ማር 1፡12-13፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥምቀተ ባሕር ከወጣ በኋላ ዛሬ እኛ እንድንጸልይ በራሱ መንፈስ ተመርቶ ወደ ምድረ በዳ ወደ ገዳም ሄደ፡፡ በዚያም ከዲያብሎስ እየተፈተነ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ ጸለየ፡፡
መንፈስ ወደ ምድረ በዳ አወጣው ነው የሚለን፡፡
ዛሬ የእኛ መንፈስ ወዴት ነው የሚያወጣን? ጾም፣ ጸሎትና ስግደት ወዳለበት ወደ ገዳምና ወደ ቤተ ክርስቲያን ነው ወይስ ዳንኪራና ጭፈራ ወዳለበት ወደ ዓለም መንደር? መንፈሳችን ወደ ዓለም በረሀ የሚመራን ከሆነ ለነፍሳችን አይጠቅመንም፡፡ ዛሬ ልንመራ የሚያስፈልገው መንፈሳችን ሊወስደን የሚገባው ለነፍሳችን ምግብ ወደሚገኝባት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሆን አለበት፡፡
ዛሬ ብዙዎቻችን ወደ ገዳማት እንሄዳለን፡፡ አካሄዳችን ግን መንፈሳዊ አካሄድ አይደለም፡፡ የብዙዎቻችን አካሄድ ፈሩን ስቷል፡፡ የምንሄደው ለመዝናናት ነው፡፡ ይዘን የምንሄደውም ነፍስን የሚጠቅም ሳይሆን ሥጋን የሚያደልብ ነው፡፡ ከዚህ ልንቆጠብ ይገባል፡፡
የምንሄደው ልንጾምና ልንጸልይ ልንጸድቅ መሆን አለበት፡፡ ወደ ገዳም ሄደን ጽድቅና በረከትን እንዲሁም ትሩፋትን ይዘን መመለስ አለብን፡፡ ጌታችን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ ሰይጣንን ድል ያደረገው አካሄዱ ትክክለኛ ሰለሆነ ነው፡፡ እኛም በጸሎት፣ በጾምና በስግደት የምንወሰን ከሆነ የሚያጋጥሙንን ችግሮችና ፈተናዎች በሙሉ ድል ማድረግ አይሳነንም::
ወደ ገዳም የምንሄድ ከሆነ መላእክት ያገለግሉናል፡፡ የመላእክት ግልጋሎትና ተራዳኢነት ደግሞ የሚደርስብንን ፈተና ያቀልልናል፡፡ ሰው ካልጾመ መላእክት አይቀርቡትም፤ አያገለግሉትምም፡፡ ዛሬ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ያልወጣን፤ጾም ያልጀመርን፤ለመታየት ብቻ ለመዝናናት ብቻ ወደ ገዳማት የምንወጣ አለን፡፡ በአገራችን ያሉትን ገዳማት ሳናይ ለታይታ ብቻ ወደ ኢየሩሳሌም ገዳማት የምንበር አለን፡፡ ከዚህ ሁሉ ተቆጥበን በጾምና በጸሎት ተወስነን ልንኖር ይገባናል፡፡
የዛሬው ትምህርት በምሳሌ የቀረበ ትምህርት ነው፡፡ ጌታ እኛ በምንሰማውና በሚገባን ቋንቋ ነበር የሚናገረው፡፡ ትምህርቱ ራሳቸውን ለሚያመጻድቁ ሰዎችና ወንድሞቻቸውን ለሚያዋርዱ ሰዎች በምሳሌ የተነገረ ትምህርት ነበር፡፡ ሉቃ. 18፡14
ታሪኩ የአንድ ፈሪሳዊና የአንድ ቀራጭ ታሪክ ሲሆን የመጀመሪያው ባለ ታሪክ ፈሪሳዊው ነው፡፡ ፈሪሳውያን ሕግንና ኦሪትን እናከብራለን ፣ እኛ የእግዚአብሔር ወዳጆች ነን የሚሉ ነገር ግን ከእግዚአብሔር በጣም የራቁ ሰዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ወገን የሆነው ይህ ፈሪሳዊም ወደ ቤተ መቅደስ መጥቶ እንደ ሌሎች እንደ ቀማኞችና ዓመፀኞች ስላላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ ፤ ይልቁንም ደግሞ እንደዚህ እነ ቀራጭ ስላላደረግኸኝ በጣም አመሰግንሃለሁ፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን እጾማለሁ ፤ ከማገኘውም ከዐሥር አንድ እሠጣለሁ በማለት ራሱን ሲያጸድቅና ሲያመጻድቅ ይታያል፡፡
ሌላው ደግሞ ቀረጥ ተቀባይ ነው፡፡ እርሱም በአጥሩ ግቢ ውስጥ ራቅ ብሎ ቆሞ እኔ ወደ ቤተ እግዚአብሔር መግባት የሚገባኝ ሰው አይደለሁም፡፡ እኔ ኃጢአተኛ ስሆን ወደ አንተ ቤት ልገባ አይገባኝም እያለ ደረቱን በመድቃት ይጸልያል፡፡ ይህ ቀራጭ ዓይኖቹን እንኳን ወደ ሰማይ ሊያነሳ አልደፈረም፡፡
እነዚህ ሁለት ሰዎች ወደ ቤተ እግዚአብሔር መጥተው በየበኩላቸው ጸልየዋል፡፡ የጸደቀው ግን ሁለተኛው ነው፡፡ ይህ ቀራጭ ሰው ሥራዬ መልካም አይደለም ፤ እኔነቴንና ሕይወቴን አውቀዋለሁና ስለ ምን ወደ እግዚአብሔር ቤት እገባለሁ ብሎ በዕንባው እየታጠበ ጸለየ፡፡
ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣ ሁሉ እንደዚህ ሰው የተሰበረ ልብ ይዞ መቅረብ አለበት፡፡ እኛም እንደ ፈሪሳዊው በመደፋፈር ወደ ቤተ እግዚአብሔር መግባት የለብንም፡፡ ነገር ግን እንደ ቀራጩ አልቅሰንና ደረታችንን ደቅተን ልንጸልይ ይገባናል፡፡ እዚህ የምንመጣ ሁሉ ጸድቀን መመለስ አለብን፡፡ እንደ ፈሪሳዊው የምንመጻደቅ ከሆነ ግን ሌሎች ይቀድሙናል፡፡
ብዙዎቻችን መንግሥተ ሰማያት እንደምንገባ ያረጋገጥን ይመስል እንዲሁ በባዶ እንመጻደቃለን፡፡ እኛ ራሳችንን ስናመጻድቅ ኃጢአተኞችና ዘማውያን ቀድመውን ይገባሉ፡፡ ‘እውነት እውነት እላችኋለሁ ፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሟችኋል’ ማቴ. 21፡31
ስለዚህ ልንቀደም አይገባም፡፡ ክርስትና የራስን ጽድቅ ሳይሆን የራስን ኃጢአት መናገር ነው፡፡ ጌታዬ ሆይ ፦ እኔ ርኩስ ነኝ ፤ ሕይወቴም መራራ ነውና አንተ ጣፋጭ አድርግልኝ እያልን መጸለይ አለብን፡፡ እግዚአብሔር ሕይወታችንን ያጣፍጥልን፡፡
እግዚአብሔር ይባርካችሁ! እግዚአብሔር ይጠብቃችሁ!
ነሐሴ 1984 ዓ.ም.
ከአያሌው ዘኢየሱስ የግል ማስታወሻ የተወሰደ
ማስታወሻ :- በረከታቸው ይደርብንና ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በድንቅ ስብከቶቻቸው እና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሠረቷቸው ገዳማትና ትምህርት ቤቶች ፣ ባፈሯቸው መምህራንና መነኮሳት ለዘላለም የሚታወሱ ሊቀ ጳጳስ ናቸው::