዚህ ባደረኳቸው ብለህ ስትመኝ ። ሌሎች እንደፈለጉት ሳይሆን ህይወትን አንተ እንደፈለካት ለመኖር።
ሰነፍ ሆነህ ሶፋህ ላይ ተቀምጠህ ቲቪ እያየህ ባሳለፍካቸው ሰዓታት ይቆጭሃል። ያለ ዓላማ በየቀኑ ለሰዓታት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተጎለትክባቸው ጊዜያት ይጸጽቱሃል። የሚፈልገውን የማያደርግ ማንም ሰው ከውስጡ ደስተኛ አይሆንም።
ለጥቂት ደቂቃዎች አስብ ፥ 80 ዓመት ሲሞላህ ለምን ትፀፀታለህ?
ሊያጋጥምህ የሚችሉ ጥቂት ጸጸቶች እነሆ፡-
1. የምትወደውን ባለማድረግህ
2. ሰነፍ በመሆንህ እና ጊዜህን በማባከንህ።
3. ከቤተሰብህ ጋር ብዙ ጊዜ ባለማሳለፍህ
4. ጤናህን እና ደህንነትህን ባለመጠበቅህ.
5. ምንም ለማያስገኝልህ ነገር ጠንክረህ በመሥራትህ
6. በወጣትነትህ ጊዜ ጉዞ ባለማድረግህ
7. ህይወትህን ባለማጣጣምህ
የምትፈልጋቸውን ነገሮች ለምን ማድረግ እንደማትችል ሰበብ ማቅረብ አቁም። እነዚህን ነገሮች አቁም።
ለአእምሮህ መልስ መስጠት አቁም ፣ ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀምር። አእምሮህ መንገድ እንዲያገኝ ያስገድደዋል።
ጊዜው ትክከለ እንስኪሆን እየጠበቅህ ጊዜህን ማባከን በጣም መጥፎው ሰበብ ነው ፣ እና
በኋላ ትጸጸታለህ። ትክክለኛ ጊዜ የለም። ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው።
ዓለምን ለመጓዝ ከፈለግህ, አሁን በጣም ጥሩው ጊዜ ነው።
ንግድ ለመጀመር ከፈለግህ አሁን በጣም ጥሩው ጊዜ ነው።
ወደ ጂምናዚየም መሄድ ከፈለግህ አሁን በጣም ጥሩው ጊዜ ነው።
በኋላ እራስህን ታመሰግናለህ።
ግቡ የምንችለውን ያህል ጥሩ ኑሮ መኖር መሆን አለበት። እና ወደፊት የምንጸጸትበት ግን በየቀኑ እያደረግን ያለነው በጣም ብዙ ነገሮች አሉ ።
በዚህ ተከታታይ ቪዲዮ የየዕለት ተግባራቶችህን እንድታውቅ ማድረግ እና ወደፊት ምን አይነት ተጽዕኖ እንደሚያደርሱብህ ላሳይህ እሞክራለሁ። ይህን ተከታታይ ቪዲዮ ካየህ በኋላ ሰነፍ መሆንህን ታቆምና ማድረግ የምትፈልገውን ማድረግ ትችላለህ ብዬ አምናለሁ።
ቪዲዮው በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ነው። የመጀመሪያው አስተሳሰብህ ላይ በማተኮር የተሻለ እና ሰላማዊ ህይወት እንዴት መኖር እንደምትችል የሚያሳይ ነው ፥ ሁለተኛው ስንፍናን አሸንፈው ውጤታማነትህን እንድታሳድግ የሚረዱህ ስልቶችንና ዘዴዎችን የያዘ ነው።
ጊዜው እያለቀ ነው። አሁንን መኖር ጀምር።
ክፍል 1
አስተሳሰብ
ቢራቢሮዎችን ለመያዝ በማሳደድ ጊዜህን ካጠፋህ በረው ይሄዳሉ ፥ የሚያምር የአበባ ቦታ በማዘጋጀት ጊዜህን ካጠፋህ ግን ራሳቸው ይመጣሉ።
አታባርር ፣ ሳብ!
100% ኃላፊነት
" ታላቅ ለመሆን የምትከፍለው ዋጋ ኃላፊነት መውሰድን ነው። "
--- ዊንስተን ቸርቺል
ለችግሮችህ ሁሉ ሌላውን መውቀስ ጥቅም የለውም። ጓደኛችህን ፣ ቤተሰብህን ፣ የትዳር አጋርህን ወይም ማንኛውንም ሰው መውቀስ ትችላለህ። ሌሎችን የመውቀስ ጥሩው ነገር በእደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ምንም ማድረግ አልችልም ነበር ብለን ራሳችንን በማሳመን ውስጣችን ደስ እንዲሰኝ ያደርጋል ፣ ግን ይህ ስህተት ነው። ሁልጊዜ የሆነ ነገር ማድረግ ትችላለህ። ሁኔታውን ባትቀይርም ካሉት አማራጮች የተሻለውን ነገር ማድረግ ትችላለህ።
ሌሎችን መውቀስ ምንም አይጠቅምም ፥ ችግሮችህን አይፈታም። ስፖርት ለመስራት በቂ ጊዜ ስላጣህ ጓደኞችህን ፣ ቤተሰቦችህን ፣ ስራህን ወይም ሌላ ነገር እየወቀስህ ነው እንበል። መላው ዓለምን መውቀስ ትችላለህ። የፈለግኸውን ነገር ብትወቅስ ስፖርት ለመስራት በቂ ጊዜ አያስገኝልህም። መፍትሄ ስለሌለው አይደለም ፥ መፍትሄ ማግኘት ከፈለግህ ታገኛለህ ። መፍትሄው አለ ፣ ልቦናህም ያውቀዋል። ሌላ ነገር ሳይሆን ድርጊት ብቻ ነው ግብህን እንድታሳካ የሚረዳህ። ማንም ግብህን እንድታሳካ አይረዳህም።
ደካማ ብትሆንም ባትሆንም ማንም ግድ አይሰጠውም።
ዛሬ መስራት ያለብህን ለነገ ብታሳድር ማንም ግድ አይሰጠውም።
ስፖርት ብትሰራ ባትሰራ ማንም ግድ አይሰጠውም።
ለምን ግድ ይሰጣቸዋል? ማንም ግድ አይሰጠውም። ነገሮችን ለራስህ ብለህ ብታደርግ የተሻለ ነው። ወደ ተግባር መግባት አለብህ ፥ ጊዜ ልታገኝ ይገባል!
ወጥተህ ለጤንነት ከመሮጥ ይልቅ ሶፋ ላይ ቁጭ ብለህ ቲቪ ማየት ይቀላል።
መጽሐፍ ከማንበብ ይልቅ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መዘፍዘፍ ይቀላል።
ጠንክረህ ከመስራት ይልቅ የዛሬን ስራ ለነገ ማሳደር ይቀላል።
አዕምሮአችን ሁልጊዜ ወደ ቀላሉ አማራጭ ያዘነብላል። ቀላሉን ምርጫ ሳይሆን ምርጡን ምርጫ እንዲመርጥ ማድረግ አለብህ!
ችግሮቻችንን ከመጋፈጥ ይልቅ የምንወቅሰውን አካል እንፈልጋለን ፥ ምክንያቱም መውቀስ ቀላል ስለሆነ። የሆነ ሰውን ትወቅሳለህ ፣ ቡም ፣ ራስህን ከኃላፊነት ነፃ ታደርጋለህ። ያደረግኸው ወይም ያላደረግኸው እያንዳንዱ ተግባር ህይወትህ ላይ ተፅዕኖ አለው። ከዚህ በኋላ ሌሎችን ስትወቅስ የሚያስከትልብህን ውጤትም አስብ! ነገህ የሚወሰነው በአሁን ድርጊትህ ላይ ነው።
ስላለፈው አታስብ ፥ አንዴ አልፏል። ያለፈው ጊዜ ሊሰጥህ የሚችለው ሁለት ነገሮችን ብቻ ነው። ትምህርት እና ፀፀት።
ከትናንት ተማር ግን ህይወትህን እንዲቆጣጠር አትፍቀድለት። ስህተት መስራት ችግር የለውም ፥ ነገር ግን አንድን ስህተት የምትደጋግመው ከሆነ ችግር አለ። ደ * ደ * ብ አትሁን! ስህተትን አትውደድም አትጥላም! ስህተትን ከጠላህ ትፈራዋለህ። ከመጠን በላይ ስለ እሱ ማሰብ ትጀምራለህ። የአዕምሮህን ሰላም ይነሳዋል። ምንም እንዳታደርግ ያሳስርሃል። ስህተትን ከወደድክ በብዛት ታደርገዋለህ ምክንያቱም የምትስበው የምትወደውን ነገር ነው።
ስህተት ከተፈጠረ ተማርበት እና ጉዞህን ቀጥል። ጊዜህን አታባክን! ወደፊት ካልተጓዝግ ሁለተኛ ስህተት እየሰራህ ነው።
የህይወት መራር እውነታዎች
ሰነፍ ከሆንክ የራስህ ጥፋት ነው።
ደስተኛ ካልሆንክ የራስህ ጥፋት ነው።
ስራህን ለነገ የምታስተላልፍ ከሆነ የራስህ ጥፋት ነው።
ኃላፊነት ከመቀበል ብትሸሽ ምን ትጠቀማለህ? ምንም። በህይወትህ የሆነ ነገር መለወጥ ከፈለግህ ለድርጊቶችህ ኃላፊነት የምትወስደው አንተ እንደሆንክ ማወቅ አለብህ! ልታሳካ የምትፈልጋቸው ነገሮች የሚሳኩት በአንተ ብቻ ነው። ማንም አያሳካልህም። ማማረር ምንም አይጠቅምም ፥ አዕምሮህን በጭንቀት እና በመጥፎ ሀሳቦች ይሞላዋል። ሁልጊዜ ከመጠን በላይ ማሰብ እና ማማረር ለአዕምሮህ ጤንነት መጥፎ ነው። ወደ ተግባር መግባት አለብህ። ዛሬ መጀመር ትችላለህ ወይም እስከ ነገ መጠበቅ ትችላለህ፥ ምርጫው የአንተ ነው።
" ዛፍ ለመትከል ምርጡ ጊዜ ከ 20 ዓመት በፊት ነው ፥ ሁለተኛው ምርጡ ጊዜ አሁን ነው። "
-- የቻይናዎች አባባል
ስህተቶች እንደምታስበው መጥፎ አይደሉም
ስህተት መስራት ችግር የለውም። የሆነ ነገር ስትሰራ መሳሳትህ የማይቀር ነው። ያለ ነው። ግን ለስህተቶችህ ኃላፊነት መውሰድ አለብህ! ለምታደርጋቸው ድርጊቶች ሁሉ ኃላፊነት መውሰድ ይጠበቅብሃል። ከስህተቶችህ ተማር እና ወደፊት ተራመድ። በህይወትህ ወደፊት ለመራመድ ፍጥነት ያስፈልግሃል። እዚያው ተቀምጠህ ስለ ስህተቶችህ ማሰብ የለብህም። ቀኑን ሙሉ ምንም ሳታደርግ ተቀምጠህ የምትውል ሰነፍ ሰው ካልሆንክ በስተቀር ስህተት ይፈጠራል። ስህተት መስራትን በመፍራት እጅህን አጣጥፈህ መቀመጥ የለብህም! ወደማታውቀው ነገር ዘለህ መግባት አለብህ!
" ስኬት ስህተት ባለመስራት ውስጥ አይገኝም ፥ ያንኑ ስህተት ባለ መድገም ውስጥ እንጂ "
--- ጆርጅ በርናርድ ሾው
ጉዳይህ ላይ ብቻ አተኩር
ይህ ቀላል ምክር የበለጠ ውጤታማ ያሰርግሃል። ጉዳይህ ባልሆነ ነገር አትጨነቅ። ነገሩ አንተ ላይ ተፅዕኖ የማያደርስ ከሆነ ስለነገሩ አትጨነቅ። ሰዎች በማያገባቸው ነገር ሁሌ ይጨነቃሉ። በሚያገባህ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት አድርግ። በህይወትህ ውስጥ ወሳኙ ሰው አንተ ነህ ፥ ግብህ ለራስህ ምርጡን ማድረግ ላይ ይሁን። ስለ ሌሎች ሰዎች አስተያየት መጨነቅ አቁም! የምትሰማቸው 99% አስተያየቶች ውሸት ናቸው እናም አይጠቅሙህም። ራስህን እመን።
" ሙሉ ትኩረትህን በራስህ ጉዳይ ላይ አድርግ ፥ ለሌሎች የሆነው ነገር የእነርሱ ጉዳይ እንደሆነ እና የአንተ እንዳልሆነ ግልጽ ይሁንልህ።"
--- ኢፒክትፕስ
ማንም ሊያድንህ የሚመጣ የለም
ማንም ህይወትህን መቀየር አይችልም። ማንም ህይወትህን ለመቀየር ፍላጎት የለውም። የራሳቸው ህይወት ተመሰቃቅሎ ሳለ ያንተን ህይወት እንዴት አድርገው ይለውጡታል? ራስህ ማድረግ ነው ያለብህ ፥ በእጅህ ነው። ሰነፍ ሆነህ ሌሎች ህይወትህን እስኪለውጡት መጠበቅ ትችላለህ ፥ ነገር ግን ለዘላለም ነው የምትጠብቀው። የሆነ ሰው ግቤን እንዳሳካ ያደርገኛል የሚለውን ሀሳብ ከአዕምሮህ አውጥተህ ጣለው። በሌሎች ሰዎች ላይ ጥገኛ መሆንህን አቁም! ሰነፍ ሆኖ ከመቆየትና በህይወትህ የሆነ ቁም ነገር ከመስራት ከሁለቱ የመምረጥ አቅም አለህ።
የአንድ ገበሬ ምሳሌ አለ
አንድ ገበሬ ነበር። የስንዴ ማሳ አለው። በስንዴ ማሳው ውስጥ የወፍ ጎጆ ነበር ፥ በጎጆው ውስጥ ለወፏ አራት ልጆች ነበሯት። ወፏ በየቀኑ ከጫካ ምግብ እያመጣች ትናንሽ ልጆቿን ትመግብ ነበር። አንድ ቀን ከጫካ ስትመለስ ልጆቿ ፈርተው አገኘቻቸው። ምን እንደተፈጠረ እና ለምን እንደፈሩ ጠየቀቻቸው። እነርሱም ገበሬው ዛሬ መጥቶ ስንዴውን ከማሳው ላይ ስለማጨድ ሲያወራ ነበር። እህሉን እንዲያጭዱ ነገ ልጆቹን እንደሚልክ ተናግሯል አሉ። ልጆቿን ካዳመጠች በኋላ ወፏ ነገ ስንዴውን ለማጨድ ማንም አይመጣምና አትፍሩ አለቻቸው።
በሁለተኛው ቀን ወፏ እንዳለችው ሆነ። እህሉን ለማጨድ ማንም አልመጣም። ብዙ ቀናት አለፉ ፣ እህሉን ለማጨድ ግን ማንም አልመጣም ነበር። ሁሉም ነገር መልካም ነበር። የወፏ ልጆችም ደስተኞች ነበሩ።
አንድ ቀን ወፏ ከጫካ ስትመለስ የልጆቿን ፊት አይታ ደነገጠች። ዛሬም ፈርተዋል። ለምን እንደፈሩ ወፏ ጠየቀቻቸው። ዛሬም ገበሬው መጥቶ እህሉን ስለማጨድ እንዳወራ ነገሯት። ነገ ሰራተኞች መጥተው እህሉን እንደሚያጭዱ ተናግሯል : ወፏ ካዳመጠቻቸው በኋላ ነገ ማንም እንደማይመጣና መጨናነቅ እንደሌለባቸው ነገረቻቸው።
በሁለተኛው ቀን ወፏ እንዳለችው ሆነ። እህሉን ለማጨድ ማንም የመጣ የለም። ከዚያም ብዙ ቀናት አለፉ። ግን እህሉን ለማጨድ ማንም አልመጣም።
በሌላ ቀንም ወፏ ከጫካ ስትመለስ የልጆቿን የፍርሃት ፊት አየች። ለምን እንደፈሩ ጠየቀቻቸው። ገበሬው ዛሬም መጥቶ እህሉን ስለማጨድ ሲያወራ ነበር። ነገር ግን ዛሬ ሌሎች ሰዎችን በመጠበቅ ብዙ ጊዜ እንዳባከነ እና ነገ ራሱ መጥቶ እህሉን እንደሚያጭድ ሲናገር ነበር አሏት። ወፏ ካዳመጠች በኋላ ነገ ይህንን ቦታ ለቀን ሄደን ጎጆአችንን ሌላ ቦታ እንሰራለን አለች። ነገ ገበሬው እህሉን ያጭዳል - ለዚያም ነው ነገ ከዚህ መሄድ ያለብን!
በቀጣዩ ቀን ላይ ወፏ እንዳለችው ሆነ። ገበሬው መጥቶ እህሉን አጨደ : ይህንን ካዩ በኋላ የወፏ ልጆች ሁሌ እሷ ያለችው እንዴት እንደሚሆን ጠየቋት :
ወፏም - ገበሬው በመጀመሪያ በልጆቹ ላይ ጥገኛ ነበር ፣ ቀጥሎ በሰራተኞች ላይ ጥገኛ ሆኖ ነበር : ለዚያም ነው ስራው ያልተጠናቀቀው :
ሶስተኛው ላይ ግን ማንም ላይ ጥገኛ አልሆነም : ለዚያም ነው በዚህ ጊዜ ነገሩን ማሳካት የቻለው።
3 ዓይነት ሰዎች
በዙሪያዬ ሁሌ የማያቸው 3 አይነት ሰዎች አሉ።
1, አንደኛው አይነት ሰዎች በፍጹም የማይጀምሩ ናቸው : ምንም ነገር አይሰሩም : ሰነፍ ሆነው ዝምብለው ይቀመጣሉ : ህልማቸውን ለማሳካት ምንም አያደርጉም : ማድረግ የሚጠበቅባቸውን ነገር አያደርጉም : የሆነ መልካም ነገር እስኪሆንላቸው ይጠባበቃሉ።
2, ሁለተኞቹ የሚጀምሩ ሰዎች ናቸው : ነገሮች ሲከብዱባቸው ግን ተስፋ ይቆርጡና ያቆማሉ : በኋላ ላይ ግን ስላቆሙ ይቆጫሉ።
3, ሶስተኞቹ ጠንክረው የሚሰሩ ናቸው። ምንም አይነት ከባድ ሁኔታ ቢፈጠር ተስፋ አይቆርጡም : ስኬታማ የሚሆኑ አንድ ፐርሰንት ሰዎች ናቸው።
አንድ ሰው ማቋረጥ የለበትም! ነገሮች ሁሌ በተሳለጠ ሁኔታ አይቀጥሉም : ነገሮች እየተበላሹ ሊሆን ይችላል ፣ ወደፊትም ሊበላሹ ይችላሉ። መንገድህ ላይ መሰናክሎች ሊኖሩ ይችላሉ : ግን ወደ ግብህ መራመድ አለብህ።
ህይወት እንደ አጭር ርቀት ሩጫ አይደለችም : እንደ ማራቶን ናት : ግማሽ ላይ ለሚያቋርጡ ሽልማት የለም : የሆነ ስኬት ላይ ለመድረስ የመጨረሻውን መስመር መድረስ አለብህ!
መቆጣጠር የምትችለውን ብቻ ተቆጣጠር
መቆጣጠር የምትችለውንና የማይትችለውን ለይተህ ማወቅ አለብህ : ልትቆጣጠራቸው የማትችላቸው ነገሮች ባቀድከው መሰረት ካልሄዱ አትዘን : ሁሉም ነገር ከቁጥጥርህ ውጪ አይደለም : ህይወትህን የሚያሻሽሉ መቆጣጠር የምትችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ : አዕምሮህን መቆጣጠር ትችላለህ : ምን ያህል መስራት እንዳለብህ መቆጣጠር ትችላለህ : ነገር ግን ሌሎች ሰዎች ስለ አንተ የሚያስቡትን መቆጣጠር አትችልም : መቆጣጠር ስለማትችላቸው ነገሮች መጨነቅ ህይወትህን ያመሰቃቅለዋል።
የምቾት ቦታ ጠላትህ ነው
የምቾት ቦታ የሚያምር ቦታ ነው ፥ ግን ምንም አይበቅልበትም!
ሰዎች ሰነፍ የሚሆኑበትና ሁሉንም ነገር ለነገ የሚያሳድሩበት ምክንያት አሁን ባላቸው ህይወት ምቾት ስለተሰማቸው ነው። ነገሮች አሁን ያሉበትን መልክ እንዲቀይሩ አይፈልጉም። ሁሌ የምታደርገውን ነገር ማድረግ ቀላል ነው ፥ ግን ወደ ምትፈልገው እድገት አይመራህም። ዕድገት ከምቾት ክልልህ ወጥተህ ከባድ ነገሮችን መስራትን የሚጠይቅ ነገር ነው። ቀኑን ሙሉ ፊልም በማየት ፣ ዜና በማንበብ ፣ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመጣድ መዋል ቀላል ነው ፥ ግን ትርጉም የለውም : አንተም ታውቀዋለህ። ጊዜህን እያባከንክ እንደሆነ ሰውነትህ ያውቀዋል : ትርጉም እና ዋጋ ላለው ነገር መሰዋት የሚገባ ጊዜህን ስታባክን የበታችነት ስሜት ይሰማሃል።
ዕድሜህን በሙሉ ጊዜህን በማባከን ማሳለፍ ትፈልጋለህ? ጊዜህ እያለቀ ነው : ከጥቂት ጊዜ በኋላ የምትፈልገውን ለማድረግ አቅም ታጣለህ : አሁን አድርገው! የሆነ ነገር እስኪሆን በተስፋ መጠባበቅህን አቁም! ምንም ነገር አይሆንም: ራስህ እንዲሆን ማድረግ አለብህ!
የምቾት ቦታውን ከለቀቀ በኋላ" ምናለ እዛው በቆየሁ" ማንም አይልም: ስራዎችን ለነገ ማሳደር ስታቆም እና የፈለግኸውን ማድረግ ስትጀምር ደስታ ይሰማሃል: የምትፈልገውን ነገር ለማድረግ ከእንቅልፍህ እንደመነሳት ያለ ደስታን የሚሰጥህ ነገር የለም!
ቀለል አድርገው
የሆነ አዲስ ነገር ስትሞክር በተቻለህ መጠን ቀለል ልታደርገው ሞክር: በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ለማድረግ አትሞክር! ሊበላሹ ስለሚችሉ ነገሮች ብዙ አታስብ: ብዙ ጊዜ ምንም አይበላሹም: ማድረግ ያለብህ ነገር በተቻለህ መጠን በፍጥነት መጀመር ነው: በአስቸኳይ ልታደርግ ይገባል: ነገሮችን በፍጥነት ለመጀመር ቸኩል: የምትፈልገውን ውጤት ለማግኘት ሳይሆን ነገሩን ራሱን መስራት ለመጀመር ቸኩል: ለምሳሌ website ( ድህረ ግጽ ) መስራትን መማር ፈለግህ እንበል: አሁን መጀመር ትችላለህ ወይም ዝምብለህ መጠበቅ ትችላለህ።
ፍጥነት ወሳኝ ነገር ነው: አለኝ ብለህ የምታስበውን ያህል ጊዜ አይደለም ያለህ! ነገሮችን ቀለል አድርገህ አስብ: በብርሃን ፍጥነት መስራት ጀምር!
" አብዛኞቹ ውሳኔዎች መወሰን ያለባቸው ስለ ነገሩ የሚጠቁሙ 70% አከባቢ ያህል መረጃ ካለ ነው: 90% መረጃ እስኪኖርህ ከጠበቅህ ልታረፍድ ትችላለህ"
------ ጄፍ ቤዞስ
በተለየ መንገድ ለማሰብ ሞክር
" ሁሉም ሰው በተመሳሳይ መንገድ እያሰበ ከሆነ የሆነ ሰው እያሰበ አይደለም ማለት ነው"
------- ጆርጅ ፓቶን
እንደ ሌላው ሰው ማሰብ አይጠበቅብህም: በራስህ መወሰን ትችላለህ : እንደ ማንም ባታስብ ችግር የለውም።
የተለየ ውጤት ማግኘት ከፈለግህ በተለየ መንገድ ማሰብ እና የተለየ ነገር መስራት አለብህ! ሁሉም የሚያደርገውን እያደረግህ የተለየ ውጤት መጠበቅ የለብህም! ባለፉት ጊዜያት ያደረግኸውን ነገር እያደረግህ በዚህ ዙር የተለየ ውጤት መጠበቅ አትችልም! ብዙ ጊዜ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው: ሰነፍ ከሆንክ ውጤቱን ታውቀዋለህ : እንደ ባለፈው አይነት ነው!
ግልጽ የሆነ ግብ አስቀምጥ
ቶሎ ሊደረጉ የሚችሉ እና ግልጽ ግቦችን ማስቀመጥ አለብን! ትልቅና የሚያጓጓ ግብ ማስቀመጥ ችግር የለውም: ግን ችግሩ ሰነፍ ሰው ከሆንክ ያንን ግብ ለማሳካት ጠንክረህ አትሰራም ምክንያቱም ለማሳካት ከባድና የማይቻል ይመስልሃል።
ለዚያም ነው ስትጀምር ትናንሽ እና ለማሳካት ቀላል የሆኑ ግቦችን ማስቀመጥ ያለብህ።
ግቦችህ ግልጽ ሊሆኑ ይገባል: ለምሳሌ :- በ1 ወር 2 ኪሎ ክብደት ለመቀነስ ማቀድ ግልጽ የሆነ ግብ ነው : ጤነኛ ለመሆን ማቀድ ግልጽ ያልሆነ ግብ ነው።
የማይለካ እና የጊዜ ርዝመት የሌለው ግብ ግብ አይደለም: ተአምር እስኪፈጠር እየጠበቅህ ነው።
ግቦችህን ጻፋቸው
ግቦችህን ወረቀት ላይ የማትጽፍ ከሆነ አሁን መጻፍ መጀመር አለብህ: አትጸጸትበትም! ግቦችህን ከጻፍክና በየጊዜው የምታነባቸው ከሆነ ያነቃቁሃል: የጻፍከውን ካልተገበርክ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማሃል: የግብህን ግማሽ እንኳን ማሳካት ከምንም ይሻላል!
በኋላ ይጸጽትሃል
ማድረግ የምንፈልገውን የማናደርግ ከሆነ እና ለነገ የምናሳድረው ከሆነ ነገሩ ይነዘንዘናል: ሰላማችንን ይነሳል ምክንያቱም ሰነፍ እንደሆንንና ያንን ተግባር ማድረግ ሲጠበቅብን እንዳላደረግን አዕምሮአችን ስለሚያውቅ!
አርቀህ አስብ
ሁለት ነገሮችን ማድረግ ትችላለህ: አርቀህ አስበህ ለወደፊት የሚጠቅሙህን ነገሮችን ማድረግ እና የአሁን ምኞትህን ብቻ እያረካህ ነገህን መርሳት:
አሁን የምታደርገው ድርጊት ነገህ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ እንዳለው ማወቅ አለብህ! በእርግጠኝነት የምነግርህ አንድ ነገር በስንፍናህ ምክንያት ሁሌ ትጸጸታለህ: ስንፍና አሁን ላይ ያስደስታል ምክንያቱም ለአሁኑ ዶፓሚን ይሰጥሃል: ነገር ግን ነገህ ላይ መስራት የምትፈልገውን ነገር ባለመስራትህ ትጸጸትበታለህ!
ጊዜያዊ ደስታዎችን መተው አለብህ: ከባድ ነገሮችን መስራት : ጥቂት የሚያስጨንቁ ነገሮችን መቀበል: መስዋዕትነትን መክፈል - የነገን ግብ ለማሳካት ሲባል።
አሁን ላይ ደስታ የሚሰጥህን ነገር ሙሉ በሙሉ ተው እያልኩህ አይደለም: አንዳንዴ ትናንሽ መስዋዕቶች ለተሻለ ነገ ወሳኝ ናቸው!
Risk ተቀበል ( አደገኛ ነገርን ተቀበል)
አደገኛ ነገሮችን አትፍራ! በህይወትህ ምንም ነገር ለማሳካት ከፈለግህ ከምቹ ቦታ ወደ ማይመች ቦታ መግባት አለብህ! Risk ባለመቀበልህ ምክንያት የሚደርስብህ ፀፀት ከባድ ነው ፥ ሙሉ ህይወትህን ልትፀፀት ትችላለህ: risk መቀበል አስፈሪ ነው ፥ መሆንም አለበት: ግን risk አለመቀበል ደግሞ የበለጠ አስፈሪ ነው።
" አደገኛው ነገር አደገኛ ነገርን አለመሞከር ነው : በፍጥነት በሚለዋወጥ ዓለም ውስጥ ትክክለኛ ያልሆነ ውሳኔ ቢኖር risk አለመቀበል ነው "
--- ማርክ ዙከርበርግ
ሁሉንም ነገር ወይ ጥሩ ነው ወይ መጥፎ ነው ብለህ ማሰብህን አቁም! ብዙ መጥፎ ነገሮች ሆነውብኛል እናም አሁን ደስተኛ ነኝ ምክንያቱም ህይወቴን ቀይረውታል። አንድ ታሪክ አለ
አንድ ገበሬ ለእርሻ የሚያገለግል ፈረስ አለው: መንደርተኞቹ ገበሬው እንደዚህ አይነት አሪፍ ፈረስ ስላለው እድለኛ እንደሆነ ሁሌ ይነግሩታል: " ሊሆን ይችላል " ብሎ ይመልሳል ገበሬው
አንድ ቀን ፈረሱ ጠፋ: መንደርተኞቹም ገበሬውን ሊያጽናኑት መጡ:
" መጥፎ ነገር ሆኖብሃል" አሉት መንደርተኞቹ
" ሊሆን ይችላል " ብሎ መለሰ ገበሬው
ከ ጥቂት ቀናት በኋላ ፈረሱ ከ 10 ጠንካራ ፈረሶች ጋር ወደ ቤት ተመለሰ:
" የሚገርም ነገር ነው ፥ አይደለም እንዴ?" አሉ መንደርተኞቹ።
" ሊሆን ይችላል" አለ ገበሬው በድጋሚ
በቀጣዩ ቀን የገበሬው ልጅ ከፈረሶቹ አንዱን ሲጋልብ ፈረሱ ረገጠውና የልጁን እግር ሰበረው።
መንደርተኞቹ ማዘናቸውን ለመግለጽ መጡ።
" መጥፎ ነገር ነው የሆነው " አሉ
" ሊሆን ይችላል" ብሎ መለሰ ገበሬው
በቀጣዩ ቀን የጦር ወታደር አዛዥ መጥቶ ሰውነታቸው ደህና የሆኑ ወጣት ልጆችን ለጦርነት መልምሎ ይዞ ሄደ: እግሩ የተሰበረው የገበሬው ልጅ ሳይመለመል ቀረ:
መንደርተኞቹ ተደስተው " ልጅህ ሳይዘምት ቀረ ፣ ምን አይነት ደስ የሚል ዕድል ነው?" አሉ።
ገበሬው ፈገግ አለና " ሊሆን ይችላል" አለ።
ዲሲፒሊን
"ሁላችንም በሁለት ምክንያቶች በህመም ውስጥ እናልፋለን: ራሳችንን ስርአት በማስያዝ ወይም በጸጸት "
--- ጂም ሮህን
ግለ ዲሲፒሊን ማለት አሁን ላይ ለማድረግ የሚከብዱህን ለነገ ግን የሚጠቅሙህን ነገሮች ማድረግ ነው።
ወደ ጂም መሄድ ከባድ ነው ፣ ሶፋ ላይ መቀመጥ ቀላል ነው።
ቢዝነስ መጀመር ከባድ ነው ፣ ስራን ለነገ ማሳደር ግን ቀላል ነው።
በጠዋቱ መነሳት ከባድ ነው ፣ በሞቀ አልጋ መተኛት ቀላል ነው።
መጽሐፍትን ማንበብ ከባድ ነው ፣ ፊልም ማየት ግን ቀላል ነው።
ህይወትህን የሚያሻሽሉ ነገሮች ሁሉ ከባድ ናቸው ፥ ሁልጊዜ ራስህን ይህን ጥያቄ ጠይቅ
ይህንን ባለማድረጌ ምክንያት ነገ ላይ ይጸጽተኝ ይሆን?
መልሱ አው ከሆነ ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም ነገሩን ማድረግ አለብህ!
መደረግ ያለበትን አድርግ
" የሚያስገርሙ ሀሳቦች እጥረት የለብንም ፥ የጎደለው ተግባሩ ነው " -- ሴት ጎዲን
ዲሲፒሊን ማለት መደረግ ያለበትን ነገር ማድረግ ነው። ጠንክሮ መስራት ከሆነ ጠንክረህ ትሰራለህ : በተሻለ መንገድ መስራት ከሆነ በተሻለ መንገድ ትሰራለህ: መስራት የምትፈልገውን ነገር ከባድ ስለሆነ ብቻ ከመስራት ወደ ኋላ አትበል!
ለነገ ማሳደር የዲሲፒሊን ጠላት ነው
ለነገ ማሳደር ማለት መደረግ ያለባቸውን ስራዎች ምክንያት እየደረደሩ ለበኋላ ማቆየት ማለት ነው። ምክንያት ካልደረደርን መጥፎ ስሜት ይሰማናል ፣ ስለዚህ የተለያዩ ምክንያቶችን እናስቀምጣለን። ከምንደረድራቸው ምክንያቶች ታዋቂው " ትክክለኛውን ጊዜ እየጠበቅሁ ነው " የሚል ነው። ጊዜ መቼም ትክክለኛ ሊሆን አይችልም : ፍጹም ጊዜ የለም: ሁልጊዜ በመንገድህ እንቅፋት ይኖራል: ብዙ ነገሮች ሰነፍ ሊያደርጉህ እና ለነገ እንድታዘዋውር ሊያደርጉ ይጥራሉ: አንተ ግን ልታሸንፍ ይገባል።
እርካታህን አቆየው
እርካታን ማቆየት ከባድ ነው : ምክንያቱም አሁኑኑ መደሰት እንፈልጋለን: ይሄ ችግር የለበትም ግን ችግሩ ነገህን የሚጎዳ ነገር ማድረግ ስትጀምር ነው:
በሁለቱም አቅጣጫ ማየት አለብህ: አሁንን እና ወደፊትን : አሁንን መደሰት አለብህ : ግን ነገህን ጎድተህ መሆን የለበትም! ሰነፍ በመሆንህ ዛሬም ላይ ነገም ላይ አትደሰትበትም!
አሁን አድርገው!
" ሳታደርገው መሞት የምትፈልገውን ነገር ብቻ ለነገ አሳድረው " - ፓብሎ ፒካሶ
ጊዜው መቼም ትክክለኛ ሊሆን አይችልም: ከሆነም ከረፈደ በኋላ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው: የፈለግኸውን ያህል መጠበቅ ትችላለህ: ምንም አይፈጠርም : ወይም አሁን ጀምረህ ግቦችህን ወደማሳካት መንቀሳቀስ ትችላለህ። ትክክለኛ ጊዜ ፣ የተሻለ ሀብት ፣ የበለጠ ልምድ መጠበቅ የለብህም! ዛሬ ላይ አሪፍ ዕቅድ ባይኖርህም ነገሩን ጀምረህ የሚሆነውን እያየህ መቀጠል ትችላለህ።
የብልሃት መንገድ የለም
ቀለል ያለ መንገድ መፈለግህን አቁም! ቀለል ያሉ የብልሃት መንገዶችን ልታውቅ ትችላለህ ነገር ግን ስራውን መስራት አለብህ! ብዙ ሰዎች ከማድረግ ይልቅ በመማር ላይ ብዙ ትኩረት ያደርጋሉ። መማር ጥሩ ነው ግን ብቻውን በቂ አይደለም: ነገሮችን መስራት መጀመር አለብህ: ከመጀመርህ በፊት ቀላል ስልቶችን መፈለግህን አቁም! መጀመሪያ ጀምር - ከዚያ ነገሩን በፍጥነት የምታስኬድበትን ዘዴዎች ተማር!
ውድቀት እንዲያቆምህ አትፍቀድለት
በህይወት ሁሌ ውጣ ውረድ አለ: አንዳንዴ ሊሳካ ይችላል አንዳንዴ ደግሞ አይሆንም:
አንድ ታሪክ እነሆ
አንድ ጊዜ አንድ ንጉስ የእሱን ጠቢባን ሰዎች ሁሉ ጠራና - በሁሉም ጊዜ ፣ ቦታ ፣ ሁኔታ ውስጥ የሚሰራ ምክር ወይም ሀሳብ ይኖራችኋል? አለ: በሁሉም ደስታ ፣ ሀዘን ፣ ድልና ሽንፈት ውስጥ የሚሰራ? ለሁሉም ጥያቄዎች አንድ መልስ:
ሁሉም ጠቢባን በጥያቄው ግራ ተጋቡ: አንድ ሽማግሌ ሁላቸውንም የሚያስማማ ሀሳብ አመጣ: ወደ ንጉሱ መጡና በወረቀት ላይ የሆነ የተጻፈ ነገር ሰጡት: ግን መቼም በመጓጓት ከፍቶ ማንበብ እንደሌለበት ነገሩት።
በጣም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ፣ ብቸኛ ሲሆን ፣ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ሲመስለው ብቻ ከፍቶ ማየት እንደሚችል ነገሩት: ንጉሱ ወረቀቱን በአልማዝ ቀለበቱ ስር አስቀመጠው።
ከጊዜ በኋላ ጎረቤቶቹ ግዛቱን አጠቁ: ንጉሱና ሰራዊቱ በኃይል ተዋጉ ነገር ግን ጦርነቱን ተሸነፉ: ንጉሱ በፈረሱ ሸሸ: ጠላቶቹ እየተከታተሉት እየቀረቡት ነበር: ድንገት ንጉሱ ራሱን በመንገዱ መጨረሻ ላይ አገኘ: መንገዱ ወደየትም አይወስድም: ከታች ረጅም ድንጋያማ ሸለቆ አለ: ከዘለለ ያበቃለታል : ወደኋላ እንዳይመለስ ደግሞ መንገዱ ጠባብ ስለሆነ አይችልም: የጠላቶቹ ፈረሶች ኮቴ በፍጥነት እየቀረበው ነው: ንጉሱ ተጨነቀ: መንገድ የለም!
ድንገት የቀለበቱ አልማዝ ፀሐይ አርፎበት ሲያንፀባርቅ ውስጡ ያስቀመጠው ወረቀት ትዝ አለው: አልማዙን ከፍቶ መልእክቱን አነበበው: መልእክቱ " ይህም ያልፋል" ይላል።
ንጉሱ ደግሞ አነበበው: በድጋሚም አነበበው: ድንገት የሆነ ነገር ነካውና - በትክክል! ይህም ያልፋል አለ: ከጥቂት ቀናት በፊት በግዛቴ ውስጥ ነበርኩ : ከሁሉም ነገስታት ኃያሉ ነበርኩ: አሁን ግን ግዛቴም እርካታዬም ሁሉም ሄዷል: ይኸው ከጠላቶች ለማምለጥ እየሞከርኩ ነው: እነዚያ የቅንጦት ቀናት እንዳለፉት ይሄም የስጋት ቀን ያልፋል! ፊቱ ላይ መረጋጋት ተነበበ: እዛው ባለበት ቆመ: የቆመበት ቦታ ተፈጥሮአዊ ውበቱ አስደናቂ ነበር: እንደዚህ የሚያምር ቦታ በግዛቱ ውስጥ እንዳለ አያውቅም ነበር።
መልእክቱን መረዳቱ ትልቅ ለውጥ ፈጠረበት: ተረጋጋ እና ሲከተሉት የነበሩትን ረሳቸው: ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የጠላቶቹ እና የፈረሶቹ ኮቴ ድምጽ እየራቀ ሲሄድ አስተዋለ: ንጉሱን ፍለጋ ወደ ተራሮች ሌላኛው በኩል ርቀው ሄዱ።
ሰራዊቱን እንደገና አቀናጅቶ ጦርነቱን በድጋሚ ተዋጋ: ጠላቶቹን አሸነፈ እና ግዛቱን አስመለሰ: ከድል በኋላ ወደ ግዛቱ ሲመለስ በሙዚቃ አቀባበል ተደረገለት: ሙሉ ከተማው በድሉ ተደሰተ።
ሁሉም ሰው የደስታ ድባብ ውስጥ ነበር: ከየቤቱ ንጉሱ ላይ የአበባ ጎርፍ ከሰዎች ይወረወርለት ነበር: ሰዎች እየደነሱ እና እየዘፈኑ ነበር: ንጉሱ " እኔ ከኃያላን እና ከታላቅ ነገስታት ውስጥ አንዱ ነኝ ፥ እኔን ማሸነፍ ቀላል አይደለም" ብሎ አሰበ። ግን ድንገት ቀለበቱ ላይ ያለው አልማዝ በፀሐይ ብርሃን አንጸባረቀ እና መልእክቱን አስታወሰው: ከፈተው እና ድጋሚ አነበበው: " ይህም ያልፋል!"
ትክክለኛውን ነገር አድርግ
ትክክለኛውን ነገር እያደረግሁ ነው? ብለህ ራስህን መጠየቅ አለብህ!
መደረግ የሌለባቸውን ነገሮች ማድረግ ጥቅም የለውም: የምትሰራውን ስራ ካልወደድከው ሁሌ ትደክማለህ: የምትሰራውን ነገር ለመቀየር ይሄ ምክንያት ነው: ትርጉም ያለውን ነገር ስራ: ትርጉም የሌለውን ነገር ስትሰራ መቼም አትነቃቃም።
ስራህ ተደጋጋሚ እና ጣዕም አልባ ከሆነ በስራው ውስጥ ትርጉም እና እርካታ ማግኘት ከባድ ይሆናል።
ከህይወት ይልቅ ዋጋ ያለው ስራ የለም: የምትወደውን ነገር ነው መስራት ያለብህ፥ ስራህ ሲከብድ ደግሞ መሸሽ የለብህም!
የሆነ ሰው ቀለም ቀቢ መሆን ይፈልጋል: ግን የሰዎችን ምክር ሰምቶ ሀኪም ሆነ። ውስጡ ያለውን ነገር ያለማዳመጡ ፀፀት ሁሌም አዕምሮው ውስጥ ይኖራል።
ስራ ደስታ ነው
የሆነ አይነት ስራ እየሰራህ ረጅም ጊዜ ልታባክን ትችላለህ: የምትፈልገውን ነገር ካልመረጥክ የሆነ ሰው ይመርጥልሃል: ግን ላትወደው ትችላለህ።
በሌሎች የተመረጠልህ ስራ ለአንተ እንደ ዕዳ ነው: ነገር ግን የምትሰራውን ስራ የመረጥከው ራስህ ከሆንክ ደስተኛ ነው የምትሆነው። ስራህ የደስታህ መንገድ ነው: ስራህን ካልወደድከው ደስተኛ መሆን አትችልም: ስራህን ካልወደድከው ስራህን ለመስራት አትነቃቃም: ስራህን ከወደድከው ስንፍና አይኖርም: ስንፍና የሚባለውን ሀሳብ ራሱ ትረሳዋለህ።
አንድ ምክር አለኝ :- ስራህን ካልወደድከው ስራህን የምታቆምበትን መንገድ በተቻለህ ፍጥነት ፈልግ: በሚያሳዝንህ ስራ ውስጥ መቼም ደስተኛ መሆን አትችልም: የምትሰራውን ነገር ውደድ:
ውስጥህን አዳምጠው - ይመራሃል።
ከከባባድ ነገሮች አትሽሽ!
የምትወደውን ስራ ማለት ከስራህ ውስብስብ ክፍሎች ሽሽ ማለት አይደለም: ሙሉ አቅምህን አትጠቀም ማለት አይደለም: ሰነፍ ሁን ጠንክረህ አትስራ ማለት አይደለም።
ሁሌም አዲስ ነገር ስንጀምር መነቃቃታችን ከፍ ያለ ነው : በከፍተኛ ደስታ ነው የምናደርገው መነቃቃታችን እስኪጠፋ ድረስ: የስራው ውስብስብ ክፍሎች መገለጥ ይጀምራሉ: ችግሮች መፈጠር ይጀምራሉ: ፈተናው ከፍ ይላል: ለስራችን ያለን ስሜት መቀነስ ይጀምራል ምንም እንኳን የምንወደው ስራ ቢሆንም።
ውስጣዊ ፍላጎታችን ነው: ውስጣዊ ፍላጎትን መከተል ሁሌ ደስተኛ ለመሆንህ ዋስትና አይደለም።
ቪንሰንት ቫን ጎግ 27 ዓመቱ በሆነ ጊዜ ሙሉ ማንነቱን ለስዕል ሰጠ: በጣም በመሰጠት ይሰራ ነበር: መሳልን ሙሉ ህይወቱ አደረገ: በጣም ውጤታማም ነበር: በብርሃን ፍጥነት ይስል ነበር: ምንም እንኳን ጠንካራ ሰራተኛ እና ጎበዝ ቢሆን ስዕሎቹ ስለማይሸጡለት እና ከጊዜው ስለቀደመ የገንዘብ ችግር ያጋጥመው ነበር። ታናሽ ወንድሙ ቲኦ ቫን ጎግ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግለት ነበር: የአዕምሮ ጤናው እየተዛባ ሄደ: ሐምሌ 27 : 1890 መስክ ላይ እየሳለ በራሱ ሽጉጥ ደረቱ ላይ ተኮሰ: ከሁለት ቀናት በኋላ ሞተ።
ቅድሚያ መስጠትን ልመድ
ሁሉንም ነገር በአንዴ መስራት አንችልም: የተገደበ ጉልበት ነው ያለን : በተገቢው መንገድ መጠቀም አለብን: እዚህም እዚያም በታትነን ራሳችንን አድክመን ያለ ውጤት መቅረት የለብንም! ውጤት ካላየህ እና ከደከምክ ተስፋ የመቁረጥ ዕድልህ የሰፋ ነው: በተወሰኑ ስራዎች ላይ ጉልበትህን ማፍሰስ አለብህ! በአንድ ጊዜ ጥቂት ነገሮችን ስትሰራ የተሻለ ነው።
አታባርር - ሳብ
ምንም ነገር አታባርር: ከምንም ነገር ኋላ አትሩጥ: ሁሉም ነገር ወደ አንተ ተስቦ እንዲመጣ ራስህን አሻሽል! ራስህ ላይ ትኩረት አድርግ! ሌላው ነገር በራሱ ይስተካከላል።
ታላቅ ሰው ነህ
ምንም ነገር ማድረግ የማትችል ሰው እንደሆንክ ለአዕምሮህ አትንገረው: ማድረግ ትችላለህ! ለአዕምሮህ አሉታዊ ነገር እየመገብክ የራስህ ጠላት አትሁን! ነገሮችን ማድረግ እንደምትችል በራስህ እርግጠኛ ሁን! ሰዎች ሰነፍ እንደሆኑ የሚኖሩበት ትልቁ ምክንያት ብቁ እንዳልሆኑ ሁሌ ስለሚያስቡ ነው: ታላቅ ሰው ነህ: ማድረግ ጀምር: በመጨረሻም ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል።
እንከን አልባነትን የሚፈልግ ሰው አትሁን
ከእንከን ነፃ የሆነ ነገር መፈለግ በሽታ ነው ፥ ስራን ለነገ ማሳደር በሽታ ነው ፥ መድኃኒቱ ተግባር ነው። -- ኒቺ ኖርቶን
እንከን አልባ መሆን መጥፎ ነው እያልኩ አይደለም: ነገር ግን በህይወትህ እያንዳንዱ ክፍል ላይ ፍጹምነት መኖሩ ጉዳቱ ያመዝናል። ውብ ነገሮች ሊኖሩ የቻሉት በጥቃቅን ነገሮች ላይ ሳይቀር የተጠበበበት ሰው ስላለ ነው: ያለ ፍጹምነት ዓለማችን ገራሚ አትሆንም ነበር: ጥራታቸው የወረደ ነገር በዙሪያችን ይሞሉ ነበር: ዓለማችን ውብ የሆነችው ከነ ፍጽምናዋ እና ከነ እንከኗ ነው።
ሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ ጥቃቅን ነገሮች ላይ ትኩረት ያደርግ ነበር: አንድ ስዕል ለመሳል ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል: የሚላንን ካቴድራል ዲዛይን ሲያወጣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዲዛይኖችን አውጥቷል: ታዋቂዋን ሞናሊዛን ለመሳል ከ10 ዓመታት በላይ ፈጅቶበታል።
ስቲቭ ጆብስም ጥቃቅን ነገሮች ላይ የሚጨነቅ ሰው ነው: የመጀመሪያውን የማኪንቶሽ ኮምፒውተር ዲዛይን ሲያደርግ የሰርኪዩት ቦርድ ላይ ሽቦዎች በቀጥተኛ መስመር የሚሄዱ እና የሚያምሩ መሆን እንዳለባቸው በጥብቅ ፈልጎ ነበር: ምንም እንኳን ውስጡን ከቴክኒሺያን ውጪ ማንም ከፍቶ የማያየው ቢሆንም።
ስዕል የምትስል ወይም የሆነ ነገር የምትፈጥር ከሆነ በተቻለ መጠን ፍጹም ቢሆን ጥሩ ነው: ነገር ግን ከቀናት በኋላ ተመልሶ የሚበቅል ሳር የምታጭድ ከሆነ እያንዳንዱ የሳር አቆራረጥህ ፍጹም እንዲሆን በማሰብ ጊዜህን ማቃጠል የለብህም።
የቱጋ ፍጹም የሆነ ስራ መስራት እንዳለብህ እና እንደሌለብህ ለይተህ ማወቅ አለብህ: አንዳንዴ ፍጹምነት ያስፈልጋል ፥ አንዳንዴ አያስፈልግም: ሁሉም ስራ ላይ ለጥቃቅን ነገሮች ካልተጨነቅሁ ብለህ አታስብ: እንደሁኔታው ተቀያየር : ስንፍናህን ነገሮችን ፍጹም በማድረግ ውስጥ አትደብቅ!
"ውሳኔው የሚቀለበስ አይነት ከሆነ በፍጥነት ወስን ፥ ውሳኔው የማይቀየር ከሆነ ዘግይተህ ወስን! " -- ሼን ፓሪሽ
ተግባር ከፍጹም ይሻላል
ግዴታ ሁሉም ነገር በፍጹም ጥንቃቄ ነው መሰራት ያለበት ማለት አይደለም: በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚያልቀውን ስራ ፍጹም ለማድረግ ቀናትን መፍጀት የለብህም: ሰነፍ ሰዎች በመጨረሻም የሆነ ፕሮጀክት ለመስራት ሲወስኑ አላስፈላጊ በሆኑ ጥቃቅን ነገሮች ላይ በማተኮር ይጨናነቃሉ: በጥቃቅን ነገሮች ይደክሙና ስራውን ሳይጀምሩት ይቀራሉ።
እንደ ሁኔታው አትሁን!
ታላቅ የመሆን ወይም እንደ ሁኔታው የመሆን ምርጫ ሁሌ አለን: ታላቅ መሆን ቀላል አይደለም: በየዕለቱ ያለህን ምርጡን ጥረት መስጠት ይጠበቅብሃል: አለመሳካቶች ያጋጥማሉ: ብዙ ትለፋለህ: እንደሁኔታው ለመሆን ግን ምንም ማድረግ አይጠበቅብህም: በህይወትህ ዓላማህ በጭራሽ መካከለኛ ሰው መሆን አይደለም: ምርጡን ጥረትህን መስጠት አለብህ: እንደሁኔታው የሚኖሩ ሰዎች ምርጡን አያደርጉም: ነገሮች ትንሽ ሲስተካከሉ ይረካሉ: ወደፊት መራመድ ከጀመሩ ነገሮች እንደሚከብዱ ያውቁታልና።
99% የሚሆኑ ሰዎች ከሚፈልጉት ነገር ባነሰ ነገር ረግተዋል: ለሚጠሉት ስራ ረግተዋል ከዚያ ለምን ውጤታማ እና ደስተኛ እንደማይሆኑ ፣ መነቃቃት እንደሌላቸው ፣ ስራቸውን ለመስራት ለምን ጉልበት እንደሚያጡ ግራ ይገባቸዋል።
የምትጠላውን ነገር እያደረግህ እንዴት ደስ ብሎህ ትነቃለህ?
" ስራህ የህይወትህን ትልቁን ክፍል ይሸፍናል ፥ ትክክለኛ እርካታ የምታገኝበት ብቸኛው መንገድ አሪፍ ስራ ነው ብለህ የምታምንበትን ነገር ስትሰራ ነው: አሪፍ ስራ የምትሰራበት ብቸኛ መንገድ ደግሞ የምታደርገውን በመውደድ ነው: ካላገኘኸው ፍለጋህን ቀጥል: አትርጋ: ነገሩን ስታገኘው ታውቀዋለህ: ልብህን ይነግርሃል።" --- ስቲቭ ጆብስ
ማንም መካከለኛ መሆን አይፈልግም: ካላመንክ የሆነን ሰው ጠይቅ " ተራ ሰው መሆን ትፈልጋለህ?" መልስህን ታገኛለህ: መልሱ ሁልጊዜም አይ የሚል ነው።
ሰዎች ተራ የሚሆኑበት አንዱ ትልቁ ምክንያት በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ተራ ስለሆኑ ነው: ትንሽ ጉጉት እንዳለህ ሲያዩ ሰዎች ያንን ጉጉትህን የሚያጠፋ ብዙ ነገሮችን ይነግሩሃል: እንድታበራ አይፈልጉም: ምናልባት ሊፈልጉም ይችላሉ: ግን ተራ ካልሆንክ ያንተ እንደዛ መሆን መጥፎ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል።
ልጅ በነበርን ጊዜ ብዙ ህልሞች እና ፍላጎቶች ነበሩን: የሆነ ነገር ተፈጠረና ከዚያም ሁሉም ተራ የሆነ ህይወትን መረጠ።
በትልቁ አስብ!
ብትወድቅ እንኳን ነገሩን ባለመሞከርህ ምክንያት ከሚሰማህ ፀፀት ታመልጣለህ: አስብ እስኪ 80 ዓመት ሆኖህ ህይወትህን ወደ ኋላ እያየህ ምናለበት ዓለምን በዞርኩ ፣ ህልሜን ባሳካሁ ፣ ሌሎች እንደሚፈልጉት ሳይሆን እኔ እንደምፈልገው በኖርኩ ብለህ ስትመኝ።
አሁንም ጊዜ አለህ: ቢያንስ አሁን አለህ: ግን አንድ ቀን ምንም ነገር ለማድረግ ጊዜ አይኖርህም: ሞት በርህ ላይ ይጠብቅሃል።
ህይወትህን ሁሌ ማድረግ የምትፈልገውን እያደረግህ ኑር: ስኬታማ የመሆን ሚስጥሮችን አትፈልግም: ሰነፍ መሆንህን ታቆማለህ ምክንያቱም የዓላማ ስሜት ውስጥህ ላይ ስለሚሰማህ።
ስራህን ካልወደድከው ቀይረው!
ጓደኞችህን ካልወደድካቸው ቀይራቸው!
አስተሳሰብህን ካልወደድክ ቀይረው!
ህይወትህን ካልወደድክ ቀይረው!
የታላቅነት ህይወት ከተራ ህይወት ይልቅ እንደሚከብድ አስታውስ! ቀላል አይደለም: ግን ልፋቱ ውጤት አለው!
በአንዴ ብዙ ስራ የመስራት ጉዳት
"ሁለት ጥንቸሎችን የሚያሳድድ አንዷንም አይዝም! "--- ኮንፊሺየስ
ብዙ ስራ በአንዴ ለመስራት መሞከር በእንግሊዘኛው multitasking ይባላል። ጥሩ ይመስላል ግን አይሰራም! በአንዴ በብዙ ጠቃሚ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ አንችልም: ሁለት መደረግ ያለባቸው ስራዎች ካሉ ሁለቱንም ለማድረግ መሞከር ውጤታማነትህን ይቀንሰዋል። ከአንደኛው ወደ ሌላኛው ስራ ቶሎ ቶሎ የምትዘል ከሆነም ሊያደክምህ ይችላል።
አሁን ላይ እያደረግህ ባለው ነገር ላይ ሙሉ ትኩረትህን ማድረግ አለብህ! ስራዎችህን ስትቀያየር ትኩረትህን ይቀንሰውና ትልቅ ተጽዕኖ የሚያመጡ ጥቃቅን ስህተቶችን ልትሳሳት ትችላለህ። ብዙ ስራህን በቀያየርክ ቁጥር ቶሎ ትደክማለህ : ለጥቃቅን ነገሮች ትኩረት መስጠት ያቅትሃል። ስራዎችን ስንቀያይር የጭንቀት መጠንም ከፍ ይላል።
የበለጠ ውጤታማ የሚያደርጉህ 3 ነጥቦች
1, ስራ መቀያየርን መተው - አንድ ስራን በሙሉ ትኩረት ስራ ከዚያም ወደ ሌላኛው ስራ ግባ!
2, ከምትሰራው ስራ የሚረብሹህን ሁሉንም ነገሮች አስወግድ - አሁን በምትሰራው ነገር ላይ ሙሉ ትኩረት ስጥ!
3, በስልክህ ላይ ያሉ አላስፈላጊ notifications አጥፋ!
ትኩረት !
ውጤታማነትህን ለማሻሻል ማድረግ የምትችለው አሪፉ ነገር በአንድ ጊዜ አንድ ስራ ላይ ትኩረት በማድረግ ነው: ጠቃሚ ነገሮች ባነሰ ትኩረት መሰራት የለባቸውም! ሙሉ ትኩረታችንን ይሻሉ።
ለምሳሌ ሶስት ነገሮችን መስራት ፈለግህ እንበል: የተሻለው መንገድ አንደኛውን ስራ በሙሉ ትኩረት ሰርቶ ወደ ሁለተኛው ከዚያም ወደ ሶስተኛው መሻገር ነው። መጥፎው መንገድ ደግሞ ሁሉንም ስራዎች በአንዴ ለመስራት በማሰብ ከአንዱ ስራ ወደ ሌላው በየ አምስት ደቂቃው መቀያየር ነው። ውጤታማ እንደሆንክ ሊሰማህ ይችላል ግን አይደለህም። ምንም ነገር ትኩረትህን እንዲሰርቅ አትፍቀድለት!
Nap አድርግ
ለረጅም ጊዜ በትኩረት ስትሰራ የአዕምሮህ ጉልበት ይዳከማል: በዚህ ጊዜ ማድረግ ያለብህ ምርጡ ነገር ሸለብ ማለት ነው። ለሁሉም ሰው ላይሰራ ይችላል ግን ማድረግ ከቻልክ ጥሩ ነው: የበለጠ በትኩረት እንድትሰራ ኃይል ታገኛለህ: ረጅም አትተኛ ፣ እጥር ምጥን ያለች nap ውሰድ: ቀን ላይ ደግሞ ረጅም ከተኛህ ማታ እንቅልፍ ልታጣ ትችላለህ።
መሰናክሎች አይኑሩ!
በጥሩ ሁኔታ መስራት የምንችለው በሌሎች በተደጋጋሚ የማንረበሽ ከሆነ ነው: አዕምሮው በጥሩ ሁኔታ መስራቱን ለመጀመር የተወሰነ ጊዜ ይፈልጋል: በነገሮች በተደጋጋሚ የምትረበሽ ከሆነ ግን ትኩረት ማድረግ አትችልም እናም ውጤታማነትህ ይቀንሳል።
በጣም ወሳኙ ነገር
ብዙ ስራዎችን የምትሰራ ከሆነ የትኛው በጣም ወሳኝ እንደሆነ እወቅ: ግብህን እንድታሳካ የማይረዱህን አስፈላጊ ያልሆኑ ድርጊቶችን አስወግዳቸው! በሁሉም ህይወት ውስጥ ባይደረጉም ልዩነት የማያመጡ ድርጊቶች አሉ: የሰዎች ትልቁ ረብሻ ወሳኝ የሆነውን ነገር ትተው አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን መስራት ይጀምራሉ።
የሁሌ ልማዶች
'በየቀኑ የምታደርገውን ነገር እስካልቀየርክ ድረስ ህይወትህን በጭራሽ መቀየር አትችልም! የስኬትህ ሚስጢር ያለው የሁልጊዜ ልማድህ ውስጥ ነው።" ጆን ማክዝዌል
የሁልጊዜ ልማድ ማበጀት በጣም ጠቃሚ ነው። የምትከተለው የሆነ ልማድ ሊኖርህ ይገባል! ጥሩ ልማድ ከሌለህ ስራህን ያለማቋረጥ ልትሰራ አትችልም: የሆነ ቀን ተነቃቅተህ ልትሰራ ትችላለህ : ሌላ ቀን መነቃቃትህን አጥተህ ስራህን ለነገ ልታሳድር ትችላለህ።
የሁሌ ልማድ እንዳታቋርጥ ያግዝሃል: የበለጠ ትኩረት እንድታደርግ ያግዝሃል ፣ ጠቃሚ ስራዎችን እንድትጨርስ ያግዝሃል። የሁሌ ልማድ ከሌለን ወሳኙን ሳይሆን ቀላሉን ስራ መስራትን ነው የምንመርጠው።
በየዕለቱ የምታደርገው ነገር ነገህን ይወስነዋል: አንተ - ባለፉት ጥቂት አመታት ያደረግሃቸው ነገሮች ድምር ውጤት ነህ: ማንነትህን ለመቀየር በየዕለቱ የምታደርጋቸውን ነገሮች መቀየር አለብህ።
ልማድ ቀጣይ ምን ማድረግ አለብኝ ብለህ እንዳትጨነቅ ያግዝሃል:
ቀላሉን ሳይሆን ትክክለኛውን ምርጫ ምረጥ!
ብቻህን ተቀመጥ
"የሰው ልጅ ሁሉም ችግሮች የሚመነጩት ብቻችንን ክፍል ውስጥ ዝም ብለን መቀመት ስላቃተን ነው " ብሌይዝ ፓስካል
ብቻህን ተቀምጠህ በህይወቴ ምን እያደረግሁ ነው ፣ የማደርገው የትኛው ድርጊቴ ነው ህይወቴን ከማሻሻል ይልቅ የከፋ የሚያደርገው የሚለውን ማሰብ አለብህ። ይህንን ቀላል ድርጊት በየቀኑ ከ 5-10 ደቂቃ ደጋግመው እና ስለ ህይወትህ ግልጽ የሆነ መረዳት ታገኛለህ።
ትኩረትህን የሚሰርቁ ነገሮችን ሁሉ አስወግድ
ትሮጃን በግሪኮች እና ትሮይ በምትባል ከተማ መሃል የተደረገ ትልቅ ጦርነት ነው: ግን በመጨረሻ ግሪኮች ጦርነቱን በታዋቂው የትሮጃን ፈረስ አሸነፉ: ውስጡ ባዶ የሆነ ግዙፍ የእንጨት ፈረስ ሰሩና የትሮይ በሮች ፊት ትተው ሸሹ: ትሮጃኖችም ጦርነቱን እንደተው እና ሽንፈታቸውን አምነው እንደተቀበሉ አሰቡ። ፈረሱን ወደ ትሮይ አጥር ውስጥ አስገቡ : ሲመሽ የትሮጃን ፈረሱ ውስጥ ተደብቀው የነበሩ ጎበዝ የግሪክ ተዋጊዎች ከፈረሱ ውስጥ ወጥተው የትሮይን በሮች ተመልሰው ሲጠብቁ ለነበሩት ሰራዊታቸው ከፈቱ : ትሮይ ወደቀች።
ረብሻ እንደ ትሮጃን ፈረስ ነው : ትኩረትህን እና ውጤታማነትህን ያጠፋዋል : የተሰወሩ ረብሻዎችን እወቃቸው: ረብሻ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል : የሆነ ነገር ለ 2 ደቂቃ ቢረብሽህ እንኳን 10 ደቂቃ ነው የሚቃጠለው ምክንያቱም ተመልሰህ ትኩረት ውስጥ ለመግባት ጊዜ ስለሚወስድ።
ትኩረትህን የሚሰርቁ የሞባይል መተግበሪያዎችን አጥፋቸው።
አይ ማለትን ልመድ
በህይወታችን ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ችግሮች የሚመጡት አይ ባለማለታችን ነው። ----- ጆሽ ቢሊንግስ
ህይወትህን እና ጊዜህን በአግባቡ ለመቆጣጠር ከፈለግህ አይ ማለት በሚያስፈልግህ ጊዜ አይ ማለትን መልመድ አለብህ። ሌላው ሰው እንዳይቀየመን ብለን እሺ ማለት ሳንፈልግ ብዙ ጊዜ እሺ እንላለን። ሌሎች ሰዎች እንድታደርግ የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ ትቀበላለህ - ነገር ግን አስተውል - ያለህ የተገደበ ጊዜና ጉልበት ነው። ሁሉንም ነገር እሺ ስትል ከጊዜ በኋላ ጫና ውስጥ መግባት ትጀምራለህ። ሌሎችን በማስደሰት ሂደት ውስጥ ራስህን ልታጣው ትችላለህ።
ስትፈልግ አይ በል!
ስትፈልግ እሺ በል!
አይ ለማለት ባለጌ መሆን የለብህም። በትህትና አይ ማለት ትችላለህ። ሁሉንም ነገር አይ በል እያልኩህ አይደለም። ያም ጥሩ አይደለም። መቼ እሺ ማለት እና መቼ አይ ማለት እንዳለብህ ማወቅ አለብህ።
ጊዜህ ውድ ነው። ሌሎች የሚሉህን ነገር ብቻ የምታደርግ ከሆነ ከራስህ ዓላማ ትወጣለህ ፣ ውጤታማነትህ ይቀንሳል ፥ ሌሎችን ብቻ የምናዳምጥ ከሆነ ራሳችንን የምናዳምጥበት ጊዜ አይኖረንም።
ሁሉንም ነገር ለማድረግ ከሞከርን ምንም ነገር አናደርግም። ወደ ሁሉም አቅጣጫ መሄድ ወደ የትም አቅጣጫ አለመሄድ ነው።
አንድ አባባል አለ :-
ወደየትኛው ወደብ እየቀዘፍክ እንደሆነ ካላወቅህ ፥ የትኛውም ነፋስ አይጠቅምህም!
24/7 አትስራ
ውጤታማ የመሆን ግቡ ረጅም ሰዓት መስራት አይደለም ፥ በትንሽ ጊዜ ውስጥ ስራህን ጨርሰህ ከወዳጆችህ እና ከቤተሰቦችህ ጋር የምታሳልፈው የደስታ ጊዜ እንዲኖርህ ነው።
በጣም ረጅም ሰዓት የምትሰራ ከሆነ የፈጠራህ እና የውጤታማነት አቅምህ ይዳከማል።
ውጤታማነት መለካት ያለበት ምን ያህል ስራ ሰራሁ በሚለው እንጂ ምን ያህል ጊዜ ስራው ላይ አሳለፍኩ በሚለው መሆን የለበትም!
አንዳንድ ሰዎች ሰርቻለሁ ለማለት ቢሮአቸው ረጅም ሰዓት ያሳልፋሉ።
ብዙ እየሰራህ ምንም ግብህን የማታሳካ ከሆነ ጠቃሚ ነገሮች ላይ ማተኮር ትተህ ተራ ነገሮችን እያደረግህ ነው ማለት ነው። የማይጠቅሙ ነገሮች የሚጠቅሙ ነገሮችን እንዳታደርግ እየከለከሉህ ነው።
ወሳኝ ነገሮችን ማድረግ ይከብዳል። ሰዎች ከባዱን ነገር ከማድረግ ይልቅ የማይረቡ ቀላል ነገሮችን በማድረግ ራሳቸውን ያጨናንቃሉ።
ብዙ እየሰራህ ግን ግብህን ማሳካት ካቃተህ ምናልባት በሁለት ምክንያቶች ነው:-
1, የምታስበውን ያህል ጠንክረህ እየሰራህ ላይሆን ይችላል ፥ ሰፊውን ጊዜ ሰንፈህ እያሳለፍክ ግን ጠንክረህ እየሰራህ እንደሆነ እያሰብክ ሊሆን ይችላል።
2, የተሳሳቱ ነገሮች ላይ እየሰራህ ሊሆን ይችላል ፥ አብዛኛውን ጊዜህን ከዋናው ነገር ይልቅ ጥቃቅን ነገሮች ላይ እያሳለፍክ ሊሆን ይችላል።
ከእያንዳንዱ ከምታደርገው ነገር የምታገኘው ዋጋ አለ ፥ የአንዳንዱ ዋጋ ከፍ ያለ ነው ፥ የበለጠው እያለ ብዙ ጥቅም በሌለው ነገር ላይ ትኩረት አታድርግ!
ቢዚ ሳይሆን ውጤታማ ሁን
መሰላሉ ትክክለኛ ግድግዳ ላይ ካልተደገፈ የምንረግጣት እያንዳንዷ እርምጃ ትክክል ወዳልሆነ ቦታ በፍጥነት እየወሰደችን ነው። ------- እስቴፈን ኮቬይ
ቢዚ መሆን ስለፈለግህ ቢዚ አትሁን ፣ ይልቅ ውጤታማ ሁን! ከግብህ የሚያርቁትን ሳይሆን ወደ ግብህ የሚያደርሱትን ተግባራት አድርግ!
አትዘግይ
" በቀጣይ የሚያደርጉትን ማወቅ ጥበብ ነው ፥ እንዴት እንደሚያደርጉት ማወቅ ክህሎት ነው ፥ ዋናው ወደ ተግባር መቀየር ነው!!" ዴቪድ ስታር ጆርዳን
ብዙ ሰዎች ሰነፍ የሚሆኑበት አንዱና ዋና ምክንያት፣ አንድ ነገር ለማድረግ “ትክክለኛውን ጊዜ” ሁልጊዜ መጠበቃቸው ነው። እና ምን ይመስልሃል? ትክክለኛው ጊዜ ፈጽሞ አይመጣም።
ለመጀመር ምንም ጊዜ ፍጹም ጥሩ ወይም መጥፎ አይደለም። ዛሬ መጀመር እና ትንሽ እድገት ማምጣት ትችላለህ፤ ወይም መጠበቅና “የእኔ ጊዜ ይመጣል” ብለህ ራስህን ማጽናናት ትችላለህ።
“አንድ ቀን ጊዜዬ በራሱ ይመጣል” ብለህ ሥራ ሳትሠራ መጠበቅን አቁም። ይህ አይሆንም። ግቦችህን ለማሳካት ሥራውን መሥራት አለብህ። ፍጹም ጊዜን ብቻ በመጠበቅ ስኬታማ የሆነ ሰው አይቼ አላውቅም።
አንዳንድ ሥራዎች ምንም ያህል ብትጥር በፍጥነት ሊጠናቀቁ አይችሉም። ይህ ግን ምንም ሳታደርግ መጠበቅ አለብህ ማለት አይደለም።
ስንፍናህን ከትዕግሥት ጋር አታምታታ። ትዕግሥትና ስንፍና በጣም የተለያዩ ናቸው። አትቀላቅላቸው። በየቀኑ ሥራህን መሥራት አለብህ፤ ከዚያም ውጤቱን በትዕግሥት መጠበቅ አለብህ።
የታላቅ ትዕግሥት ታሪክ
አንድ ጊዜ አንድ ገበሬ የቀርከሃ ዛፍ ተከለ። ገበሬው ለአንድ ዓመት በየቀኑ ተክሉን አጠጣ፣ ነገር ግን የሕይወት ምልክት አላየም። እድገት የለም፣ ቡቃያ የለም፣ ተስፋም የለም።
ሁለተኛው ዓመትም እንደዚሁ ነበር፤ ሦስተኛውና አራተኛውም እንዲሁ። በዚህ “ተአምረኛ” የቀርከሃ ተክል ላይ ያለው ትዕግሥቱና እምነቱ መቀነስ ጀመረ።
በአምስተኛው ዓመት፣ ተስፋ ሊቆርጥ ሲል፣ ተክሉ ቡቃያ ማውጣቱን አየ። ቀርከሃውም በቀጣዮቹ ስድስት ሳምንታት 60 ጫማ ያህል ከፍ ብሎ አደገ!
ይህ ስለ ትዕግሥትና ትጋት በጣም ጥሩ ታሪክ ነው። ሕይወትም እንዲሁ ነው። በአንድ ጀምበር የሚገኝ ስኬት የለም። ስኬት ለመምጣት ረጅም ጊዜ ይወስዳል። ይህ ግን ቁጭ ብሎ ምንም ሳያደርጉ በመጠበቅ አይደለም።
ቀርክሃው በራሱ አላደገም፤ ገበሬው መትከል፣ መንከባከብና በትዕግሥት መጠበቅ ነበረበት።
ለተግባር አትታገስ፤ ለውጤቱ ታገስ
አንድ የዜን ተማሪ ወደ መምህሩ ሄዶ በጉጉት ጠየቀ፦
“ዜንን ለመማር ቆርጬ ተነስቻለሁ። እሱን በሚገባ ለመማር ምን ያህል ጊዜ ይወስድብኛል?”
መምህሩም፦ “አሥር ዓመት” አለው።
ተማሪው መልሶ፦
“እኔ ግን ከዚያ በበለጠ ፍጥነት መማር እፈልጋለሁ። በጣም ጠንክሬ እሠራለሁ። አስፈላጊ ከሆነ በየቀኑ ከአሥር ሰዓት በላይ እለማመዳለሁ። ታዲያ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?”
መምህሩ ለጥቂት ጊዜ አሰበና፦ “ሃያ ዓመት” አለው።
የምታገኘውንም ሆነ የማታገኘውን ውጤት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አትችልም። መቆጣጠር የምትችለው ድርጊትህንና የምትሠራውን ሥራ ብቻ ነው።
ሁሉም ሰው በጠንካራ ሥራ ላይ ሲሆን ውጤቱን በፍጥነት ማየት ይፈልጋል፤ “የሥራዬን ውጤት አሁኑኑ ካላየሁ” ብሎ ያስባል። ብዙ ጊዜ ግን እንዲህ አይሆንም። የምትፈልገውን ውጤት ከማግኘትህ በፊት ለዓመታት ጠንክረህ መሥራት ሊኖርብህ ይችላል።
ስለዚህ ውጤቱን በትዕግሥት ጠብቅ፤ ለተግባርህ ግን አትታገስ። ሁሉም ነገር እጅ በእጅ እንደሚሰጥ ከሚያስቡ ሰዎች አትሁን። የምትፈልገውን ውጤት ከማግኘትህ በፊት ቀድመህ ሥራውን መሥራት አለብህ።
“የትዕግሥት ጌታ የሁሉም ነገር ጌታ ነው።” — ጆርጅ ሳቪል
ምርጥ የሚባል ጊዜ የለም
አዲስ ነገር ለመጀመር ምርጥ ጊዜ የሚባል ነገር የለም። ዛሬ መጀመርና ትንሽ እድገት ማምጣት ትችላለህ፤ ወይም ተስማሚውን ጊዜ እየጠበቅህ ያለ ስራ መቀጠል ትችላለህ።
ምርጡ ጊዜ አሁን ነው። ወደ ግቦችህ መሄድ ለመጀመር ከዛሬ የተሻለ ጊዜ የለም። ስንፍናን አቁምና የሚያስፈልገውን ሥራ መሥራት ጀምር።
ወጥነት ቁልፍ ነው
በማንኛውም ነገር ላይ ጎበዝ ለመሆን፣ ነገሩን በየቀኑና ለረጅም ጊዜ ማድረግ አለብህ።
የተሻለ ሰዓሊ ለመሆን → በየቀኑ መሳል አለብህ።
የተሻለ ጸሐፊ ለመሆን → በየቀኑ መጻፍ አለብህ።
የተሻለ ተናጋሪ ለመሆን → በየቀኑ መናገር አለብህ።
ብዙ ሰዎች በፍጹም አይጀምሩም። አንዳንዶቹ ይጀምራሉ፣ ነገር ግን ነገሮች እየተወሳሰቡ ሲሄዱ ይተዋሉ። ጥቂቶች ብቻ ወጥነት ያሳያሉ፤ በየቀኑ ያደርጉታል፣ ነገሩ ምንም ያህል ቢከብድም አይተዉትም።
ቀስ በቀስ ቀላል ይሆናል
“መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ ሊመስል ይችላል፤ ግን ሁሉም ነገር መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ ነው።” — ሚያሞቶ ሙሳሺ
በጣም አስቸጋሪው ነገር መጀመር ነው። 95% የሚሆኑ ሰዎች የሚቆሙት እዚህ ላይ ነው። በፍጹም አይጀምሩም። ሁልጊዜ ይጠብቃሉ፣ ሰበብም ይፈልጋሉ።
መጥፎ ልማድን መተው ከፈለግህ፣ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በጣም አስቸጋሪዎቹ ይሆናሉ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ግን መቀጠል በጣም ቀላል ይሆናል።
የምትናገረውን አድርግ
ማዘግየትን የምትወድ ከሆነ የራስህን ቃል አታከብርም። አንድ ነገር እንደምታደርግ ተናግረህ ካላደረግኸው፣ ሰዎች አንተን ማመን ማቆም ይጀምራሉ።
ይህ ማለት ሌሎች ሰዎች የሚጠይቁህን ነገር ሁሉ ማድረግ አለብህ ማለት አይደለም። ነገር ግን አንድ ነገር እንደምታደርግ ከተናገርክ፣ ቃልህን መጠበቅ አለብህ።
“ከነገ ጀምሮ ጂም እሄዳለሁ” ካልክ፣ ምንም ነገር ቢከሰት ጂም መሄድ አለብህ።
የምትናገረውን አድርግ። ነገሮችን ብቻ እየተናገርክ ሰንፈህ ሳታደርጋቸው አትተው! ቃልህን አክብር፤ የምትለውንም ነገር አድርግ።