የዓለም መድኅን የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደቡባዊ የይሁዳ ክፍል ልዩ ስሟ ቤተ ልሔም በተባለችው ስፍራ፣ ሄሮድስ በነገሠበት ዘመን ተወለደ፡፡ ሰብአ ሰገል ለተወለደው ሕፃን ለንጉሥ የሚገባውን እጅ መንሻ ሊያቀርቡለት መጡ፡፡ ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፡፡ በኢየሩሳሌም ከእርሱ ጋር የካህናትንም አለቆች የአሕዛብንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንደሚወለድ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “አንቺ ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ በይሁዳ ከነገሡ ነገሥታት ከቶ አታንሽም ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢዩ ሚክያስ ነግሧልና ቤተ ልሔም” ነው አሉት (ሚክ. 5፥2)፡፡
ሄሮድስ የካህናት አለቆች የሕዝብ ጻፎች የነገሩትን ከያዘ በኋላ ሰብአ ሰገልን (የጥበብ ሰዎች) በስውር ጠርቶ ኮከብ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፡፡ ወደ ቤተ ልሔም እነርሱን ልኮ፤ ሒዱ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው፡፡ ሊሰግድለት ፈልጎ አይደለም ሊገድለው ወዶ ነው እንጂ፡፡
ሰብአ ሰገልም ንጉሡ ሄሮድስን ሰምተው ሔዱ፡፡ እነሆም በምሥራቅ ያዩት ኮከብ (መልአኩ) ሕፃኑ ባለበት ቦታ ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር፡፡ ኮከቡን መልአኩን ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው፡፡ የሁለት ዓመት ጎዳና መርቶ ኢየሩሳሌም ሲገቡ ከሄሮድስ ጋር ሲገናኙ ተሰውሯቸው ነበርና አሁን ሲታያቸው ደስ ተሰኙ፡፡
ከዚያም ወደ ቤተ ልሔም የከብቶች በረት ግርግም ውስጥ ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፣ ወድቀውም ሰገዱለት ሳጥናቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ አቀረቡለት፡፡ ሰብአ ሰገል የጥበብ ሰዎች የሁለት ዓመት መንገድ ተጉዘው እጅ መንሻን አቅርበው የተወለደውን ሕፃን ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክነቱን ከተረዱ በኋላ ወደ ንጉሡ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ከመልአኩ ተረድተው “ወነገሮሙ በሕልም ከመ ኢይግብኡ ኀበ ሄሮድስ ” እንዲል ” በሄሮድስ በኩል እንዳይመለሱ በራእይ ተነገሯቸው በሌላ መንገድ በሌላ ጎዳና ወደ ሀገራቸው” ተመልሰዋል፡፡ማቴ.2፥12
ሰብአ ሰገል ሁለት ዓመት ፈጅቶባቸው ወደ ቤተልሔም የመጡትን መንገድ ሲመለሱ ግን ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አግኝተው ለእርሱ ሰግደው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ (ሲሔዱ) በሌላ መንገድ ኃይል ተሰጥቷቸው ፵ ቀን ብቻ ነው የፈጀባቸው፡፡ የይሁዳ ንጉሥ እያሉ መጥተው አምላክ እያሉ ተመልሰዋል ሲል (በማቴ. 2፥1-12 ትርጓሜ ወንጌል) ይገልጥልናል፡፡
በመጡበት መንገድ አለመመለሳቸውን እና በሌላ መንገድ (ፍና ካልዕ) መሔዳቸውን ወደ ሄሮድስ አለመመለሳቸውን “And being warned of God in a dream that they should not return to Herod, they departed into their own country another way.” Matthew 2፥12 (KJV) (Fr.Tadros Y.Malaty) የግብፅ ቤተ ክርስቲያን አባት ታድሮስ ያዕቆብ ማላቲ የማቴዎስ ወንጌልን በተረጎሙበት መጽሐፍ የቀደምት ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ትርጓሜ በመጥቀስ ስለ ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) የሚከተለውን ብለዋል።
ሰብአ ሰገል ለአማኞች ለኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ለበዓል አከባበርና ለሥርዓተ አምልኮ አርአያ ምሳሌ ናቸው፡፡ በቤተ ልሔም በኤፍራታ የተወለደውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ማክበር ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት ነውና እርሱን ካገኙ በኋላ በሄሮድስ በጊዜያዊ ገዥ በሰይጣን መንገድ መመለስ ፤ በዓላትን ክርስቲያናዊ ባልሆነ መንገድ ማክበር እንደማይገባን አስተምረዋል።
ቅዱስ አንብሮስ ዘሚላን እና ታላቁ ጎርጎርዮስም በአዲሱ መንገድ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሊጓዙ፣ ሊመላለሱ፣ በዓላትን ሊያከብሩ እና ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚወስደውን መንገድ ሊይዙ እንደሚገባ ገልጸዋል። በሄሮድስ መንገድ መመለስ፣ በዓላትን በኦርቶዶክሳዊ መንገድ አለማክበር (እንደ ክርስቲያን አለማክበር) በቤተልሔም የተወለደውን፣ በቀራንዮ የተሰቀለውን አዳኙን መሲሑን ኢየሱስ ክርስቶስን ዳግመኛ መስቀል እና ለቤዛ ቀን የታተምንበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ማሳዘን ነው(ዕብ.10፥28-30፣ኤፌ.4፥30)
በዓለ ልደቱን ስናከብር እግዚአብሔርን እና ሰዎችን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ሊሆን ይገባል እንጂ ፤ ድሆችን ፣ ጠያቂ የሌላቸውን በየአብያተ ክርስቲያናት ደጅ የሚጠኑትን በመዘንጋት መሆን አይገባም ፡፡ በዓለ ልደት አካላዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ሆኖ የተወለደበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡ ይህም የሰውን ዘር ለማዳን የተደረገ ደገኛ በዓላችን ነው።
የጌታችንን የልደት በዓል በማክበር የሚገኘውን ጥቅም “እመቦ ዘአክበረ ልደተ እግዚእ ይከውን ክብሩ ምስለ ሰብአ ሰገል፤ የጌታችን በዓለ ልደት የሚያከብር ሰው ቢኖር ክብሩ (በተወለደ ጊዜ ተገኝተው መብአ ሰጥተው እንዳከበሩት) እንደ ሰብአ ሰገል ይሆንለታል” እንዳለ ትርጓሜ ወንጌል ከበዓለ ልደቱ ጥቅም በረከት ለማግኘት የሚጠበቅብን ባልተገባ መንገድ ባለመመላለስ እና በዓሉን በሚገባ ማክበር ነው፡፡
ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከተገናኙ፣ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከተወለዱ፣ ወደ ቤቴል ቤተ እግዚአብሔር ከመጡ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ የቀደመውን ያልተገባ አኗኗር መከተል ውጤቱ ሞት የሆነ ከእግዚአብሔር መለየት ነው የሚሆነው። በቤተልሔም የተወለደውን ሕጻን ከአገኘን በኋላ ከኃይል ወደ ኃይል ለመሸጋገር የኋላውን እየተውን የፊቱን ለመያዝ ይበልጥ መትጋት ወደፊት መራመድ ይጠበቅብናል (ፊል.3፥13፣ ሉቃ. 21፥31፣ ሮሜ.8፥6)፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በጻፋቸው ቀዳማዊና ካልአይ መልእክቱ በሃይማኖት ለወለዳቸው በምግባር ላሳደጋቸው ክርስቲያኖች ቀድሞ በሥጋ ፈቃድ እንደ አሕዛብ በሥጋ ምኞት ይኖሩ የነበረበትን የቀደመውን የሥጋ ምኞት ተከትለው በሚያመጣው ወጥመድ እንዳይወድቁ ከክፉ ምኞት እንዲርቁ፣ ከኃጢአት እንዲጠበቁ በምኞት እንዳይወድቁ፣ በመጡበት መንገድ እንዳይመለሱ ከክፉ ምኞት ባርነት እንዲላቀቁ “አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ” በማለት ጽፎላቸዋል (1ኛ ጴጥ. 1፥14)፡፡
ከዚያ በማስቀጠልም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ብርቱዎችና ትጉሃን ምእመናንን አይቶ ደግሞ የጀመሩትን በጎ ትጋትና በጎ ቅንነት ሳይነቅፍ በቀጣይ ኑሮአቸው የያዝነው ይበቃናል ሳይሉ የበለጠ እንዲተጉ፣ እንዲበረቱ፣ እንዲያስቡ ወንድሞቹን ሲያጸና “ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ” በማለት ጽፏላቸዋል። (2ኛ ጴጥ. 1፥10)፡፡
ነብዩ ሆሴዕ የአምላካችን የእግዚአብሔር በዓላትን ማክበር በተመለከተ “በእግዚአብሔር በዓላት ቀን ምን ታደርጋላችሁ? (ሆሴ.9፥5) ብሎ ሕዝበ እስራኤልን እንደጠየቀው፤ እኛም እስራኤል ዘነፍስ የተባልን በሐዲስ ኪዳን ያለን ኦርቶዶክሳውያን በዓላትን ስናከብር እንዴት እንደምናከብር ይጠይቀናል!?፤ የሥርዓት መጽሐፍችን ፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ ገጽ 259 እና 263 ስለ በዓላት አከባበርን በተመለከተ መንፈሳዊ ተድላ ደስታ ልናደርግ እንደሚገባን ሲገልጽ “ረብህ ጥቅም የሌለውን ነገር ልትናገሩ፣ የማይገባ ሥራ ልትሠሩ አይገባም፣ ይልቁንም መንፈሳዊ ተድላ ደስታን ልታደርጉበት ይገባል ‘እንጂ’… ልደት እና ትንሣኤ ከጾም በኋላ ስለሆኑ የተቻለው (ከቅ
ዳሴ መልስ) ያልተቻለው ደግሞ በነግህ (ሲነጋ) ጾምን በመብልና በመጠጥ ማሰናበት አለበት በዚህም ፈጽሞ ደስ ይበላቸው” ይላል፡፡
ምንም እንኳን መብል መጠጥ የሚያፋቅር ደስ የሚያሰኝ መሆኑ ቢታወቅም ፤ ክርስቲያኖች በሚያከብሯቸው በዓላት ላይ ከመብልና ከመጠጥ ይልቅ በዋናነት በጸሎት፣ በማኅሌት፣ በምሥጢራት፣ በትምህርት፣ በተዘክሮና በመሳሰሉት መንፈሳዊ ተግባራትን በማከናወን ማክበር ይገባል፡፡ መንፈሳዊ በዓላት – መንፈሳዊ ሐሴት የሚገኝባቸው ናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት “በቃለ አሚን ወበትፍሥሕት ደምፁ እለ ይገብሩ በዓለ፣ በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና የምስጋና ቃል አሰሙ” (መዝ.42፥4) ያለው መንፈሳዊ በዓልን በመንፈሳዊ ደስታና በምስጋና ማክበር እንደሚገባ ጽፎልናል።
የእግዚአብሔር በዓላት በፍጹም ደስታ ሊከበሩ ይገባቸዋል፡፡ ደስታውም የሥጋ መሻትንና የዓይን አእምሮትን በማሟላት ሥጋዊ ደስታን በመደሰት ብቻ ሳይሆን፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ባልተለየው መንፈሳዊ ሐሤት ከማኅበረ ምእመናን ጋር በፍጹም መንፈሳዊ ደስታ ማክበር ይጠበቃል፡፡ሠለስቱ ምእትም “የጌታችን በዓላት እናከብር ዘንድ፣ ተአምራቱንም እንገልጥ ዘንድ እንዲሁም ምስጋናውንም እንናገር ዘንድ” አዝዘዋል (ፍት.ነገ. ትርጓሜ. ገጽ.260)፡፡
በ፲፭ ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ርቱዐ ሃይማኖት ስለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዜና ልደቱን ለመጻፍ ሲጀምር “አቤቱ የፈቀድህላቸው ይሰሙ ዘንድ ስለ መወለድህ እንድናገር የድርሰትን መንገድ አቅናልኝ” ብሎ ጸሎትን ልመናን ካስቀደመ በኋላ የበዓሉን ታላቅነት እና እንዴት ማክበር እንደሚገባን በግሩም ጽሑፉ
“ቤተልሔም ዛሬ ሰማይን መሰለች፣ አህያና ላም፣ ዮሴፍና ሰሎሞን የአርባዕቱ እንስሳ ምሳሌ ናቸው፡፡ በረት ክርስቶስ አምላክ በውስጧ ስለተገኘባት በኪሩቤል ሰረገላ ትመስላለች፡፡ ድንግል ልጇን በቀኟ የያዘች የአብ ምሳሌ ናት። ጌታ የተወለደበትን ዕለት በምድር ይህ ሁሉ የተደረገባት ይህች ዕለትም የተከበረች ናት ደስ እንሰኝባት” እያለ የጌታችንን ተአምራቱን ይገልጣል፡፡
ክርስቶስ የተወለደባት ይህቺን ዕለት እንዴት ማክበር እንደሚገባን ርቱዐ ሃይማኖት ሲገልጥ፡- “በምንም መንገድ ኀዘን ከእኛ ሊኖር አይገባም፡፡ በክርስቶስ በዓላት ማልቀስ ኃጢአት እንደሆነ፣ ክርስቲያንም ሆኖ በሕማማት የሚደሰትም ታላቅ በደል ይሆንበታል፡፡ መልካምን በማድረግ ይደሰት፣ በሕማማት የሚያለቅስም ያልቅስ፡፡ በዚህች ዕለት (ጌታችን በተወለደባት ዕለት፣ እግዚአብሔር በሥጋ የተወለደባት ዕለት ናትና በዘመዶቹ ሞት፣ በበሽታ፣ በሀብቱ መጥፋት የሚያዝን የሚያለቅስ ሰው በሰማያት ደስታ የለውም፡፡ በወንድሙ ቂም በቀል የያዘ የተጣላ በዚህችም ዕለት ይቅር ያላለ ይህ ዐሥራ አራት እልፍ ከአራት ሺሕ ሕፃናት የገደለ የሄሮድስ ወንድም ነው” ይላል፡፡
ምክንያቱን አክሎ ሲገልጥም “ሄሮድስ የመሲሕ ክርስቶስን ልደት በሰማ ጊዜ ሕፃናቱን ይገድል ዘንድ አዘዘ፡፡ ዐሥራ አራት ዕልፍ ከአራት ሺሕ ሕፃናትን ገደለ፣ ዘካርያስንም ስለ ልጁ ስለ ዮሐንስ ገደለው፡፡ በዚህም የተረገመ ሄሮድስ ተደሰተ፡፡ መድኃኒታችንን ያገኘው መስሎት ነበርና፡፡ ሰነፍ ሄሮድስ ሆይ ነፋስን ትይዘው ዘንድ ቀንንም ታስቀርበው ዘንድ ይቻላልን!?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ስለዚህም ያለፈውን በይቅርታ በመተው፤ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊና ሀገራዊ ኑሮአችን ማስተካከል እንደሚገባን ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል።
ኦርቶዶክሳውያን በዓላትን ስናከብር ይልቁንም የጌታችን ልደት እንደ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን በመሰብሰብ፣ ምሕረትን ይቅርታን በማድረግ እና በመጣንበት በዚያ በኃጢአት መንገድ ባለመመለስ፤ ከገቢረ ኃጢአት በመራቅ ገቢረ ጽድቅ መልካም ሥራ በመሥራት ልናከብረው ይገባናል፤ ስለዚህም “ወደ ቤቴል- ቤተልሔም (ቤተክርስቲያን) በመጣንበት መንገድ አንመለስ” 1ነገ. 13፥1፤ በዚያ በኃጢአት መንገድ ዳግማኛ አንመለስ ዘዳ.፲፯፥፲፮ ፤ ይልቁንም በቤተልሔም የተወለደውን በቀራንዮ የተሰቀለውን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር ስጋውን ቅዱስ ደሙን እንቀበል እና ” ስብሐት ለእግዚአብሔር በስማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ -ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ።” ሉቃ.2፥14 በማለት በዝማሬ በምስጋና ሕይወት እንኑር! ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣የሰብአ ሰገል የመንፈሳዊ ጉዟቸው በረከት አይለየን!
በግእዙ ምሥጢር የምንለው በግሪክ ሚስትሪ Mystery ሲባል፤ በላቲን ደግሞ Sacrament የሚባለው በነጠላ መጠሪያው ነው።
ምሥጢራት፣ Mysteries (Sacraments) ስንል ደግሞ በብዙ የምንጠራበት ነው። የግሪኩ ሚስቲሪዮን ከላቲኑ ሳክራመንት ጋር አቻ ቃል ነው::
ምሥጢር ማለት ድብቅ፣ሽሽግ፣ለልብ ወዳጅ ለቅርብ ዘመድ ካልሆነ በስተቀር የማይገለጥ ማለት ነው። ምሥጢር ላመኑ እንጂ ላላመኑ የማይሠጥ፣ በዓይን የሚታየው በእጅ የሚዳሰሰው ነገር በመንፈስ ቅዱስ ሲለወጥ አይታይም፣ ምእመናን በሚታየው አገልግሎት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሲቀበሉ አይታይምና ምሥጢር ነው።
ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን የሚፈጸሙት በግብር አምላካዊ በመንፈስ ቅዱስ የሚፈጸም ስለሆነ ምሥጢር ተብሏል። “ይህቺ ቀን ምን ያህል የምታስፈራ ናት? መንፈስ ቅዱስ ከሰማየ ሰማያት የሚወርድባት…መሰዋዕቱን የሚሰውርባትና የሚያከብርባት።” እንዲል መጽሐፈ ቅዳሴ።
በግእዙ ምሥጢረ ምሥጢራት፣በአማርኛው የምሥጢራት ምሥጢር፣ በላቲኑ Sacrament of Sacraments በግሪኩ ደግሞ Mystery of Mysteries በማለት የምንጠራው ቃል በሁለት መልኩ ይተረጎማል።
ምሥጢረ ምሥጢራት የሚለው ቃል የመጀመሪያው ለምሥጢረ ሥላሴ ሰጥተን የምንተረጉመው ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ ለምሥጢረ ቁርባን ለአምላካችን ለክርስቶስ ሰጥተን የምናብራራው ነው። የመጀመሪያውን እንመልከት፦
ምሥጢረ ሥላሴ
___
ምሥጢረ ምሥጢራት ማለት የምሥጢራት ሁሉ የበላይ መጀመሪያ ምሥጢር ማለት ነው። ሰማይ፣ ምድር፣ መላእክት፣ ደቂቀ አዳም ከመፈጠራቸው የሚቀድም የማይቀደም( ‘ቀ’ አጥብቅ) ቀዳማዊ ምሥጢር ፤ ምሥጢረ ሥላሴ ነው።
ከምሥጢረ ሥላሴ ከሌሎችም ምሥጢራት በቅድምና መታወቅ ያለበት ሦስትነት አንድነት ነውና ምሥጢረ ምሥጢራት የምሥጢራት ሁሉ የበላይ ምሥጢር ምሥጢረ ሥላሴ ነው።
“መቅድመ ኲሉ ንሰብክ ሥላሴ ዕሩየ ወቅዱስ ዘውእቶሙ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ – ከሁሉ አስቀድሞ በአካል ልዩ በክብር አንድ የሚሆን ሦስትነትን እናስተምራለን። እኒህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው” እንዲል ሊቁ ( ሃይ.አበው ፷ ፥፪ ) ምሥጢረ ሥላሴን ከምሥጢራት ሁሉ ቀድሞ መጀመሪያ መማር ይገባል።
“በእንተ ምሥጢር ዘትትወሀብ ለመንፈሳውያን ሊቃውንት ወትትነገር ለምእመናን በስመ ቅድስት ሥላሴ ዘትዜኑ ምሥጢረ ምሥጢራት ዛቲ ይእቲ”
ትርጉም- ለመንፈሳውያን ሊቃውንት ስለምትገለጽና በቅድስት ሥላሴ ስም አምነው ለሚኖሩ ምእመናን ስለምትናገር ምሥጢረ የምትናገር ከምሥጢራት ሁሉ የምትቀድም ምሥጢር ይህቺ ናት ይህቺውም ምሥጢር፤ ምሥጢረ ምሥጢራት ምሥጢረ ሥላሴ ናት።” እንዲሉ የ”ምሥጢረ ምሥጢራት – ፩ ” መጽሐፍ ጸሐፍያን መ/ር ገብረ መድኅን እንየው እና መ/ር መዝገበ ቃል ገ/ሕይወት ምሥጢረ ምሥጢራት ምሥጢረ ሥላሴ ነው።
የሰው ልጅ በቅድሚያ ለሃይማኖት ያህል ሁሉን ሚያሳውቀውን ሁሉን የሚያውቅ ፈጣሪን ማወቅ ይገባል። የትምህርት፣ የሃይማኖት ፣የምግባር ፣ የትሩፋት መጀመሪያ ሁሉ ስመ ሥላሴ ምሥጢረ ሥላሴን- ምሥጢረ ምሥጢራትን መማር ነው።
ምሥጢረ ቁርባን
___
የግሪኩ ሚስቲርዮን ከላቲኑ ሳክራመንት ጋር ትይዩ ሲሆን በኦርቶዶክስ ነገረ መለኮት የመለኮታዊ ጸጋ መገለጥ ላለው ለማንኛውም ሥርዓት የሚገባ ቃል ነው:: (Maria Gwyn McDowell, Concise Encyclopedia of Orthodox Christianity , Anthony McGukin, 2014, 329)
ከክርስቶስ ጋር ያለን ኅብረት ዕውን የሚኾነው በምሥጢራት ተሳትፎ ያለበትን ሁኔታ መሠረት አድርጎ ነው። በጥምቀት ያገኘነው ልጅነት፣ በምሥጢረ ቁርባን የምናሳካው ኅብረት (ዮሐ.15፥4-7)፣ እና ሌሎችም በምሥጢራቱ አማናዊነት ላይ ባለን ጽኑ እምነት መነሻ ኦርቶዶክሳዊ ማንነታችን የሚሠራባቸው ናቸው።
ምሥጢረ ምሥጢራት ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ሁላችንንም ግባችን ወደኾነው ሱታፌ አምላክ (የመለኮታዊ ባሕርይ) ተካፋይነት(2ጴጥ 1፥4) የሚያደርሰን የሕይወት ስንቅ ነው። [Geo Pallikunnel, Elevation to the divine state Through Holy Qurbana, 2016,232]
የቤተ ክርስቲያን አንድነት በምሥጢረ ቁርባን ላይ የተመሠረተ ሲሆን ቅዱስ አግናጥዮስም ” ቤተክርስቲያን ምሥጢረ ቁርባን ሲፈጸም ምልዓትዋ ላይ የምትደርስ ቁርባናዊ ማኅበር ናት” እያለ በዚያ ቀዳሚዊ ዘመን (ኹለተኛው ምዕት ዓመት መጀመሪያ)አስተምሯል።
በምሥጢራት አማካኝነት ብዙ ስንኾን አንድ እንደኾንን ይነግረናል፣ በዚህም የሰው ዘር ኹሉ የሚተባበርበት የሰላም መሠረት ነው። ” አንድ ስለምታደርግ ሥጋውና ደሙ እግዚአብሔር አንድ ያደርገን ዘንድ “በማለት በቅዳሴ ሰዓት በዲያቆኑ የሚነበበው የሚጸለየው በእንተ ቅድሳት የተባለው ክፍል የሚያስረዳን አንድ የሚያደርገን ምሥጢረ ቁርባን መሆኑን ነው። (በእንተ ቅድሳት፣ መጽሐፈ ቅዳሴ፣ 1984፣22)
በምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በምሥጢረ ቁርባን ብዙዎች ስንሆን አንድ መሆናችንን፦”እንዘ ብዙኃን ንህነ እም ጾታ ዘመን ዘዚአሁ:: ነአምን ሞቶ ወንሴፎ ትንሣኤሁ:: ለእግዚእ ክርስቶስ ለእመ ተኀትመ ጸጋሁ:: መለያልየ አሐደ ይረስየነ ምስሌሁ:: በአጽናፈ ዓለም ይጠባህ አሐዱ ሥጋሁ፤ እንዲሁ ብዙዎች ስንኾን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፣ እርስ በእርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን” (ሮሜ 12፥5) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በተግባር የተረጎመና የሰው ልጅን ኦርቶዶክሳዊ ማንነት በምሥጢራዊ መንገድ የሚያውጅ በምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በኩል የሚፈጸም መሆኑን እንረዳለን ነው።
ከሰማያት የወረደው ኅብስት በአካለ ሥጋ ምድራውያን ለሰማያዊ ዋጋ እንዲበቁለት በመስቀል ላይ ተቆርሶና ተቀድቶ የተሰጠው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው “ሰማያዊውያን መና ምድራውያን በሉ፥ በኃጢአት ትቢያ ከነበሩት በመንፈሳዊው ኅብስት ተወስደው በረሩ፣ በገነትም አበሩ። በዚህ ኅብስት እያንዳንዱ ሰው እንደ ንሥር እስከ ገነት የሚበር ይኾናል። የልጁን ሕይወታዊ ኅብስት የበላ ኹሉ በደመናት ውስጥ ወደ እርሱ ይበራል” እያለ ለመንፈሳዊው ዕድገትና ጥንካሬ ሥጋ ወደሙ ያለውን ከፍተኛ ሚና እንደሚከተለው በዝማሬው ያስተምራል።
“ምድራውያን ሰማያዊውን መና ተመገቡ::
በኃጢአታቸው ምክንያት ትቢያ ሆነው ነበር:: መንፈሳዊው እንጀራ ግን ወደ ገነት አሳርጎ ብሩሃን አደረጋቸው:: የወልድን ሕያው ሥጋ የሚበላ ሰው በደመናት መካከል እየበረረ እንደ ንስር ወደ ሰማይ ይወጣል” [Hymns on the unleaved bread, 17.8-9,12-13.Geo Pallikunnel,Elevation to the divine state through Qurbana,2016,79-80]
የክርስቶስ ሥጋና ደም በረጅሙ መንፈሳዊው ጉዞአችን የሚያስፈልገን ስንቃችን ነው። በዚህ ምክንያት በምግበ ነፍስ፣ ምግበ ሕይወት ደረጃ ዘላለማዊ ሕይወት የሚገኝበት ምሥጢር ኾኖ ነው የቀረበልን።[John D.Zizioulas, The Eucharistic Communion and The World,2011,24 ] የነገረ መለኮት ትምህርት መግቢያ መጽሐፍ ፣መ/ር ግርማ ባቱ ገጽ 239)
በምሥጢረ ቁርባን ውስጥ የምናገኘው ከክርስቶስ ጋር ያለ ሕይወት የሐሳብና የስሜት ደረጃዎችን ያለፈ ኅብረት ነው።ብዙዎች ስንሆን አንድ የሚያደርገን ምሥጢረ ምሥጢራት ነው።
___
ምስጢረ ቁርባን ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት (ምስጢረ ሥላሴ፣ምስጢረ ስጋዌ፣ ምስጢረ ጥምቀት፣ምስጢረ ቁርባን እና ትንሣኤ ሙታን) አንዱ ሲሆን፤ ምሥጢረ ንስሐ ደግሞ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን (ጥምቀት፣ ሜሮን፤ ቁርባን፣ክህነት፣ ተክሊል እና ቀንዲል) አንዱ ሆኖ ከ 7 ዓመት በኋላ ላሉ ኦርቶዶክሳውያን ወደ ምሥጢረ ቁርባን ለመድረስ ቅድመ ሁኔታው ራስን ለካህን ማሳያው እና ማስፈቀጃው መንገድ ነው።
ምሥጢረ ቁርባን የአንዲት ቤተክርስቲያን ቅድሳት ነው። ሃይማኖታቸው የቀናና እውነተኛ የሃይማኖትን መንገድ ያቀኑ ቀደምት አበው አምስቱ አዕማደ ምሥጢርን በያዘ በዘወትር የጸሎተ ሃይማኖት ክፍላችን ላይ፦ “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት ፤ ትርጉም- ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን።” በማለት ሠልስቱ ምዕት-318 የሃይማኖትን ድንጋጌ አስቀምጠዋል። ያስቀመጡበትም ምክንያትም በአንዲት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ምስጢረ ምስጢራት (የምሥጢራት ሁሉ ማጽኛ ማኅተም) የሆነው ምስጢረ ቁርባን የሚግለጥ ነው።
ሁሉን አንድ የሚያደረግ ቅድስት የእግዚአብሔር ልጅ የክርስቶስ ሥጋና ደም ሥልጣነ ክህነት ባላቸው በካህናት እና በምእመናን የኅብረት ጸሎት አማከኝነት በመንፈስ ቅዱስ አሠራር አማናዊ የክርስቶስ ሥጋና ደም በአንዲት ቤተክርስቲያን ይፈጸማል ፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴያችንም በበእንተ ቅድሳት ጸሎት ላይ “አንድ ስለምታደርግ ሥጋው እና ደሙ ” እና ” ቅድሳት ለቅዱሳን” በማለት ምሥጢረ ቁርባንን ቅድሳት ልዩ ምሥጢር እንደሆነ ገልጧል።
ምሥጢረ ቁርባን የምሥጢራት የአገልግሎት ሁሉ መክብብ ነው። ይኸውም ምስጢር የሌሎች ምስጢራተ ቤተክርስቲያን (ጥምቀት፣ቁርባን፣ሜሮን፣ክህነት፣ ንስሐ እና ተክሊል) እና ሥርዓተ አምልኮ፣ ሰዓታት ማኅሌት ኪዳን መክብባቸውና መፈጸሚያቸው ምሥጢረ ምሥጢራት ነው፡፡
ምሥጢረ ቁርባን ለመንግስተ ሰማያት የተገባን የምንሆንበት የሰው ልጆች ድኅነትን (የዘላለም ሕይወትን) የምናገኝበት፣ በክርስቶስ ቤዛነት ያገኘነውን ነፃነት በሥጋዊ ድካም በኃጢአት ስናሳድፈው ደግሞ ለዘለዓለም ሕያው ከሆነ መስዋዕት በመንፈስ ቅዱስ ጸጋን የምንካፈልበት ታላቅ ምሥጢር ነው።
ምሥጢረ ቁርባን በድቅድቅ ጨለማ የተመሰለ ኃጢአትን ድል አድርገን ለሰርጉ ቤት ለመንግስተ ሰማያት የተገባን የምንሆንበት ታላቁ ምሥጢር ሲሆን ምሥጢራዊ ዕራት ተብሎም ይጠራል። ግብጾች ዩክሪስት (Eucharist ) ይሉታል፡፡ ይህም ቃል የግሪክ ሲሆን ትርጉሙ ‹‹ምስጋና ማቅረብ›› ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹የጌታ እራት››፣ ‹‹ምስጢራዊው እራት››፣ ‹‹አንድ የመሆን ምስጢር›› በማለትም ምሥጢረ ቁርባን ይተረጎማል።
ምሥጢረ ቁርባን የምሥጢራት ሁሉ ማጽኛ ሲሆን፣ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ከተፈጸሙ በኋላ ማጽኛው ማኅተሙ ምሥጢረ ምሥጢራት (Sacrament of Sacraments) በመባል የሚታወቀው ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡
ምሥጢረ ምሥጢራት ቅዱስ ቁርባን በንስሐ እና በጋብቻ ውስጥ ያለው ድርሻ ስንመለከት ለምሥጢረ ንስሐ ወደ ንስሐ አባት ቀርቦ ንስሐን የፈጸመ ሰው ንስሐው ሙሉ የሚሆነው የምሥጢረ ንስሐ ማጽኛ የሚሆነው ምሥጢረ ቁርባን ሲፈጸምለት ነው።
ምሥጢረ ጋብቻም የሚጸናው የሚታተመው አንድ የሚያደርገው ምሥጢረ ምሥጢራት በተባለው በቅዱስ ቁርባን የተፈጸመ እንደሆነ ነው። ቅዱስ ቁርባን የጸጋዎች ሁሉ አክሊል ነው። አንድ ጊዜ ስለ ዓለም ሁሉ ቤዛ መሥዋዕት ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም አካሉ እንሆን ዘንድ የምንካፈልበት፣ ከክርስቶስ ለቤተክርስቲያን የተሰጠ የጸጋዎች ሁሉ አክሊል ነው፡፡
ምሥጢረ ቁርባን ግሩም የሚያድን እሳታዊ ምሥጢር ሲሆን ይህን ምሥጢር ደጉ አባታችን አባ ሕርያቆስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በተናገረው የቅዳሴ ማርያም አንቀጽ “ዛሬ በዚህች ቀን በፍቅርና በትሕትና ግሩም በሚሆን በዚህ ምሥጢር ፊት እቆማለሁ በዚህም ማዕድና ቁርባን ፊት…
መንፈሳቸውን ያረከሱ ሰዎች ከርሱ ሊቀምሱ የማይቻላቸው በእውነት ቁርባን ነው፡፡ በበግ በጊደርና በላም ደም እንደ ነበረው እንደ ቀደሙት አባቶች መሥዋዕት አይደለም፤ እሳት ነው እንጂ፡፡ ፈቃዱን ለሚሠሩ ልቡናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው፡፡ ስሙን ለሚክዱ ለዓመፀኞች ሰዎች የሚበላ እሳት ነው፡፡” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 5-7)ብሎል።
በእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት (በምስጢረ ስላሴ) አምነው በክርስቶስ ደም የተዋጁና በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቁ ምዕመናን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በመቀበል ምስጢረ ቁርባንን ይፈጽማሉ፡፡
ጌታም በቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› (ዮሐ 6፡54) ብሎ እንደተናገ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን የሚቀበሉ ምዕመናን የዘላለም ሕይወት አላቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ሳይገባው ይህንን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት›› (1ኛ ቆር 11፡26) ብሎ ገልጿል።ቅዱስ ቁርባን መዳናችን የተፈጸመበትና የታተመበት የምሥጢራት ሁሉ ዘውድ ፣ ማጽኛ፣መክብበ ምሥጢረ ምሥጢራት Sacrament of sacraments ነው።
ምሥጢረ ቁርባንን ያስተማረን በተግባር ፈጽሟ ያሳየን በጸሎተ ሐሙስ ማታ መጋቢት ሃያ ስድስት ከአንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ አንድ ዓመት በፊት መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ዮሐ.6፥41-60፣ ማቴ. 26፥26-28።
የምሥጢረ ምሥጢራት ምስጢረ ቁርባን ተካፋይ የሆነ ሁሉ ስለ ቅዱስ ቁርባን ትርጉም፣ አስፈላጊነት፣ አፈጻጸም …ወዘተ ማመንና ማወቅ መፈጸም ይጠበቅበታል።