መጽሐፈ ዘፍጥረት የአምስተኛውን ቀን ፍጥረታት ሲተርክ “እግዚአብሔርም አለ፡- ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፤ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈርም በታች ይብረሩ” በማለት ይጀምራል፡፡ ዘፍ 1፡20 አእዋፍ ጌታ እግዚአብሔር ከውኃ ከፈጠራቸው መካከል ናቸው፡፡ ከውኃ ተፈጥረው የተሰጣቸው ተፈጥሯዊ ጸጋ ደግሞ “ከምድር በላይ” እንዲበርሩ ነው፡፡ በዚህ የዘፍጥረት ተረክ ውስጥ ጌታ እግዚአብሔር ስለ እኛ ሕይወት ምን ታላቅ ምሥጢር ሊነግረን እንደ ወደደ ለማየት እንሞክራለን፡፡
ከምድር መጥቀው እንዲበርሩ የተፈጠሩት አእዋፍ የተገኙ ከውኃ መሆኑ፤ ውኃ የጥምቀት ከውኃ የተገኙትም የጥሙቃን (የክርስቲያኖች) ምሳሌ ናቸው ይሉናል አበው፡፡ ጌታችን ስለ ምሥጢረ ጥምቀት ለኒቆዲሞስ ሲነግረው “ከሥጋ ተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ፡፡ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፤ ድምጹንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” ብሎታል፤ ምሥጢሩን ለጊዜው ሊረዳው ባይችልም፡፡ ዮሐ 3፡6-8 ከመንፈስ የተወለዱ ሁሉ በምን ደረጃ ሊኖሩ በአዲስ ተፈጥሮ ከውኃና(በሚታይ) ከመንፈስ እንደ ተወለዱ አበሠረን፡፡
በዚህ ማዓርግ በአዲስ ተፈጥሮ ከብረን ሳለን በእኛ ዘንድ የሚታየው ሕይወት ምን እንደሚመስል የአእዋፍን ተፈጥሮ በመመርመር ለማየት እንሞክር፡፡
የአእዋፍን አኗኗር በሦስት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡
፩. ክንፍ እያላቸው ፍጹም ከምድር መነሣትና መብረር የማይይሉ እንደ ሰገኖ (ሰጎን)ያሉ፤
፪. ከምድር ለመነሣት የሚውተረተሩ መልሰው ግን የሚወድቁ እንደ ዶሮ ያሉ፤
፫. ከምድር መጥቀው መብረር የሚችሉ፤ እንደየ ደረጃቸው በቅርብ ከፍታ ከሚበርሩ ጀምሮ በዓይነ ሥጋ ለማየት እስኪያዳግት ድረስ በአስደናቂ ከፍታ ላይ እስከሚወጡ እንደ ንስር ያሉ በማለት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡
ሁሉንም በየተራ ምሳሌነታቸውን ለማየት እንሞክር፡-
፩. ክንፍ እያላቸው ፍጹም ከምድር መነሣትና መብረር የማይችሉ እንደ ሰገኖ (ሰጎን) ያሉት ችግራቸው የሰውነታቸው ክብደት ለመብረር እንቅፋት መሆኑ ነው፡፡ ክርስቲያኖችም በተለያየ ሸክም ኅሊናቸው (ልቡናቸው) ከከበደ መድረስ የሚገባቸው ልዕልና ነፍስ ላይ መገኘት ፈጽሞ አይችሉም፡፡
መንፈሳዊ ልዕልናን ገንዘብ እንዳያደርጉ የመጀመሪያው ሸክም ኃጢአት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እናንት ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ያለን ለዚህ ነው፡፡ ማቴ 11፡28 የኃጢአት ሸክምን ከልብ በሆነ ንስሐ ማስወገድ በክንፈ ጸጋ መጥቆ ለመብረር የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ ኃጢአት ከምድር እንዳንነሣ ቁልቁል የሚስብ Gravity ነው፡፡ ክብደት በጨመረ ቁጥር ወደ ላይ ለመውጣት ያለው ዕድል እየጠበበ ትግሉ ደግሞ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
ሁለተኛው ሸክም ምድራዊ ሀሳብ ነው፡፡ ጌታችን በወንጌል “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና” ሲል አስጠንቅቋል፡፡ ሉቃ 21፡34-36 ጨምሮም “. . . በኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፡፡ በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናል” ማቴ 24፡36-42
ዛሬ በንስሐ ሕይወት እንመላለሳለን ብለው በድፍረት የሚያስቡ እንኳ ከዚህ ሸክም ያልተላቀቁ ናቸው፡፡ ሰው ከነፍሱ በላይ ነገ ለሚፈርስ ሥጋ ብዙ ይደክማል፡፡ የቀን ሀሳቡ የሌት ቅዠቱ ስለ መብልና መጠጥ ነው፡፡ የሌለው ለማግኘት ያለው ለመጨመር ይባዝናል፡፡ የድንግልናን ምሥጢር ለክርስቶስም ራስን ሙሽራ አድርጎ የማቅረብንም ክብር ጠንቅቃና አጉልታ በምታስተምር ቤተክርስቲያን እየኖረ ያላገባው/ችው ትዳር የመያዝ ሀሳብ ዕረፍት ነስቷቸዋል፡፡ የልባቸው ምኞት ተፈጽሞላቸው በትዳር የሚኖሩም ክብደቱ አስጨንቋቸዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ “ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው፡፡ በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ፡፡ ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፤ እኔም እራራላቸዋለሁ” ይላል ስለ ትዳር ማሰብና በትዳር መኖር ያለውን ሸክም ሲገልጽ፡፡ 1 ቆሮ 7፡27-35 (ይህን ያለበትን ምክንያት ለመረዳት ሙሉውን በጥንቃቄ ማንበብ)
ሦስተኛው ሸክም ዓለምን መውደድና ምኞት ነው፡፡ ዓለምን መውደድ የሚለው ሀሳብ ብዙ ነገሮችን ያካትታል፡፡
በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ዐውድ በሰው ዘንድ ለሚኖር ተቀባይነት መድከም፣ በልጦ መታየት፣ ክብር፣ ዝና፣ ገንዘብ፣ ዕውቀት፣ ሥልጣን. . . እና የመሳሰሉት ብለን ካላለፍነው ሁሉን ለመዘርዘር ጊዜ ያጥርብናል፡፡ የሰው ሀሳቡ በምድራዊ ምኞት ተገርኝቶ ሲያዝ ልቡናው ይከብዳል፡፡ የሚሻለውን ለመምረጥና ለመከተልም ማስተዋል አይኖረውም፡፡ ጌታችን በወንጌል “የሰውነት መብራት ዓይን ናት፡፡ ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል” ይለናል፡፡ ማቴ 6፡22 ይህን የተረጎመ አንድ ሊቅ በአማርኛ “ዓይንህ ጤናማ ብትሆን. . .” የሚለው በግሪኩ ሲነበብ “ዓይንህ simple ብትሆን. . .” (ቀላል ከሚለው ቀጥተኛ ትርጉም ይልቅ የእኛ መተርጉማን ጤናማ ያሉት በእውነት የተሻለ ቃል ነው) ሕይወትን ቀለል አድርገህ ትኖራለህ፤ ይህም ከምኞት ሸክም ያድንኃል፤ ክበደ ልቡናህም በመንፈሳዊ ሕይወትህ በክንፈ ጸጋ ለመብረር እንቅፋት አይሆንብህም ሲል ነው ብሎ ተርጉሞታል፡፡ ቀለል ያለ ኑሮ ማለት ከፉክክር የራቀ ለሰው አስተያየት (ሙገሳም ሆነ ነቀፌታ) በማይጨነቅ ማንነት የሚገለጥ ሕይወት ማለት ነው፡፡
ዮሐንስ ወንጌላዊም በመልእክቱ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፤ ማንም ዓለምን ቢወድድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም” ይለናል፡፡ ከፍቅረ እግዚአብሔር በላይስ ወደ ላይ በክንፈ ጸጋ መጥቀን እንድንወጣ የሚያደርግ ምን ይኖራል? 1 ዮሐ 2፡15-16
ጌታችን ደቀመዛሙርቱ የሆንን ሁላችን ከሸክም ነጻ የሆነ ሕይወት እንድንኖር ከማስተማሩም በላይ ሥጋዊ ሸከም ቀርቶ በመንፈሳዊነት ስም እንኳ የሚጫንን ሸክም ተቃውሟል፡፡ ፈሪሳውያን ከተዘለፉበት ምክንያት አንዱ በሌሎች ሸክም መጫናቸው ነው፡፡ “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፤ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም” ብሏል፡፡ ማቴ 23፡4-5 እርሱ ግን “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ. . . ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” ብሎናል፡፡ ማቴ 11፡29 ቤተክርስቲያንን ከጌታችን አደራ የተቀበሉ ሐዋርያትም መንጋውን ሲያስተዳድሩ “. . . ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ፤ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና . . .” ሲሉ እናያቸዋለን፡፡ የሐዋ.ሥራ 15፡22-29 በራሳችን ላይ ፈቅደን በጫነው ሸክም ብንኖር ግን ተጠያቂነቱ የእኛው ነው፡፡
፪. ሁለተኞቹ ነገደ አእዋፍ ከምድር ለመነሣት የሚውተረተሩ መልሰው ግን የሚወድቁ በእንዲህ ያለው ምልልስ የሚኖሩ እንደ ዶሮ ያለ ሕይወት የሚኖሩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ይኽኛው ምድብ ከመጀመሪያው ምድብ የሚሻሉ የሚመስሉት በመሞከራቸው ነው፡፡ ሀሳባቸው አልፎ አልፎና ጽናት በሌለው ሁኔታ ቢሆንም ጨርሶ በምድራዊ ሀሳብ ተገርኝቶ የተያዘ አይደለም፡፡ ኃጢአትን ከመሥራት መታቀብ ባይኖርም እንኳ ጸጸት የሚጎበኘው ኅሊና አላቸው፡፡
የእነዚህ ትልቁ እንቅፋት የሚያጡትንና የሚያተርፉትን አለማወቅ፣ ልማድና በተጋድሎ አለመጽናት ናቸው፡፡ ይህም ሕይወታቸውን በየትኛው አቅጣጫ መምራት እንዳለባቸው ቁርጥ ውሳኔ ላይ እንዳይደርሱ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡ እግዚአብሔርን በመምሰል መኖር ማትረፊያ መሆኑን በፍጹም ልባቸው ለመቀበል ይከብዳቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ፤ ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” በማለት የሚመክረው እንዲህ ላሉት ነው፡፡ 1 ጢሞ 4፡8 በመሆኑም የክርስትና ሕይወታቸው ወቅታዊ (seasonal) ነው፡፡
የጾም ወራት ሲሆን፣ በሕይወታቸው ከባድ ነገር ሲገጥማቸው ወይም በሆነ አጋጣሚ የሰሙት ስብከት ሙቀቱ እስኪለያቸው ድረስ ፍጹም የተሰበረ መንፈስ ሊታይባቸው ይችላል፤ ግን አይቆይም፡፡ ፈቃዳቸውን ወደ መፈጸም ሲመለሱ የቆዩበትን ለመርሳት ብዙም አይቸገሩም፡፡
በዚህ የሚገኙት ሌላው ቀርቶ በአገልጋይነት ደረጃ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንደ ዶሮ በጩኸታቸው ሌሎችን የሚቀሰቅሱ እነርሱ ግን በቆሙበት የሚያንቀላፉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በድቅድቅ ጨለማ መቀጣታቸው እንደማይቀር ከተናገረ በኋላ ምክንያቱን ሲያስቀምጥ “እነዚህ ውኃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው፡፡ ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፤ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ፡፡ ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፡፡ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል፡፡ አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትዕዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና፡፡ ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤ ደግሞ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል” ብሏል፡፡ 2 ጴጥ 2፡17-22
በዮሐንስ ራእይ 3፡15 በሌላ ምሳሌ ትኩስ ወይም በራድ አለመሆን ተብሎ የተገለጠ ሕይወት አደገኛነቱ ለመዳን ያለው ተስፋ እጅግ የመነመነ መሆኑ ነው፤ መተፋትን ያስከትላል፡፡ ትልቁ እንቅፋቱ ደግሞ ከቃለ እግዚአብሔር፣ ከንስሐ፣ በአጠቃላይ ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር የሚኖር ጎጂ መላመድ ነው፡፡ ምናልባት ለቤተመቅደሱ ቅርበትና በዚያ ከሚያገለግሉ ጋርም መልካም መግባባት ሊኖረን ይችላል፡፡ ራሳችንን ሳንሰጥ ያለንን ግን በመለገስ ላንታማ እንችላለን፡፡ ይህም በብዙዎች ዘንድ ከሚያሰጠን ሞገስ የተነሣ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለሟል የሆንን መስሎ እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል፡፡ የምንኖረው ሽንገላ የበዛበት ሕይወት ባይተዋር ቤተኞች መሆናችንን እስክንረሳ ያደርሰናል፡፡ በዚህ ደረጃ ካለነው ይልቅ ከላይ በቁጥር አንድ የተጠቀሱት በንስሐ ተመልሰው የቅድስና ሕይወትን ለመኖር የተሻለ እድል ይኖራቸዋል፤ ቢያንስ ልማድ ፍርሃታቸውን አልነጠቃቸውምና፡፡
፫. ከምድር መጥቀው መብረር የሚችሉ፤ እንደየ ደረጃቸው በቅርብ ከፍታ ከሚበርሩ ጀምሮ በዓይነ ሥጋ ለማየት እስኪያዳግት ድረስ በአስደናቂ ከፍታ ላይ እስከሚወጡ እንደ ንስር ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ራሳቸውን ክደው፣ ፈቃዳቸውን ሰውተው፣ ሕይወታቸውን ወደ ኋላ ከሚስባቸው የትኛውም መጣበቅ (attachment) ራሳቸውን ነጻ አድርገው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ፈቃዱን ለመኖር መጨከን በእነርሱ ዘንድ አለ፡፡ የሕይወታቸው ብርሃን የምድር አሕዛብ እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ ያስገድዳል፡፡ እውነትን ያውቋታል ይኖሯታልም፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው” የሚሉ ናቸው፡፡ ገላ 2፡ 20-21 ሁል ጊዜም የኋላቸውን እየተዉ ወደ ፊት የሚዘረጉ እንጂ በደረሱበት የሚጽናኑ አይደሉም፡፡ ለሚበልጠው ጸጋ መቅናትና ትሕትና መጥቀው የሚበሩባቸው ሁለቱ የጸጋ አክናፍ ናቸው፡፡
የመንግሥቱ ምሥጢር ስለ ተገለጠላቸውና ጥበባቸውን በሞኝነት፣ ኃይላቸውን በድካም፣ ልዕልናቸውን በውርደት፣ ቅድስናቸውን በዕብደት ስለ ሠወሩ፤ ሁሉን በሚያውቀው ዘንድ ታውቀው በዘላለማዊው ልቡና ስለ ተሣሉ፤ የሕይወታቸው ምሥጢር የክብራቸው ድንበር ሥጋዊ ደማዊ አእምሮን ስለሚረታ ስለ እነርሱ ምን እንል ዘንድ ይቻለናል? የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ተውሰን “መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል፤ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም” ከማለት በቀር!!! 1 ቆሮ 2፡15
ማሳረጊያ የምናደርጋት በመብረሯ ወፍ ብለን የምንጠራት በባሕርይዋ ግን አጥቢ እንደ ሆኑ እንሰሳት የሆነችዋን የሌሊት ወፍን ነው፡፡ ይህቺ ፍጥረት በሌሊት ስትንቀሳቀስ ዓይኗ ማየት ስለማይችል እንቅስቃሌዋን የምትወስነው ከራሷ የምታወጣው የድምጽ ሞገድ ከፊቷ ካለ ማንኛውም ነገር ጋር ተጋጭቶ በሚሰጣት ነጥሮ በሚመጣ ድምጽ (Echo) በመመራት ነው፡፡ የሌሊት ወፍ በዚህ ጨለማ ዓለም በራሳቸው መረዳት በመታመን ለመጓዝ ለሚሞክሩ ሰዎች ምሳሌ ትሆናለች፡፡ ለሰዎች የተገለጸው እውነተኛውና የመጨረሻ እውቀት ክርስቶስ ነው፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ያለን ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ 8፡12 ክርስቶስን ሳያውቁ ከራሳቸው ኅሊና የሚወጣ የሀሳብ ሞገድን እየተከተሉ በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው፡፡ እንደ ራስ ድምጽ አታላይ ነገር የለም፡፡ እንኳን ክርስቶስን ባለማወቅ ጨለማ ለወደቁ ቀርቶ እርሱን በማወቅ ለምንኖር እንኳ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ለሰው የራሱ ድምጽ መጥፎ ሆኖ ተሰምቶት አያውቅም፡፡ ወጥመዱም ያ ነው፡፡
በራሳቸው መረዳት የሚመሩት ሰዎች መልካምነት ሊኖራቸው ይችላል፤ ሰውም በዚህ ከፍ ያለ ሥፍራን ስለሚሰጣቸው የመብረራቸው ምሥጢርም ይኸው ነው፡፡ ክርስቶስን ባለ ማወቅ ጨለማ ውስጥ እስከ ቆዩ ድረስ ግን መልካምነታቸው የሚረባቸው ነገር አይኖርም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው መልካም ሰዎች እንድንሆን አይደለም በቅድስና እርሱን ወደ መምሰል እንድናድግ እንጂ፡፡ የልጁን መልክ የሚመስሉ ብቻ ናቸው በአባት ዘንድ ለመታየት የሚበቁ፡፡
በዘመኑ የተያዘ ሃይማኖት አልቦ መንፈሳዊነት ወይም መንፈሳዊነትን ከሃይማኖት ለመነጠል የሚደረግ ሩጫ ፍጻሜው በጨለማ ከመዳከር ያለፈ ወደ ዘላለማዊው ብርሃን የሚያደርስ አይደለም፡፡ የብርሃን ልጆች ከጨለማ ልጆች የሚለዩበት የመጀመሪያው መሥፈርት ሃይማኖት ነው፡፡ ጌታችንም “መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ያለ ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ 14፡6 ዛሬም ሠልጥኖ የምናየው ሁለቱ ከጥንት የክርስትና ተቃራኒ የሆኑ መንገዶች ናቸው፤ አይሁዳዊነትና ግሪካዊነት! አይሁዳዊነት ምልክትን መሻት ሲሆን ግሪካዊነት እውቀትን መከተል ነው፡፡ እናምናለን የሚሉት ምልክት በመሻት ጠቢባን ነን የሚሉት ደግሞ እውቀትን በመከተል ይጠፋሉ፡፡ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን!” መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት ተብሎ የተገለጠ ብርሃን ነው፡፡ ብርሃን ሃይማኖት ነው፤ ሃይማኖትም ክርስቶስ ነው፡፡ 1 ቆሮ 1፡18-31
ሰው በብዙ ውሳጣዊና ውጪያዊ ምክንያት እንዲሁም ዓላማ መልካም ሰው ሊሆን ይችላል፤ ከሃይማኖት ውጪ ግን ቅዱስ መሆን ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ቅድስና ቅድስናን በሚሰጥ ነው፡፡ በግብጽ በረሃ ለብዙ ዓመታት የኖሩት ኢትዮጵያዊው ባህታዊ አቡነ አብደል መሢህ “ልግስና በዝቷል ክርስቶስ ግን የለም” የሚለው አባባል መንፈሳዊነትን ከሃይማኖት ለይቶ ቅድስናን በመልካም ሰውነት ተክቶ ለመኖር የሚደክምን የዘመኑን ሰው ለመግለጽ የተጠቀሙበት ድንቅ ቃል ነው፡፡
ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::
“ሰው ለምቾትና ለተቀማጠለ ሕይወት ራሱን አሳልፎ ሲሰጥ ለንስሓ ያለው ቁርጠኝነት ይቀንሳል፡፡ ”
(ፍና ቅዱሳን – ገጽ 51)
ብዙ ጊዜ በምቾት የተቀማጠለ ሕይወትን እና ኑሮን ቀለል ባለ (በዘመናዊ ዘይቤ) መኖር የሚሉትን ሃሳቦች ቀላቅለን እናያቸዋለን ፡፡ ነገር ግን ሁለቱ ሃሳቦች የሚለያዩ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም እኛ እየኖርን ያለነው (ለመኖር የምንጥረው) የትኛውን ዓይነት ኑሮ ነው? በአካል፣ በነፍስና በአስተሳሰብ መኖር የሚገባንስ እንዴት ነው?
መልስ፦ ሰው ለምቾትና ለተቀማጠለ ሕይወት ራሱን አሳልፎ ሲሰጥ ለንስሓ ያለው ቁርጠኝነት ይቀንሳል? እውነት ወይም ሐሰት መሆኑን ለማወቅ ሩቅ መሔድ አይጠበቅብንም ራሳችንን ማየት እንጂ። አበው “ዝናም ዘነበ ቢለው፥ በየደጅህ እየው” እንዲሉ በየራሳችን ሕይወት ስናየው እውነት ነው ምቾትና የተቀማጠለ ሕይወት ምን ያህል ለንስሐ ልምሾ እንደሚያደርገን ማየት እንችላለን።
እስቲ ተጠየቁ ፦
በዘመኑ ቋንቋ በዚህ በዚያ ብሎ ማለት ሰርቆ ፣ አጭበርብሮ ፣ ጉቦ ተቀብሎ፣ ደሀ አስለቅሶ የተቀማጠለ ሕይወት ይጀምርና ሲጠየቅ የሰው ሕይወት ተፍትፎ ያገኘውን፤ ተፍ ተፍ ብዬ የሠራሁትና ያገኘሁት ነው የሚል ሰው ንስሐ ሊገባ ሲመጣ፤ ይህንን ሁሉ ነገር ያገኘሁት ሰርቄ ነው ሲል፤ በል እውነት ከልብህ ንስሐ መግባት ከሆነ የፈለከው “የወሰድከውን መልስ ፥ የበደልከውን ካስ” ቢባል ያ ሰው ተመልሶ ይመጣል?
መልሳችን፦ አይመጣም ነው። ስለዚህ ለጥያቄው መልስ ተሰጥቷል ማለት ነው!
አሁን ደግሞ ሻል ያልን ነን፤ በቤቱ እንኖራለን የምንል ለንስሐ እንመጣና ምን አጠፋችሁ? ስንባል፥ “እንዲህ አድርገን ፣ እንዲህ አድርገን . . . ” ስንል በሉ እመቤታችን በጸሎቷ በምልጃዋ እንድትቆምላችሁ ውዳሴዋን እየደገማችሁ ስድሳ አራት ስገዱ ስንባል ምንድነው መልሳችን? የዚህን ጊዜ የችግር ብዛት መምዘዝ ይጀመራል ፤ እንዲህ ሆኜ፣ በዚህ ወጥቼ ፣ በዚህ ወርጄ . . . ማለት እንጀምራለን። የወገባችንን ጤንነት የሚያረጋግጥ ኃጢአት ሠርተን ለንስሐ የመጣነው ሁሉ ቀኖናው ሲሰጠን ለመስገድ ጉልበቴን ወገቤን እያልን ለእኛ የሚስማማን ቀኖና እንዲሰጠን ለማሳመን እንጥራለን። ጨከን ሲባልብን ደግሞ እሳቸው ጋር አለመሄድ ነው እንላለን። ለምን? ሲባል እሳቸው ያከብዳሉ እንላለን።
በነገራችን ላይ አሁን እኮ አባቶች ካህናት ንስሐ የሚሰጡን በድርድር ነው። ይህንን ብንላቸው አይፈጽሙትም በዚያው ይቀራሉ ብለው በመስጋት አባብለው ይዘውን ነው እንጂ በመጽሐፉ የተደነገገውን ተከትለው አይደለም። አያችሁ ለዚህ ያበቃን ቅምጥልነት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፥ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤ ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት” (1 ጢሞ 5: 5-6 ) እንዳለ በጠዋት ተነስታ ጥሩ ነገርን ወደ አፍዋ ማለት የለመደችን ቅምጥል ሴት ጾም ስናዛት ይፈትናታል። ስለዚህ አባብለን ነው ሁሉን የያዝነው።
ቴክኖሎጂን ፣ ሌላ ሌላውንም በመጠቀም ኑሮን ማቅለል ጥሩ ነው። እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፦ ኑሮን ማቅለል ለምን? ኑሮ እንዲቀልላችሁ የምትፈልጉት ለምንድ ነው?
ላለመድከም የሚል መልስ ከጉባዔው ሲመለስ ፤ ጉባዔው አባብሎ የመለሰውን መልስ አባታችን “ለስንፍና እንዲመቸን ነው” ብለው አሰተካከሉን ። አባቶቻችን ሰባት ዋና ዋና ኃጢአቶች ብለው ከሚሏቸው ውስጥ ስንፍና አንዱ ነው።
ሰነፍ ሰው የኃጢአት መደብር ነው። ሰነፍ የሆነ ሕሊናውም ሰውነቱም ሥራ የፈታ ሰው የሚሄደው ኃጢአትን ወደ መሥራት ነው። አስተውሉ! ድሮ ሕይወት ከባድ በነበረበት ጊዜ ሰው ጭንቀቱ ፣ ሓሳቡ ሁሉ ኑሮውን ለማሸነፍ ነው። አሁን ግን ኑሮ ቀለል ሲል ጭንቀቱ ጠፋ። አሁንም ልብ ብላችሁ ራሳችሁ ታዘቡ እስቲ ፤ ኑሮን አቀለልን ስንል አንዱ በጣም ያቀለልነው ነገር ቢኖር ኃጢአት የመሥራት መንገድን ነው። ልክ ኑሮን ያቀለልነውን ያህል ኃጢአት የመሥራትንም መንገድ ቀላል አድርገነዋል።
📙 አንድ መጽሐፍ ሳነብ እንዲህ ይላል፦ “ነፃ መሆን መልካም ነው ፥ ነፃ የሆንከው ግን ከምንና ለምን እንደሆነ ጠይቅ” ይላል። በአሜሪካን የጥቁሮች ታሪክ ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ነፃ ከወጡ በኋላ ነፃነታቸውን ምን እንደሚያደርጉት እና ምን እንሁን ብለው እንደጠየቁት እና ግራ እንደገባቸው ፥ የተወሰኑት ደግሞ ተመልሰው ወደ ጌቶቻቸው እንደሄዱት እንዳንሆን ነፃ የምንሆነው ከምንና ለምን እንደሆነ በደንብ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ጌታ እግዚአብሔርም ሰው ነፃነቱ ግራ ሊያጋባው እንደሚችል ስለሚያውቅ እንዲህ ብሏል:- “አንተም ወንድምህን ዕብራዊውን ወይም ዕብራዊቱን ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግሉህ በሰባተኛውም ዓመት ከአንተ ዘንድ አርነት አውጣው። ከአንተም ዘንድ አርነት ባወጣኸው ጊዜ ባዶውን አትስደደው፤ ነገር ግን ከመንጋህ፥ ከአውድማህም፥ ከወይንህም መጥመቂያ ትለግስለታለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ባረከህ መጠን ትሰጠዋለህ። አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደ ነበርህ አምላክህም እግዚአብሔር እንዳዳነህ አስብ፤ ስለዚህ እኔ ዛሬ ይህን ነገር አዝዝሃለሁ። እርሱ ግን አንተንና ቤትህን ስለወደደ፥ ከአንተም ጋር መልካም ስለ ሆነለት፦ ልወጣ አልወድድም ቢል፥ አንተ ወስፌ ወስደህ በቤትህ በር ላይ ጆሮውን ትበሳዋለህ፥ ለዘላለምም ባሪያ ይሆንልሃል። በሴት ባሪያህ ደግሞ እንዲሁ ታደርጋለህ።”
(ዘዳግ 15: 12-17) (ዘጸአ 21: 2-6 )
እኔና እናንተም አንዳንድ ጊዜ እንዲሁ ነው። እረፍት ነው የናፈቀኝ በጣም እንደው እረፍት ወጥቼ እንልና ከመሥሪያ ቤት አሥራ አምስት ቀን እረፍት ሞልተን ወጥተን በሦስተኛው ቀን ምን እንደምናደርገው ግራ ይገባናል። ከዚያ በኋላ እቤት ውስጥ በሆነው ባልሆነው መነጋገርና መጨቃጨቅ እንጀምራለን። ይህንን የምናደርገው ማድረግ ፈልገን ሳይሆን እረፍቱን እንዴት አንደምንጠቀምበት ስላላወቀን ነው። ስለዚህ ሊያርፍ የወጣው ሰው ወደ መሥሪያ ቤት ሲመለስ ተደብሮ፣ ደክሞት ፣ ዝሎ፣ የሥራ ፍላጎቱ ሞቶ ነው ።
📣 አንድ ነገር ከመጠየቃችሁ በፊት ለምን እንደፈለጋችሁት ግን እርግጠኛ ሁኑ!
♦️ ሀብት ፈልጎ ሲያገኝ ምን እንደሚያደርገው ግራ የሚገባው ሰው አለ፤
♦️ ትዳርን ፈልጎ ሲሰጠው ምን እንደሚያደርገው ግራ የሚገባው ሰው አለና፥ ሌላም ሌላም እንዲሁ ።
✍️ አሁንም ሕይወታችንን ማቅለል ነው አልን ። እሺ ብሎ አቀለለው። የኑሮን መቅለል ለምን ፈለግነው? ለምን እንደምትፈልጉት እርግጠኛ ሁኑ ! ብዙ ነገር ጠይቀን እግዚአብሔር የሚያዘገይብን ያንን የጠየቅነውን ነገር ለምን እንደ ፈለግነው እርግጠኛ እስከምንሆን ነው። እርግጠኛ ሆናችሁ መልስ ስትሰጡ ይሰጣችኋል። እርግጠኛ ሆናችሁ ካልነገራችሁት ግን ጌታ እግዚአብሔር እንድትጠፉበት ብሎ አይሰጥም። ይህን ልብ በሉ!
📌📌 አስተውሉ! እስካሁን ያየናቸው ሁሉ ክርስትና ሕይወት ነው እንዳልን እንድንኖርባቸው የሕይወት መመሪያ ነው እየተማርን ያለነው እንጂ ሌላ አይደለም። ስለዚህ በየእለት የሥጋ ሕይወታችሁ ላይ አምጡና ተጠቀሙበት ። አንድ ሰኞ የምትማር ልጄ ለምን እንደሚማሩ ለተጠየቁት ጥያቄ መልስ እንዲህ ብላ መልሳለች:- “እኔ የመሰለኝ ዝም ብሎ ስብከት ልማር የመጣሁ ነበር የመሰለኝ ፥ ግን አሁን እዚህ ከመጣሁ የተማርኩት የሕይወት ፍልስፍናን ነው። በዚያ የሕይወት ፍልስፍና ከባድ ቢሆንም ለመኖር እያተገልኩ ነው “
ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::
ሙሽራው ሠርግ ማድረግ ሸቶ ከሕዝብ፣ ከነገድና፣ የተለያየ ቋንቋ ከሚናገር ወገን ሚስት ያጩለት ዘንድ ሽማግሌዎችን ላከ። ሽማግሌዎቹም የሙሽራውን ማንነት ለሰብአ ዓለም በተለያየ ኅብረ አምሳልና ቃል ገለጡ። ከባቢሎን እስከ ግብፅ ፣ ከኢየሩሳሌም እስከ ግሪክ፣ ከፋርስ እስከ ሮም ለሙሽራው ራሳቸውን ለማቅረብ ፈቃደኞች ለሆኑ ሁሉ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪው ቀረበ።
የሽማግሌዎቹ መልእክት የገባቸው ባለጠጎች ድህነትን መረጡ። ሌሎቹም ከኖሩበት ቀዬ ከዘመዶቻቸው ተለይተው ወጡ፡፡ ንፁሐን፣ ኃያላን፣ ልዑላን ዘማ፣ ደካማ፣ ስደተኛ አድርገው ራሳቸውን ሰጡ:: ጥጋባቸውን በረሃብ ፣ ደስታቸውን በኀዘን፣ ክብራቸውን በውርደት ለውጡ። ነገር ግን እንደ ናፈቁ ሳያዩ፣ እንደ ተራቡ ሳይመገቡ፣ እንደ ተጠሙ ሳይጠጡ ዓረፍተ ዘመን ገቷቸው በሞት ተዋጡ። በሞት አገርም እንኳ ሆነው “ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲዖል አትተዋትምና” ሲሉ የተወደደችውን የመዳን ቀን ለማየት የልባቸውን ተስፋ ገለጡ::
የሙሽራው መምጣት በዘመናት ጀርባ እየተሻገረ 5500 ዓመታትን አስቆጠረ። “ነፍሴ እንደ ምድረ በዳ ተጠማችህ” እስኪል የፍጥረት ናፍቆት ጨመረ።
ከዕለታት በአንዱ ግን በዮርዳኖስ ማዶ ባለ በረሃ የሚጮኽን ድምጽ ሰዎች ቀርበው አንተ ማነህ? ለላኩን ምን ብለን እንናገር? ብለው በጠየቀት ጊዜ “እኔ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይቻለኝ እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል” ሲል በኖሩበት ሥርዓት መስሎ የሙሽራውን መገለጥ ነገራቸው። ኋላም “ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው” በማለት ገልጦ አበሰራቸው፡፡
ነገር ግን የሙሽራው ሙሽራይቱን ሊያጭ እንደሚመጣ ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ ራሳቸውን ለማቅረብ ይዘጋጁ የነበሩ ሁሉ ሙሽራው ምን ሊመስል እንዴትም ሊገለጥ እንደሚችል የየራሳቸውን የምኞት ሥዕል አስቀምጠው ይጠባበቁ ነበር። የተወሰኑት ካለባቸው ችግር በመነሣት፤ ሌሎችም ሙሽራ ከሆነ ሊመስል የሚችለው ይህን ነው ብለው የስቀመጡትን ቅድመ ግምት ለማየት፤ ሙሽራውን በየራሳቸው መንገድ ጠበቁት።
ኢየሩሳሌም በጦር ኃይል የበረታ፤ ዘፋኑን ከፍ አድርጎ የሚዘረጋ፤ በወታደሮች ታጅቦ የሚመጣ ሙሽራ ስለ ጠበቀች ሠርጓ ተስተጓጎለ። አቴናም በጥበብ የተራቀቀ ስለ ጠበቀች አልፏት ሄደ። ሮምም ባለጠጋ ተመኘች የሙሽርነት ዕድሉም አምልጧት ቁሞ ቀር ሆነች።
ጠቢብም፣ ባለጠጋም፣ ኃያልም ባይሆንም ፍቅር ብቻ ይኑረው ብላ ሙሽራዋን የናፈቀች ቤተክርስቲያን በዘርና በእርሾ መስሎ የሚናገረውን ሰምታ እውቀት የለውም ሳትል፤ “የሰው ልጅ ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም ” በማለት በአደባባይ ድህነቱን መግለጡን አይታ ሳትንቅ፤ ሲተፋበት፣ ሲሰደብ፣ ሲገረፍና ሲቸነከር ተመልክታም በደካማነቱ ሳታፍር ፤ የሚሰጠው አጥቶ ደሙን ማጫ አድርጎ ቢያቀርብላት እንዴት ያለ ነገር ነው? ብላ ሳታመነታ ሙሽራዋ እንዲሆን ፈቀደችው። ትሕትናን አጥንቷ (የምትጠራበት ኩራቷ)፣ ንጽሕናን ውበቷ፣ መዓዛ ቅድስናዋን ዕፍረቷ (ሽቱዋ)፣ ራስን መካድን ምንጣፏ፣ እምነትን እልፍኟ አድርጋ ፍቅሩን ተቀበለችው:: ለሚያሽሟጥጧት ሁሉ “ውዴ የእኔ ነው፤ እኔም የእርሱ ነኝ” ስትል ቁርጡን ነገረቻቸው።
በሠርጉ እንዲታደሙ ተጠርተው የነበሩ እያንዳንዳቸው ምክንያት እየሠጡ ቢቀሩ ባልንጀሮቹ በተመሳቀለ መንገድ ቁመው ማንንም ከማን ሳይለዩ እንዲጠሩ ላከ፤ ሠርግ ቤቱ በተጋባዦች ሞላ።
ሙሽራው አባቱ ለግዛቱ ድንበር የሌለው ንጉሥ እንደሆነና ያሳደገው ወላጅ አባቱ እንዳልሆነ ሲወራ ብዙዎች ሰምተዋል። እናቱ ዝምተኛ ከመሆኗ የተነሣ እርግጡን ለማወቅ ጨንቋቸዋል። እናቱ አግኝተው ያጡ ቀን የጣላቸው ድሆች ልጅ ናትና፤ በታላቁ ሠርግ ላይ አዳራሹን ሞልተው ለታደሙ ሁሉ የቀረበው አንድ ጽዋ ወይንና የታረደውም አንድ በግ ብቻ ነበር። ዕድምተኞቹም ግብዣው ሲጀምር አሁን ይህ ስንት ሰው ሊስተናገድበት ነው? ብለው እንዳልነበር ከሠርጉ በኋላ የረሃብና የጥም ነገር ተረሳቸው አሉ!
ሙሽራይቱንም እንዴት ሊያኖራት ነው? እያሉ ቢያንሾካሹኩም መሸቶ ሲነጋ ግን ድሃ፣ ደካማና አላዋቂ መስሎ ያጫት የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ የጠቢባን እውቀት መሆኑ ኋላ ላይ ታወቀ። ወደ ሩቅ ሀገር ከሄደበት እስኪመለስ ባልጠበቀት መንገድ ለሙሽራው መታጨቷ ያስቀናቸውና ያበሳጫቸው ሁሉ በጠላትነት ተነሡባት። ዳግመኛ ተመልሼ ስመጣ እኔ ወዳለሁበት እወስድሻለሁ፤ እስከዚያ ለእኔ ያለሽን ታማኝነት መጠጊያሽ ፍቅሬን መፅናኛሽ አድርገሽ ቆይኝ ስላለት እነሆ እስካሁን ለቃሉ ታምና አለች። ሲሆንላቸው በኃይል ሳይሆንላቸው በማባበል እምነቷን ሊያስጥሏት ቢጥሩም እርሷ ግን ሁልጊዜ በማለዳ፣ በቀትር፣ በምሽትና በእኩለ ሌሊት ጎረቤቶቿ እስኪገረሙ የሙሽራዋን ስሙን እየጠራች ማዶ ማዶ ማየት አልታከታትም፤ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!” ማለትን አላቆመችም::
ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::
የእግዚአብሔር ቃል የነካው ልብ በማያቋርጥ አለማረፍ ውስጥ ያርፋል። የያዘውን እያፀና የፊቱን ለመያዝ ይዘረጋል። ሁል ጊዜ ራሱን “ይህን ሁሉ ፈጽሜአለሁ፤ የሚጎድለኝ ምንድር ነው?” ሲል ይጠይቃል። ተስፋው የተረጋገጠ የሚሆነው ፍርሃት በገፋው ንስሐው፣ ልምድ በቃኘው ክርስትናው፣ ፍቅር በተለየው አምልኮቱ ሳይሆን “በእግዚአብሔር ቸርነት” ላይ ነው። በእርግጥ ይህም ቃል ተደጋግሞ ከመሰማቱ የተነሣ ውበቱ እና እውነቱ ደብዝዟል።
አንዲት በብዙ የሥራ፣ የትምህርትና የቤተሰብ ኃላፊነት የተያዘች ልጄ ልትጎበኘኝ መጥታ ሳለ፤
“አንድ ቀን ሲያስተምሩ ለመሆን ወይም ለማድረግ፣ በማሰብና በመሆን ወይም በማድረግ ያለውን ክፍተት ለማስታረቅ ድልድዩ ውሳኔ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ። ለመወሰንና በውሳኔዬ ለመጽናትስ ምን ማድረግ አለብኝ?” በማለት ጠየቀችኝ።
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያቀበለኝ መልስ “ክርስትናን በሕይወትሽ ውስጥ አስፈላጊ ናቸው ከምትያቸው ዝርዝር ውስጥ አውጪው!” የሚል ነበር። ምን ለማለት እንደፈለግሁ ግር ስላላት ለማብራራት ሞከርኩ።
“በሕይወትሽ ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ናቸው የምትያቸውን በዝርዝር አስቀምጪ።” ስላት
“ቤተሰብ፣ ሥራ፣ ትምህርት፣ የክርስትና ሕይወቴ፣ ጓደኞቼ . . . “ ስትል በመጣላት ቅደም ተከተል አስቀመጠቻቸው።
“እንግዲያው እነዚህን ሁሉ በእኩል ደረጃ፣ በእኩል ትኩረት፣ በሚገባቸው መሥዋዕትነት የምትኖሪያቸው ይመስልሻል?” ስል ጠየቅኋት።
“ይከብዳል!ለአንዱ ወይም በጣም አስፈላጊ ለምለው የበለጠ ትኩረት አደርጋለሁ፤ የጊዜና የሕይወት መሥዋዕትነትም እከፍላለሁ። በዚያ መካከል ሌላውን ልዘነጋ እችላለሁ፤” ስትል አረጋገጠችልኝ።
በምላሼም “እንግዲያው ችግሩ ያለው እዚያ ጋር ነው። በክርስትና ውስጥ ፍሬ ልታፈሪ እና በልብሽ መታደስና መለወጥ ሐሤት ልታደርጊ የምትችይው ክርስትናን በሕይወትሽ ውስጥ እንደ አንድ አስፈላጊ የሕይወት ክፍል አድርገሽ ስትኖሪ ሳይሆን ክርስትና ሕይወትሽ ሲሆን ነው። ክርስትና ሕይወትሽ ሲሆን የምታስቢው፣ የምታቅጂው፣ የምትወስኚው፣ የምትሠሪው፣ የምትሆኚው፣ . . . ሁሉ ክርስትናን ማዕከል አድርገሽ ይሆናል። በሕይወትሽ ውስጥም ከክርስትና ጋር የሚጋጭ ውሳኔና አካሄድ ስለማትከተይ ለመሆን በመፈለግሽና በመሆንሽ ወይም ለማድረግ በመፈለግሽና በማድረግሽ መካከል ልዩነት አይፈጥርም።
መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገውን ሁሉ ያደረገውና የሆነውን ሁሉ የሆነው ለእኛ ድኅነት ነው። ያን መስመር ስትከተዪ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር ታደርጊዋለሽ። በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታ ከታጠረ ክርስትና ነጻ መውጣትና በሁሉ ቦታ ክርስቲያን መሆን ማለት ይህ ነው። ክርስቲያን ተማሪ፣ ክርስቲያን ሠራተኛ፣ ክርስቲያን ሚስት ወይም ባል፣ ክርስቲያን ልጅ፣ ክርስቲያን ጓደኛ፣ ክርስቲያን ነጋዴ፣ ክርስቲያን አገልጋይ፣ ክርስቲያን ባለሥልጣን፣ ክርስቲያን ወታደር፣ ክርስቲያን ዜጋ፣ የመሳሰሉትን መሆን ማለት ነው።
እነዚህን ሆኖ ክርስትናን ሲያስፈልግ በአጃቢነት መጠቀምና እነዚህን በክርስትና ውስጥ መሆን ትልቅ ልዩነት አላቸው። ክርስትናን እንዳንኖር ያደረገንም ክርስትናን በሕይወታችን ውስጥ እንደ አንድ አስፈላጊ ነገር መቁጠራችን ነው። ከዚያ ዝርዝር ውስጥ አውጪው።
ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::
ቅዱስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር ተራራ የጌታችን መልኩ ተለውጦ ሲያበራ፤ ልብሱም በምድር አጣቢ ሊያነፃው ከሚችለው በላይ ነጭ ሲሆን፤ ሙሴና ኤልያስም መጥተው ከጌታ ጋር ሲነጋገሩ አይቶ የመጣለትን ሀሳብ የገለጠበት ቃል ነው ” በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው”።
አባቶች ቢርበንና ቢጠማን ሙሴ መና እያወረደ ውሃ እያፈለቀ፤ ጠላት ቢነሣብን ኤልያስ እሳት አውርዶ እያጠፋ፤ አንተ ደግሞ ብንታመም እየፈወስኸን ብንሞት እያነሳኸን በዚህ መሆን መልካም ነው ማለቱ እንደ ሆነ ይተረጉማሉ።
ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ንግግሩ በዚያ ሥፍራ ብንገኝ ልናስበውና ልንመኘው የምንችለውን ሁላችንን ወክሎ ስሜታችንን ነው የተናገረው። ለሥጋችንና ለስሜታችን ምቾትና ደስታ የሚሰጥ ቦታ መሆን የሁላችን ምኞት ነው:: ቢሆንልን መሆን የምንፈልግ የት ይሆን? አሁን ያለንበት ቦታና ሁኔታ ውስጥ ያለነውስ ተመችቶን ወይም ያን ሆነን መኖርን አምነንበት ነው?
በእውነታው አንድ ነገር መሆንና (ሆኖ መገኘትና) የሆነውን መኖር እጅግ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ከትንሹ ብንጀምር በተሰማራንበት ሙያ ባለሙያ መሆንና ሙያውን መኖር ይለያያል። አንድ ሰው ፖሊስ ቢሆን ዩኒፎርም ለብሶ በሚንቀሳቀስበት የሥራ ሰዓቱ ወንጀል እየተከላከለ ከሥራ ውጭ ነኝ ብሎ ባሰበበት ሰዓት ወንጀል ሲፈፀም አይቶ በግዴለሽነት ካለፈ ፖሊስ ሆነ እንጂ ሙያውን አይኖረውም፡፡ የሕክምና ባለሙያስ ሙያውን መኖር ያለበት የት ይሆን? ብዙዎቻችንን የምንደስተው በ “መሆን” አችን እንጂ የሆነውን ስለ “መኖር” ተጨንቀን አናውቅም። መሆን ውስጥ ያለው ደስታና ምቾት ሲሆን መኖር ውስጥ ግን የሚጠብቀን ተግባርና ኃላፊነት ነው። ብዙዎቻችን ጌታ እግዚአብሔርን የምንለምነው የለመነውን ነገር እንድንሆን እንጂ የሆነውን እንድንኖረው አይደለም።
ትዳር የምንለምን ባል/ሚስት ስለ መሆን አብዝተን እንለምናለን የለመነውም ይሰጠናል። ትልቁ ችግር መሆን የለመነውን ለመኖር ፍላጎቱ፣ ዝግጁነቱና ቁርጠኝነቱ ስለሌለን በ “መሆን” ገነት የመሰለን ሕይወት በ “መኖር” ደረጃ ሲዖል ይሆንብናል። ስለዚህ ብዙዎቻችን ባል/ሚስት መሆን ችለናል ፤ ያልቻልነው ነገር ቢኖር ባል/ሚስት ሆነን መኖር ነው። ባል/ሚስት መሆን ምቾት አለው። ከቤተሰብ ጭቅጭቅ፣ ከጓደኞች የነገር ጉንተላ፣ ከማኅበረሰብ ሐሜት፣ ከዕድሜ ጋር የጎሪጥ ከመተያየት፣ ሰው ሁሉ በፈሰሰበት ቦይ መፍሰስ አለመቻል ከሚፈጥረው ጭንቀት፣ ወዘተ . . . ያሳርፋል። ባልነት/ሚስትነት የሚጠይቀውን መኖር ግን ያደክማል፤ ያታክታል። በመሆኑም ሚስትህን ባልሽ ነኝ ከማለትህ በፊት ባልነትን መኖርህን ጠይቅ፤ ባልሽን ሚስትህ ነኝ እኮ ከማለትሽ በፊት ሚስትነትን መኖርሽን ጠይቂ፤ ሁለቱ ለየቅል ነው:: መሆን ከብዶ አያውቅም የሆነውን መኖር እንጂ !!!
አባት/እናት መሆንም እንዲሁ ደስታና የኅሊና ምቾት አለው፤ ከምላስ ያድናል። ወላጅነትን መኖር ግን ስንቶቻችንን አታክቶን ልጆቻችን እንደ ምድረ በዳ አበቦች በክረምቱ ዝናምና በፀሐይ ብርሃን ብቻ አድገው እንዲፈኩ አስመኝቶናል። የመሆንና የመኖር ልዩነቱ አይጣል!!!
ከፍ ወዳለ ሀሳብ ሰንሄድ ሰው መሆንና እንደ ሰው መኖር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ሰው ለመሆን የፃፍነው ማመልከቻ፣ ያወጣነው ወጪ ወይም የደከምነው ድካም የለም። እኔ ስለ ራሴ እስከማስታውሰው ድረስ ሰው ያልነበርኩበት ጊዜን አላስታውስም። ስፀነስም ስወለድም ሰው ተብዬ እውቅና ተሰጥቶኛል፡፡ ሁላችንም እንዲሁ ነን። የሁላችንም ችግር ደግሞ ሰው መሆንን መኖር አለመቻላችን ነው:: ዳዊት ሰው የሆነውን ልጁን ሰሎሞንን “ልጄ ሆይ ሰው ሁን!” ያለዉ ሰውነትን ኑረው ሲለው ነው። ፈረስን ፈረስ ሁን፤ አንበሳን አንበሳ ሁን፤ እባብን እባብ ሁን ልንለው አንችልም። ምክንያቱም የሆኑትን ይኖሩታልና። ሰው ግን በመጀመሪያ የሆነውን የማወቅ ጸጋ ስለተሰጠው ማለት ፈረስ ፈረስ፣ አንበሳ አንበሳ፣ እባብም እባብ ምን መሆኑን አያውቁም፤ ሰው ግን ሰው መሆኑን ስለሚያውቅ። ሁለተኛ ሰው የሆነውን የመኖርም ሆነ ያለመኖር አቅም ስላለው ሌሎቹ ግን ስለሌላቸው የሆነውን በተግባርና በኃላፊነት እንዲገልጥ (እንዲኖር) ይጠየቃል፤ ይነገረዋል። የሆነውን በመኖር ካልገለጠው ግን የሆነውንም ያጠፋዋል።
የበለጠ ከፍ ወዳለው ስናልፍ ደግሞ እኛ ክርስቲያን ሆነናል። ክርስቲያን የመባል ቀጥተኛ ፍቺ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ማለት ነው። በመሆንና በመኖር ግን ትርጒሙ ይለያያል። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ማንም ሊነጥቀን አይችልም። ሲፈርድብን እንኳ እንደ ልጅ ነው:: ለፍርድ የሚያበቃን ግን የሆነውን አለመኖራችን ነው።
እንደ እውነቱ ይህን ጽሑፍ ከምናነበው ውስጥ ክርስቲያን በመሆኑ የሚከፋና “ምን አቅብጦኝ ነው ክርስቲያን የሆንኩት” የሚል ወይም በአቅፋቸው ወስደው ያስጠመቁትን የሚረግም እንደሌለ እተማመናለው። ክርስትና ግን ክርስቲያን ከመሆን ባለፈ መኖርን ባትጠይቀን ምንኛ መልካም ነበር?! የምንልም ቁጥራችን ቀላል አይሆንም። እንደው በመሆን ብቻ ያቺ መንግሥት ብትወረስ ምን ነበረበት?! ግን የሆንከውን “መኖር” የሚል ግዴታ ተከተለው።
አሁንም እናስተውል አብዛኞቻችን ክርስቲያን ለመሆን ምንም አልደከምንም:: ማስታወስ ከምንችልበት ጊዜ አንስቶ ክርስቲያን ያልነበርንበት ጊዜ ትዝ አይለንም። የሚገርመው ክርስትናን መኖር የቻልንበት ጊዜንም እንዲሁ አናስታውስም። ክርስቲያን መሆንንም በመታወቂያ ደረጃ ያልተውነው በዚህ መሆን ለእኛ መልካም መስሎ ስለታየን እንጂ መኖር ለሚጠበቅብን ቁርጠኛ ስለሆንን አይደለም። በክርስትና አስተምህሮ የሰማነው አምላክና እርሱን ከበው በሚኖሩ ቅዱሳን ዙሪያ ስለ መሆን የሰማነው ትርክት የሰጠን ምቾት ስላለ በዚህ መሆን መልካም ነው ብለን እናስባለን። ከገናናው ክብር ግን የሆነውን መኖር እንዳለብን የሚያስገነዝበው “እርሱን ስሙት” የሚለው ቃል ሲመጣ ለ “መኖር” ወድቀን እንደ ሞተ ሰው እንሆናለን፤ ሁሉን ወደ መኖር ያመጣው እጅ እስኪዳስሰን ድረስ።
ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::