በክርስትና ትምህርት ሞት የሕይወት ፍጻሜ ሳይሆን የምድራዊ ሕይወት መጨረሻ፤ የሰማያዊ ሕይወት መጀመሪያ ነው። ክርስቲያኖች በሞት ምክንያት የሚመጣ ኃዘን የማይጸናባቸውም ስለዚህ ነው። ከሞት በኋላ ለማንም በምድር ላይ ዕድል ፈንታ የለውም። በእርግጥ ይህ የሚሆነው በዓለም ዘንድ ነው እንጅ በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ግን ማንም ቢሆን ከአባልነት አይወጣም። የቤተ ክርስቲያን ኅብረት የስማያውያን መላእክት፣ የምድራውያን ጻድቃንና በገነት ያሉ ነፍሳት ኅብረት ነውና።
ለዚህም ነው ዛሬ በኅብረት የምናገለግለው። መላእክት ጸሎታችንን መሥዋዕታችንን ያሳርጋሉ፤ ባህታውያንን በገዳም፣ ምዕመናንን በዓለም፣ ሰማዕታትን በዐውደ ስምዕ፣ ካህናትን በጊዜ ቁርባን ይራዳሉ። በዐፀደ ሥጋ ለሌሉ ነፍሳትም በቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ መታሰቢያ ይደረግላቸዋል። ሞት ከዓለም ይለያቸዋል እንጅ የክርስቶስ አካል ከመሆን አይለያቸውምና።
የሞተ ሰው ቢወዱት የማይደሰት፣ ቢጠሉት የማይቆጭ ነው።
ሢራክ “ዘሞተሰ አዕረፈ፤ የሞተ ሰውስ አረፈ” ሲል ስንሰማው ሞት የዕረፍት መጀመሪያ እንደሆነ እንረዳለን። ምን እበላለሁ፣ ምን እጠጣለሁ፣ ምን እለብሳለሁ፣ የት አድራለሁ፣ የት እኖራለሁ ማለት የሌለበት፤ ሰዎች ጠሉኝ ወደዱኝ ብሎ መጨነቅ የሌለበት ሕይወት ስለሆነ ደስ የሚል ነው። ብርድና ሙቀት፣ በጋና ክረምት በማይፈራረቁበት ዓለም መኖር መልካም ነገር ነው። ይህን ወደመሰለ ዓለም እስክንመለስ ድረስ በኑሯችን ሁሉ ማግኘትና ማጣት፣ መውደድና መጥላት፣ መሳቅና ማዘን ያጋጥመናል።
ለማንኛውም ዛሬ ልነግራችሁ የፈለግሁት አንድ ቀን ከየኔታ ጋር ስንጫዎት ያስገረመኝ ጥያቄና መልስ ነው። የኔታ ከምናውቃቸው ጓደኞቻችን የአንዱን ስም በመጥራት የጠየቃቸውን ጥያቄና የመለሱለትን መልስ ሲያወጉን እንዲህ አሉ “እኔ ለሰዎች የማደርገው ነገር መልካም ነገር ነው ሰዎች ግን የሚመልሱልኝ ክፉ ነገር ነው፤ እኔ ሰው እወዳለሁ ሰዎች ግን በተቃራኒው ይጠሉኛል ምን ባደርግ ይሻለኛል” አለኝ።
እና ምን ብለው መለሱለት አልኋቸው። “የዚህ ዓለም ሰው ምንም አስተያየት ሳይሰጥ አጠገብህ የሚቆም ስትሞት ብቻ ነው” አልሁት አሉኝ። ለጊዜው ባይገባኝም ቤቴ ገብቸ ነገሩን በሀሳቤ ሳመላልሰው በእርግጥም የዚህ ዓለም ሰው ከፊት የሚያስቀድምህ፣ ከኋላ የሚከተልህ ስትሞት ብቻ ነው። ሊሸከምህ እንጅ እንድትሸከመው የማይፈልገው የሞትህ እንደ ሆነ ብቻ ነው። መኖርህን ያልሰሙ ሰዎች ሁሉ መሞትህን ሊሰሙ ይችላሉ። መኖርህ የመሞትህን ያህል ገናና ሆኖ ሊነገር አይችልም።
ምንም ብትከብዳቸው የሞትህ ቀን ታግሠው ይሸከሙሃል። የሞተን ሰው ከበደኝ ብሎ ማን ያማዋል? ምንም ቢሆን ከሚደርስበት ድረስ ሳያደርሰው ማንም ወደ ቤቱ ላለመመለስ ይሞክራል። ሰው ሲሞት ወዳጁ ይበዛል። የነቀፉት ሁሉ ያመሰግኑታል። ምናልባት በዚያ መካከል እንደ ቅድስት ሐና፣ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ያለ ንጹሕ ሰው ተገኝቶ ጥላውን ቢጥልበትና ቢነሣ ሀሳቡን የሚቀይር ብዙ ሰው ማግኘት ይቻላል። ጌታ አልዓዛርን ካስነሣው በኋላ መልሰው ሊገድሉት የተማከሩ ሰዎች መኖራቸውን ስለምናውቅ ይህ ነገር ለእኛ እንግዳ ነገር አይሆንብንም:: ዮሐ. 12፥10
ችግሩን ይዞት የሚመጣው መነሣታችን ነው ማለት ነው። አልዓዛር በመቃብር ውስጥ ሳለ ያለቀሱለት ሁሉ ሲነሣ ደስ አላላቸውም። በአልዓዛር መነሣት የእግዚአብሔር ክብር ይገለጣላ! አንተ ተነሥተህ የእግዚአብሔር ክብር ከሚገለጥ ቢቀር ይሻላቸዋል። ትዝ የሚላቸው ያንተ መነሣት ነው እንጅ የእግዚአብሔር ክብር በሕዝቡ ዘንድ መገለጥ አይደለምና። መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በስብከቱ ከትንሣኤው ይልቅ ስለሞቱ ደጋግሞ ተናግሯል። ነገር ግን አይሁድ ያስታወሱት “በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ” የሚለውን እንጅ እሞታለሁ የሚለውን አልነበረም። ለዚህም ነው ገድለነዋል ብለው ሳይዘናጉ ተሰብስበው ሂደው ጲላጦስን “በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን፤ እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተለይቶ ተነሣ እንዳይሉ መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ መቃብሩን እንዲጠበቅ እዘዝ” ማቴ 27፥64 ያሉት። ከቻሉ እንዳትነሣ ይደራጁብሃል። ያ ካልሆነላቸው ደግሞ ትንሣኤህን በሰዎች ዘንድ የሚያጥላላ ወሬ ይነዙብሃል።
የትኩረት አቅጣጫቸው በዙሪያህ ካሉ ካልተነሡ ብዙ ሰዎች ይልቅ ከሞት የተነሣኸው ከመቃብር የተመለስኸው ያንተ ጉዳይ ነው። አልዓዛር በተነሣበት ወቅት ስለማርያም ስለማርታ ማን ያወራል? አልዓዛር ሳይነሣ ግን ሰው ሁሉ የተሰበሰበው ስለማርያምና ስለ ማርታ ብሎ እነሱን ለማጽናናት ነበር ዮሐ 11፥19 ከአልዓዛር ትንሣኤ በኋላ ግን በመነሣቱ ደስ ያላቸውም የሚመጡት እሱን ለማየት ሆነ፤ በመነሣቱ የከፋቸውም የሚመካከሩት እሱን ለመግደል ሆነ።
የተነሣ ሰው በዚህ ይታወቃል − ዓለምን ከሁለት ይከፍለዋል። ዜናውን የሰሙት ሰዎች ሁሉ ያለ እርሱ በቀር ሌላ ወሬ እንዳይኖራቸው ያደርጋቸዋል። የተነሣ ሰው ለብዙዎች መዳን ምክንያት እንደሚሆን ሁሉ ለብዙዎች ጭንቀትም ምክንያት ነው። አይሁድ ክርስቶስን ለመግደል ከከፈሉት ይልቅ የክርስቶስ ትንሣኤ እንዳይሰማ ያወጡት ወጭ ይበልጣል ማቴ 28፥12። ሞት ጠላት ይቀንስልሃል መነሣትህን ከታወቀ ግን ጠላት ይደራጅብሃል።
ማንም ቢሆን ወንድሙን በክብር መግለጥ ካልቻለ እግዚአብሔርን በክብር ሊገልጥ አይችልም። በወንድሙ ትንሣኤ ደስ ካላለው በክርስቶስ ትንሣኤ ደስ ሊለው አይችልም። በአልዓዛር ትንሣኤ ያልተደሰተ በክርስቶስ ትንሣኤ ደስ ሊለው አይችልምና። ነገር ግን በዚያ ዘመን በአልዓዛር ሞት ከተጨነቁት ይልቅ በአልዓዛር ትንሣኤ የተጨነቁት እንደሚበዙ በዚህ ዘመንም በወንድሙ ትንሣኤ ከሚደሰተው ይልቅ በወንድሙ ሞት የሚደሰተው ብዙ ነው።
ስለዚህ ወንድሜ ሆይ በትንሣኤ ከኖርህ ብዙ ወዳጅ እንደማይኖርህ ማመን አለብሕ ካልሞትህ በቀር ስላንተ በጎ ነገር ማውራት የማይፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን አስብ። ሕያው መሆንህን ሲያውቁ በማይመለከታቸው ሁሉ ይጣሉሃል። ስምህን በክፉ የማያነሡት ከሞትህ ብቻ ነው። ስሜ በክፉ እንዳይነሣ ብለህ እንደ ሞተ ሰው መሆን ትፈልጋለህ? ካልሞትህ አንወድህም ከሚሉህ ሰዎች ይልቅ “ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” ዮሐ 11፥11 ብሎ አንተን ለማስነሣት ወደአንተ የመጣውን ጌታ ልታከብረው ይገባል።
መነሣትህ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ ወደ መቃብር ሊመልስህ የሚችል ማን ነው? መነሣትህን ለማያምኑ ሰዎች መልስ መስጠትም አይገባም፤ ክርስቶስ ሞቱን እንጅ ትንሣኤውን በጠላቶቹ ፊት አላደረገውም፤ ነገር ግን ጠላቶቹ በትንሣኤው ማፈራቸው አልቀረም። ለጠላቶችህ ስትል አትሙት። ጠላቶችህ አጋንንት ደስ እንዳይላቸው ብለህ ከገባህበት የሞት ወጥመድ ውጣ − እሱም ኃጢአት ነው።
ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆን የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው::
የተፈጠርነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ሰው ሆነን ወደ ምድር የመጣንበትን ዘመን፣ የተገኘነበትን ምድር፣ የወጣንበትን ማኅበረ ሰብእ እና ሌሎችንም ጉዳዮች የመረጠ እርሱ እግዚአብሔር ነው። አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በራሱ ምርጫ ራሱን ያስገኘ ማን አለ? አጭር ወይም ረዥም፣ ቀጭን ወይም ወፍራም፣ ነጭ ወይም ጥቁር ሆኖ ስለመወለዱ ከእግዚአብሔር ጋር የተማከረስ ማነው? ሁሉም በእግዚአብሔር ፈቃድ የተከናወነ ነው። ገበሬ ዘሩን በምድር ላይ በበተነ ጊዜ ምድሩን ለዘሩ የሚመርጥለት ገበሬው ነው እንጅ ዘሩ እንዳልሆነ ሁሉ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ምርጫ እንጅ በራሱ ምርጫ ወደ ዓለም ሊመጣ አይችልም።
በዚህ መንገድ ወደ ምድር የመጣ የሰው ልጅ የሚኖረውም የእግዚአብሔርን ፈቃድ መሠረት አድርጎ ነው። በማኅፀን በሠራን ጊዜ ለሕይወታችን የሚያስፈልገንን አንዳች ሳያጎድል ሠርቶ ከማኅፀን ስላወጣን በምድር ላይ ስንኖር የምንኖርበትን ትዕዛዝ ቢያዝዘን አንዳች እንደሚያጎድልብን ሳንጠራጠር አምነን እንታዘዝለታለን። በባሕር የሚኖሩትን በባሕር ለመኖር የሚያበቃቸውን፣ በየብስም የሚኖሩትን በየብስ ለመኖር የሚያስችላቸውን አካል ሰጥቶ ፈጥሯቸዋል። አካላችንን ከሥርዓተ ዓለም ጋር አስማምቶ ምንም የማይጠቅም አካል ሳይጨምር የሚበቃንን እና የሚያስፈልገንን ብቻ ሰጥቶ ወደ ዓለም እንድንመጣ ማድረጉ ለእኛ የሚያስፈልገንን ሁሉ በመስጠት የሚያኖረን እርሱ ብቻ መሆኑን እንድናምን ያስገድደናል።
ከዚህም የተነሣ ነው ሰባኪዎቻችን፥ በሰው እንዳንታመን “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆችም አትታመኑ ነፍሳቸው ትወጣለች ወደ መሬትም ይመለሳሉ” መዝ 145፥3 ብለው ብለው መታመናችንን በሥጋዊና በደማዊ ፍጥረት ላይ እንዳናደርግ የመከሩን።
ልንኖረው ከተፈቀደልን ሦስት ክፍል ካለው ኑሯችን የመጀመሪያውን ያለ እግዚአብሔር በቀር ከእኛም ሆነ ከሰዎች አንዳች ምክር የሰጠበት የለም። ከማኅፀን ከወጣንም በኋላ የምንኖረው ሁለተኛውን ክፍል ኑሯችንን ሲሆን ከማኅፀን ከወጣንበት ጊዜ ጀምሮ ራሳችንን በሰዎች ዕቅፍ ስለምናገኘው ነው መሰለኝ ከእግዚአብሔር ሀሳብ ይልቅ በራሳችንና በሰዎችም ፈቃድ የመኖር ዝንባሌ ይታይብናል።
በውስጣችን ባለው አድሮብን፣ ተዋሕዶን ከሚኖረው አምላካችን ይልቅ አጠገባችን ከጎናችን ባሉ ሰዎች ተስፋ እናደርጋለን። ይልቁንም በቤተ እግዚአብሔር ለሚኖሩ ሰዎች በሰው መታመን እንዴት ያለ አስቸጋሪ ነገር መሰላችሁ?
ይህንን ያልሁት የዛሬውን መጻጉዕን ጉዳይ ሳስብ ቀድሞ የሚመጣብኝ እግዚአብሔር ሰዎችን ወድ ሚያድንበት ስፍራ ሂዶ ሰው መጠበቁ ስለሚያስገርመኝ ነው። የመጻጉዕን መዳን ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያዘገየበት በሰው ስለሚታመን ሳይሆን አይቀርም። “ጌታ ሆይ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት” ዮሐ 5፥5 በሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የሚታየው ሀሳብ መጻጉዕ በእግዚአብሔር ደጅ እየኖረ በሰው የሚታመን በሽተኛ እንደነበረ የሚያሳይ ነው። ከሩቅ ቦታ አምጥቶ የመጠመቂያው ስፍራ ያደረሰው ማነው? ይሄ ሰው ይህንን ያኽል ዘመን እንዴት አንድ ሰው ወደ መጠመቂያው እንዲወርድ ሊረዳው አልፈቀደም? አብረውት በመጠመቂያው ስፍራ ተኝተው የሚሰነብቱ አንካሶችን በሽተኞች ከዳኑ በኋላ እንኳን ይህንን ሰው ወደ መጠመቂያው ስፍራ አውርደውት ድኖ እንዲመለስ እንዴት አላደረጉትም? እያልሁ ብዙ ጊዜ አስቤ አውቃለሁ።
ይህ ሰው ከመጀመሪያው እምነት የጎደለው ነው። የዳኑት ሁሉ እግዚአብሔር ስለፈቀደላቸው ሳይሆን ሰው ስላላቸው ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ነው። የመጣው የእግዚአብሔር መልአክ በወረደ ጊዜ በሚናወጠው ውኃ ውስጥ ገብቶ ተጠምቆ ፈውስ ለማግኘት ነው ነገር ግን በሃይማኖቱ ላይ የሰዎችን እርዳታ ካልተጨመረበት በቀር መዳን እንደማይችል በማሰብ ይሄንን ሁሉ ዘመን ሰው ሲፈልግ ነው የኖረው። በእግዚአብሔር ፊት ሆኖ ሰው መጠበቅ የሚያስገርም ነገር ነው። ለዚህም ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ካዳነው በኋላ ራሱን ሳይገልጥለት በሰዎች መካከል ሆኖ የሄደው። እሱም ያዳነው ማን እንደሆነ ሊመረምር አልተመለሰም። ሰው ሲጠብቅ የኖረ ሰው እግዚአብሔር አዳነኝ ማለት እንዴት ይችላል? አይሁድ በጠየቁትም ጊዜ “ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” ነው እንጅ ያለው እግዚአብሔር አዳነኝ አላለም።
እምነታችን ሳይጸናልን ገንዘብ ብንቀበል፣ ሥልጣን ብናገኝ፣ ጤና ቢኖረን፣ ጉልበታም ብንሆን፣ ውበትና ደም ግባት ቢስማማልን፣ ዓለምን በመላው የእኛ ማድረግ ብንችል ምንም ጥቅም እንደሌለው ተመልከቱ።
መጻጉዕ ያዳነውን ትቶ አልጋውን ተሸክሞ መሄዱ ያሳዝናል። ከዚያች ቀን ጀምሮ ሰይጣን ዝም ብሎ ሊተወው አልወደደም። እስከ ዕለተ ዐርብ ድረስ ተከታትሎ ፍጹም ኃጢአት አሠርቶታል። በሕይወቱ ውስጥ ከሕማሙ ቀጥሎ ሌላ ፈተና ይዞበት የመጣው ፈውሱ ከእምነቱ በመቅደሙ ነው። ከዳነ በኋላ ከዐሥሩ ለምጻሞች እንደ አንዱ እግዚአብሔርን እያመሰገነ በቤተ መቅደስ ሊገኝ ይገባው ነበር እርሱ ግን ይህንን ሲያደርግ አልታየም። ያለ ሃይማኖት የሆነ ነገር ሁሉ ፈተናው ከባድ ነው።
ከሁሉም ነገር በፊት ሃይማኖትህን እንዲያጸናልህ ለምን። ሕይወትህን ከሚገጥምህ ፈተና ሁሉ ጠብቆ ሊያኖራት የሚችል በልብህ ውስጥ ያለው ሃይማኖትህ ነው። ሁሉንም ነገር ከተቀበልህ በኋላ ከሁሉም አስቀድሞ እግዚአብሔርን ለማመስገን ጊዜ ይኑርህ። ንብረትህን ከመሰብሰብህ በፊት ልብህን ሰብስበህ አስብ። ቀጥሎ ለምትጓዝበት መንገድ የሚረዳህ ይህ ነውና። ዳዊት ጎልያድን በማሸነፉ “አቤቱ ጉልበቴ ሆይ እወድሀለሁ” ብሎ ዘመረ እንጅ በራሱ ወይም በሌላ ሰው አልተመካም። ስለዚህም እግዚአብሔር ለሌላ ከፍ ላለ ጸጋ መረጠው። በሰዎች ላይ የጀመረውን ማሸነፍ በአጋንንት ላይ ደገመው። ሳኦልን ከሰዎች እጅ ብቻ ሳይሆን ከመናፍስትም እጅ የሚያድንበትን መንፈሳዊ ጉልበት ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበለ። ራሱ ለእግዚአብሔር መዝሙር እያዘጋጀ ስለነበረ ጎልያድን በመግደሉ ሰዎች ስለራሱ የዘመሩትን ዝማሬ አልሰማቸውም።
ወንድሜ ከእግዚአብሔር እጅ ከዚህ የሚበልጥ ሌላ ስጦታ ስለሚጠብቅህ ያዳነህን መርምረህ ሳታውቅ የተሰጠህን አልጋ ብቻ ይዘህ አትውጣ። ከግዚአብሔር ፊት ስትወጣ የሚያገኙህ ሁሉ የሚመለከቱት መዳንህን ሳይሆን የተሸከምኸውን አልጋ ነው። ስንት ዘመን ታመህ እዚህ እንደደረስህ እነሱ አይገባቸውም። ለሕጋቸው እንጅ ለሰው የሚጨነቁ አይደሉም። ስህተቱ፥ ላንተ የሚያስብ እግዚአብሔርን ትተህ እነሱ ወዳሉበት መሄድህ ነው። ሰው አድርጎ በፈጠረህ ጊዜ ለሰውነትህ የሚያስፈልጋትን ሁሉ አስማምቶ የፈጠረህ ጌታ ዛሬም አንተን ለማኖር የሚበቃ ኃይልና ፈቃድ ስላለው ሁልጊዜም ከፊቱ አትጥፋ። ሳታምን ምንም እንዲደረግልህ አትለምን። በእምነት ድል ወደማትነሣው ክብር ለመግባትም አትሞክር።
በጸና እምነት ወስጥ ካልኖርህ፦ ክብር ቢኖርህ ከንቱ ውዳሴ ይጥልሃል። ሀብት ቢኖርህ ጥጋብ ያጠፋሃል። ዝና ቢኖርህ መታበይህ ማዕበል ሆኖ ያሰጥምሃል። ውበት ቢኖርህ ለዝሙት አሳልፎ ይሰጥሃል። ጌጠኛውን ልብስ የመልበስ ዕድል ቢያጋጥምህ ለትውዝፍት ይዳርግሃል። ወንድሜ ያለ እምነት ከሆነ በምንም ነገር እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና ከሁሉም ነገር በፊት እግዚአብሔር ሃይማኖትህን እንዲያጸናልህ ለምን።
“ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንደሚሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል” ዕብ 11፥6 እንዲል!
ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆን የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው::
በሕይወት መጨረሻ፤ በዘመን ፍጻሜ ላይ የተመኙትን ማግኘት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። የሰው ልጅ መንገድ በፍለጋ የተሞላ ነው። አንዳንዱ የተመኘውን አግኝቶ ደስ ብሎት ወደ መቃብር ይወርዳል፤ አንዳንዱም ወደ ተመኘው ዓለም ሲገሰግስ ሞት ያደናቅፈውና በምኞቱ ሳለ ነፍሱን ይነጠቃል።
በጌታ የልደት ዘመን ከነበሩትና በቅዱስ ወንጌል ስማቸው ከተመዘገቡት ሰዎች መካከል ድንቅ ነገር የተመኘ ምኞቱም የተከናወነችለት ስምዖን የሚባል ሰው አለ። በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ ሰዎች ስላሉ ከእነዚያ ለመለየት ስምዖን አረጋዊ ተብሎ ይጠራል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሲመላለስ በነበረ ጊዜ ብዙ ስምዖኖች አግኝተውታል። ለምጻሙ ስምዖን ማቴ 26፥6፣ ፈሪሳዊው ስምዖን ሉቃ 7፥40፣ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን ዮሐ 1፥42፣ እና ሌሎችም ማቴ 10፥4።
እነዚህ ሁሉም ስማቸው እንጅ ግብራቸው የተለያየ ነው። እነዚህ ሁሉም አንድ የሚያመሳስል ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ እሱም ጌታን ማየታቸው ነው። ሕይወት ግዙፍ አካል ኖሯት በሰዎች መካከል ስትመላለስ ማየት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገርም አይደል? በሰማይ ላይ የሚታዩት ፀሐይ እና ጨረቃ ሥጋ ለብሰው ብታገኟቸው አትገረሙም? ሚካኤልና ገብርኤል ቤታችሁ መጥተው እንግዳ ቢሆኑላችሁስ ዜናውን ለሰው ሁሉ በደስታ አታወሩም? መልሳችሁ አዎ ከሆነ ለእነዚህ ሰዎች ከዚህ የሚበልጥ ነገር እንደተደረገላቸው አስተውሉ።
መላእክትን የሾመ፣ ፀሐይና ጨረቃን በማያረጅ ብርሃን የሸለመ እግዚአብሔር በሥጋ በመካከላቸው ሲመላለስ አዩት። ከዚህ የሚበልጥ ምን አለ?
ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በሕይወት አጋጣሚ እንዲህ ያለውን መልካም ነገር ተቀብለዋል እንጅ አስበውበት የተቀበሉት ስጦታ አይደለም። አንዳንዶቹ ግን የልባቸው ምኞት ይህች ነበረች − ክርስቶስን ማየት። ስምዖን አረጋዊ ረዥም ዓመታትን በምድር ላይ የዘገየው ክርስቶስን ጥበቃ ነው። በዘመኑ ብዙ ነገር ሲከናወን አይቷል፤ ገናናው የጽርዕ መንግሥት ዓለምን አሸንፎ ሲገዛ አይቷል። የጽርዕ መንግሥት ወድቆ የሮማ መንግሥት ሲቋቋምም ነበረ።
ከእስክንድር እስከ ቄሣር ብዙ ነገሮችን ተመልክቷል። የእሱ ፍለጋ ግን ገና አልተቋጨም። ስንቱን አየው? እስራኤል ቀድሞ ለባቢሎን ሲሰግዱ፣ በኋላም ለግሪክ ሲያጎበድዱ፣ ቀጠሉና ለሮም ሲያደገድጉ አይቷል እሱ ግን ከቆመበት የሃይማኖት መድረክ አልወረደም።
ነፍሱ የቃተተችለት ፍለጋ ገና አልተጠናቀቀም። ዘመን ሲለወጥ ሀሳቡን አልለወጠም። ንጉሥ ሲቀየር ተስፋው አልተቀየረም። ግሪክ ወድቃ ሮም ስትተካ የእሱ ተስፋ አሁንም ባለበት ነው። የእግዚአብሔርን መምጣት ተስፋ ያደርጋል። የመጡትም ሆነ ያለፉት ተሰፋውን አልፈጸሙለትምና ተስፋውን የሚፈጽምለት ይፈልጋል። የተሾሙትም ሆነ የተሻሩት ከተስፋው ፈቀቅ አላደረጉትም። አሁንም ክርስቶስን ፍለጋ። እሱ የሚያርፈው የወገኖቹን የእስራኤልን የመጽናናት ዘመን ሲመጣ ሲያይ ብቻ ነው። መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ፍለጋ ይህ ነውና።
ዛሬ ለዚያ ሰው ምኞቱ ትፈጸምለት ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ በመንፈስ ወጣ። ሊያየው የተመኘው ክርስቶስም በዚያ ቀን ወደ ቤተ መቅደስ የሚገባበት ቀን ነበረ። አገኘው፤ አየው፤ አቀፈው።
ሰምታችሁኛል ወገኖቼ? ስምዖን የእስራኤልን መድኃኒት አቀፈው እያልኋችሁ እኮ ነው። ዳንኤል ከረዥም ተራራ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ሲወርድ ያየውን ድንጋይ ስምዖን በዐይኖቹ አየው ዳን 2፥34። ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ከሐመልማል ጋር ተዋሕዶ ያየውን የእሳት ነበልባል በክንዶቹ ታቀፈው ዘፀ 3፥2። አዳም በገነት መካከል ሲመላለስ ሰምቶት የፈራውን ስምዖን ሳይፈራ ዳሰሰው ዘፍ 3፥10።
እንደ አዳም የሚናዘዝ፤ እንደ ቃኤል የሚቅበዘበዝ ሰው አልነበረምና ተስፋ ያደረገውን ክርስቶስን በዕቅፉ ይዞ ምስጋናውን ቀጠለ። ቅዱስ ወንጌል እንደ ተናገረ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲህ አለ። “ጌታ ሆይ እንደ ቃልህ ዛሬ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ዓይኖቼ በሰው ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና” ሉቃ 2፥29−32 እያለ ምስጋናውንም ልመናውንም አቀረበ። የአንዳንድ ሰው ታሪክ በአንድ ቀን ተጀምሮ በአንድ ቀን የሚፈጸም ነው።
አንዳንዱ ሰው አንድ ቀን ብቻ ኖሮ የሚሞት ነው። ይህች ቀን ለዚህ ሰው እንዲሁ ናት። ከዚህች ቀን አስቀድሞም ሆነ በኋላ በወንጌል ለመጻ’ፍ የሚያበቃ ታሪክ የለውም። ከኖረባቸው ቀናት መካከል ያለዚህች ቀን የኖረበት ቀን የለም። ሊሎቹ ቀናት ይህችን ቀን ሲፈልግ የቆየባቸው ቀናት ስለሆኑ አይቆጠሩም። ዕድሜው አንድ ቀን ናት − ግን በቂ ናት። ለዚህም ነው “ዛሬ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ” ብሎ መለመኑ።
ሽማግሌው ስምዖን ስንብት ለመነ። ከሦስት መቶ ዓመት በላይ የቆየባትን ዓለም ሊሰናበታት ለመነ። ወዳጆቼን ልሰናበት፣ ሀብቴን ንብረቴን ላስተናብር አላለም። እንደ ዮፍታሔ ልጅ ለድንግልናው፣ እንደ ዳዊትም ለሽምግልናው ዕድሜ አልለመነም መሳ 11፥37፣ መዝ 102፥24። “አሰናብተኝ” አለ።
ምን ያደርጋል ዕድሜ፣ ምን ሊያደርግ መቆየት ሰው የሕይወቱን ግብ ካደረሰ። እነዚያ ሁሉ ዘመናት ከዚህች ቀን አይበልጡም። በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ያየው ነገር ሁሉ ዛሬ ያየውን አያኽሉም። ይሄ ሰው አንድ ዘመን ላይ በገናናው ንጉሥ በበጥሊሞስ ቤተ መንግሥት በጥበባቸው ከተመረጡት ሰዎች መካከል ነበረ። ይሄ ሰው በምቹ የቤተ መንግሥት ሰገነቶች የተመላለሰባቸው ቀናት በሕይወቱ ውስጥ አልፈዋል። እንዲህ ያለ የስንብት ልመና ሲያቀርብ አልተሰማም። በንጉሥ ድንኳን ማደር፣ ከልዑላን ጋር መኖር እንደዚህች ቀን ያለ ደስታን እንደማያስገኝ ያውቀው ነበርና።
ዛሬ ግን ከዚህ የሚበልጥ ቀን እንደማይመጣ ያውቃልና አሰናብተኝ ብሎ ለመነ። ከዚህ በኋላ የሚመጣውን የሔሮድስን ቀን ሳያይ ሊሞት ተመኘ።
የገሊላ አውራጃ በደም የምትሞላበት በእናቶቻቸው ዕቅፍ ያሉ ሕጻናት አንገት የሚቀላበት ዘመን ሳይደርስ መሞት አማረው። አስጨናቂው ዘመን ሳይመጣ “ድምፅ በራማ ተሰማ ለቅሶና ብዙ ዋይታ ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች መጽናናትም አልወደደችም የሉምና” የተባለው ቃል ሳይፈጸም መሄድ ፈለገ ማቴ 2፥18። የሚመጡት ዐመታት የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት በአደባባይ ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱባቸው ዘመናት ናቸው። የጽዮን ቆነጃጅት በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ሙሾ ያወጣሉ የሚሰማቸው ግን የለም፤ ከዚህ የሙሾ ጉባኤ መካፈል አልፈለገምና ዛሬ አሰናብተኝ አለ።
በሚመጡት ቀናት በከተማ ሁከት ያስነሣውን በርባንን አስፈትተው ከሞት ማሠሪያ የፈታቸውን ኢየሱስን ስቀልልን የሚል ትውልድ ይነሣል፤ ይህን ክፉ ትውልድ ሳያይ ሊሞት ወደደ። እንዴት በአንድ ዘመን ከቤተ ክህነትም ከቤተ መንግሥትም ፍርድ ጎደለ፣ ድሀ ተበደለ የሚል ይጠፋል? ከዚህ ቀንስ አታድርሰኝ ብሎ በጌታ ፊት ማንም ያላቀረበውን ልመና አቀረበ − “ዛሬ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ”።
ክርስቶሳውያን ወገኖቼ ሆይ! ከሕይወት የሚሻል ሞት አለ። ነቢዩ ዳዊት “ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላል” መዝ 63፥3 ያለው እንዲህ ያለውን ሞት ነው። ከመኖርም የሚበልጥ አለመኖር አለ። ይልቁንም በሰማዩ መንግሥት ለሹመት የምታበቃንን ቀን ካገኘናት ከዚያ በኋላ ያለው ቀን አይጠቅመንም። ወደ እግዚአብሔር የተመለስንበት፣ ንስሐ የገባንበት፣ ንስሐ በመግባታችን በሰማይ መላእክት ዘንድ ሰለኛ ታላቅ ደስታ የተደረገበት፣ ሥጋውን ደሙን የተቀበልንበት ያ ቀን ለእኛ የአረጋዊው ስምዖነ ቀን ነው። ከኖርንበት ዓለም ለመሰናበት የመልቀቂያ ደብዳቤ ማቅረብ ያለብን በዚህ ቀን ነው። ይህን ቀን ከቀናቶቻችሁ መካከል ፈልጉት።
ለጠፉ በጎች ግን ከዛሬ ነገ ይሻላቸዋልና “ዛሬ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ” ብለው ስንብት ሊጠይቁ አይገባም። ዓይኖቻቸው ማዳኑን ማየት ያለባቸው በምድር ሳሉ እንጅ በሰማይ አይደለም። የእግዚአብሔርን ምሕረት በምድር እንጅ በሰማይ አናየውም። ይቅርታውን በምድር እንጅ በሰማይ አናገኘውም። ከካህናት እጅ ያልተቀበልናትን የእግዚአብሔር መንግሥት ከሰማይ መላእክት እጅ የምንቀበል የሚመስለው ካለ ተሳስቷል። መንግሥተ ሰማያትን በምድር ሳለ ያልተቀበላት በሰማይ አያገኛትም። በምድር ሳለ የመምህራንን ቃል የሚንቅ ሰው በሰማይ ያለ የእግዚአብሔርን ድምጽ እንደማይሰማ ጌታ በቅዱስ ወንጌል አስጠንቅቋል ሉቃ 10፥16 የወጣንያን ጸሎት “አቤቱ በእኩሌታ ዘመኔ አትውሰደኝ” መዝ 102፥24 ነው። የፍጹማን ጸሎት ግን ይህ ነው “ጌታ ሆይ እንደ ቃልህ ዛሬ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ” ሉቃ 2፥29
ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆን የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው::
ምድር ከጥፋት ውኃ መድረቅ በኋላ በኖኅ መርከብ ውስጥ ከነበሩ እንስሳትና አራዊት በቀር ሌላ አንዳች ፍጥረት አልነበረባትም። በምድር ላይ የሚርመሰመሰውን ሥጋ ለባሽ ፍጥረት ሁሉ ለጥፋት የዘነበው ውኃ ሙልጭ አድርጎ ደምስሶታል። ኖኅ ከመርከብ ሲወጣ ምድርን በዝሙታቸው ያበላሿት የቃኤል ልጆች በከተሞቻቸው አልነበሩም። ቅዱስ መጽሐፍ “በምድር ላይ ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ” ዘፍ 6፥4 ብሎ የሚጠራቸው ኔፊሊሞች አሁን የሉም። የደብር ቅዱስ ባህታውያንን በውበታቸው ያሳቱ የቃኤል ቆነጃጅትም እንደ ቀድሞው በከተሞች መካከል ሲመላለሱ አይታዩም።
እግዚአብሔር ከተቆጣ ጉልበት አያድንም፤ ውበትም ልብ አያራራም፤ ደም ግባትም አያኖርም፤ ሀብትና ዝናም መሸሸጊያ ሊሆን አይችልም። የእግዚአብሔር ትዕግሥት ምድርን ከዝሙቷ ካልመለሳት በቀር ከቁጣው የሚያስጥላት ምንም ነገር የለም።
ምድርን ሁሉ ባዳረሰው በዚያ ጥፋት መካከል ራሱንና ቤተሰቡን ማትረፍ የተፈቀደለት ኖኅ ብቻ ነበረ፤ በእግዚአብሔር ፊት ብቻውን ጻድቅ ሆኖ ተገኝቷልና። ከገነት ያስወጣችን ኃጢአት በዚህ ምድርም ከመኖር ከለከለችን። በገነት ሳለን እርግማንን አመጣችብን፤ በዚህ ምድርም ላይ የጥፋት ዝናምን አዘነመችብን። ወዮ! ከኃጢአት የተነሣ በሰው ላይ የደረሰው መከራ ብዛቱን ማን ቆጥሮ መጨረስ ይችላል?
እሳት ከሰማይ ቢዘንብብን፣ ንፍር ውኃ ቢያቃጥለን፣ ምድር ተከፍቶ ቢውጠን፣ ረሀብና ቸነፈር ቢያጠቃን፣ ድርቅ ምድራችንን እንዳታበቅል ቢያደርግብን፣ እርስ በእርሳችን መስማማት ቢያቅተን ይህ ሁሉ የሆነው በሌላ አይደለም፥ በኃጢአት ምክንያት ነው። ወደን በሠራነው ኃጢአት የማንወደው መቅሰፍት እየመታን እንኖራለን። ጣፍጦን የፈጸምነው ኃጢአት መራራ ሞትን እያስፈረደብን ወደ ሲዖል ያወርደናል። እኛ ኃጢአትን መሥራታችንን፣ ኃጢአትም እኛን ማስጠፋቷን ቀጥላለች።
ከአባታቸው ጻድቅነት የተነሣ ከሞት የተረፉት የኖኅ ልጆች ከመርከብ ከወጡ በኋላ በሌላ መንገድ ኃጢአት በራቸውን ስታንኳኳ ተመልክተናል። ለካ ያ ሁሉ ምድርን ለመቶ ሃምሳ ቀናት የሸፈናት ውኃ ኃጥአንን እንጅ ኃጢአትን ከምድር ላይ አላጠባትም ኖሯልና ኃጢአት አሁንም በሰዎች ልብ ውስጥ ሥር መስደድ ጀመረች። ሰይጣን አዲስ አዲስ የኃጢአት አሠራሮችን ማምጣት ልማዱ ነው። ከመርከብ የወጣው ትውልድ እንዳያመልጠው የቀደመውን ኃጢአት ይዞ አልቀረበም፤ አዲስ የኃጢአት አሠራር ይዞ ብቅ አለ እንጅ። እስካሁን የአባቱን ዕርቃን አይቶ በገዛ አባቱ የሚሳለቅ ትውልድ አልነበረም ዛሬ ግን ከሦስቱ የኖኅ ልጆች መካከል አንዱ የሆነው ካም የአባቱን ዕርቃን አይቶ ተሳለቀ፤ ብቻውንም አይቶ ሊቀር ስላልፈለገ ለወንድሞቹ ሁሉ የአባታቸውን ሀፍረት እንዲያዩ ቅስቀሳ አደረገ። “የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው” ዘፍ 9፥22 እንዲል።
ሰይጣን ዘመናዊ ነው፤ አሠራሩም ለትውልድ እንዲስማማ አድርጎ ማቅረብም ልዩ ችሎታው ነው። የአንድ ዘመን ትውልድ የተቀጣበትን ኃጢአት ለሌላ ትውልድ በማቅረብ ተከታይ ማጣት አይፈልግም። ስለዚህ ምን ያደርጋል መሰላችሁ፥ የፅንሰ ሀሳብ ልዩነት ባይኖረውም የንድፈ ሀሳብ ልዩነት አድርጎበት በሌላ መንገድ ያቀርበዋል። ያን ጊዜ ተከታዮችን ማግኘት ይችላል ማለት ነው። በዓለም ላይ ታላላቅ ጥፋቶችን ያስከተሉ ታላላቅ ኃጢአቶች ከአዳም ኃጢአት {አምላክነትን መሻት} ጀምሮ እስከ ሞተ ወልደ እግዚአብሔር ድረስ ሰባት ናቸው። እነዚህን ለአዲሱ ትውልድ በሌላ መንገድ ያቀርባቸዋል እንጅ ሌላ አዲስ ኃጢአት አያቀርብም።
ዮሐንስ በራእዩ የተመለከታቸው ሰባቱ የአውሬው ራሶች የተባሉትም እነዚሁ እንደሆኑ የሐዲስ ኪዳን መምህራን ያስተምራሉ ራዕ 13፥1 ከመርከብ በወጣው ትውልድ መካከል የገባችው ይህች የዛሬዋ በደል ኖኅ ወደ መርከቡ ከመግባቱ በፊት የነበረው ትውልድ የማያውቃት ሌላ በደል ናት − እሷም የአባትን ዕራቁትነት ማየት ናት። አዳም ዕራቁቱን በነበረ ጊዜ በገነት ዕፀዋት መካከል መሸሸጉ ዕራቁትነት አሳፋሪ ነገር በመሆኑ ነው። እግዚአብሔርም ዕርቃኑን ያሳይበት ዘንድ የገነትን ዕፀዋት በቅጠላቸው እንዳይሠውሩት አላደረጋቸውም። ዕርቃንን መግለጥ የማይገባ ስለሆነ ነው።
ሴምና ያፌት እንደ እግዚአብሔር ሆነዋል፤ የኖኅን ዕርቃን አላዩምና። ይህንን ነገር በሰሙ ጊዜ በማስተዋል ያደረጉትን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገርላቸዋል። “ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ የኋሊትም ሂደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም” ዘፍ 9፥23 ተባለላቸው።
አስተዋይ ትውልድ እርቃንን በማየት አይደሰትም። እርግማን ከምድራችን ላይ እንዲወገድ የሚያደርግ እንዲህ ያለ ትውልድ ያስፈልገናል! ወደ ኋላ ሂዶ የታሪክ ዕርቃንን የሚሸፍን። እንዲህ ያለ ዘመን እንዲመጣልን እንጸልያለን፤ የአባቱን ሀፍረት ላለማየት በትክሻው ላይ ልብስ የሚያኖር ትውልድ እንዲሰጠን። ሴምና ያፌት በዚህ ዘመን ሊኖሩን ያስፈልገናል።
የሆነ ዘመን ላይ ከጭንቅ ያወጡን፣ ክፉውን ዘመን ያሻገሩን ሰዎች ጥቂት ኅፀፅ ስናገኝባቸው በሰዎች ፊት መሳቂያና መሳለቂያ የምናደርጋቸው ከሆነ ሰውነታቸውን ረስተናል ማለት ነው። ያኔ የታላቁ ቀላይ ምንጮች ተነድለው የሰማይም መስኮቶች ተከፍተው ከላይና ከታች የጥፋት ዝናም በዘነመ ጊዜ በጥበባቸው የምንሳፈርበትን መርከብ የሠሩልንን ሰዎች መሆናቸውን መዘንጋት አይገባንም።
ወደ ኋላ ተመልሶ በአባቶቹ የሚሳለቅ ትውልድ መፍጠር ምን ያደርጋል። ምንም ይሁን ምን ከጥፋት ውኃ ያተረፈን አባቶቻችን የሠሩት ሥራ ነው። ያንን ሞት ያለፍነው አባቶቻችን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ስለነበራቸው ነው። ወደ ኋላ ከተመለስንም የምንሻገርበት መርከብ፤ የምንጠጋበት ወደብ የሠሩልን መሆናቸውን ማሰብ ይገባናል እንጅ ዕርቃናቸውን እያነሣን ብናሳይ ከመረገም በቀር ምንም ጥቅም የለውም።
ከእኛ በፊት የነበሩ አባቶቻችን የሠሩትን ታሪክ ቀድሞ ያጠና ካለ ለሚሰሙት ሁሉ መናገር ያለበት ኖኅ ደክሞ መተኛቱን እንጅ ዕርቃኑን መሆኑን አይደለም። ይህ ዛሬ ዕርቃኑን ያየነው ኖኅ ነው ዛሬ በሕይወት እንድንኖር ያደረገን። በቤተ መንግሥት፣ በቤተ ክህነት፣ በማኅበራት፣ በግለ ሰቦች፣ በመኳንንት፣ በካህናት የደረሱ ጥፋቶች የተነገሩ የማይገቡ ቃላት ሊኖሩ ይችላሉ። ዛሬ ላለው ትውልድ በየቀኑ ብናዘክረው እግዚአብሔር በመርከብ ጭኖ ከሞት ቢያሻግረው ሌላ ሞት እንዲገጥመው ማድረግ ካልሆነ ሌላ ጥቅም የለውም። ይህንን ቀን እንድናይ መጽሐፍ ጽፈው፣ ጉባኤ ዘርግተው፣ አገር ለአገር ዞረው አስተምረው ክፉውን አመል በመልካም አመል እንድንለውጥ አድርገው የደከሙልን ብዙ አባቶች አሉ።
የፖለቲካ፣ የጎሣ፣ የሃይማኖት መሪ የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባት የማይጠቅም ታሪክ ሠርተው እንኳን ብናገኛቸው ለሚመጣው ትውልድ የማይነበብ የሚል ከላዩ ላይ ጽፈንበት እንጅ እንዲሁ ማስተላለፍ አይገባም። ሴምን ያፌትን መሆን ይገባናል። “የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፤ እግዚአብሔር ያፌትን ያስፋ በሴምም ድንኳን ይደር ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን” ዘፍ 9፥26 ብሎ የሚመርቀን አባት የምናገኘው ሴምና ያፌትን በመሰለ ሥራ ብንገኝ ነው። የሌሎችን ኃጢአት በትዕግሥት የራሳችንን ኃጢአት በንስሐ ማለፍ ከቻልን ከጻድቁ ኖኅ አፍ የወጣው የሴምና የያፌት በረከት ዛሬም በኛ ላይ ነው። ከእኛ መካከል የሌላውን ነውር የሚሠውር ሴምና ያፌትን የሚመስል ማነው?