Blogs

ያልተፈለገው የኢሮብ ህዝብ ሕልውናና ረጅሙ ተቃርኖ!!

ክፍል አንድ፤ 

"የትግራይ የነፃነት ትግል" እና የኢሮብ ህዝብ ተቃርኖ አጀማመር



ከዮሴፍ አዳዩ                                                                              ጥቅምት 2014

መግቢያ

አብዛኛው ጊዜ እንደታዘብኩት ከሆነ ስለ ሕዝባችን ስናነሳ ‘መውደቃችንን እንጂ ያንሸራተተንን' በተመለከተ ልብ አላልንም:: የዛሬው የሕዝባችን የውድቀት ደረጃ እንዲሁ በድንገት የመጣ ሳይሆን የዓመታት የሰው ሰራሽና የተፍጥሮ የስራ ውጤት ነው በሚለው በፅኑ አምናለሁ። በመሆኑም የዛሬውን የሕዝባችን ፈተናና ቀጣይ አደጋ ትክክለኛውን ስዕል ለማመላከት ወደ ኋላ ቢያንስ 47 ዓመት ወደ ኋላ መሄድ የግድ ይሆናል የሚል የግል እምነት አለኝ። በመሆኑም በተቻለ መጠን ለማሳጠር ሲባል በ"ቁንፅል" አቅርቤዋለሁ። ቁንፅል ማለት ዛሬ ሕዝባችን የሚገኝበትን ተጨባጭ ሁለመናዊ ጉስቁልና ሳላካትት፤ ለዛሬው ተጨባጭ የህልውና አደጋ ዳርገውታል ብዬ በማምንባቸው ውስጣዊ ቅራኔዎች/ችግሮችና በይበልጥ በውጫዊ ጫናዎች ላይ ትኩረት ማድረጌን ለመጠቆም ያህል ነው:: ይህንኑ ሃላፊነት በራሴ ተነሳሽነት ስወስድ በጉዳዩ ላይ ከኔ ይበልጥ ጥልቅ እውቀትና ግንዛቤ ያላቹህና እጅግ የማከብራቹህ ወንድሞቼና እህቶቼ መኖራችሁን በመርሳት አይደለም:: በመሆኑም አቀራረቤ ላይ ግድፈት ሆነ ይዘታዊ ውሱንነት ቢኖር የአቅም ጉዳይ ከመሆኑ ውጭ ከዳተኝነት/ቦህሣ/ ወይንም ጊዜ ባለመስጠት ስላልሆነ ይህንን እንደመነሻ በመውሰድ በይበልጥ እንደምታዳብሩት፣ ስህተት ካለበትም እንደምታርሙት በመተማመን ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የፅሁፉ ርእስ፤ "ያልተፈለገው የኢሮብ ሕዝብ ሕልውናና ረጅሙ ተቃርኖ !!" የሚል ሲሆን ፅሁፉን እስከ ፍፃሜው ካነበባችሁ በኋላ የርዕሱን መልእክት ገፅታውን ከሁለት አቅጣጫ እንድትገነዘቡልኝ አደራ እላለሁ:: ማለትም ከውጭ አካላት ፍላጎትና ግብ (የህወሓት አመራርና መሰሎቹ)፤ እንዲሁም  ከራሳችንም (በተለይ ኤሊቱ) ካለበት የቆየ በጋራ ለመስራት አለመቻል/አለመፈለግ፣ እንዲሁም በግሉም ቢሆን ሙሁራዊ ግዴታውን ያለመወጣት ችግርን ታሳቢ ማድረግ አገባብ ሆኖ ታይቶኛል።

 

"የትግራይ የነፃነት ትግል" እና የኢሮብ ህዝብ ተቃርኖ አጀማመር

1967 ላይ ሲመሰረት ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ (ተሓሕት) ከ1972 በኋላ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት/TPLF/) የተመሰረተው ከተማ ሳይሆን ደደቢት/ሽሬ በረሃ ነው:: (አቶ ገብሩ አስራት #ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ# መፅሃፉ ላይ በግልጽ አስቀምጧል):: በርግጥ በውስን የውይይት መድረኮች እየተገናኘ የሚመክር ማገብት የሚባል እና በጥቂት ተራማጅ ነን በሚሉ የትግራይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተመሠረተ ማሕበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ (ማገብት) የሚባል ማሕበር የነበረ ቢሆንም የወቅቱ አንኳር የመወያያ ርዕሰ ጉዳዮች በሚመለከት ግን ጥልቅ መረጃ የለኝም:: በቀጣይ የትግራይ ሕዝብ ማንነትና የነፃነት ዙሪያ ስለነበረው ግንዛቤ የሚገለጽ የጠራ መረጃም ግልጽ አይደለም። የሆነ ሆኖ ድንገተኛው የ1966ቱ አብዮት ከተነሳበት የካቲት ወር ጀምሮ እሰከ የክረምት ወራት መጨረሻ ግን የማገብት መስራቾች ተደጋጋሚ ስብሰባዎች ያደርጉ እንደነበር በተለያዩ መረጃዎች ተገልጿል:: በዚሁ ዓመት መጨረሻ ማብቂያ ነሓሴ ላይ በአዲስ አበባ  ጊዮርጊስ  ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ እጅግ የተወሰኑ የትግራይ ተወላጅ ባለሀብቶች፤ የቢሮ ሰዎች እና ውስን የማሕበሩ አባል ተማሪዎች የተገኙበት ስብሰባ መደረጉ መረጃዎች ያመላክታሉ። በወቅቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረ ዖቅባዝጊ "ትግራይ ብሔር" የሚለውን መመዘኛና ስያሜ እንደምታሟላ እና የራሷ የነፃነት ትግል ማድረግ እንደምትችል የሚገልጽ ሰፋ ያለ ፅሑፍ ማቅረቡ ይታወቃል:: ዖቅባዝጊ የመቀሌ ልጅ ሲሆን፤ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ዝነኛና በውቅቱ #አዞቹ# (The Crocodiles) እየተባለ ሲጠራ የነበረ በነ ብርሃነመስቀል ረዳ፣ ዘርኡ ክሕሸን፣ ጸጋዬ ገ/መድህን የሚመራ የነበረ ቡድን አባል የነበረው መለስ ተኽለ ቅርብ ጓደኛና በኋላም አ/አ ማዘጋጃ ቤት ላይ ቦምብ ወርውራችኋል ተብለው አብረው መረሸናቸው የሚታወቅ ሆኖ በትክክል የማገብት አባል ይኑር አይኑር የሚያሳይ የተገኘ መረጃ የለም። አንድ የሚታወቅ ነገር ዖቅባዝጊ በስብሰባው ያነበበው ፅሁፍ በኋላ በረሃ ከገባው ቡድን አንዱ የሆነ ግለሰብ ወደ ሜዳ ይዞት እንደወጣ ይታወቃል::

አብዛኛውን የማገብት አባላት የያዘው በአቶ አየለ ገስሰ/ስሑል የተመራው ቡድን ትጥቅ ትግል ለመጀመር በሽረ አውራጃ ልዩ ስሙ ደደቢት በረሃ  በ1967 የካቲት ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራት (ተሓህት) በሚል ስም መመመስረቱ፣  የድርጅቱ ዓላማ የግራውን አድዮሎጂ የሚከተል በብሄር ጥያቄ ዙሪያ የሚታገል መሆኑ ከሚገልፅ ውጭ ግልፅ የሆነ የፖልቲካ ፕሮግራም እንዳልነበረው ይታወቃል። ተሓህት በሚል ስም ትጥቅ ትግል የጀመረው ቡድን ይዞት ከተነሳው ዓላማ አንድ ግልፅ የነበረው አንድ ዓይነት ባህል፤ ቋንቋ ፤ ስነልቦና ያለው ህዝብ የሚኖርባት፣ የራሷ ጂኦግራፊያዊ ወሰን  ያላት ትግራይ የምትባል ብሄር መኖሯና ለዚች ብሄር የነጻነት ትግሉ ታክቲካዊ ስልቶችና ስትራቴጂካዊ ግቦችን ያስቀመጠ መኖሩ ነው።

 

ተሓህት በሚል ስም ትጥቅ ትግል የጀመረው ቡድን የተወሰኑ የቡድን አባላት ደደቢት በረሃ ሲያስገባ የተወሰኑትንም በኤርትራ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ከሻዕቢያ ጋራ ገና ከጅምሩ ነበር ጥሩ ግኑኝነት የመሰረተው። በዚህ መሰረት የድርጅቱ እንቅስቃሴ በቅርበት ሲከታተሉ ወደነበሩት ኢሳያስ እና ስብሐት ኤፍሬም ትግራይ አንድ ዓይነት ባህል፤ ቋንቋ፤ ስነልቦናና ጂዮግራፊያዊ ወሰን ያለው አከባቢ አድርጎ ያስቀመጠ በቶሎ ቶሎ የተዘጋጀ ማንፈስቶ ቀረበ:: ሁለቱ ጉምቱ የሻዕቢያ ፓለቲከኞች የተሓህትን የይድረስ ይድረስ የብሔር ትንታኔና ግቡን የትግራይ ነፃነት ያደረገው ማኒፈስቶ አልጣማቸውም። በመሆኑም  በቸልታ የሚያልፉት ጉዳይ ስላነበረ በአስተያየት የተደገፉ ቀጥለው የተቀመጡ ጥያቄዎች አቀረቡላቸው።

1.      አንድ ቋንቋ ሲባል ምን ማለት ነው? በትግራይ ውስጥ የሚኖሩ እንደ "ኢሮብ ፤ኩናማን፤ አገውን፣ አፋር እንዴት አይታችሁ ነው?  

2.      ሌላ ደግሞ "አንድ ቋንቋ ስትሉ ያው ትግርኛ " ማለት ስለሚሆን ኤርትራ ውስጥ ያሉትንም ትግርኛ ተናጋሪዎችን የማካተት ተልዕኮ ስለሚያመላክት ይህም በግልፅ መቀመጥ አለበት።

3.      “ጂኦግራፊያዊ ድንበር” በሚል የተቀመጠውም ገና በትግል ላይ ስላለን፤ ገና በውል ያልተሰመሩ ወሰኖች ስላሉ ይህም አያስኬድም አሉዋቸው።

 

እዚህ ላይ በግሌ ሳስበው "ስለኩናማ፣ አፋርና አገው" ብዙ ባላውቅም በወቅቱ ድንገት ከዩኒቨርስቲ ትምህርታቸው ብድግ ብለው  በረሃ የገቡ የመኻል ትግራይ ወጣቶች፤ ስለ ኢሮብ ህዝብና አከባቢ የተሟላ እውቀትና ግንዛቤ ነበራቸው የሚል ግምት ፈፅሞ የለኝም። (እንኳንስ ያኔ አሁን የሚመሰረቱ መሰል የትግራይ ድርጅቶችም ስለሌላቸው) በመሆኑም የተሓህት መስራቾች ይዘዉት የተነሱት (አንዲት ትግርኛ ተናጋሪ የሚኖሩባት ትግራይ) ዓላማ የኢሮብ ህዝብ ሊቀበላቸው የማይችል መሆኑ ገና ከጥዋቱ ግልፅ ነበረ ማለት ይቻላል። እነሱ ሊመስርቱት ለሚፈልጉት ትግራይ የኢሮብ ህዝብ እንቅፋት ሊሆንባቸው እንደምችል ገና ከጅምሩ ግልፅ ነበር።  በርግጥ ይህ የኢሮብ ሕዝብ በመጥላት የሚገለፅ ላይሆን ይችላል፤ የወቅቱ የድርጅቱ ዓላማ የፈጠረው እንጂ።

ያም ሆነ ይህ ተሓህት በዚሁ ወቅት ከሻዕቢያ ጋር የመጋጨቱ ጉዳይ በየትኛውም መለኪያ የሚያዋጣው ስላልነበረ ከምንም በላይ በብልሃትና ስልት መጓዝ የግድ ነበር። ስለሆነም የሻዕቢያ የኤርትራ የቅኝ ግዛት ጥያቄ እንዳለ ተቀብለው፣ ወቅቱን የሚመጥን የአካሄድ ለውጥ በማድረግ ትግራይን በሚመለከት ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ትኩረት አደረጉ።  አንደኛ የድርጅቱን ህልውና ለማስረገጥ በትግራይ በሁሉም አከባቢ ራሳቸውን ማስተዋወቅና የኣባላት ምልመላ ማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ በዋናነት በትግራይ ውስጥ እንደነሱ ትጥቅ ትግል በመጀመር ላይ የነበሩ አማራጭ ሃይሎችን በማጥፋት የትግራይ ሕዝብ በብቸኝነት ሁሉን- አቀፍ ውክልና (Shift of representation claim). ማስረገጥ የሚል ታክቲክ ነደፉ።

በዚህ እቅድ መሰረትም በወቅቱ ትግራይ ውስጥ ትጥቅ ትግል በመጀመር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዴህ)፤ ግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ (ግገሓት) የኢትዮጵያ ህዝባዊ አቢዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ተራ በተራ ከትግራይ ለማስወገድ መጀመሪያ ግገሓትን በእንዋሃድ ስም በ1968 መጀመሪያ አከባቢ/ሕዳር ላይ በዛጋብላ በረሃ መሪዎቹን በመግደልና በማሰር አጠፉት። ቀጥሎ በ1969 በውቅቱ የሽረ አውራጃ ላይ አብሮ ጎን ለጎን ሲንቀሳቀስ የነበረ ኢዴህ ላይ ወራቶች የፈጀ እልህ አስጨራሽ ጦርነት ከፍተው ኢዴህን ከትግራይ አስወጡ። በመቀጠልም ኢህአፓ ላይም በ1970 አጋማሽ ላይ ጦርነት ከፍተው ከትግራይ አስወጡ። ይህንን የማጥፋት ተግባር በመታዘብ በአንድ ወቅት ኢሳያስ አፈወርቂ  "እስከመቼ ነው እንደ እባብ ከሁሉም ጋር መናከሱን የምታቆሙት" በማለት እንደወቀሳቸው በግልጽ ተቀምጧል።

 

ከላይ እንደተገለፀው ተሓህት ትጥቅ ትግሉን የጀመረው በምዕራብ ትግራይ ስለነበረ ወደ ምስራቅ ትግራይ/ዓዲ ኢሮብ የመጣው በ1968 ሕዳር ላይ ነበር። ተሓህት ከመምጣቱ በፊት ግን ኢህአፓ ኢሮብን ዋና መቀመጫ/መናሀሪያ/ቤዙ አድርጎ ምስራቅ ትግራይ ላይ ከ1967 መጀመሪያ ጀምሮ ተንቀሳቅሶ ከኢሮብ ህዝብ ጋራ ጥሩ ግኑኝነት አድርጎ ጥሩ ተቀባይነትም አግኝቶ ነበር። ተሓህት በ1968 ወደ አከባቢው መጥቶ ገና ከኢሮብ ህዝብ ጋራ መገናኘት ሲጅምር የኢሮብ ህዝብ ጥያቄዎች አንስቷል። አንደኛ "አናንተ ማን ትባላላችሁ?" ማንስ ብለን እንጥራቹህ? አለ። እነሱም "እኛ ተጋድሎ ትግራይ” በግርድፉ ሲተረጎም “የትግራይ ታጋዮች እንባላለን" አሉ። ህዝቡም ታዲያ "ታጋይ አገር ላይ ሌላ ታጋይ ምን ይፈይዳል? "በማለት መልሱን በጥያቄ መልክ መለሰ። “ታጋይ አገር” የተባለው ህዝቡ ራሱ ኑሮውን ለማሸነፍ ትግል ውስጥ የሚኖር ህዝብ በመሆኑ ተጨማሪ ታጋይም ሆነ ትግል መሸከም አይቻለውም የሚል መልእክት ያለው ጭብጥ ለማመላከት ነበር።  ሁለተኛው የህዝቡ ጥያቄ "ለመሆኑ ዓላማቹህ ምንድነው?" የሚል ሆነ። የተሓህት ካድሬዎቹ ትግራይን የአማራ ገዢ መደብ ካደረሰባት የባህል፤ የቋንቋ፤ የማንነት ወዘተ ጭቆና ለማላቀቅ" ነው ብለው መልስ ሰጡ። ይህ መልስም ለኢሮብ ህዝብ የሚዋጥ አልሆነም። እንዲያውም ስለቋንቋ፤ ባህልና ማንነት ጭቆና ከተነሳና ትግሉ ከዚህ ጭቆና ነፃ ለመውጣት ከሆነ ትግላችሁ "እኛ ላይ የቋንቋ፤ ባህልና ማንነት ጭቆና የሚደርስብን በናንተው በተጋሩ በመሆኑ ቀድማችሁ እናንተ ተጋሩ እኛን ነፃ ልቀቁን" በማለት የቅጩን በመናገር "ይህ ካልሆነ ግን እኛም ለቋንቋችን፤ ባህላችንና ማንነታትች ነፃነት ከናንተ ጋራ ትግል መግጠም  የግድ ይሆናል" አላቸው።


በዚሁ አላበቃም ህዝቡ ከዚህ በኋላ ተጨማሪ ኃይል የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም በማለት ለነሱ ፕሮፖጋንዳ ጀርባ መስጠቱን በግልፅ ተናገረ/አሳየ። እንዲያውም በድፍረት "ይህን እኛን ለማስተማር ብላችሁ እኛ ዘንድ ጊዜያችሁን አታባክኑ" አላቸው። ተሓህቶች በኢሮብ ኢህአፓ ቀድሞ ገብቶ መስራቱን በሚገባ ያውቁ ስለነበር እናንተ የተቀበላችሁት የታላቋ/ የዓባይ/ ኢትዮጲያ ድርጅት/ኢሕአፓ/ወደ አገሩ ይባረራል! ተወደደም ተጠላም ውሎ አድሮ ትግራይ "የተጋሩ ትሆናለች" አሉ። በዚህም የተነሳ የኢሮብ ህዝብና የተሓህት ተቃርኖ ገና ክጅምሩ ግልፅ ሆኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና እየጠነከረ ሄደ። ይህ በእንዲህ እያለም የኢሮብ ህዝብ ተቀብሎት የነበረ ኢህአፓ ከተሓህት ጋራ በተደረገው ጦርነት ህዝቡን ሳያስውቅ ከአከባቢው ወጣ። ከ1970 አጋማሽ በኋላም ተሓህት አከባቢውን በብቸኝነት ተቆጣጠረ።

እርግጥ የኢሮብ ሕዝብ በቁጥሩ አናሳ ነው። ይሁንና በትግራይ የነፃነት ትግል ሆነ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ አንድነት በተደረጉት ትግሎች የነበረው ድርሻና ተፅዕኖ የጎላ መሆኑ ግን ጥርጥር የለዉም። በሌላ አገላለፅ ከላይ እያየን እንደመጣነው ይኸው የህዝቡ አወዛጋቢ ሚና ደግሞ ድርጅቱ ትግራይን ነፃ ለማውጣት ሆነ ካወጣ በኋላ ከሚከተለው ሥነ-ዘዴ አንፃር አሉታዊ ጎኑ እየሰፋ ተቃርኖውም በዛው ልክ እያደገ እንደሆነ በቀላሉ ማየት ይቻላል። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ መረሳት የሌለበት መሰረታዊ ጉዳይ አለ። ይኸውም የኢሮብ ሕዝብ በተለምዶ ከሚታወቀው "የአንድ ውሑድ ሕዝብ አካሄድ እና ልምድ በተቃራኒ" ራሱን የሚመለከትበት የከፍታ ሥነ-ልቦናና በትግራዋይነት የጋራ ማንነት/Shared Identity/ላይ ያለው የቆየ አሉታ ነው። (ይህ በዜያዊ ንግግር እንዲሁም ዓዳር በስፋት ይገለጻል)

 

ይህ በኢሮብ ህዝብና በተሓህት ገና ከጅምሩ የታየው ተቃርኖ ገና ኢህአፓ አከባቢውን እንደለቀቀ ተሓህት ያስተናገደበት መንገድ እንመልከት። ሂደቱና አካሄዱ (ተቃርኖዎችን በማስታረቅና በማክሰም ወይንስ ይበልጥ በማባባስና ሕዝቡን በማክሰም) እንደነበረ አብረን እንቀጥል!! እላይ አንደተገለፀው ቀድሞ አከባቢውን ተቆጣጥሮ የነበረውና በነሱ አባባል "ዓባይ ኢትዮጵያ" እያሉ ሲጠሩት የነበረው ኢህአፓ አከባቢውን ለቋል። ኢህአፓ ውስጥ ከአመራር ጀምሮ እስከ ተራ አባል ደረጃ ብዙ ኢሮቦች የተሳተፉበት ድርጅት ስለነበረ  በውጊያው ውስጥም ብዛት የነበራቸው የኢሮብ ተወላጆች አባላትና ሚልሻዎች ስለነበሩ በተደረገው ጦርነት ብዙዎች መስዋዕትነት ከፍለዋል፣ ድርጅቱ አከባቢውን ለቆ ሲወጣ  በርካቶች ከድርጅቱ ጋር ሲሰደዱ ቁጥራቸው የማይናቅ ደግሞ "ህዝባችንንና አከባቢያችንን ጥለን አንሄድም" በማለት በሕዝቡ ውስጥ ተበትነው በመደበቅ ሳይሄዱ ቀርቷል።

 

ኢህአፓ ጠቅልሎ ከወጣ በኋላና የኢሮብ ህዝብና መሬቱ በተሓህት ቁጥጥር ስር ከገባ በኋላ የነበረው ጊዜ  ለኢሮብ ህዝብ  እጅግ አስቸጋሪ ወቅት ነበረ:: ኢህአፓ በህዝቡ ፍላጎትና ሙሉ ተሳትፎ መስርቶዋቸው የነበሩ ዴሞክራሲያዊ የስተዳደር መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ በተሓህት እንዲፈርሱ ተደረገ፤ በቀደመው የአስተዳደር መዋቅር በህዝቡ ተመርጠው በሃላፊነት የነበሩ ጠንካራ ኢሮባዊ ማንነትና ስነልቦና የነበራቸው ሰዎች በኢህአፓ አባልነት ተመድበው ከሃላፊነታቸው ተባረሩ ገሚሶቹም ታሰሩ፤ ተደበደቡ፤ ተሰደዱ:: በምትካቸው በማሕበረሰቡ ዘንድ በየግላዊ የስነምግባር ችግርና መሰል አሉታዊ ልምድ ተገልለው የነበሩ ግለሰቦች እየተፈለጉ በሃላፊነት ተመደቡ:: በሕዝቡ ዘንድ ተሰሚነት የነበራቸው  ኣባቶች ወደ ጠርዝ ተገፉ፤ እንዲሸማቀቁ ተደረጉ፤ የኢህአፓ አባል/ደጋፊ የሚል ታፔላ እየተለጠፈባቸው አፋቸውን ዘግተው ጥግ እንዲይዙ ተደረጉ፤ የሕዝቡ ነባር እሴቶችንና ሁሉን ባሳተፈ የኢሮብ ባህል መሰረት መሬቱን ይዘው በነበሩና በመሬት ፈላጊ ወጣቶች መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት ተግባራዊ ሆኖ የነበረና በፍትሃዊነቱ የተመሰከረለት የመሬት ክፍፍል ፈረሶ መና ቀረ፣ መሬትና የእርሻ መሬት አጠቃቀም በተመለከተ ወጥቶ የነበረው ሥሪት ልቅ ሆነ፤ መኖሪያና፤ መሰናዘሪያ (ዋፍረና) ተደባለቀ። እዚህ ላይ ሁላችሁም ወደየአከባቢያቹህ ነባር የሕዝባችን የመሬት አጠቃቀምና አሰፋፈር ወደ ኋላ መለስ በማለት ብትቃኙ ደስ ይለኛል። እኔ ግን በቅርብ ከማውቃቸው የተወሰኑትን እንደ አብነት ላንሳ። ለምሳሌ፤ የካፍና፤ የዓባበና፤ ጋራሳ፤ በሮይታ፤ ዓይጋ፤ ዓዳጋ፤ ወዘተ ምንም የማያፈራ የተራራ ላይ ዓለታማ መሬት ላይ አሰፋፈርና የመሬት አጠቃቀም ልብ በሉ።

 

ይኸው በተለምዶ በእቅድ ሲመራ የነበረ መሬት ለሁሉም ክፍት ሆነ፣ ነዋሪውም ያለ ማንም ቁጥጥር እየተሽቀዳደመ ወደፈለገው በየአቅጣጫው መኖሪያውን ገነባ። የመሬት ሀብት ብክነት ተስፋፍቶ መሬቱ እንዳልነበረ ሆኖ ምድረበዳ ሆነ። የሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ መሠረት የመናዱ እቅድ ከሚጠበቀው ፍጥነት በላይ ተቀላጠፈ። ነባር እሴቱን ሳይለቅ በታዋቂው የህዝባችን አደረጃጀት ሃላፊ /ገረይ/ በየገበሬ ማሕበራቱ ነፃ ፈቃድና ይሁንታ ተዋቅሮ የነበረው፤ አንደኛ፤ በሕዝብ የተመረጡት የሊቀ-መናብርት ኮሚቴ (አስፈፃሚው ዘርፍ ) ሁለተኛ፤ የሕዝባዊ ሸንጎ (ተቆጣጣሪው ዘርፍ) ሙሉ በሙሉ ፈረሰ። መሰረቱን ይዞ የነበረው የመሬት ክፍፍል፤ ፍትሕና ፍትሓዊ አሰራር መና ቀረ። ህዝቡም ፍትሕን በየግል ዓቅሙ ማፈላለግ ጀመረ። በሂደትም በህዝባችን ዘንድ ያልተለመዱና ባዕድ የሆኑ በስዉር የመጠፋፋት ልምዶች ተስፋፉ። (ዛሬ ሁሉም እንደ እውነት እየተቆጠረ (ሓላል) ሁነው ያለምን ሞራላዊ ክልከላ ይተገበራሉ።)

ሌላውና ዋናው ጉዳይ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ግድያና ህዝብን የማሸማቀቅ ሴራ ነው። እዚህ ላይ ምናልባት ለማሳያነት ያህል ከያንዳንዳቸው አንድ፤ አንድ አብነት ላንሳ፤ አንደኛ፤ 1970 (የዓመት በዓል ጭፈራ ላይ ጳጉሜ አምስት ቅዱስ ዮሓንስ ምሽት በመምረጥ ከወርዓትለ እስከ ያሆ ዳጋ የተፈፀመው ግድያ ነው። እናት ጀርባ ላይ ያለው ጨቅላ ሕፃን ጨምሮ የሁለት ጀግኖች የተስፋይ ሃይሉ (ጋራሣ/እና የደበሱ ካሕሳይ ሞትና፤ አምስት ቁስለኛ ሁሉም ሲቪል። (ይህ ሁሉ የሆነው ከኢሕአሠ የቀሩት የኢሮብ ልጆች ለመመንጠር ነበር።) ሁለተኛውና እጅግ የሚገርመው ደግሞ የማሸማቀቂያ ስልት ሲሆን፤ ይህ የሆነው ዓሊተና (አግለት ሓዳ) ሙሉ የቡክናይቲ ዓረ ነዋሪዎች በተሰበሰበበት ነው። ሰብሳቢው ደግሞ አሸብር በሚል የትግል ስም የሚታወቅ ከላይ የተዘረዘረውን ድርጊት በዋና መሪነት ያስፈጸመ ሰው፣ ህዝቡ ፊት ቁሟል፤ ሕዝቡም አጀንዳውን በመጠባበቅ ላይ ነው። እሱ ግን በድንገት "እናንተ!” ይላል "እናንተ እኮ ምንም አይደላችሁም" ይልና "ዒባ ኢኹም" ሲተረጎም እበት ናችሁ በማለት በመቀጠል ደግሞ ክላሽንኮቩን ተሰብሳቢዎች ፊት ያስቀምጥና፤ እስቲ ከመካከላቹህ "ወንድ" ካለ አንስቶ ይግደለኝ፤ በማለት መሳሪያውን ጥሎ ወደተከበሩ አባታችን ወደ ሃለቃ መድህን ቤት አቅጣጫ ይሄዳል። እንግዲህ ልብ በሉ ወደ አንድ ህዝብ ገና በመግባት ላይ ያለ አንድ ሕዝባዊ ነኝ፣ ለህዝብ መብት እታገላለሁ  የሚል ታጋይ ሃይል!!!! ተግባር። እነዚህን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በርካታ የተደረጉ ድርጊቶች መዘርዘር ይቻላል። ነገር ግን ከሚገባ በላይ እየሰፋ ስለሚሄድ  ለማነፃፀሪያ ያህል አንድ ነጥብ ማንሳቱ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘሁት ብቻ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

 

ጊዜው 1968 ሚያዚያ አከባቢ ነበር። ዶክተር ተስፋይ ደበሳይና አንድ ስሙን የዘነጋሁት የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት/ከኤርትራ መልስ ወደ ኢሮብ ገብቷል። እግረ መንገድ 'ካላዓሣ' የኢሕአሠ ወታደራዊ ኮማንድ አመራር ስብሰባ ላይ ታድመው ተገኝተዋል። የሰራዊቱ አመራር አንድ ሃሳብ ያነሳል። "ይህ ድርጅት (ተሓህት/እንቅፋት እየሆነብን ይገኛል" ስለዚህም በወቅቱ መመታት ይኖርበታልና እርምጃ ለመውሰድ አስበናል ይላሉ። ዶ/ር ተስፋይ ግን ይህ በፍጹም የሚታሰብ አይሆንም። የትግራይ ልጆች ደም አፍስሰን ትግራይ ውስጥ መስራት አዳጋች መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከአንድ "አብዮታዊ ህዝባዊ ድርጅትና ሰራዊት" የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፤ ስለዚህም መብታቸውን /exercise/ያድርጉ! ይህንኑ እንዳታደርጉ ብሎ ጥብቅ ትእዛዝ ያስተላለፋል። ሌላው በዚሁ መርህ መሠረት በዚሁ ዓመት ኢሕአሠ ወሎ ላይ ባደረገው ውጊያ "ሕዝብ ላይ አንተኩስም" በማለት /ደበሳይ ካሕሳይ፤ አለማ አጋዳ፤ ሺፋረ ተካ፤ ሐጎስ ብሩ/ የተባሉ ምርጥ የኢሮብ ወጣቶችና ሌሎች ብዙ የኢህአፓ ኣባላት በገበሬ ሰራዊት "በጦር" እየተወጉ መሰዋታቸው ተዘግቧል። ያም ሆኖ ህወሓት ወደ ሕዝባችን የገባበት አገባብና የተከተለው የአያያዝ ስልት፤ ይህን ሕዝብ በተመለከተ ያነገበው ቀጣይ ድርጅታዊ ፍላጎትና ግቡን በቀላሉ ተገማች (predictable) ብቻ ሳይሆን ግልፅ ያደርገዋል። የተሓህትና የኢሮብ ህዝብ ተቃርኖና ወከባውም በዚህ መልክ ቀጥሏል። ሕዝቡም ለሚደርሱበት ተቃራኒ ድርጊቶች በተለያየ ዘዴ አፀፋዊ ምላሽ መስጠትን ቀጥሏል።

 

የኢሮብ ህዝብና የተሓህት ተቃርኖ ከመጥበብ ይልቅ በመስፋት ጥልቅ የሆነ ሥር እየሰደደ እሰከ 1983 ዓ ም ደርግ ውድቀት ድረስ ቀጠለ። 1983 . 17 ዓመታቱየነፃነት” ትግል አብቅቶ እስከ 1987 . የአዲስቷ የኢሕአዴግ ኢትዮጲያ/ትግራይ/የወደፊት ግንባታ ቅድመ- ዝግጅት ዓመታት ሁነዋል። ድርጅቱ በመጪው (prospective) የትግራይ ክልላዊ መንግስትና ትግራይ ውስጥ በማንም የማይገሰስ የብቸኝነት "የሕጋዊ ሰውነት" ጉልበት ተቀዳጅቷል። ከዚህ በኋላ ሌላው ቢጠፋ ትግራይ የድርጅቱ የመጥፎ ቀን መጠጊያ ስለመሆኗ ሳንካ መኖር የለበትም። ለዓመታት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት የነፃነት አጀንዳው ከመጋረጃው በስተጀርባ ቢሆንም እንኳ ዛሬም በቦታው አለ። በሌላ አነጋገር ለብዙ ዓመታት የተሰራበት "የድርጅቱ የብቸኝነት ውክልና (sole representation claim) ሳይሸራረፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። እጅግ አሳሳቢ የሚሆነው ግን "እኛና እነሱ" የሚሉት የኢሮብ ሕዝብ አሁንም በቦታው አለ። በአጭሩ፤ ይህንን የድርጅቱ የሁለት ኣማራጭ ውጥን፤ ማሳያ የሚሆን አንድ ነጥብ ላንሳ።

 

ጊዜው 1986 ነው።  ለአቶ ስዬ 'አሰር' የትግርኛ መፅሔት ላይ አንድ የማጠቃለያ ጥያቄ አቅርባላቸው ነበር። ይህም “ኢሕአዴግ በተለይ መኸል አገር ላይ የተጠበቀው ያህል ተቀባይነት እያገኘ አይመስልም፤ ይሁንና ነገሮች አመቺ ካልሆኑ ሌላ አማራጭ አለ ወይ? የሚል ነበር። አቶ ስየ ግን ባጭሩ "ደርብይናሎም ንኸይድ" “ጥለንላቸው እንሄዳለን" ነበር ያሉት። ልብ በሉ፣ በዚህ ዓመት ሕገ መንግስት ረቂቅ ላይ ውይይት ነበር። ያም ሆነ ይህ አሁን ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳያችን ለመመለስ 83 ዓ ም ቀጥሎ ባሉት የሽግግር ዓመታት ሕዝቦች ለየራሳቸው ሕልውናና በመቀጠል ደግሞ "ብሔርን" መሠረት በማድረግ "ከታች ወደላይ" ለሚደረገው ለአዲሱ ሀገረ - መንግስት ግንባታ በመሸባሸብ ላይ ናቸው። ለዚህ ሲባል ደግሞ የየክልሉ ተወላጅ ሙያተኞች ከያሉበት ወደየክልላችው ተጠርተው በመሄድ ላይ ናቸው /ከኢሮብ በስተቀር/ በቀጣይ ደግሞ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ተመስርቷል። በክልሉ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ደግም "የኢሮብ ሕዝብ ግንባታ" ሕገ መንግስታዊ መብት አለ። በመሆኑም ከብሔር ግንባታ ጋር የማይታለፉ መሠረታዊ ጉዳዮች በርካታ ሲሆኑ፤

 

በትግራይ ክልል ክልላዊ መንግስት ምስረታ ላይ የኢሮብ ሕዝብ ጉዳይ አልተካተተም። ይህ ብቻ አይደልም የቆየው ወከባው ኣላቋረጠም። ሰዎቾ እንደውጭ ዜጋ ከገዛ ቀያቸው 24 ሰዓት እንዲለቁ ይደረጋል (ለዚህ እኔ የማስታውሳቸው አቦይ ተስፋይ ገዛሃይ እና በየነ ሐጎስ /ካፍና/እንደአብነት ይጠቀሳሉ/፤ ሕዝቡ መብቶቹ እንዲከበሩለት ይጠብቃል::የሚገርመው ግን የክልሉ መንግስት የሕዝቡን መብቶች በግላጭ መከልከሉ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ ለመገደብና ለማደናቀፍ በእቅድ መስራቱ ነው። እነደማሳያ የሚሆኑ የተወሰኑ ተጨባጭ የማደናቀፊያና የገደብ ስልቶችን እንመልከት::

1. ውክልና በሚመለከት ለኢሮብ ሕዝብ የተወከሉት ሁሉም ተጋሩ ታጋዮች ማለትም ገብረ/ እና የገብረ(crew) ቡድን በቋሚነት ሲሆን (በርግጥ ይህ ቡድን 1993 በዓመጽ ቢባረርም) እስከአሁን ኢሮብን የሚያስተዳድረው ገብረ ‘ኢሮብ’ መሆኑ ግን ፀሓይ የሞቀው ሃቅ ነው:: /በያንዳንዱ ዓመት 52 ቅዳሜዎች ገብረ ዳውሃን መገኘት ይኖርበታል/ ቀኑን ሳያዛንፍ ከአዲግራት ወደ ዳው'ሓን ይወርዳል፤ ይገመግማል፤ መመሪያ ይሰጣ።

2. ማንነትን በሚመለከት፣ የኢሮብ ህዝብ የራሱ ቋንቋ ሳሆ እያለው ሙሉ ሕዝባዊ ግልጋሎቱን በትግርኛ ቋንቋ እንዲያገኝ ተጭኖበታል። ይህ ጉዳይ በዚሁ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ቀደም ሲል በእቅድ ሲሰራበት ቆይቷል። ለአብነት

2.1 ሰበያን አንደ እጬ "ዋና ከተማ" ሁላችንም እንደምናስታውሰው በመጀመሪያዎቹ የዞባና ወረዳዎች ሽንሸና ወቅት ማለትም ገና የዓሊተና ጉዳይ ሳይነሳ ኢሮብና ሱሩኽሶን አንድ ላይ በማጠቃለል ሰበያ ዋና ከተማ እንድትሆን ከፍተኛ ግፊት ተደርጎ ነበር::/እዚህ ላይ ሰበያ የገብረ የትውልድ አከባቢ መሆኗን ሳንረሳ / በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ሕዝባችን አቋም የሚቀመስ አልሆነም። ስለሆነም ሌላ አማራጭ ተፈልጎለታል።

2.2 የዓሊተና ወደ ዳው'ሓን መዛወር፤ የዓሊተና ዝውውር ለኢሮብ ህዝብ ያለው አሉታዊ ትርጉም ሰፊና ጥልቅ ነው። ባጭሩ የዘመናት የታሪክ፤ የባህልና የማንነት እሴቶቹን በመናድ "የግሌ" የሚለውን የማሳጣት ተግባር ነበር። ይህ ውሳኔ የሕዝቡን ቁጣ ከቁጥጥር ውጭ ያደረገና አንዳንዱን እስከ እስር የዳረገ ነበር። ምንም ቢባል ግን ውሳኔውን መቀልበስ አልተቻለም። የኢሮብ ዋና ከተማም ከዓሊተና ወደ ደውሃን  በጉልበትተቀየረ። ሁለተኛውና የዚሁ ውሳኔ ተቀጽላ ምክንያት የነበረው ደግሞ፤ /በኋላ በግልፅ እንደወጣው/ገና በረሃ ላይ እያሉ' ከዘጋሩት' ወንዝ መልስ ለኤርትራ የተሰጠው የኢሮብ መሬት የወደፊት ርክክብ የቀዳሚ ምዕራፍ ቅድመ- ዝግጀት የአፈፃፀም መርሃ-ግብር አካል ተደርጎ መወሰዱ ነው።

3. የኢሮብ ህዝብ "በግላጭ ተሽጠናል" የሚለው ጩኸቱን ቀጥሏል። እዚህ ላይ /የጠረፍ ስምምነቱ ሂደት በ1976 ዓም በሻዕቢው ስብሓት ኤፍሬምና በወያኔው ስብሓት ነጋ ስለመደረጉ አቶ ገብሩ አስራት በመፅሃፉ ላይ በቁጭት አስፍሮታል/)

4. የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መብት፤ ይህ መብት በየትኛውም የሃገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ ዋነኛ ምሶሶ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የመንግስታት ትክክለኛ የዲሞክራሲያዊነት መገለጫ ጭምር ተደርጎ ይወሰዳል። ኢሮቦች ዘንድ ግን የሚታሰብ አልሆነም። ህዝቡ በሰይፍትነት ተጠቃሏል። ኢሮብና መሰረተ-ልማት አይተዋወቁም። ከዛላንበሳ ወደ ዓሊተና በ1965 ዓም በብፁዕ አባታችን /በወቅቱ አባ ዮሐንስ /ብርታት በልዑል ራስ መንገሻ ስዩም የተዘረጋው መንገድ /12 ኪ/ ሜትሩ ብቻ የኢሮብ ምድር ውስጥ የተካተተ/ያለምንም እድሳት እስከዛረ ያኔ በተሰራበት ደረጃ ቀርቷል። ሕዝቡ ብሶቱን ቢያሰማም ሰሚ አላገኘም። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ አብነት ላንሳ፤ ይህ ሁሉ የህዝባቸውን ብሶት በርቀት የሚከታተሉት አቡነ ዮሐንስ ዝም ማለት አልቻሉም። ይልቁንስ ቀጠሮ በማስያዝ ወደ የወቅቱ ጠቅላይ/ሚ መለስ ዜናዊ ቀረቡ። ሁሌም በሚታወቁበት እጅግ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ አነጋገራቸውን "መለስ ወደይ!" ይሉታል "መለስ ወደይ ምነው የኢሮብን ሕዝብ ረሳችሁት?" ይሉታል። "እርሱም "የኢሮብ ሰዎችን እኮ አናገኛቸውም እኛን አይቀርቡንም፤ አሁን እርስዎ አንድ ሰው ቢጠቁሙኝ አሁኑኑ ወደ ወረዳ እልከዋለሁ"፤ በማያያዝም እርስዎ ግን ሮም የጵጵስና መዓረግ ሲቀቡ/ሲቀበሉ፤ ከመንስግስትዎ ሰዎች ተወካይ መጥራት እንደሚፈቀድ ሲነገርዎ፤ የለም እነሱን ሰዎች መጥራት አልፈልግም" ያሉት ለምንድነው? ይሏቸዋል። ይህን ጉዳይ ያነሱበት ምክንያት ሁለቱ የተገናኙት ጵጵስናውን ከተቀበሉ ከትንሽ ጊዜያት በኋላ ስለነበር ይህን ስለማድረግዎ መረጃ ደርሶኛል ለማለት ነበር። በርግጥ ብፁዕነታቸው በቃል እንዳጫወቱኝ ከሆነ እሳቸው ያቀረቡት ጥያቄ የውክልና ሳይሆን የልማት ነበር። ያም ሆነ ይህ ግን ያቀረቡት ጥያቄና የተሰጣቸው መልስ ግን ለየቅል ሆነ። ብፁእ አባታችን ደግሞ ጭራሽ ሌላ "ቅያሜ ፈጥሬ" እንዳልሆን በሚል ስጋት ቢሮውን ለቀው ወጡ።

በዚህ ክፍል አንድ በኢሮብ ህዝብና በያኔው ተሓህት በኋላ ህወሓት የነበረው መሰረታዊ ተቃርኖ ምን እንደነበረ፤ ይህን ተቃርኖ ለመፍታት ህወሓት የተከተለው አካሄድ፤ ከ1970 እስከ 1987 የኢሮብ ህዝብ ከየት ወዴት እንደተጓዘ እጅግ ባጭሩ ለውይይት መንደርደሪያነት ቀርቧል። 

በክፍል ሁለት ህወሓት የኢሮብ ህዝብ ኢሮባዊ ማንነት በአስሚለሽ ለማጥፋት የዘየደው ሴራ በተለይ የካቶሊክ ቤተክርስትያንን ከኢሮባዊ መዋቅ ለማወጣት እንደሰራ ለማቅረብ ይሞከራል። 

ዮሴፍ አዳዩ  

ያልተፈለገው የኢሮብ ህዝብ ሕልውናና ረጅሙ ተቃኖ!!

ክፍል ሁለት፤

ኢሮባዊ ማንነት ለማጥፋት በህወሓት የተሸረቡ ሴራዎች፣


ከዮሴፍ አዳዩ                                                                              ሕዳር 2014 ዓ/ም

ሀ) ከአሃዳአዊ ስርዓተ መንግስት ወደ ፈደራላዊ ስርዓተ መንግስት የተደረገው ሽግግር፣

1987 የትግራይ ክልላዊ መንግስት በውል ተቋቁሞ፣ አዲሱ ከታች ወደላይ (Bottom up) የሀገረ መንግስት (ፈደራል መንግስት) ግንባታ ጅማሮ ተጧጡፏል። "በቀድሞዎቹ መንግስታት የተሞከረውና ኢትዮጲያ የተሰፋችበት የሀገረ-መንግስት ግንባታ ያልተሳካው ትክክለኛ አወቃቀርና አካሄዱን ስለሳተ ነው"። በመሆኑም አዲሱ ጅማሮ እንከንየለሽ አማራጭ መሆኑ ሳይሆን"ብቸኛ/Exclusive/ መንገድ" እንደሆነ በመስራቾቹ ታምኖበት ሕገመንግስታዊ ቁመናውንም ተጎናጽፎዋል። ቀጣይ ሀገሪቱ (ኢትዮጵያ) ደግሞ በሕዝቦች የከታች ወደላይ፤ እንዲሁም ወደጎን በሚጎለብተው የብሄር ብሄረሰቦች ፍላጎትና መፈቃቀድ መሰረት በአዲስ መልክ ይገነባል ተባለ። በዚሁ አወቃቀርና የአካሄድ አፈፃፀም ላይ እንከን ቢፈጠር፣ በተለይም የብሄረሰቦች ሆነ የሕዝቦች መብት መሸራረፍ ቢኖር፤ ውጤቱ መበታተን ብቻ ይሆናል ተባለ። ባጭሩ የሀገራችን ብሔሮችና ህዝቦች በማንም በምንም የማይገሰስ የበላይ ስልጣን ባለቤት ሆነዋል ተባለ። ከዚህ በኋላ ሌሎችን በተለይም ትንንሽ ብሄረሰቦችን በማስገደድ በማዋሀድ፣ በማጠቃለል፤ ወይም በመዋጥ ዘዴዎች የሚደረግ የአንድ አገር (ኢትዮጵያ) ግንባታ የሚታሰብ አይሆንም ተባለ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ ወደ የኢሮብ አናሳ ብሄረሰብ ጉዳይ ስንመለስ ገና ከጅምሩ በሁለት ተቃርኖዎች (ተፃራሪ ፍላጎቶች) መካከል እየተሰነቀረ መሄዱን በተግባር እናያለን። ይኸውም በአንድ በኩል የኢሮብ ህዝብ ለዘመናት የገነባው የፀና የራስ ማንነት ምስል፣ የራስ ማንነት ሥነ-ልቦና መኖሩና በዚሁ ማንነቱና ሥነ-ልቦና የመቀጠል ተፈጥሯዊ መብት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዚሁ ሕዝብ መብት ሆነ ፍላጎት በግዙፉ የትግራዋይነት ፍላጎት መዋቅር ውስጥ assimilate ተደርጎ  ከጨዋታ ውጭ የማድረግ ፍላጎት ገና ከጅምሩ በግልፅ መታየት ተጀመረ። በርግጥ እነዚህ ተቃራኒ ዝንባሌዎች በየትኛው ሀገርና የተለያየ ማንነት ባለው ህዝብ መካከል የነበሩና የማይቀሩ እንደሆኑ ይታወቃል። ይህ ክስተትም በኢሮብ ህዝብና በጎረቤቶቹ ህዝቦች መካከል በተለያየ ጊዜ እንደተከሰተ ታሪክ ይነግረናል።  የኢሮብ ህዝብ ታሪካዊ መዋዕል እንደሚያሳየን ህዝቡ ራሱን ከሌላው (ከተጋሩ፣ እንደሱ የሳሆ ቋንቋ ከሚናገሩ ሳሆ) ለይቶ የሚያይበት የራሱ መዋቅራዊ ድንበር ያለው ሕዝብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለትግራይም ብሎም ለኢትዮጵያ አንድነትና ግንባታም ከፈተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተም ታሪክ አስቀምጦታል። ሌላ ዛሬ በተለያየ መንገድ የኢሮብ ህዝብ ከተጋሩ ጋራ አንድ እንደሆነ ሊነገር ቢሞከርም፣ በርግጥ አንዳንድ የሚያገናኙትና የሚያመሳስሉት ነገሮች ቢኖሩም የተለየ ማንነቱ ገላጭ የሆነ የራሱ ታሪክ፣ መልክዓ- ምድር፤ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሥነ-ልቦናና ትውፊት፣ ባለቤት መሆኑ ነው። ስለሆነም ከዚህ ራሱን ከጎረቤቶቹ የሚለይባቸው የራሱ የሆነ የተለየ የፖለቲካ አደረጃጀት፣ አወቃቀር፣ ሥነ-ልቦና፣ ባህልና፣ አስተዳደራዊ መዋቅር ያለው መሆኑ ነው።

 ለማብራራት ያህል የኢሮብ ሕዝብ የራሱ"መዋቅራዊ ድርጊት" ያለው አንድ "መዋቅር" ነው ስንል ምን ማለት እንደሆነ ለአብነት 'መኪና' እንውሰድ!! መኪና/ከሞተር፤ ከካምቢዮ ጎማ ፤ መብራትና. . . ወዘተ.  ከሌሎችም የተለያዩ ክፍሎች ተገጣጥሞ የተሰራ 'መዋቅር' ሲሆን መዋቅሩ ደግሞ እነዚህ የተለያዩ አካላት በመግባባት እና በመቀናጀት በሚፈጥሩት እንቅስቃሴ "ድርጊት" ይሆናል። ለመዋቅሩ ሆነ ለመዋቅራዊ ድርጊቱ ቀጣይነት ደግሞ የመዋቅራዊ አካላቱ ጤንነትና ጥበቃ ያስፈልጋል። ይሁንና መዋቅሩን ከገነቡ ወይንም መዋቅራዊ ማንነቱን ከፈጠሩት የተለያዩ ክፍሎች አንዱ ከተበላሸ ወይንም ያለቦታው ከተገጠመ ግን መዋቅራዊ ድርጊቱ እየደከመ ስለሚሄድ ዋናው መዋቅር ቀስበቀስ እየከሰመ ይፈርሳል።


ለ) ለኢሮብ ህዝብ እንደ ጋሻ ስትታይ የነበረች የካቶሊክ ቤተክርስትያን ከህዝቡ ለመነጠል የተሰራው ደባ፣

ወደ ዋናው ርእሰ ጉዳያችን የኢሮብ ህዝብ አንድ መዋቅር ነው ወደሚለው ስንመለስ፤ ሁሉም እንደሚያውቀው የካቶሊክ ቤተክርስትያን በኢሮብ 'መዋቅር' እና መዋቅራዊ ድርጊት ውስጥ ያላት ከፍተኛ ድርሻ መመልከት/ማወቅ ተገቢ ነው:: ከዚህም በመነሳት የካቶሊክ ቤተክርስትያንን "እንደየወቅቱ ሁኔታ" እና "የየጊዜያቱ " አጀንዳ አመቺነት ጋር በመቀያየር የኢሮብ ህዝብ መዋቅርን ለማዳከም ዓላማ ለመጠቀም የተደረገውን የተለያየ  ሴራና እንቅስቃሴ ልብ ብሎ መመርመርና ማጥናት ተገቢ ነው። እንደሚታወቀው  ቤተክርስትያንዋ በሃይማኖታዊ ስራዎች ብቻ ሳይሆን፤ የኢሮብ ህዝብ የኢኮኖሚያዊ ኑሮ መሰረትና የክፉ ቀን መተማመኛ ምሰሶ ሁና በአከባቢው ያከናወነችው የመሰረተ ልማት፣ ትምህርት፣ ማስፋፋት፤ የመንገድና ውኃ ስራ ቀላል አይደለም:: ባለፉት 27 ዓመታት የኢህአዴግ አስተዳደር በኢሮብ ቤተክርስትያኗና መንግስት ያከናወኑዋቸው  የመሰረተ ልማት ሥራዎች ሲነፃፀሩ ተቋሟ የሰራችው መንግስት ከሰራው በብዙ እጥፍ ይበልጣል።  በመሆኑም ህዝቡ ለመንግስት ከሚሰጠው ቱክረትና አክብሮት ይልቅ ለቤተክርስቲያንዋ የሚሰጠው ትኩረትና ክብር በግልጽ የሚታይ ነው። በመሆኑም "ጠላትን በራሱ ከዘራ" እንዲሉ ይህንን ሚናዋን በማዳከም፣ ብሎም በማስቀረት ከህዝቡ በመነጠል ህዝቡ ላይ ጫና ማሳደር እንደሚቻል ታውቆ ለዚህ እቅድ ወጥቶለት ገና በትግራይ ህወሓት በብቸኝነት የመንግስት ሥልጣን እንደያዘ የሴራው እንቅስቃሴ ተጀመረ። ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል፣

 

ሐ) ኢሮባዊ ማንነትን አዳክሞ ከተጋሩ ጋራ አሲሚለት (Assimilate) ለማድረግ የተሰራው ሴራ፣

 ሌላው ኢሮባዊ ማንነት ለማዳከምና ብሎም ለማጥፋት ህወሓት ከ1970ዎቹ እስከ ዛሬ ኢሮባዊ ማንነትን ለማዳከም ብሎም ለማጥፋት ከተጠቀመባቸው ዘዴዎች ቀጥለው የተዘረዘሩት ዋናዎቹ ናቸው።


 ክፍል ሶስት፣ የኢሮብ ህዝብን ህልውና የናደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትና ውጤቱ በሚል ርእስ ይቀጥላል፣


ዮሴፍ አዳዩ   

ያልተፈለገው የኢሮብ ህዝብ ሕልውናና ረጅሙ ተቃኖ!!

ክፍል ሶስት፤  

የኢሮብን ሕዝብ ህልውና የናደው የኢትዮ የኤርትራ ጦርነትና ውጤቱ፤  


ከዮሴፍ አዳዩ                                                                              ሕዳር 2014 ዓ/ም

ሀ) የ1990 ዓ.ም. የኢሮብ ሕዝብ ወገብ የሰበረው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት፣


 መ ግ ቢ ያ፣

የኢሮብ ህዝብ በታሪኩ በድንበሩ ጉዳይ ላይ ድርድር አያውቅም። በአጎራባች ሕዝቦች የተወሰደበት ጭራፍ መሬት እንደሌለ ታሪክ ይመሰክራል። ዒንደሊ፣ ዳይሲዓለ፣ ዛጋብላ፣ ማይጭዓ-አራሞ፣ አራዕ-ዳራ፣ ማድዓ-ሰበያ ምስክር ናቸው። በህዝቡ ዘንድ የኢሮብ ይዞታ የሆነው መሬት በኤርትራ የባለቤትነት ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል የሚል ሕልምም ግምትም አልነበረም። ምክንያቱም ሕዝቡ ታሪኩን መሬቱንና ድንበሩን ጠንቅቆ ስለሚያውቅና በየትኛውም ታሪካዊ አጋጣሚ ወደ ኤርትራ የተካለለበት ወይንም በኤርትራ የአስተዳደራዊ ማዕቀፍ ውስጥ የገባበት መሬትም ታሪክም አልነበረም፣ የለምም።

ሻዕቢያ በወቅቱ በድንበር አከባቢ ሲያደርገው የነበረ ዝግጅት በግልፅ የሚታይ ስለነበረ፣ ባንፃሩ በኢትዮጵያ በኩል በክልልም ሆነ በፈዴራል መንግሥት በኩል ምንም የሚታይ ዝግጅት ስላነበረ በሻዕቢያ በኩል ለሚፈፀምበት ጥቃት ራሱ ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለበት የኢሮብ ህዝብ አውቆ በሻዕቢያ የደረሰበትን ጥቃት በራሱ አቅም ለመጋፈጥና ወራሪውን ኃይል በብቸኝነት ለመመከት ወሰነ። ወራሪውን ኃይል ለመጋፈጥ በላቀ ወኔና ቁጭትም ተረባረበ።

የኢሮብ ህዝብ ከራሱ ውጭ በተለይ ከመንግስት በኩል አስፈላጊ ጥበቃ እንደማይደረግለት፣ መንግስት ከህዝቡ ፍላጎት ውጭ እየሄደ መሆኑ የሚያሳዩ ገና ከጅምሩ ብዙ ምልክቶች ነበሩ። ለምሳሌ፣ ቀደም ሲል የወረዳው ዋና ከተማ ከታሪካዊቷ ዓሊተና ወደ ዳው-ሓን ተሻግሯል። ይህ ደግሞ ገና ቀድሞ ከዘጋሩት ወንዝ መልስ ወደ ሰሜን ያለው የኢሮብ መሬት በሚመለከት ጥልቅ ስጋት እንዲያሳድር አድርታል። ይህ ስጋት የተፈጠረው፣ አንደኛ፣ ዳው-ሓን በምንም መለኪያ ለከተማነት አመቺ አይደለችም። ይህን ለመረዳት  የተለየ ሞያ አያስፈልግም። ሁለተኛ፣ ዳው-ሓን ከዘጋሩት ወንዝ ማዶ ወደ ደቡብ የወንዙ አፋፍ ላይ የምትገኝ ትንሽ መንደር ናት። ስለዚህ ዋናው ጉዳይ የዋና ከተማ ቦታውን ከዘጋሩት ወንዝ የማሻገር ተልዕኮ ካልሆነ በስተቀር ዳው-ሓንን ለኢሮብ ወረዳ ዋና ከተማነት መወሰን ብቻ ሳይሆን ማሰብ በራሱ እጅግ ብቻ ሳይሆን ከእጅግም በላይ ከባድ ነበር። ሶስተኛ፣ ዓሊተና ማለት ነባር የኢሮብ ዋና ከተማ ሁና የኖረችና፣ ለወደፊትም ለከተማነት በቀላሉ የመስፋፋት አንፃራዊ አመቺነት ያላት፣ የህዝቡ ታሪካዊ መሠረትና የማንነት የግንባታ አካል አንደሆነች ይታወቃል።

በመሆኑም ዓሊተናን ወደ ዳው-ሓን ማዛወር በሕዝቡ ላይ ጥልቅ ቁጣ፣ የሞራል ውድቀትና አሉታዊ ስሜት ያሳደረ ውሳኔ ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ በልመና የተገኘ በርካታ ሚሊዮን የውጭ እርዳታ ብር ፈሶበት በመገንባት ላይ የነበረው የዓሳ-ቦል ግድብ ቀጣይ ልማት በዋናነት ያተኮረው በዳው-ሓን መንደር በነበሩት ትናንሽ ማሳዎች የአትክልት ልማት ሲሆን ይህም ከጥቅም ውጭ ሆኗል፣ የዓሳ-ቦል ግድብ ላይ የሆነ አደጋ ቢደርስ ወይም በሆነ አጋጣሚ ቢደረመስ ዳው-ሓን ያለ ምንም ጥርጥር በግድቡ ውሃ ተጠራርጋ ጠፊ ስለመሆኗ የተለየ የዘርፉ ሞያተኛ መሆን አያስፈልግም፣ ከከተማዋ ወደ ምስራቅ ኪትራ፣ አሳ-ዓለይታ እልም ያለ ገደል ነው። ወደ ደቡብ፣ ያሆ-ዳጋ፣ አዎ፣ የባሰበት ተንሸራታች ተራራማ መሬት እንዲሁም ወደ ምዕራብ ዓሳ-ቦል፣ ኪን-ኪንታይ ጭራሽ የማይታሰብ ተራራና ገደል ነው። ባጭሩ ዳው-ሓንን ወደ የትኛው አቅጣጫ ማስፋት ወይንም የመንገድ መተላለፊያ (access) ይሰራ ቢባል በምንም ዓይነት ቴክኖሎጂ ይሁን በሌላ የሚታሰብ አይሆንም።

ይህ በውል የተገነዘቡ አዋቂ ኢሮቦች ገና ስትፈጠር 'ግራ' የሆነች ከተማ በማለት" በሕይወት ዘመናቸው " ላይረግጧት እርም" ብለው ራሳቸውን በቃለ ማህላ ገዝተው፣ በዚሁ ቃላቸው ፀንተው ያለፉ የኢሮብ ታዋቂ ወላጆች አንደነበሩ ይታወቃል። ለምሳሌ፣ ያባ ሓጎስ ጊደይ (ዳያ)" አጉላዕ ባሊህ ሓበ'ኒህ አካዲህ ጉራል ራዕታ ካታማ" ብለው ሲሉ ቀላል አባባል አልነበረም። ይህን ሲሉ በርግጠኛነት ይቺን ከተማ በመኸል ሰንጥቆ ወደየትኛውም አቅጣጫ የሚተላለፍ መንገድ እንደማይኖር በወቅቱ ተረድቷል።

ይህ ሁሉ ተደማምሮ ባለበት ሁኔታ የተደረገው ዓሊተናን ወደ ዳው-ሓን የማዛወር ውሳኔ ታዲያ ህዝቡን ምናልባትም "ከዘጋሩት" መልስ ወደ ሰሜን ያለው የኢሮብ መሬትና ህዝብ ለኤርትራ "ተሽጧል" ወይም"ሆን ተብሎ ለመስጠት" ከወዲሁ የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ነው፣ የሚል ከባድ ስጋትና ጥርጣሬ ውስጥ ከቶታል። ለውሳኔው በተደረጉ የይስሙላ ህዝባዊ ውይይቶችም "ተሽጠናል"/ኒተ'በሒን/ የሚል ግልፅ አቋም ተንፀባርቋል። ይህን አቋም በድፍረት በማቅረባቸው ለእስር የተዳረጉ አባቶቻችም እንደነበሩ ይታወቃል። በመሆኑም ህዝቡ፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ውሎ አድሮ አንድ ቀን፣ "የድንበር"ጉዳይ እንደሚቀሰቀስ የራሱ ግምት ነበረው ማለት ይቻላል።

 

ለ) የ1990 ግንቦት 23 የውግያ ውሎ፣

የኢትዮ -ኤርትራ ጦርነት በ1990 ዓ.ም ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ተጀመረ፣ እንደ በደንበር ነዋሪም የኢሮብ ህዝብ ግንባር ቀደም የጦርነቱ ሰለባ ሆነ። እንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ከጦርነቱ በፊት በተፈጥሮና በዋናነት በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት እየተዳከመ በመሄድ ላይ የነበረ የብሄረ-ሰቡ ህልውና ልክ እሳት ላይ ቤንዚን የመጨመር ያህል ተቀጣጥለው የኢሮብ አናሳ ብሄረ-ሰብ ህልውና አደጋ በግልፅ መከሰት ጀመረ ማለት ይቻላል።

እንደሚታወቀው የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በባድመ በኩል የተጀመረው ግንቦት መባቻ ላይ ሆኖ በኢሮብ ግንባር የተጀመረው ግን ግንቦት 22 ወደ 23 አጥቢያ ወደ 20 ቀን ያህል ዘግይቶ ስለነበረ በመንግስት በኩል ቀድሞ ቢታሰብበት በድንበሩ በቂ ዝግጅትና ሰራዊት ለማስቀመጥ ጊዜ ነበር። ሆንም ግን ከተወሰኑ ከምስራቃዊ ዞባ የዞባ ፀጥታ ሃላፊዎች በአብዛኛው ከሓውዜን የተውጣጡ የተወስኑ የምልሺያ አባላት ወደ አከባቢው ከመላክ ውጭ ሌላ ሃይል ስላልነበረ በወቅቱ የነበረው ውሱን ሚሊሻና የኢሮብ ህዝብ ድንበሩን መጠበቅ የሱ እዳ መሆኑ ተገንዝቦ ነበርና የኢሮብ ሚልሻና ከዞባ የመጡት ውሱን ሚልሻ በመቀናጀት ቦታ ቦታቸውን ይዘው መጠባበቅ ጀመሩ። የቦታ አያያዙ ይህን ይመስል ነበር። ይኸውም በአብዛኛው የመካከለኛ ርቀት ውስን መሳሪያ የያዙ አባላት ያካካተተ ቡድን ዓይጋ ከካቶሊክ ቤ/ያን በላይ ዳ'ት-ቦል ጀርባውን ይዟል። ሁለተኛውና ተመሳሳይ ስኳድ ደግሞ ' ሳራ - '-ጉምበ ወገቡ ላይ መሽጓል፣ ሶሰተኛው ደግሞ ያባ ደስታ ዓዶዑማር ዲክ ወደ ዘገብላ ተዳፋት ላይ በመመሸግ ምዕራቡን/በመነኽሰይቶ አቅጣጫ ያለውን የጠላትን እንቅስቃሴ ይከታተላል። ሌላውና አብዛኛው ኃይል ደግሞ ዋንካቦ፣ ሳካራ፣ አቡርታ፣ ሙጉላይ አስከ ማካታ ያለውን ገዢ መሬት በመያዝ በመጠባበቅ ላይ ነበር።

ግንቦት 22,1990 ቅዳሜ በተለይም ከቀኑ 9/10 ሰዓታት በኋላ የጠላት እንቅስቃሴ በግልጽ እየታየ ነበር። የጠላት ሰራዊት በሶስት አቅጣጫ ማለትም በምዕራብ (በመነኽሰይቶ)፣ በሰሜን ምዕራብ (በነድወ) እና በሰሜን " ከሽመዛና እስከ አረሞ"፣ እንዲሁም ወደ 'ማከታ' ኩታ ገጠም አከባቢ ካሉት የኤርትራ የገጠር ቀበሌዎች መጠጋት ጀምሯል። በሁሉም አቅጣጫ የሚታየው ሃይል እጅግ ግዙፍና በከባድ መሳሪያዎች የተደገፈ ነበር። ይህ ግዙፍ ኃይል ደግሞ ሌሊቱን ሙሉ ሲጠጋ አድሯል። ከቅዳሜ 22 ለእሁድ አጥቢያ ሌሊቱን ከሁሉም መስመር ሲጠጋ ያደረው የኤርትራ ሰራዊት ግንቦት 23 1990 እሁድ ከጥዋቱ አስራ አንድ ሰዓት ላይ ማጥቃት ጀመረ። ጥቃቱ የተሰነዘረው በሁሉም ግንባሮች በተመሳሳይ ሰዓት ላይ ሲሆን ከዓይጋ /ሳራ-ጉምበ እስከ 'ማካታ' ጫፍ እንደ ሰንሰለት በታያያዙ የኢሮብ ገዢ ተራሮች ላይ የመሸገው የወገን ምልሻ ሰራዊት በሁሉም ግንባር ጠላትን ገትሮ ያዘ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አንድ ያልተጠበቀ አጋጣሚ ተፈጠረ። ይኸውም ከዓዲግራት ለድጋፍ የተላከው የሚልሺያ ኃይል ውጊያው እየበረታ ሲሄድ ሳይታሰብ ተመድቦበት የነበረው ከሳካራ እስከ ኣቡርታ ያለው ቦታ ወጣ። ይህ ድንገት ያፈገፈገው ኃይል ይዞት የመጣው 'ማርሶ'የሚባል ታጋይ ሲሆን፣ ይዞት የመጣው ኃይል ቢያፈገፍግም እሱ የኢሮብ ህዝብ ጥዬ አልሄድም በማለት ቀርቶ ሓይዲለ በሚባል ቁሸት በተደረው ውጊያ ተሰዋ።

ይህ ኃይል የለቀቀው ሳካራና ዋንካቦ ፈፅሞ መለቀቅ ያልነበረበት ቁልፍ ቦታ ስለነበረ የተለቀቀውን ቦታ ለመሙላት 'ማካታ'አከባቢ የነበረው ሰራዊት ወደኋላ በመሳብ አዲስ ሽግሽግ አሰፈላጊ ሆነ። ስለሆነም ወደጎን የሚሳበው ኃይል ተኵስ ሳያቋርጥ' ከአቡርታ' ወደ 'ሳካራ'ቀጥሎም ወደ 'ዋንካቦ' በመጠጋጋት የተለቀቀው መስመር እንዲሞላ ተደረገ። ምክንያቱም ከ 'ነዱወ' በኩል የገባው የጠላት ኃይል 'ዋንካቦን' ከቆረጠ የኢሮብ ሰራዊት ሁለት ላይ ስለሚከፈል አደገኛ ይሆናል። በመሆኑም ማካታ ክፍት ቀረ፣ በዚሁ አቅጣጫ የገባው የጠላት ኃይል አጋጣሚውን በመጠቀም ከስር ራሱን ከእይታ ውጭ በማድረግ ከማካታ-ሒዶ - ሓይዲለ - ቀጥሎም 'ሱሓለ' ዳገቱን በማሳበር 'ጊዕዶ' 'ካፍና' ላይ በቀኝ ጀርባውን ይዞ ገባ። ይህ ማለት ሳካራና ዋንንካቦ የነበረው የኢሮብ ሰራዊት በሁለቱ የኤርትራ ኃይል ከፊትና ጀርባ ሳንዱች ይሆናል። ዋናው ጉዳይ ግን መቁረጥ አይችልም። መስመሩን ይዞ በጋራሳና ሐምቦ-ካለ በኩል በቀላሉ ወደ ዓይጋ መጠጋት ይችል ነበር። ይሁን እንጂ የዋን-ካቦና የሳካራ ኃይል ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ወደ ፅራዕ ተራራ፣ ተሻግሮ ጋራሳ፣ ዓባበና ቀጥሎም ከበሮይታ ወደ ጋላላዕ የሚባሉ የተያያዙ ጋራዎች ይዞታውን በማስፋት መሽሎኪያ መስመሩን በማጥበብ ገትሮ ያዘ። ይህ ሲሆን የዓይጋና ሳራ-ጉምበ ጀግኖች በቦታቸው አሉ፣ በመዋደቅ ላይ ናቸው።

ምናልባት አካባቢውን ለማታውቁ የተሻለ ስዕል ለማግኘት እንዲረዳ ግምባሩን እና በወቅቱ የነበረው አሰላለፍ ዘርዘረ አድርጎ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል። በመሆኑም፣ ማካታ ማለት የኢሮብ የሰሜናዊ የኤርትራ ኩታገጠም ጣቢያ ስትሆን የውጊያውን እንቅስቃሴ በዓይነ - ህሊናቹህ ለማየት ያህል ከግምባሩ የሰሜን ጫፍ/ማካታ/ የደቡብ ጫፍ ደግሞ ዓይጋ በማድረግ ከዓይጋ እስከ ማካታ ቀጥታ መስመር፣ ከግራ ወደ ቀኝ ወደ ጎን በማስመር፣ በአራቱም አቅጣጫ፣ /ሰሜን ፣ ደቡብ ፣ ምዕራብና ምስራቅ/ በመመላለስ ተከታተሉ። ከዓይጋ ቀጥሎ ዋን-ካቦ ~> ሳካራ ~> አቡርታ ~>ሙጉላይ --------> ማካታ ድረስ ቀጥ ያሉ የሰንሰለታማ ተራሮች መሰመር ሆኖ በግምት ሙጉላይ አካባቢ ደግሞ የሁለቱ ጫፍ አማካይ/የመኻል ቦታ ይሆናል። ይህ ጠቅለል ብሎ የኢሮብ ህዝባዊ ሰራዊት/ምልሻ የግምባር አሰላለፍ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት ዓይጋ ሶስት ስትራቴጂካዊ ቦታዎች ላይ የተሰየመው ሰራዊታችን ምድብተኛ ክንፍ ከመነኽሰይቶ የተጠጋውን የጠላት ኃይል የመመከት ሃላፊነት ወስዷል። የዋን-ካቦና የሳካራ ደግሞ ከነዱወ በኩል፣ ለሚመጣው፣ የአቡርታና መጉላይ ደግሞ ከማይጭዓና አረሞ በኩል፣ እንዲህ እያለ እስከ ማካታ ጫፍ ድረስ ደርሷል። በዚህም መሰረት በየምድብ ቦታዎቹ ላይ የመሸገው የወገን ኃይል የየራሱ ተጓዳኝና ትይዩ የኤርትራ ኃይል የመመከት ተልዕኮ ነበረበት።

ያም ሆኖ በውጊያው መኻል በነበረው የቦታ ሽግሽግ ወይም ለውጥ ከደቡብ ወደ ሰሜን ቀጥሎ ላለው ተነሺ ኃይል ለምሳሌ ለአቡርታው የሳካራ፣ ለሳካራው ደግሞ የዋን-ካቦ፣ ለዋን-ካቦ ደግሞ የዓይጋ ሽፋን እየሰጠ፣ ቀጣይ ቦታ የማስያዝ ተጨማሪ ግዳጅ ተሸከመ። ይህም ማለት እያንዳንዱ ምድብ ወደ ሁለቱም አቅጣጫ ይዋጋል ማለት ሲሆን፣ አንድ፣ ወደ ራሱ ምሽግ ከተጠጋው ኃይል ጋር፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የመጀመሪያውን ምሽግ ለቆ የቦታ ለውጥ ለሚያደርገው የወገን ኃይል ሽፋን ይሰጣል ማለት ነው። እንዲህ እንዲህ እያለ ሁሉም መስመሩን ያዘ። ከዚህ በኋላ እንግዲህ በየትኛውም አቅጣጫ የተደረገው የኤርትራ ሰራዊት ሙከራ ፍፁም ሊሳካለት አልቻለም። በምንም መለኪያ ቦታውን የሚለቅ የለም። የመጣው ኃይል ከየትኛውም አቅጣጫ ቢሞክር ክፍተት አጣ። ጊዜ በሄደ ቁጥር የያዘው የሰው ኃይል ከመመናመን ወውጭ መፍትሔ አልነበረውም። እጅግ ከፍተኛ ኪሳራ ደረሰበት።

 በታጠቀው ሚልሻ ሰራዊት የነበረው አሰላለፍና ውጊያ ከላይ እንደተቀመጠው ሆኖ ጠቅላላ የኢሮብ ህዝብ ሽማግሌ፣ ህፃን፣ ወንድ፣ ሴት ሳይል ቀፎው እንደ ተነካ ንብ ባንድነት በውጊያው ያደረገው ተሳትፎም እጅግ የላቀ ነበር። ምክንያቱም ሕዝቡ ለድንበሩ/ለመሬቱ በራሱ ከመዋደቅ ውጭ ሌላ አማራጭ የለኝም የሚል የስነ-ልቦና ዝግጅት ነበረው። ሌላ ደግሞ "(ላብሃ ኢሲ- 'ባዶል ባሶካህ ራብታ) ወይም ቀድመህ ለድንበርህ በመውደቅ አርአያ መሆን አለብህ"የሚል የቆየ የኢሮቦች ብሂል አለ።

ስለሆነም ሕዝቡ ከሰራዊቱ ጋር ሙሉ በሙሉ ተሰይሟል። ዓቅም ኖሮት ቤት የዋለ ኢሮብ እንዳልነበር በተደጋጋሚ ተዘግቧል። ከዓይጋ ወደ ደቡብ አቅጣጫ የሚገኘው ነዋሪ በሙሉ ዕድሜና ፃታ ሳይለይ ገና በጥዋቱ ዓይጋ ግምባር ገብቷል። የመሳሪያ መጋዘን ለሕዝቡ ክፍት ተደርጓል። አብዛኛው ወጣት ልምድ የሌለውም ጭምር መሳሪያ ከመጋዘን እያነሳ በመውሰድ ሌላው ደግሞ፧ ምሽጉን ለቆ ከሚሄደውና በየመንገዱ በመንጠባጠብ ላይ ከነበረው "የሐውዜን" ምልሺያ መሳሪያ በመቀበል፣ ውጊያውን ለመካፈል ከሚልሻው ጎን ቦታ ቦታውን ይዟል። ሂደቱ በዚህ ብቻ አያበቃም። እናቶች፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ትንሽ ትልቅ ሳይባል ወደ ግንባር ከትሟል። ህዝቡ ከአራዕ ጫፍ፣ ሳብዓታ፣ ማጋዑማ፣ ዳግዓ ከሌሎችም ሳይቀር ሌሊቱን እየተጓዘ በማደር ከሰራዊቱ ጋር ተሰልፏል። ያለ ማንም ምንም ግፊት ሁሉም የየራሱን የሃላፊነት ድርሻ ወስዷል። አናቶች እንደ ዝናብ የሚፈሰው የጥይትና የመሳሪያ እሩምታ ሳይበግራቸው ውኃ፣ ወተት ፣ ምግብ፣ በጀበና ቡና ጭምር እያቀረቡ ሱሰኞችን በማጠጣት ተዓምር በመስራት ላይ ናቸው። በዕድሜ የገፉ አባቶችና ታዳጊዎች ደግሞ የወደቁትን የማንሳትና ጥይት የመሙላት የሃላፊነት ድርሻ ተያይዟል። ወጣት ጎረምሶች ከዕለቱ በፊት ምንም ዓይነት የመሳሪያ ልምድ ወይም እውቀት ያልነበራቸው ጭምር እርስበረስና ከሌላ በመማር ማቀባበልና መተኰስ ጀምሯል። ፍፁም ዕረፍት የሚባል ነገር የለም። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ጉዳዩን በማዕከል የሚያስተባብር አልያም የሚከታተል ሙያተኛ የአመራር ዕዝ ወይም የስምሪት አካል አልነበረም።

ግንቦት 23 ዕለተሰንበት 1990 ዓ.ም. የተወስኑ ሚሊሻዎችን በማስቀደም የኢሮብ ህዝብ እንደ አንድ በመሆን ዘመናዊ መሳሪያ እስከ አፍንጫው ከታጠቀው የኤርትራ ወራሪ ሰራዊት ጋር በመዋጋት ከጥዋቱ የእሁድ አጥቢያ አስራ አንድ ሰዓት አስከ ቀኑ (እሁድ) አስራ አንድ ሰዓት የጠላትን ኃይል ገትሮ ዋለ። ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት አከባቢ አንዲት የኢ/ያ የኮማንዶ ሻለቃ በመድረስ በውጊያው ላይ ተካፍላለች። (ሻለቃ ከ500-600 የሰው ኃይል ትይዛለች) ሻለቃዋ ' በኦራል' ወታደራዊ መኪና በመጓጓዝ የመጣች ሲሆን ፣ፈጣን እንቅስቃሴ አድርጋለች። ወደ ኢሮብ እንደ ደረሰች የተወሰነውን ኃይል'ማሳኑ' ላይ ካራገፈች በኋላ ከቀኑ አስር ሰዓት አከባቢ ዓሊተና ገባች። ማሳኑ የቀረው ኃይል ቀጥታ በሳራ-ጉምበ ተራራውን ይዞ ወደ ዓይጋ ወጣ። ቀሪው ደግሞ ከዓሊተና እሰከ ጋራን-ጎይራ በመኪናው ተጓዘ። ይሁንና ከጋራን-ጎይራ በኋላ ሁለት'ክንፍ' በመሆን አንዱ በአር-ጉሎ፣ ዳት-ቦል ስሩን ይዞ በጎዳፊ-ዳጋ፣ ወደ ጋራሳ ሲጓዝ ሁለተኛው ደግሞ ቀጥታ ወደ ዓይጋ ወጣ። በርግጥ ይቺ ሻለቃ ቀኑን ሙሉ ደክሞ ለዋለው ሰራዊትና ህዝብ ተጨማሪ ሞራል ገነባች። ቀድሞውኑ ተዳክሞ የዋለው የኤርትራ ኃይል ግን ምቱን መቋቋም ባለመቻሉ ማምሻውን ወደኋላ ፈረጠጠ። ከሻለቃዋ ጋር በአዲስ መልክ የተቀናጀው የኢሮብ ሚሊሻ ሰራዊትና ህዝብ ደግሞ እየተከታተለ እስከ ጫፍ የኤርትራር ሰራዊትን በማባረር ድንበሩን ለመከላከያ አስረከበ። ከላይ አንደተገለፀው በኤርትራ በኩል የደረሰው ኪሳራ እጅግ ከፍተኛ ነበር። በዕለቱ ውሎና ኪሳራ የተማረረው የኤረትራ መንግስት ደግሞ ዕለቷን "ፀላም ሰንበት"(ጥቁር ሰንበት) በማለት የራሱ ስያሜ ሰጣት። የሚገርመው ግን በኤ/ትራ በኩል ስለደረሰው ኪሳራ መጠን የተያዘ ሁነኛ መረጃ ያለመገኘቱ ነው። በርግጥ በማግስቱ ዓይጋ አከባቢ የወደቁትን ለመቅበር ነዋሪው ሰፊ ጥረት አድርጓል።

በዚሁ ሰንበት ውጊያ ስድስት የኢሮብ የሚልሺያ አባላት /ፍሱሕ መድህን፣ አብርሃ ገብራይ፣ ሃይሉ ሐጎስ፣ ካሕሳይ ሃይሉ፣ ዮሓንስ ወልዱ/ሃምበዳ/ (ከቀናት በፊት ዓይጋ ላይ አንደሚሰዋ በራሱ የተነበየና፣ "ጠላት እየተጠጋህ ስለሆነ ቦታህን ልቀቅ" ሲባል "ዓይጋኮ አውላል አዳዎ"፧ "ከዓይጋ ወዴት ነው የምለቀው ? በማለት ጥዋት መትረየሱን ተክሎ የመሸገበት ቦታ ሳይለቅ ውሎ ወደ ማታ ላይ የተሰዋ ጀግና።) ወ/ገርጊስ አማረ ጥዋት ከማካታ ጀምሮ አመራር ሲሰጥና ሲዋጋ የዋለ፣ ቀኗም የሕይወቱ መጨረሻ እንደሆነች በመናገር ተግባራዊ ያደረገ የመሳሰሉ ጀግኖች ክቡርና በታሪካዊነቱ ወደር የሌለው መስዋዕትነት ከፍሏል። ሌላው ደግሞ ዳት-ቦል ከጎብታው ላይ መትረየስ (ብሬን) ተክሎ ጥዋት የተሰየመበት ቦታ ሳይለቅ የዋለና ሁሉምንም ሰው ያስደመመ አለማ በየነ፣ አንዱ ሲሆን፣ ይህ ወጣት ገና ከልጅነት ሻዕቢያ ውሰጥ ያደገ ነው። በወቅቱ ከምንም ሳይሆን ቤተሰቡ ዘንድ በሰላም ይኖር ነበር። ያም ሆኖ ግን በዕለቱ ተካፋይ በመሆን፣ ሌላው ቀርቶ ራሳቸው የሻዕቢያ ተዋጊዎች በስም ባያውቁትም ቀደም ሲል እነሱ ውስጥ የቆየ ሰው እንደሆነ በአተኳኰሱ ብቻ በመለየት እነሱ ጭምር አንደተደነቁበት የሚነገርለት ወጣት። ሌላው ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት የበርሀ ተስፋይ (ማጋዑማ)" ሒያው ኒም-ማኪክ ዮያ አድ-ኦሳይ ሳባዓየ"በሚል ታሪካዊ ንግግሩ የሚታወስ። ጉዳዩ እንዲህ ነው። የሻዕቢያ ሰራዊት እስከ ሳራ-ጉምበ ወገብ ድረስ ተስቦ ተጠጎቶ አድሯል። ጥዋት ሊነጋጋ ሲል ከኢሮብ ሰራዊት ጋር በቅርብ ርቀት ተያዩ። በመቀጠል "እኛ ወገን በመሆናችን እንዳትተኲሱብን አሉ" ሻዕቢያዎቹ። በርግጥ ሻዕቢያዎቹ በአለባበስ ተመሳስለዋል። በዚህ ድርጊት ጥርጣሬ ውስጥ የገባው በርሀ ታዲያ፣ በግንባር ለማረጋገጥ ሰዎቹ እስከነበሩበት ቦታ ወረደ። ሲደርስ ግን ያጋጠመው ሌላ ኃይል (የኤርትራ) ነበር። ከዚሁ በመነሳት ነበር፣ "እኔን ጨምራችሁ ምቱ ያለው ይህ ጀግና። በተባለው መሰረት ተግባራዊ ቢሆንም እሱ ግን በሕይወት አመለጠ። እዚህ ላይ እጅግ ጥቂቶችን እንደአብነት ለማንሳት እንጂ በዕለቱ ውሎ ከአንዱ ሌላውን መለየትና ማበላለጥ በፍጹም አይቻልም። ባጭሩ የአጠቃላይ የኢሮብ ሕዝብ ታሪካዊ ተግባር እና ፍፃሜ የታየበት ታሪካዊ ቀን ነበር። በስፋትና በጥልቀት መጠናት ይኖርበታል። በየትኛውም አከባቢ መሰል ታሪካዊ ክስተት ስለመደረጉ ወይም ስለማለፉ እጅግ አጠራጣሪ ቢሆንም፣ ወይንም የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ምንም ዓይነት መረጃ ባይኖረውም በተለይም ከወቅቱ የኢሮብ ህዝብ ቁመናና አቅም አንፃር ሲለካ ግን ይህን ማድረግ ቀርቶ የሚታሰብም እንዳልነበረ በልበ-ሙሉነት መናገር ይቻላል ።

ለምሳሌ ሩቅ ሳንሄድ በወቅቱ መሰል ችግር ያጋጠማቸው የክልሉ የጠረፍ አከባቢ /የባድመ፣ ዛላንበሳ ወዘተ ታጣቂዎችና ነዋሪዎች ስንመለከት፣ ገና ለገና ወራሪው ሃይል እየተጠጋ በነበረበት ሁኔታ ጊዜ ሳይሰጡ አከባቢያቸውን ለቀው መውጣታቸው ይታወቃል። ይህን ሃቅ ለማስረገጥ ከብዙ በጥቂቱ አንድ አብነት ማንሳት ይቻላል። ወረራውን ተከትሎ የባድመና አከባቢው ሚልሺያና ነዋሪዎች ወደ ሽራሮ ተፈናቅለዋል። ጀነራል ሳሞራ የኑስ ደግሞ ቦታዎቹን ለቆ የተፈናቀለውን ህዝብና ሚልሺያ'ውን በማሰባሰብ በተለይ ሚልሺውን ኃይል ከመከላከያ ኃይሉ ተቀናጅቶ ወደአካባቢው ተመልሶ የኤርትራውን ሰራዊት እንዲከላከል ቀሰቀሱ። ይሁንና ተቀባይነት አላገኙም፣ ወይም ፈቃደኛ አልተገኘም በዚሁ ያልተደሰቱት ጀነራሉ ታዲያ እንደአብነት ያነሱት የኢሮብን ሕዝብ ነበር። እንዲህ በማለት። "በዚሁ በሰሜን ምስራቅ ትግራይ ውስጥ ኢሮብ የሚባል አንድ መጠኑ እጅግ አነስተኛ የሆነ ህዝብ አለ። ያ ህዝብ በራሱ ተነሳሽነት የኤርትራ ሰራዊት ጋር ተዋግቶ ድንበሩን ለኢ/ያ መከላከያ ሰራዊት አስረክቧል። እናንተ ግን "ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን "ድንበራችሁን ተከላከሉ" ስትባሉ ፈቃደኛ የማትሆኑበት ምክንያት ምንድነው? በማለት እንደ ወቀሷቸው ተዘግቧል። የኢሮብ ህዝብ ይህን ውሳኔ የወሰነው ያለ ምክንያት አልነበረም። አንደኛ፣ ህዝቡ በገዛ ቀዬው ላይ ከመዋደቅ ውጭ ሌላ አማራጭ የለምኝም በማለት የስነ-ልቦና ዝግጅት አድርጓል። ሁለተኛ፣ "በገዛ መሬትህ ላይ (ላብሃ ኢሲ'ባዶል ባሶካህ ኤልራብታ) ቀድመህ በመውደቅ አርአያ መሆን አለብህ"የሚል የቆየ የኢሮቦች ብሂል አለ። ሶስተኛው ፣ ከላይ በተወሰነ ደረጃ እንደተገለጸው ከራሴ ውጭ "የሚደርስልኝ የመንግስት ኃይል የለም" የሚል ድምዳሜ ላይ ያደረሱት ወደፊት በስፋት የምዘረዝራቸው የቆዩ ስጋቶች ነበሩት።

በመጨረሻም፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲወሳ፣ በተለይም ከኢሮብ ህዝብ አኳያ አንድ መረሳት የሌለበት ልዩ ታሪክ አለ። ይኸውም "የዕጡቓት ሰንበት" የሚል ስያሜ የተሰጠው ወታደራዊ ኦፐረሽን ሲሆን፣ትርጉሙ ደግሞ "የሰንበት ታጣቂዎች" በኦፐረሽኑ ወይም በዕለቱ ውጊያ ላይ ያደረጉትን ተሳትፎ ለመዘከር ከጊዜ በኋላ የተሰጠው "የአድናቆት" ስያሜ የህዝባችን ገድል በአግባቡ ለመንተንተን በዘርፉ የተካነ (በወታደራዊ ዘርፍ) ሙያዊ ድጋፍ አስፈላጊ ይሆናል። የሆነ መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮ አልያም የተለየ ጥረትና ጊዜ ተወስዶ "ሂደቱ" በፊልም፣ ካልሆነ ደግሞ "በዶኩመንታሪ" መልክ በደምብ ቢዘገብ እጅግ መልካም ነበርና ሁሉም ቢያስብበት እላለሁ። የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ የኢትዮ-ኤርትራ የ1990 ጦርነት ላይ የኢሮብ ህዝብ ተሳትፎ ሂደቱን በተጣራና የተሟላ ስዕል በሚሰጥ መልኩ ቀርቧል የሚል እምነት ፈፅሞ የለዉም። ስለሆነም ሁሉ የሚያውቀው በፅሁፍም፣ በቪዲዮም. . . የሚያውቀውን አቅርቦ ቀጣይ ጥልቅ ምርምርና ጥናት አስፈላጊ ይሆናል እላለሁ። አንድ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ ቢኖር ግን ማንኛውም ኢሮብ በተለይም ዓቅሙ ያለው ይህን ግምባር በአካል ለመጎብኘት ማቀድ ይኖርበታል። ነገሩ ቀላል ሲሆን አንዲት የቱሪዝም ባይኖኩላር (ወታደራዊ መነፅር) በመያዝ/በመከራየት ዓይጋ/ዳት-ቦል/ጀርባ ላይ ሁኖ አጠቃላይ ግምባር እና የዕለቱ የሁለትዮሽ አሰላለፍ ወለል ብሎ ይታየዋል። ዋናው ሰላም ይሁን። ሌላውና የመሰረታዊው ሁላችን ልንስማማበት የሚገባው ጉዳይ የኢሮብ ህዝብ ታሪክ ግንባታ የጠቅላላው የማሕበረሰቡ የጋራ ድምር የድርጊት ውጤት መሆኑን ነው ። የኢሮብ ታሪክ እንደ አብዛኞቹ የሀገራችን ታሪኮች በታዋቂ ግለስብዕና ወይም መሪዎች ላይ መንጠልጠል አይችልም። "ናኑ ኡግትነክ ኡጉታየ ጉማ" እየተባለ በሕብረት እንቅስቃሴ ነው፣ የተገነባው። ኢሮቦች ዘንድ "ሁሉም እኩል ነው፣ አንዳንዶቹ ግን ይበልጥ እኩል ናቸው "የሚል የታዋቂው የጆርጅ ኦርወል (George Orwell) አባባል ቦታ የለዉም። ባጭሩ የኢሮቦች ታሪክ የጋራ ነው። ዋናው ግን ሕዝቡ ይኑር።

 

ዮሴፍ አዳዩ         

ያልተፈለገው የኢሮብ ህዝብ ሕልውናና ረጅሙ ተቃርኖ!!

ክፍል አራት፣

የኢሮብ ህዝብ በኤርትራ ወረራ ስር ቆይታ፣ (1990-1992 ዓ/ም)


ከዮሴፍ አዳዩ                                                                              መጋቢት 2014 ዓ/ም

በክፍል ሶስት በዝርዝር እንደተገለፀው በዕለተ ሰንበት (ግንቦት 23 ቀን) በተደረገው የመከላከል ቀጥሎም የማጥቃት እርምጃ የኤርትራው ኃይል ከኢሮብ መሬት ተጠራርጎ ወጣ ። ይሁንና በዚሁ ውጊያ ሽንፈትና ሃፍረት የተከናነበው የኤርትራ ኃይል ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ፣ በሶስተኛው ቀን ግንቦት 26/27 1990 ዓ ም ዳግም ወረራ አካሄደ ። ከጀርባ በከፍተኛ የሜካናይዝድ ኃይል ታግዞ ብዙ ሺ ሰራዊት በማሰለፍ በሰነዘረው የማጥቃት እርምጃ ዓይጋን ጨምሮ ሙሉ አድጋዲ-ዓረ በቁጥጥር ሥር አደረገ ። ከቀናት በፊት ለእርዳታ የመጣችው ሻለቃ፣ የኢሮብ ሚልሻና መላው የኢሮብ ህዝብ በጋራ የተወሰነ የመከላከል ሙከራ ቢያደርጉም በመኻሉ ግን የዛላንበሳ ከተማ በቁጥጥር ሥር ገብታ ዋናው መሰመር በመቆረጡ ሻለቃዋ በፍጥነት ወደ ዓዲግራት አፈገፈገች። የኢሮብ ሕዝብና ወደ 50 የሚሆኑ ሚሊሻ ሰራዊት ደግሞ ከዚህ በላይ በከባድ መሳርያ የታገዘውን ብዙ ሺ የኤርትራ መደበኛ ሰራዊት ለብቻቸው መጋፈጥ አልቻሉም። ስለሆነም የኤርትራ ሰራዊት በዋናነት 'ዓይጋን' የአንድ ግዙፍ መካናይዝድ ኃይል ማዕከል በማድረግ አቅሙን አደላደለ። (ዓይጋ ማለት ለሁለቱም ወገን እጅግ አመቺነት የነበረው ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው ። ለኢትዮጵያ ሰራዊት የዓይጋ በቁጥጥር ሥር መዋል ከባድ ቁጭት ነበር ። በመጨሻው የ1992ቱ ጦርነትም ከባድ ዋጋ እንዳስከፈለ በስፋት ተተንትኗል ። (በጌታቸው ሃይሉ የዋልታ ጋዜጠኛ ከግምባር እየተዘጋጀ ፣ በዓለምነህ ዋሴ በቲቪ ሲቀርብ የነበረውና ዓይጋ "የተራሮች ንጉስ" እየተባለ የተሞገሰበት ረጂም ዘገባ ልብ ይለዋል።)

የኤርትራ ሰራዊት የዓይጋ ተራራን ከተቆጣጠረ በኋላ ይዞታውን በማስፋት መላው አድጋዲ ዓረና እስከ ዓሊተና ከተማ ያለውን የቡክናይቲ ዓረ ክፍል በቁጥጥር ሥር አስገባ፣ በተቆጣጠራቸው አከባቢዎችም ሕዝቡን ያለ ርህራሄ ማንገላታትና ማዋከብ ጀመረ። በመሆኑም ገና ከወዲሁ የጭካኔ አካሄዱ ያልጣማቸውና ቀጣዩም የባሰ ይሆናል የሚል ስጋት ያደረባቸው ነዋሪዎች ጊዜ ሳይወስዱ ወደ የኢሮብ ወረዳ አንዱ አካል የሆነው ሓሳባላ በብዛት መሸሽ ጀመሩ። የመጣውን መከራ እንሸከማለን እንጂ ቤት ንብረታችንን ለማን ጥለን እንሄዳለን ያሉት ግን በየቤታቸው ቀሩ ። ቤታችንና ንብረታችን ለቀን አንሸሽም ያሉ ነዋሪዎችም ያለ ርህራሄ ተደበደቡ፣ አከባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ተገደዱ ፣ ቋሚም ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውም  እንዳለ ተዘረፈ፣ ልክ ሰራዊቱ አከባቢውን እንደተቆጣጠረ በርካታ የቤት እንስሳት( ከብት ፍየል፣ ዶሮ) ከየነዋሪ ቤት እየተነጠቁ ወደ ኤርትራ ተጋዙ፣ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ከየበረቱ ተመርጠው እየታረዱ በቦታው የሰፈረ ሰራዊት ቀለብ ሆኑ።

የኤርትራ ሰራዊት አከባቢውን ተቆጣጥሮ በአከባቢው መስፈር እንደጀመረም በርካታ ሴቶች ተደፈሩ፣ በርካቶች በተለያየ ምክንያት መታሰርና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መፈታት የዕለት ተዕለት ክንውን ሆነ፣ ይህ በእንዲህ እያለም ከ1990-1992 መጀመሪያ አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ 97 ንጹሃን አርሶ አደሮች በኤርትራ ስራዊት ተወስደው የኸው እስከ ዛሬ ደብዛቸው እንደጠፋ፣ ይኑሩ ይገደሉ ሳይታውቅ 22 ዓመት አልፎአቸዋል።

የኤርትራ ሰራዊት 3/4ኛውን የኢሮብ ወረዳ (ኣድጋዲ ዓረና ቡክናይቲ ዓረ) እንደተቆጣጠረ፣ በቡክናይቲ ዓረ ቤታችን ለቀን አንሰደደም ያሉትን ከአከባቢው እንዲነሱ በማስገደድ ወደ መኻል ኣድጋዲ ዓረ ተወሰዱ ። አቅመ-ቢስ ወላጆችና በሽተኞች በቃሬዛ ሲጓጓዙ፣ ካህናት አባቶችና ደናግል ወደየአቅጣጫው ሕዝቡን ተከትለው ተበተኑ ። ቤተ-እምነቶች ባዶ ቀሩ ፣ተመዝብረው የሰራዊት መኝታ ሆኑ ። ከዓሊቴና ማሪያም ቤተ/ያን በስተቀር ሳይመዘበር የቀረ አልነበረም ።

በሁለቱም አቅጣጫ (በአድጋዲ ዓረም፣ ሓሳባላም) የነበረ ወንድም ሕዝብ የቡክናይቲ ዓረ ተፈናቃዮችን የመሸከም ሃላፊነት ወሰደ፣  ወደ ደቡብ አቅጣጫ ሸሽተው የተሻገሩት፣ በሳብዓታ፣ አራዕ ፣ ሓራደ፣ አራዕሮ ወዘተ ከተሙ፣ ወደ ሰሜን አቅጣጫ የተወሰዱት ደግሞ በአድጋዲ ዓረ (ማይጺዓና አከባቢው እንዲሰባሰቡ ተደርጎ  መካከለኛው የኢሮብ ክፍል (ቡክናይቲ ዓረ) ሙሉ በሙሉ ከነዋሪው ነፃ ሁኖ የኤርትራው ሰራዊት ሰፈር ሆነ። 

በዚህ መፈናቀል ህዝቡ እግር ወደመራው ወደ ተለያየ አቅጣጫ በመሸሽ አንድ ቤተሰብ ሁለት ሶስት ላይ በመከፋፈል ተለያይቶ መኖር ጀመረ ፣ የአድጋዲ ዓረና ሓሳባላ ነዋሪዎች ከቡክናይቲ ዓረ የተፈናቀሉትን ተቀብሎ ማስተናገድ የግድ ስለነበረ በሁሉም ተቀባይ አከባቢዎች ቤቶች በተፈናቃዮች ተጣበቡ። በየቤቱ መካተት ያልቻሉት ተፈናቃይ ወገኖች በየዋሻውና በየዛፉ ሥር መኖር ጀመሩ። ይሁንና አስተናጋጅ አከባቢዎች ወንድም እንግዶችን የተንከባከቡት በላቀ ሃልዮትና ደግነት ነበር።  ለራሳቸው ውጭ ወጥተው ለእንግዶቹ ቤት የለቀቁ ጭምር እንደነበሩ በስፋት ይነገራል። ተፈናቃዮቹ አንድ ቤት ለመግባት አንፃራዊ የስጋ ዝምድና አልያም ቅርበት አያስፈልግም፣ ቦታ እስኪሞላ ቀድሞ የደረሰ ገብቶ ተስተናገደ ።

እዛው ኢሮብ ወረዳ ከአንዱ አከባቢ ወደ ሌላው የነበረው መፈናቀለ እንዳለ ሆኖ ሌላውና ፈታኝ የነበረው የመፈናቀል ገፅታ ደግሞ ወደ ከተሞች የተደረገው በተለይ የወጣቶች መፈናቀል ነበር ። በርካታ ወጣቶች (ወንድም ሴትም) ወደ ተለያዩ ከተሞች ተፈናቀሉ። እነዚህ ወጣቶች ሁሉም በየፊናው በማደር ከወላጅ ቁጥጥር ውጭ ሆኑ፣ በየግልና በጋራ ቤት በመከራየት ከወላጅ ቁጥጥር ውጭ መኖር ጀመሩ፣ በዚህ አኗኗርም በሕዝቡ ታሪካዊ መዋዕል ያልተለመዱ አጉል መጥፎ ልምዶችና ሱሶች መላመድ ጀመሩ፣ ቀድሞም ቢሆን በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ ለነበረው የኢሮብ ህዝብ ይህ መፈናቀል ቤንዚን ላይ እሳት የመጨመር ያህል ሆኖ የኢሮብ አናሳ ብሄረሰብ ህልውና የከፋ ጥግ እየያዘ መጣ፣ በዚህ መልክም ሕዝቡ ከሁለት ዓመታት በላይ በከባድ ስቃይና እንግልት ሥር ኖረ።

የ1992 ዓ/ም የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት

በ1992 አጋማሽ አከባቢ ሁለቱ ሀገራት ለወሳኙና የመጨረሻው ጦርነት ተፋጠጡ ። ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በየግንባሩ የመስክ ጉብኝት አድርገው ነበር። ማዕቢኖ ላይ በርካታ ከባድ መሳሪያዎች ተጠምደው የነበሩ ሲሆን ፣ ብዛት ያላው እግረኛ ሰራዊትም ዙሪያውን መሽጓል። በኔ ግምት ጠ/ሚንስቲሩ በዋናነት ይህን ሰራዊት መጎብኘት ይኖርባቸዋል፣ አልያም ፕሮግራም ይዟል። የኢሮብ ተፈናቃዮች ዋነኛ ማዕከል የነበረውና ኣራዕሮ የሚባለው ቦታ ደግሞ በማዕቢኖ የቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል። በመሆኑም እግረ - መንገዳቸውን ህዝቡን አነጋግረው ነበር። የንግግራቸው አንኳር መልእክት ደግሞ ኢትዮጵያ ባላሰበችውና በማትፈልገው ጦርነት ውስጥ በግዴታ ስለመግባቷና የምታካሄደው ጦርነት ደግሞ ፍትሃዊ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአሸናፊነት ትወጣዋለች የሚል እንደነበር ይነገራል ። እጅግ የሚገርመው ግን ከህዝቡ ያገኙት መልስ በትንሹም ቢሆን እሳቸው ከጠበቁት ወጣ ያለ መሆኑ ነው። ለጠቅላይ ሚንስትሩ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በአቦይ ግደይ ተስፉ ጊቢዳዎ በኩል የተሰነዘረው አስተያየት ግን ለየት ያለ ይዘት ነበረው። እኛ እንደማንኛውም የጠረፍ ሕዝብ! አሉ አቦይ ግደይ እኛ ቀድመን ተወረናል፣ ከቤት ንብረታችን ተፈናቅለናል፣ ከግማሽ በላይ ህዝባችን በሻዕቢያ ቁጥጥር ሥር ቀርቶብናል ። በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ ምንም መረጃ የለንም፣ ሌላውም በየቦታው ተበትኗል ፣ ሴቶቻችን እንደ እንስሳት በየዛፍ ሥርና ዋሻዎች ውስጥ ለመውለድ ተገዷል፣ ታማሚዎችም እንደዚሁ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አንድም ጊዜ የጠየቀን ሆነ ስማችን ያነሳ የለም።  ..በሁሉም መገናኛ ብዙሃን ባድመ ፣ ባድመ እና ሌላም ሲነሳ እንሰማለን። ስለኛ ግን የሚደመጥ ነገር የለም። ባጭሩ እኛን (ኢሮብን) የ "እላቂ ሳሙና" (ሒቃቅ ሳቡናት ኢዳ) ያህል የቆጠረን የለም። እኛኮ...ብለን ነው እንጂ ተመሳስለን መሞከርም አያቅተንም ። ከብዙ የአቦይ ጊደይ ንግግር እጅግ በማሳጠር የተወሰደ) ።።።። ይሁንና ከላይ እንደተገለጸው ጠ/ሚሩ የጠበቁት ምላሽ ወይንም አስተያየት አልነበረም ፣ አልያም በተለይም "ተመሳስለን መሞከር " የምትለዋ ሽሙጥ ብሂል አልጣማቸውም ይሆናል ። በመሆኑም ድሞፃቸውን ከረርና ጠበቅ በማድረግ "ህዝቢ ኢሮብ ኩሉ ጊዜ አይተሸፍጡና!"... ፣ ትርጉም ኢሮቦች ሁሌም በነገር አትጎንትሉን እናንተ ኮ! ... ካሉ በኋላ .."ለማንኛውም ወራሪውን ኃይል አባርረን መጪውን ፋሲካ በየቤታቹህ ታከብራላቹህ" በማለት ተሰናብው እንደሄዱ ይነገራል ።

በኔ እምነት ጠ/ሚ'ሩ እውነቱ ጠፍቶባቸው አይመስለኝም ። ይልቁንስ እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ቆንጠጥ ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ እጅግ የተካኑ ነበሩ ይባላል። በርግጥ በዚሁ ወቅት መንግስት ለመዋጋት የወሰነበት ወቅት ነበር ይባላል ። ምክንያቱም ህዝብም የጦርነት ጊዜ መራዘም በማየት፣ መንግሥት እየተለሳለሰ ነው በሚል ስጋት ግራ እየተጋባ ምነው ትዕግስትም ልክ አለው !" በማለት ግፊት ማሳደር ከጀመረ ውሎ አድሯል። እውነትም ለመራዘሙ ምክንያት የሆነው ድርጅቱ ውስጥ (ህወሓት ውስጥ) በጦርነቱ አስፈላጊነትና አላስፈላጊነት ዙሪያ በተነሳ ውዝግብ ነው የሚሉም አልጠፉም።  አላስፈላጊነቱን የሚገፉ ኃይሎች፣ አንደኛ ጦርነት ከጀመርን ልማትና እድገት በእጅጉ ይጎተታል፣ ሁለተኛ ገና በሁለት እግሩ ያልቆመውን ማዕከላዊ መንግስት ቀጣይነት ይፈታተናል። ለዚህም (ከአፄ ቴድሮስ ግትር አቋምና የመጨረሻ እጣፈንታ እንዲሁም፣ ከአፄ ምኒልክ ስልታዊ የውጫሌ ስምምነትና ብልጠት) በመማር አሁን ሻዕቢያ ጋር ከመዋጋት ይልቅ ከጦርነት በመለስ ያሉትን አማራጮች አሟጠን ማየት ይኖርብናል፣ ለዚህም ሻዕቢያ ከገባበት ምሽግ እንዳይወጣ በማድረግ የያዛቸው መንደሮችና ተራሮች ለዓመታትም ቢሆን ሻዕቢያ ቁጥጥር ሥር ቢቀጥሉ ጉዳት አያመጣም የሚል በአንድ ወገን፣ ሌላው ወገን ደግሞ ትላንት ከኢትዮጲያ የተነጠለች ኤርትራ በእብሪት ከወረረችው መሬታችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድትወጣ ሁለት ዓመት ተሞከረ፣ይህ ደግሞ አልተሳካም ። ኢትዮጲያ ደግሞ ሉዓላዊነቷን የማስከበር ያልተገደበ መብት አላት፣ ይህ ብቻ ሳይሆን የህዝቡም ግፊት ጫፍ ደርሷል፣ ህዝቡም በቂ መልስ ይፈልጋል። ደግሞስ ጉያችን ሥር እሳት አስቀምጠን ልማት እንዴትስ ይታሰባል? በማለት ሞገቱ ። ያም ሆነ ይህ ክርክሩ የወሰደውን ጊዜ ወስዶ በኢሕአዴግ ታሪክ ያልተለመደና አወዛጋቢ በተባለለት የድምፅ ልዩነት ሁለተኛው አቋም በማሸነፉ ወደ ጦርነት ተገባ ።

ጦርነቱ 1992 አጋማሽ በኋላ የተጀመረ ሲሆን፣ የሁለቱ ሀገራት የመጨረሻውና ወሳኙ ጦርነት ተደርጎ የኤርትራ ሰራዊት በኃይል ይዞት ከነበረው የኢትዮጵያ መሬት በአጭር ጊዜ ጦርነት ተጠራርጎ ወጣ ። በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ በወታደራዊ መስኩ በአጭር ጊዜ የኤርትራ ወራሪ ጦርን ከኢትዮጵያ መሬት ጠራርጋ በማስወጣት የኢትዮጵያ ሰራዊት ከየአቅጣጫው ወደ ኤርትራ ግዛት ገባ። ይህ በእንዲህ እያለ ግን ያኔ ጠቅላይ ሚንስተር የነበሩት አቶ መለስ ጦርነቱ እንዲቆም አዘዙ። በዚህ ጦርነት የኤርትራ ሰራዊት በርግጥ ከኢሮብ መሬት ተጠራርጎ ወጥቷል፣ ሆኖም ግን ከጦርነቱ በኋላ መምጣት የነበረበት ሰላምና መረጋጋት ለኢሮብ  አላረጋገጠም። ይልቁንም በህዝቡ ቀጣይ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ሕይወት ላይ "የበለጠ መርዘኛ" ሰንኮፎችን እያባባሰ ሄደ፣ በመንግስትና በህዝቡ መካከል የነበረው የሻከረ ግኑኝነት ይበልጥ እንዲሻክር ሆነ፣ በራሱ በህዝቡ ማካከል የነበረው ጥሩ ግንኙነት እንዲበላሽ አስደረገ። ይህን ትንሽ በዝርዝር እንመልከት ፣

ሀ) የህዝቡና የመንግሰት/አስተዳዳሪ ግጭት፤

በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ላይ የሕዝቡ በድል መሰባሰብና አንፃራዊ መረጋጋት ምክንያት በማድረግ ዳው-ሓን ላይ ትልቅ የተሃድሶ በዓል ተዘጋጀ። በዓሉ በሰፊ ዝግጅት የታጀበ ነበር። ዝነኛው የኢሮብ ጠጅ ተጥሎበታል። የክልሉ የመንግስትና የፓርቲው ባለስልጣናት ታድመውበት የሞቀና የደመቀ ቀን ዋለ፣ እንግዶችም በጨዋ ደምብና በሰላም ተሸኙ።  ከቀኑ የሽኝት ሂደተ በኋላ ወደ ማታ ላይ ግን ያልተጠበቀ አጋጣሚ ተፈጠረ። ኢሮብን ከትግሉ ማብቂያ ዓመታት ጀምሮ ሲያስተዳድር የነበረና በኋላም በወረዳ አስተዳዳሪነት የቀጠለው ታጋይ ገብረ ካሕሳይ ስልጣን ለቆ በወረዳው ተወላጆች ይተካ! በሚል መነሻ ከፍተኛ ረብሻ ተነሳ። በዓሉ ክፉኛ ተበጣብጦ በተኩስ ጭምር በመታጀቡ በቀላሉ የሚረጋጋ አልሆነም። ጎራ ለይተው የተነሱ የረብሻው ጠንሳሾች በቀላሉ የሚመለሱ አልሆኑም። በዚሁ ስጋት ውስጥ የገቡት እነ ገብረ ደግሞ ለደህንነታቸው ያመቻል በተባሉ ቤቶች ለመደበቅ ተገደዱ። በወቅቱ የምስራቅ ዞባ ዋና አስተዳዳሪና የዕለቱ ታዳሚ የነበሩት ወ/ሮ ትርፉ (የአቶ አባይ ወልዱ፣ ባለቤት) የመከላከያ ኃይል በመያዝ ሌሊቱን ወደ ዳው-ሓን ወረዱ። ከቦታው ደርሰው የነ'ገብረ'ን ደህንነት ከጠየቁ በኋላ ገብረን ይዘው ወደ ዓዲግራት ተመለሱ። በተለይ በረብሻው ግንባር ቀደም ከነበሩት ውስጥ አንዱ የሆነው መምህር ሥዩም ምስግና ወዲያው በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን ራሱ እንደነገረኝ ከሆነ ቀደም ሲል ወ/ሮ ትርፉ ዘንድ ቢሮ ድረስ በመሄድ ቀጣይ የገብረ ቆይታ አደገኛ እንደሚሆን በግልጽ ማስጠንቀቁን ይገልጻል። ይሁንና ተግባራዊ ምላሽ ሳያገኝ በእንጥልጥል ቆየ፣ ወይም አልተፈለገም ። በርግጥ አቶ ገብረ በጉርብትናም (ሰበያ) ሆነ በደም ትስስር ከኢሮብ የራቀ አይደለም። ይሁን እንጂ ህዝቡ ዘንድ በቂ ተቀባይነት ነበረው ለማለት ኣያስደፍርም። ለምሳሌ፣ ለመሸኛ ዝግጅት መዋጮ በተጠራው ስብሰባ ላይ አቶ አለማ ብስራት(ልጅ) በግልፅ አንደተናገሩት "እኛ ፊትም ቢሆን የሚያስተዳድረን አላጣንም፣ አፈር ያልነካው የምሁራን ልጆቻችን ለስላሳ እጆች አሉ፣ ይሁንና እሱ ከኛ ምን ሽኝት ያስፈልጋል? ይልቅስ ለበርካታ ዓመታት እሱን በመሸከማችን እኛን (ህዝቡን) አመስግኖ ወደሚሄድበት ይሂድ.." አሉ ይባላል። ገብረ ከወረዳው አስተዳዳሪነት እንዲነሳ በህዝቡ ከፍተኛ ግፊት ስለነበረ እሱን ከአከባቢው ገለል ማድረግ የግድ ስለነበረ ገብረ ተነሳ፣ ፍሱሕ ግደይ ወልዱ (ዳሮ) በቦተው ተተካ። በዚህም ህዝቡ በመንግሥት ጥርስ ገባ፣ በርግጥ ገብረ በቀጥታ እንደ ድሮው የወረዳው አስተዳዳሪ ባይሆንም በተዘዋዋሪም ቢሆን ከኢሮብ ወረዳ አስተዳዳሪነት እጁን ስላላወጣ ችግሩ ቀጠለ።

ለ) የመልሶ ማቋቋሚያ ብር አከፋፈልና በህዝቡ መካከል የተወው መጥፎ ጠባሳ፤

(1.1) ጦርነቱ ተጠናቆ ህዝቡ ወደ ቦታው የተመለሰው በታላቅ ሞራልና ደስታ ነበር ። ይሁን እንጂ ከሁለት ዓመታት በላይ ፣ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ የቆየው ህዝብ አጠቃላይ ኑሮ ወደ መደበኛ ሂደት መመለሰ ቀላል አልነበረም ። ቤት ንብረት ተዘርፏል ፣ ቤቶች ፈራርሰዋል ፣ ወድመዋል ወይም ባዶ ናቸው፣ ወጣቱ ኃይል ቦታውን ለቆ ውጭ መኖርን ተላምዷል ። እንዲህ ነገሮች በተወሳሰቡበት ወቅት ነበር የመልሶ ማቋቋሚያ ብር በእርዳታ መልክ የተገኘው ። ይህ ገንዘብ በጦርነቱ ተጎጂ ለነበሩት የጠረፍ አከባቢዎች መልሶ ማቋቋሚያ እንዲሆን ከዓለም ባንክ በእርዳታ መልክ የተገኘ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ ። ስለመጠኑ ይሁን ስለየአካባቢው ድርሻ ግን የተገለፀ ነገር የለም ወይንም የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ መረጃ የለዉም። ያም ሆነ ይህ የኢሮብ ድርሻ የተባለው ዳውሃን ለወረዳው አስተዳደር ተላከ ። ይህ ብር በወረራው ሁለቱ ዓመታት በኤረትራ ሰራዊት ሥር ለነበሩትና ከሰራዊቱ ሸሽተው ለተፈናቀሉት ማለትም "ቀጥተኛ ተጎጂ"ነበሩ ለተባሉት ብቻ እንዲሆን ተወሰነ ። ይህም ማለት በወረራው ወቅት ተፈናቃዩን ህዝብ ተሸክመው የነበሩት የኢሮብ ቀበሌዎችን (ሓሳባላ) አያካትትም ማለት ነው ። ይሁን እንጂ በአግባቡ ተጠንቶ ቢሆን እነዚህ አከባቢዎች ውኃ ፣ እንጨት እፀዋት ብክነት፣ መኝታ ወዘተ (ላየ'ይታህ ፣ ቦሖ'ይታህ ፣ ኑዋይቲህ ፣ ዲንቲማህ ፣ ኢቦል ኣይዳሃይ) እውነትም የደረሰባቸው ጉዳት ከተፈናቀሉቱ የተናነሰ አልነበረም ። በመሆኑም የደረሰብን ጉዳት ተረስቶ እርዳታ ላይ ሲደርስ እንዴት ተገፋን በሚል ከፋቸው ። በዚህም የተነሳ የዓሊቴና ቀብር ላይ ላለመገኘት እስከመወሰን የሚደርስ ቅሬታ ተክሎ እንዳለፈ እስካሁን በቁጭት የሚያነሱ እንዳሉ ይወሳል ።

(1.2) ገንዘቡ በተከፋፈለበት አከባቢም ቢሆን ከላይኛው የባሰ ልዩነትና የእርስበርሰ ቁርሾ ተክሎ ያለፈ ሆነ ። ምክንያቱም የአሰጣጡ ሂደት ተጠንቶ "ከባድ"፣ "ቀላል" መካከለኛ" በሚል ተለይቶ በጦርነቱ ቤት ለፈረሰባቸው ቤት ግንባታ እንዲውል ነበር ። በአሰጣጡ ሂደት ግን የተሳካና በጥናት ላይ ተመስርቶ ተግባር ላይ የዋለ አልነበረም። ይልቁንም ጉልበትና ወገን" ያላቸው ብቻ እንዲቀራመቱት ሆነ ። አንድ አብነት ላንሳ ፣ አባትና ልጅ የሚኖሩት በአንድ መንደር ነው ። ልጁ ባለትዳር ሲሆን፣ አባትም በተመሳሳይ የየራሳቸው ኑሮ ይኖራሉ። በጊዜው ወደ አንድ ቦታ ነበር የተፈናቀሉት። በደረሰባቸው ቁሳዊ ጉዳት አይበላለጡም፣ እንዲያውም አባት በዱላ ተደብድበው ነበር በሽማግሌ ዓቅማቸው ። በእርዳታው ወቅት ግን ልጅየው በ'ከባድ ጉዳት' ምድብ ተመድቦ ብር 15,000 ሲያገኝ አባትየው ግን በ "መካከለኛ " ምድብ ተመድበው ብር 7000 አገኙ ። እውነትም ከዚህ ስንነሳ የክፍፍሉን ኢ-ፍትሓዊ አፈፃፀም ግልፅ ነበር ለማለት ያስደፍራል ። እንዲያውም ልጁ እንደነገረኝ ከሆነ አባቱ ይህንንም ማግኘት የቻሉት በራሱ በልጅየው ሰፊ ጥረትና ሩጫ እንደነበር ነው ። ጉዳዩ የከነከናቸው ሌላ የኢሮብ አባት ታዲያ እንዲህ በማለት እንዳቀነቀኑ/ዓዳር እንዳደረጉ ይነገራል ።

"ሚሚ~ሒዳሮይ ዓንጊ ጊደ ፣

ሲ-ነ አክ-ሃይሲተኒህ ከቢዲደ ፣

ሲ-ኒ-ኣቦብቲ አክሃየኒህ ማእከላደ፣

ዮከ ሓሊማ ካዶሊህ ኒኒ~ቦ'ሎደ።" የኒህ ዓዳረን።

ትርጉም ምናልባት የኚህን አባት አይዲዮማቲክ ብሂል በትክክል ያስተላልፍ እንደሆነ እርግጠኛ ባልሆንም ፣ ከሞላጎደል ግን ፣ ምምሕዳር የወረዳው አስተዳዳሪዎች ስያሜ ሲሆን ፣ "እናንተ ራሳችሁን "በከባድ"፣ አባቶቻችሁን "ማእከላዊ" ፣ በመመደብ ያለአግባብ የተጠቀማቹህ አስተዳዳሪዎች፣ የጠላት ድርሻ(ጊደ) ሁኑ በማለት ከተራገሙ በኋላ ፣ ያው ወገንና ጉልበት የሌለን "እኔና ሓሊማ" ግን እነደድሮአችን ገደል ዋሻ ውስጥ ቀርተናል በማለት የነበረው ኢፍትሐዊነት የገለፁበት አባባል ነበር ። ሓሊማ ማግኘት የነበረባት ነገር ግን ወገን ወይም አቅም ስላልነበራት ባዶ የቀረችው ሙስሊም ነዋሪ ነበረች። እንዲያውም አንዳንዶቹ በጦርነቱ ምክንያት የፈረሰባቸው ለማስመሰል ቤታቸውን ሌሊት በማፍረስ ተጠቃሚ የሆኑ ብልጣብልጦች እንደነበነበሩ ታውቋል። ዞሮ ዞሮ ይኸ ሁሉ በጥቅሉ ሲመዘን ግን በወቅቱ የነበረውን ኢ- ፍትሓዊነትና በዚህም ዘርቶት ያለፈውን ቅያሜና የእርስ በርስ በቀል ፍንትው አድርጎ ያሳያል ። ወይም ይህ የእርዳታ ገንዘብና የአሰጣጡ ሂደት በሁሉም የኢሮብ ህዝብ (በዘገነውም ፣ ባልዘገነውም) ጥሎት ያለፈው ቁርሾ ቀላል አለመሆኑ ነው ። ይህ ደግሞ " ይህ ሆን ተብሎ የታቀደና ሁሌም ገና በትግል ሜዳ እያሉ የጀመሩት የተለመደ ስልታዊ ህዝብን የመለያየት ፓሊሲ ኣካል ነው ።" በማለት ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የተጠቀሙት ኃይሎች እንደነበሩ የሚያወሱም አልጠፉም።

ያልተጠበቀው የአልጀርሱ ስምምነት

ይህ ስምምነት በዚህ ፍጥነትና መልክ ፍፁም የተጠበቀ አልነበረም ። ስለሆነም ህዝብን በእጅጉ ከማስደንገጡም በላይ የከፋ ሥጋት ወስጥ ከተተው። ምክንያቱም ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ የነበረው የህዝቡ እምነትና ተስፋ ሌላ ነበር። በጦርነቱ የተከፈለው ሕይወትና ንብረት እጅግ ከፍተኛ ነው፣ በዋናነት ደግሞ በኃይል ተይዞ የነበረው መሬታችን ክቡር የሆነ የመቶሺዎች ደምና አጥንት ተከፍሎበት ወደነበረበት ተመልሷል የሚል የሁሉም እምነት ነበር። በመሆኑም ሻዕቢያ ከዚህ በኋላ የሥጋት ምንጭ አይሆንም። ህዝቡ ዘንድ ላለፉት ዓመታት ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረውና ዋነኛ የስጋት ምንጭ ሆኖ የቆየው የድንበር ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሰተማማኝ መቋጫ አግኝቷል የሚል ነበር የህዝቡ ተስፋና እምነት። ከዚህ ወዲያ ኢትዮጲያን ለአዲስ ድርድር የሚዳርጋት አስገዳጅ ሁኔታ አይኖርም፣ ድርድር ቢኖር አንኳን የደረሰውን የጦርነት ኪሳራና ተያያዥ ካሳ የሚመለከት ብቻ ይሆናል፣ ስለሆነም የኢሮብ ህዝብ ጦርነቱን "ኡምነህ ኢጊድ መዕነ" ወይም ክፋት የወለደው መልካም አጋጣሚ፣ በማለት ተረጋግቶ ነበር። ይህ በእንዲህ አንዳለ ግን ከህዝቡ ምኞትና እምነት ወጣ ያለ አዲስ ክስተት ተፈጠረ። ይኸውም የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ከጦርነቱ ማግስት ለአዲስ ድርድር መድረክ ላይ ብቅ አሉ፣ ሸምጋይ ሀገርም አልጀርያ ሆነች። የሚገርመው ደግሞ ይህ ድርድር ጊዜ የወሰደ አልነበረም መሪዎቹ የተፈራረሙት ወዲያው ሆነ፣ ድርድሩ ቀድሞ ያለቀ ይመስላል። በመቀጠል ደግም ሁለት የህዝቡን ስጋት ይበልጥ ያጠናከሩ ስምምነቶች ተከተሉ ።

ይግባኝ አልባ ብይን ተደረገ፣

በአልጀርስ ስምምነት መሠረት የድንበር ጉዳይ ለሔጉ የግል ፍርድ ሰጪ አካል የሚቀርብ ሆኖ በዚሁ ተቋም የሚሰጥ ብይን የመጨረሻውና አሳሪ (binding) ይሆናል ተባለ። ያም ሆኖ ግን የኢሮብ መሬት አሁን ከኤርትራ ተብላ ከምትታወቀው ሀገር የተካለለበት አንድም የታሪክ አጋጣሚ አልነበረም። በመሆኑም፣ ህዝቡ የሄግ ብይን የኢሮብ መሬትን ለሁለት ይከፍላል የሚል የከፋ ስጋት ውስጥ አልገባም ነበር። ባጭሩ ከኢሮብ መሬት አንድ ጠጠር ይነሳል የሚል ግምት አላሳደረም። የኋላ ኋላ ግን ኢትዮጵያ በከባዱ አውደ- ውጊያ አሸንፋ በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት በሄጉ በችሎቱ ላይ ስለመሸነፏ ለህዝቡ ተነገረ ። በትንሹ አንድ ሶሰተኛው የኢሮብ ህዝብና መሬት ወደ ኤርትራ እንዲካለል ተወሰነ /ተፈረደ/ ተባለ። በዚህ ምክንያትም ህዝቡ አዲስ ጭንቀትና ፍርሃት ውስጥ ገባ። አቤት እንዳይባል የይግባኝ መብት የለም ፣ ይህ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ የፍርድ ውሳኔውን በፀጋ እንዲቀበልና ለአፈፃፀም እንዳዘጋጅ ሰፊ ቅስቀሳ በመንግስቱ ካድሬዎች ተከተለ። የካድሬዎቹ ቅስቅሳ ህዝቡ ወሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርግ እስከ መማፀን  የደረሰ ነበር። የኢሮብ ህዝብ ግን "በመቃብሬ ላይ" በማለት ለካድሬዎቹ ቅስቀሳና ተማጽኖ አልቀመስ አለ።

 

ክፍል አምስት፣ ኢሮብ የጦር ሰፈር ሆኖ የቆየበት 20 ዓመት በሚል ርእስ ይቀጥላል።

ዮሴፍ አዳዩ

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ

ቁጥር አንድ

የምስራቃዊ ትግራይ ገጠሮች ፣ ከ1966 አጋማሽ-1968 መጀመሪያ



ከበየነ ገብራይ/ደንማርክ መስከረም 2014 ዓ/ም

ማሳሰቢያ

ይህ ታሪካዊ ተከታታይ መጣጥፍ እኔ/በየነ በግሌ የፃፍኩትና መወሰድ ያለበት ሃላፊነት/ተጠያቂነት ካለ በግሌ እኔ የምጠየቅበት/ሃላፊነት የምወስድበት መሆኑን በቅድሚያ አሳውቃለሁ። ስለሆነም ጥያቄ፣ ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ተቃውሞ ካለ ለኔ ለግሌ መቅረብ አለበት እንጂ ከታገልኩበት ድርጅት/ኢህአፓ ሆነ አሁን አባል ከሆንኩበት ኢኣኣ ጋራ ፈፅሞ መያያዝ የለበትም። መጣጥፉን መሰረት በማድረግ ዝርዝር መረጃ የምትፈልጉ ቀጠለው ከሀ እስከ ሐ ከተዘረዘሩት መገናኝ መንገዶች ባመቻችሁ/በፈለጋችሁ (ሀ. ሶሺያል ሚዲያ፣ Beyene G. Tesfu ለ. በጥሪ፣ 004520545658 ፣ ሐ. ኢመይል፣ btesfu45@gmail.com  ኮንታክት ካደረጋችሁኝ የማውቀውን ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኔን አሳውቃለሁ። የመጣጥፉ አሁን መፃፍ ዋና ዓላማም ታሪክን በታሪክነቱ አውቆ፣ የ60ዎቹ ወጣት ትውልድ የፈፀምነው ስህተት እንዳይደግም ይረዳ እንደሆነ በሚለ መሆኑ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ።

መግቢያ፣

የኢሮብ ብሄረሰብ ከ19ኛው ክፍለዘመን እስከ 21ኛ ክፍለዘመን መጀመሪያ የቁልቁለት ጉዞ በጨረፍታ በሚል ርእስ በተቆርቃሪ ኢሮቦች/Concerned Irobs በተፃፈው ታሪካዊ መጣጥፍ ውስጥ በ1968 ዓ.ም. የቦካለማኮ/ዓሊተና የ3ቱ ኢሮብ (ቡክናይቲ ዓረ፣ ኣዳጋጺ ዓረ፣ ሓሳባላ) ተወካዮች የተገኙበት ስብሰባ ላይ የተሓህት ተወካይ ስለ ድርጅቱ ማነትና ዓላማ  ከገለፀ በኋላ የኢሮብ ህዝብ ምክንያቶቹን በማስቀመጥ  የተሓህት ዓላማ እንደማይቀበል ባጭሩ ተቀምቷል። በዚህ ታሪካዊ ስብሰባ የኢሮብ ህዝብ የተሓህት ዓላማ እንደማይደግፍ በግልፅ ስላስቀመጠ፣ በማንነቱ/ኢሮባዊነቱ ፈፅሞ እንደማይደራረድ ግልፅ ስላደረገ ከዛን ጊዜ ጀምሮ  በተሓህት አመራር ጥርስ ውስጥ ገባ በሚለው በፅኑ ስለማምን፣ እኔ ራሴ በስብሰባው በአካል ስለነበርኩ፣ ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ ነውና ስብሰባውና በወቅቱ በአከባቢው ስለነበረው ሁኔታ ለሶሺያል ሚዲያ በሚያምች መንገድ በመከፋፈል በዝርዝር ለማቅረብ  እፈልጋለሁ። በቀጥታ ወደ ርእሱ (የቦካለማኮ/ዓሊተና ስብሰባ) ዝርዝር መፃፍ ከመግባቴ በፊት ግን በወቅቱ በአከባቢው (ምስራቅ ዓጋመ አውራጃ) ገጠርማ አከባቢ የነበረ ሁኔታና በወቅቱ በአከባቢው እየተጀመረ ስለነበረው የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ባጭሩ ማስቀመጥ ነገሩን ከመሰረቱ በሚገባ ለማወቅ ለሚፈልጉና በጉዳዩ መመራመር ለሚፈልግ ምሁራን የተወሰነ መነሻ ይሰጣል ብዬ ስለማምን የመጀመርያ ክፍል በዚህ ላይ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

የምስራቃዊ ትግራይ ገጠሮች ፣ ከ1966 አጋማሽ-1968 መጀመሪያ

ከ1966 አጋማሽ-1968 መጀመሪያ የኢሮብ ወረዳን ጨምሮ የምስራቃዊ ዓጋመ ገጠር አከባቢ (ኢሮብ፣ ጉለማክዳ፣ ሱቡሓ ሳዕሲዕና የተወሰነ ጋንታ አፈሹም) የመንግስት መዋቅር ፈርሶ ህዝቡ አስተዳደራዊ ችግሮች ሲገጥሙት አቤት የሚልባቸው መንግሥታዊ መዋቅሮች አልነበሩም። አከባቢዎቹ በተለያዩ መንግስትን በትጥቅ ለመፋለም እየተዘጋጁ የነበሩ ኃይሎች እንቅስቃሴ ጀምረዉበት የነበረ ቢሆንም ከ1966 አጋማሽ እስከ 1967 መጀመሪያ አጋማሽ ሌብነት በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋበት የነበረ አከባቢ ነበር። በወቅቱ በአከባቢው ትጥቅ ትግል ለመጀመር ይንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች በቀደም ተከተል፣ 1. ከ1964- 1967 ነሓሴ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝቦች አርነት ድርጅት/ኢህአድ በ1967 ነሓሴ ላይ ራሱን ወደ ፓርቲ ደረጃ አሳድጎ ስሙን ወደ ኢትዮጵያ ህዝባዊ አቢዮታዊ ፓርቲ/ኢህአፓ የቀየረው ቡድን ካድሬዎቹን (ህዝብ መካከል ህዝቡን መስለው የሚሰሩ ውሱን አባላት) ከ1966 መጀመሪያ ጀምሮ መድቦ በአከባቢው (በተለይ በኢሮብ) በዓዲግራት ከተማ ያንቀሳቅስ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በውጭ በዋናነት በሶሪያ በPLO እርዳታ ያሰለጠናቸው ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድኑን  የየካቲት አቢዮት ከመፈንዳቱ በፊት ለማስገባት ቡድኑ 1966 መባቻ ላይ ሳሕል/ኤርትራ ቢያስገባም በህግሓኤ/ሻዕቢያ አመራር ማጓተት ምክንያት በ1967 አጋማሽ ላይ አስገብቶ ‘ቤይዙ’ን ዓሲምባ በኢሮብ በማድረግ በአከባቢው እንቅስቃሴ ጀመረ። 2. ግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ/ግገሓት በ1966 አጋማሽ ላይ ቤዙን ማካታ/ኣድጋጺዓረ በማድረግ በአከባቢው መንቀሳቀስ ጀመረ። 3.የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት/ኢዴህ በ1967 መጀመሪያ ጀምሮ በአከባቢው መንቀሳቀስ ጀመረ። 4. ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ/ተሓህት ትጥቅ ትግሉን የጀመረው ምዕራብ ትግራይ ሽረ/ደደቢት በ1967 አጋማሽ ሲሆን ከ1968 ሕዳር ጀምሮ ወደ አከባቢው መጥቶ ቤዙን ማርዋ/ሳዕሲዕ አድርጎ መንቀሳቀስ ጀመረ።

ግገሓት ገና ትጥቅ ትግሉን የጀመረበት ሁለተኛ ዓመት ልደቱን ሳያከብር በእንዋሃድ ሴራ በህወሓት ዛጋብላ በሚባል በርሃ ተመቶ ዕድሜው ባጭሩ ተቀጨ። ስለ ግገሓት ከትግል ሜዳ መጥፋት፣ ድርጅቱን ያጠፋው ተሓሕት/ህወሓት ከነገረን ውጭ በትክክል ለምን በዛ መልክ ክትግል እንዲወገድ ተደረገ በሚለው አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ጋህዲ በሚል መፅሃፉ ካሰፈረው ውጭ ከሌላ ነፃ ምንጭ የማዳመጥ ዕድል አልገጠመኝም። የኢዴህ አባላትም በተሓሕትም በኢህአፓም/ሰም ጫና ይበዛባቸው ስለነበረ በተለይ ከግገሓት መመታት በኋላ ለነሱም እንደማይቀርላቸው በመረዳት ከአጭር ጊዜ (ወደ አንድ ዓመት) ቆይታ በኋላ ምስራቅ ትግራይን ለቀው ወደ ምዕራብ ትግራይ ጠቅልለው ስለሄዱ ከ1968 የመጀመሪያ አጋማሽ በኋላ በምሥራቅ ትግራይ የቀሩት ተፋላሚ ድርጅቶች ኢህአፓ/ሰና ያኔ ተሓህት ከ1972 በኋላ ህወሓት ብቻ ሆነው ቀሩ።

የምስራቅ ዓጋመ ህዝብ 4ቱንም ድርጅቶች በእኩል ዓይን በማየት ሁሉንም እኩል ያስተናግድና ያዳምጥ ነበር። ይህም የሆነው፣ አራቱም ድርጅቶች የተለያየ ዓላማ የነበራቸው ቢሆኑም፣ ከአብራኩ የተፈጠሩ ልጆች ስለነበሩ ነበር።። የድርጅቶቹ አባላት ይዘት ሲታይ፣ የሶስቱ (ተሓህት፣ ግገሓትና ኢዴህ) በወቅቱ የነበሩ አባላት በሙሉ ተጋሩ የነበሩ ሲሆን ከኢህአፓ/ሰ አባላትም በወቅቱ ከነበሩት 2/3ኛ የሚሆኑት ከትግራይ ነበሩ።  የወቅቱ የድርጅቶቹ መሪዎች የነበሩ ደግሞ፣ ግገሓት በመምህር ዮሃንስ ተክለሃይማኖት ይመራ ነበር። ኢዴህ በልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ይመራ ነበር። ኢህአፓ/ሰ በብርሃነ መስቀል ረዳ ይመራ ነበር። ተሓህት በበሪሁ በርሀ/አረጋዊ ይመራ ነበር። ሌላም በአመራር ደረጃ የነበሩ ሆነ ተራ አባላቱ ከዓላማ ልዩነት ውጭ በትግራዋይነት የማይበላለጡ እኩል ተጋሩ መሆናቸው ህዝቡ በሚገባ ያውቅ ነበር። ያኔ ህዝቡ እንደ ዛሬ በአንድ ድርጅት/በህወሓት ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭነት ቁጥጥር ሥር ስላልነበረ በነፃነት የሁሉንም ሓሳብ የማዳመጥ መብቱ አልተነጠቀም ነበር። የየድርጅቱን ዓላማና ራእይ አዳምጦ ይበጀኛል የሚለውን ለመደገፍ፣ የማይመስለው ሃሳብ ሲነሳ ለመቃወም፣ የፈለገውን ድርጅት ለመደገፍ ሆነ ለመቀላቀል፣ የማይደግፈውን ድርጅት ወይም ሃሳብ ለምን እንደማይደግፈው በግልፅ ለመናገር ብቃት፣ድፍረት፣ ዝግጁነትም ነበረው፣ በግልፅም ይናገር ነበር።

ከላይ ባጭሩ እንዳስቀመጥኩት ግገሓት በተሓህት በተወሰደበት እርምጃ፣ ኢዴህ ደግሞ በኢሕአፓና ተሓህት ፖለቲካዊ ተጽእኖ   አከባቢውን በመልቀቅ በህዝቡ የነበራቸው ተቀባይነት ሆነ ሊፈጥሩት ይችሉ የነበረውን ተጽእኖ ብዙ ሳይታወቅ ባጭር እንደተቀጩ ቀሩ። ግገሓት ዓላማውን ህዝቡ ውስጥ ብዙ አሰርፆ ያልነበረ ቢሆንም በዛጋብላ በርሃ በተሓህት መመታቱ፣ በበረሃው በጅምላ መቃብር የተቀበሩ ጉድጓዱ ጥልቅ ስላለነበረ ፅሕሪያ የሚባል አራዊት ጉዷዱን ከፍቶ አከባቢው ስለ ሸተተ፣ የሞኖክሶይቶ እረኞች አይተው ለዝቡ ነግረው ህዝቡ እንደገና ስለቀበረ መገደላቸ በጉለማክዳ ህዝብ በሚገባ ይታወቅ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ከተገደሉት ውስጥ በአከባቢው በሚገባ የሚታወቁት የባራምባራስ ገ/መስቀል/ቀፅቀፂያ ልጅ የማነ ገ/መስቀል ስለነበረ፣ ግዲያውን ካመለጡት ደግሞ እንደ ኃይለሚካኤል አባጎበዝ፣ ደጀን ተሰማ፣ ደስታ ተስፋይ፣ ዓነቶቹ የአክባቢው ተወላጆችና በብዙዎች የሚታወቁ ስለነበሩ ስለ ድርጅቱ አጠፋፍ በስፋት ያወራ ነበር፣ የተሓሕት ድርጊትም ህዝቡን አስቆጥቶና አሳዝኖትም ነበር።

 ከ1968 መጀመሪያ ጀምሮ አከባቢው ኢህአፓ/ሰና ተሓህት ሙሉ ቁጥጥር ሥር ገባ። ሁለቱም ድርጅቶች ህዝብን የሚያስተምሩና የሚያደራጁ ካድሬዎቻቸውን (ብዙሃን ድርጅት እየተባሉ ሲጠሩ የነበሩ) በመመደብ በሁሉም የገጠር አከባቢዎች በስፋት ይንቀሳቀሱና ደጋፊዎቻቸው/አባላት ይመለምሉ ነበር። እንዲሁም በወቅቱ በጋንታ ደረጃ ተደራጅቶ የነበረ ሠራዊታቸው (አንድ ጋንታ ማለት ከ20-30 ሰው የሚይዝ) በሚያርፉባቸው መንደሮች ህዝቡን በመሰብሰብ ዓላማቸውን ለህዝቡ በስፋት ያስተምሩ ነበር። ስለሆነም ህዝቡ ስለ ሁለቱ ድርጅቶች ማንነትና ዓላማ ገና ከ1968 አጋማሽ ጀምሮ በሚገባ እንዲያውቅ ተደርጎ ነበር።

ኢህአፓ/ሰ ዓብይ ቅራኔ (በጠምንጃ እንጂ በውይይት የማይፈታ ቅራኔ) ሲፈርጅ፣ በገጂዎች (መሳፍንቶች፣ አቀባባይ ከበርቲዎች) እና በጭቁን የኢትዮጵያ ህዝቦች መካክለ ያለው ቅራኔ አድርጎ፣ ደርግን ስልጣን ላይ እንደመጣ የጭቁኖች ወገን ሊሆን ይችላል የሚል ግምት የነበረው ቢሆንም የደርግ ትክክልኛ ፋሽስታዊ ባህሪው ገና ስልጣን በያዘ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ 60ዎቹን የድሮ ሚንስትሮች በመረሸን ስለጀመረ፣ ገና በአዋጅ ስልጣን እንደያዘ በወቅቱ የነበረው ሰላማዊ ትግልና እንቅስቃሴ ሁሉ በአዋጅ ከልክሎ ማሰር፣ መግደል ስለጀመረ ደርግንም በዋና ጠላትነት ደረጃ ፈርጆ ሁለገብ ህብረ ብሄራዉ ትግል በ1968 ጀመረ። ተሓሕት ዓብይ ቅራኔ ስፈርጅ፣ ዓብይ ቅራኔ (በጠምንጃ እንጂ በውይይት የማይፈታ ቅራኔ) በገጂው የአማራ ብሄርና በተቀሩት የኢትዮጵያ ጭቁን ብሄር/ብሄረሰቦች መካከል ያለ ቅራኔ ነው ብሎ ፈርጆ፣ መካሄድ ያለበት ሁለገብ ትግል ፀረ  የአማራ ሆኖ በየብሄሩ የሚካሄድ ትግል መሆን አለበት በማለት ነበር ትግሉን የጀመረው።

ሁለቱ ድርጅቶች እርስ በርስ መፈረጃጀት፣ ማጥላላት ስም መሰጣጠት የጀመሩት ገና ከጅምሩ ነበር። ተሓህት የኢህአፓ/ሰ  የአንድ ብሄር (አማራ) ተወላጆች ድርጅት አድርጎ በማስቀመጥ፣ ትምክህተኛ፣ የብሄር/ብሄረበሰብ ጥያቄ/ጭቁና የማይቀበል፣ # ናይ ዓባይ ኢትዮጵያ ናፋቒ/ተሓላቒ# የታላቋ ኢትዮጵያ ናፋቂና ጠበቃ፣ ብሎ በመፈረጅ ከኢህአፓ/ሰ ጋር ተሰልፈው ለነበሩ ተጋሩ ደግሞ #ኮራኹር አምሓራ# (የአማራ ቡችሎች) ብለው ይፈርጃቸው ነበረ። ኢህአፓ/ሰ እንደ ድርጅት ተሓህትን፣ በዴሞክራሲያዊ የብሄር ጥያቄ ስም የሚነግድ ለግል ጥቅምና ስልጣን የቆመ የጠባብ ብሄረተኛ ስብስብ ብሎ ይፈርጀው ነበር። በኢህአፓ/ሰ ተሰልፈው ሲታገሉ የነበሩ ተጋሩ ተሓህትን ጠባቦች በትግርኛ # ካብ ዓይኒ ዑንቂ ዝፀበብኩም ፀበብቲ# ይሉዋቸው ነበር። በድርጅት ደረጃ የነበረው ጥላቻ እንዳለ ሆኖ በኢህአፓ/ሰ ውስጥ በነበሩ ተጋሩና በህወሓት አባላት መካከል የነበረው ጥላቻ ግን የላቀ ነበር። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎቹ ከትምህርትቤት ጀምሮ በሚገባ የሚተዋወቁ አንዳንዶቹም ወደ ትግል ሜዳ ከመውጣታቸው በፊት ጥሩ ጓደኞች የነበሩ ስለነበረ፣ በተለይ በኢህአህአፓ/ሰ ውስጥ የተሰለፉት የአማራ ቡችሎች የሚለው ስድብና እነሱ/ተሓህቶች ለትግራይ አሳቢ እነሱ/ በኢህአፓ/ሰ የተሰለፉ ደግሞ ለትግራይ ምንም የማያስቡ ትግራይን ውጭ ያደረገች ታላቋ ኢትዮጵያ ህልመኞች ተደረገው መቀመጥ በጣም ያማቸው ነበር።

ተሓህት ኢህአፓን በብሄር ጥያቄ ላይ ግልፅ አቋም የሌለው የታላቋ ኢትዮጵያ ናፋቂ ድርጅት ነው ብሎ ፈርጆ ቢቀሰቅስበትም ኢህአፓ የብሄር ጥያቄን በፖለቲካ ፕሮግራሙ ካስቀመጣቸው 9ኙ ዓበይት ነጥቦች አንዱ አድርጎ አስቀምጦ ጥያቄው ለአንዲት ዴሞክራሲያዊትና ሉዓላዊት ኢትዮጵያ ለመመስረት በሚደረገ ህብረብሄራዊ የመደብ ትግል ስር ሊፈታ ይችላል የሚል ግልፅ አቋም ነበረው። ኢህአፓ በብሄር ጥያቄ ላይ ያኔ የነበረው አቋም ለማታውቁ ድርጅቱ መሰረታዊ አቋሞቹን ለህዝብ ይፋ ያደርግበት የነበረው በድርጅቱ ልሳን በዴሞክራሲያ “ዴሞክራሲና የብሄር ጥያቄ” በሚል ርእስ ጥር 7 ቀን 1967 የወጣውን በያ ትውልድ ድረ-ገፅ በመግባት ቀጥሎ በተቀመጠው ሊንክ መሰረት ማግኘት ይቻላል።

ከላይ በሰፈረው ሊንክ ሙሉውን በአደፍርስ ተባዝቶ የተሰራጨውን ሰነድ ለማንበብ አስቸጋሪ ለሆነባችሁ የአቋሞቹን አንኳር አንኳር ነጥቦች እንደሚከተለው ሰፍሯል፣

#የአንድ ሶሺያሊስት እውነተኝነትና ትክክለኛነት የሚፈተነው የማያወላውል ዴሞክራሲያዊነቱ ከሚረጋገጥባቸው አንዱ

በብሄር ጥያቄ ላይ በሚወስደው አቋም መሆኑ ከሳይንሳዊ ሶሺያሊዝም አስተማሪዎች አንዱ አስተምሯል። ትክክል በመሆኑም

ይህ ሃሳብ ተቀብለናል፣ አቋምችንም አሳውቀናል፣ እንደገና ማሳወቅ ካስፈለገም፣


በነዚህ  የድርጅቱ መሰረታዊ የአቋም ነጥቦች መሰረት ኢህአፓ/ሰ ከ1967 ግንቦት እስከ 1968 አጋማሽ በነበረው ወደ 10 ወር ያህል ጊዜ በአከባቢው ያለ ተቃናቃኝ (ተሓህት በወቅቱ በአከባቢ ምንም እንስቃሴ አልነበረውም) ትጥቅ ትግል ጀማሪ አባላቱንና ዓላማውን ለማስተዋውቅ ጥሩ ዕድል አገኘ። ያለ ማጋነን ኢህአፓ/ሰ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን ውስጥ ለህዝቡ በራሱ ቋንቋ/ትግርኛ ትምህርት ሊሰጡ የምችሉ ብቃት የነበራቸው አባላት ስለነበሩት ህዝቡ ድርጅቱን ገና ከጅምሩ በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎትና ደግፎት ነበር። ለዚህ ማስረጃው ደግሞ በምስራቅ ትግራይ ከ1968 መጀመሪያ አጋማሽ ጀምሮ ተፈጥሮ የነበረው የአስተዳደር ክፍተት ለማሟላት ከራሱ ከህዝቡ የሚመረጥ አስተዳደርና የገበሬ ማህበራት በምስራቃዊ ትግራይ ከአንድ ከሰበያ ቁሸት ውጭ የተመሰረቱት በኢህአፓ/ሰ ነበር። በምስራቅ ትግራይ የመጀመሪያ የመሬት ማከፋፈል ስራም ከሰበያ ውጭ የተካሄደው በኢአፓ/ሰ ነበር። ስለሆነም፣ በምስራቃዊ ዓጋመና ሰራዊቱ ሲንቀሳቀስበት በነበረው የዓድዋ፣ ክልተ አውላዕሎ ወረዳዎች ገጠራማ አከባቢ በህዝቡ ኢህአፓ/ሰ ከተሓህት የበለጠ ድጋፍና ተቅባይነት ነበረው፣ ያኔ ከአከባቢው ወደ ኢህአፓ/ሰ የተቀላቀሉትና ለመቀላቀል ይፈልጉ የነበሩ ወደ ተሓሕት ሲቀላቀሉ ከነበሩ ይበልጡ ነበር።

ኢሮብ ወረዳ በጅዮግራፊያዊ አቀማመጥ በምስራቅ ትግራይ የሚመደብ ሲሆን የኢሮብ ብሄረሰብ ከጥንት ጀምሮ ራሱን፣ ራሱ የቻለ ብሄረሰብ አድርጎ የሚያይ በቁጥር አናሳ የአስተሳሰብና ማንነት ጉዳይ ሲነሳ ግን ራሱን እንደ ትልቅ አድርጎ የሚያስቀምጥ፣ በትግራይ ሆነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ፖለቲከኖች የወጡበት ብሄረሰብ ነበር። ለዚህ ማስረጃ Suba Hais በሚል የብእር ስም በእንግልዝኛ ከተፃፈውና www.advocacy.irobpeople.org ከሚገኘው ስለ ኢሮብ ህዝብ ሰፊ መረጃ ከያዘው ጠቃሚ አርትክል ቀጥሎ የተቀመጠውን መመልከት ይቻላል። እጠቅሳለሁ፣ “Irob, despite its physical location by the border area, in essence, is a core part of Tigray. In fact, most Tigrayan leaders who played important roles in regional and national politics were fully or partly Irob descendants. Just to mention a few randomly: Sum ‘Agame Woldu, Dej Subagadis, Emperor Yohannes IV, Iteghie Denqnesh, Ras Sebhat, Shum Agame Desta, Ras Araya, Dej. Hagos, Dej. Derso, Dej. Maru, Dej. Tedla Abaguben, Shum Agame Aregawi, Dej. Belay Weldiye, Dej. Kassa, Azmach Ayele, Dej. Gebreselassie, Dej. Zewde Gebreselassie, Betweded Hailemariam, Fitwrari Tessema Tesfay, Major Biru Sebhat, Colonel Gebray Gebrezghi, Colonel Adhanom, Colonel Abraha Adagis (Yeogaden Anbesa), Dr. Abraham Demoz, Dr. Tesfay Debessay etc.”

ያኔ (1968) የነበረው የኢሮብ ህዝብ በኢሮባዊ ማንነቱ ፈፅሞ የማይደራደር፣ ብሄራዊ ጭቆና ከተነሳ የኢሮብ አናሳ ብሄረሰብ ጨቋኞች ተጋሩ ናቸው ብሎ የሚያምን፣ ለዘመናት የነበረው ራስ ገዝ የኦና ስርዓት በአፄ ኃ/ስላሴ ቢነጠቅም ገና በኦና ስርዓት ጊዜ የነበረው አስተሳሰብ፣ ባህል፣ ስነልቦናና ኢሮባዊ ማንነትና አንድነቱ እንዳለ ይዞ የነበረ ህዝብ ስለነበረ የትሓህት ዓላማ ሊቀበል የምችልበት ሁኔታ ሆነ ምክንያት አልነበረም። ስለሆነም ወረዳው ኢህአፓ/ሰ ጠቅልሎ ከትግራይ እስክወጣበት 1970 ግንቦት (ከ1967-1970 ወደ 3 ዓመት) በኢህአፓ/ሰ ቁጥጥር ስር ነበር። ገና ከጅምሩም ብዙ የኢሮብ ወጣቶች ኢህአፓ/ሰን ተቀላቅለው ነበር፣ ህዝቡም ኢአፓ/ሰን ይደግፍ ነበር።

በሚቀጥለው #የቦካለማኮ/ዓሊተና ስብሰባ በተመለከተ፣ ስብሰባው መጥራት ለምን አስፈለገ፣ ስብሰባውን የጠራውስ ማን ነበር፣ በሚል ርእስ ዝርዝር ይዤላችሁ እቀርባለሁ።


የነገ ሰው ይበለን!

በየነ ገብራይ/ደንማርክ 

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ

 ቁጥር ሁለት

የ1968ቱ የቦካለ፟ማኮ/ዓሊተና ስብሰባ መጠራት ለምን አስፈለገ፣ የጠራውስ ማን ነበር፣



ከበየነ ገብራይ/ደንማርክ ጥቅምት 2014 ዓ/ም

መጣጥፉን ለመፃፍ መነሻ ምክንያት፣

ተቆርቃሪ ኢሮቦች/Concerned Irobs በሚል የፈስቡክ ስም፣ ኢሮብ ከ19ኛ -21ኛ ክፍለዘመን የቁልቁለት ጉዞ በሚል ርእስ ሰፕተምበር 19 በቀረበው መጣጥፍ ውስጥ ከሶስቱ ኢሮብ (አድጋዲ ዓረ፣ ቡክናይቲ ዓረ፣ ሓሳባላ ዓረ) ከ300 በላይ ተወካዮች የተገኙበት ስብሰባ በቦካለ፟ማኮ/ዓሊተና መደረጉ፣ ለስብሰባው መጠራት ዋና ዓላማ የመሬት ማከፋፈል የጋራ ስሪት/ህግ ለማውጣት መኖሩና ስብሰባውን የጠራው ደግሞ ኢህአፓ/ሰ እንደነበረ ባጭሩ ተጠቅሷል። ሆኖም ግን ለመሬት ማከፋፈሉ በህዝበ ውሳኔ የሚፀድቅ አዲስ ስሪት/ህግ ማውጣት ለምን አስፈለገ፣ ለምን ኢህአፓ/ሰ በራሱ ውሳኔና አሰራር መሬቱን አላከፋፈለም፣ የስብሰባው ተሳታፊዎች እነማን ነበሩ፣በማንና እንዴትስ ተመረጡ፣ የስብሰባው አካሄድ ምን ይመስል ነበር፣ የስብሰባው ውጤትስ ምን ሆነ፣ ለዚህ ስብሰባ መጠራት ሆነ የኢሮብ ህዝብ ማንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ ማን ነበር. . . ወዘተ. በሚለው የቀረበ ዝርዝር የለም።

በቁጥር አንድ በወቅቱ በአከባቢው (ምስራቅ ዓጋመ አውራጃ) ገጠርማ አከባቢ የነበረ ሁኔታና በአከባቢው እየተጀመረ ስለነበረው የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ባጭሩ ያስቀመጥኩት እዝህ ታገኙታላችሁ፡፡

ይህ ስብሰባ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጠው የኢሮብ ብሄረሰብ የቅራኔ/ችግር በውይይትና በዴሞክራሲያዊ ውሳኔ አፈታት ባህልና ስነልቦና በግልፅ የታየበት፣ በስብሰባው መጨረሻ የተሓህት ተወካዮች ስለ ድርጅታቸው ማንነትና ዓላማ ገለፃ ባደረጉበት ጊዜ የኢሮብ ህዝብ በኢሮባዊ ማንነቱ ፈፅሞ የማየደራደር መሆኑ፣ የኢሮብ ብሄረሰብ ተጋሩ ብለው ራሳቸውን ከሚጠሩ የትግራይ ብሄረሰብ የተለየ ራሱን የቻለ ብሄረስብ መሆኑ በግልፅ ቋንቋ ያስቀመጠበት ታሪካዊ ስብሰባ ስለነበረ እኔም በስብሰባው በአካል ስለነበርኩ፣ ያኔ (46 ዓመት) በፊት የነበረው የኢሮብ ብሄረሰብ ምን ይመስል እንደነበረ በመጠኑም ቢሆን ስለማውቅ፣ ዛሬ ወደ መጥፋት አፋፍ ላይ ደርሶ ያለው የኢሮብ ብሄረሰብ የዛሬ 46 ዓመት በፊት ምን ይመስል እንደነበረ ለዛሬ ወጣት ትውልድ ባጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ሃቁን ማወቅ ለሚፈልግ የኢሮብ ወጣት ትውልድ ታሪኩን የማሳወቅ ግዴታ ስላለብኝ ስለ ስብሰባውና ስብሰባውን ያዘጋጀው ያኔ ኢሮብን ዋና ቤይዙን አድርጎ ይንቀሳቀስ ስለነበረው የኢህአፓ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን የመጀመሪያ እንቅስቃሴ በኢሮብ ባጭሩ ለማሳየት እሞክራለሁ። ስለ ቦካለ-ማኮ ስብሰባ ዝርዝር መፃፍ ከመግባቴ በፊት ግን ይህን ስብሰባ የጠራውና ከ1967- 1970 ግንቦት ድረስ አከባቢው በቁጥጥሩ ስር ስለ ነበረው ኢህአፓ/ሰ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን የመጀመሪያ እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበረ ባጭሩ በመግለፅ ልጀምር።


አከባቢውንና ህዝቡን ለማወቅ በኢህአፓ/ሰ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን የተደረገ የመጀመሪያ እንቅስቃሴ፤

የኢህአሰ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን ኢሮብ/ዓሲምባ 1967 እንደገባ ከእናት ድርጅቱ ኢህአፓ ጋራ እስከሚገናኝ ወደ 2 ወር ያህል ጊዜ በዓሲምባ ተራራ ዙሪያ ተወስኖ ኣከባቢው ጋር እየተዋወቀ ነበር የቆየው። ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይና ፀጋዬ ገ/መድህን/ደብተራው ከከተማ መጥው ከቡድኑ ጋራ ተገናኝተው ቡድኑ በአከባቢው ራሱንና እናት ድርጅቱን (ኢህአፓን) ማስተዋወቅ በተመለከተ መመሪያ ሰጥተው፣ ዶክተር ተስፋይና ብርሃነመስቀል ረዳ ወደ ከተማ ሲሄዱ፤ ፀጋዬ ገ/መድህን (ያኔ አማሃ በሚል የትግል ስም ይታወቅ የነበረ) የቡድኑ የፖለቲካ መሪ ሮባ/ኣብዲሳ አያና ብርሃነመስቀልን ተክቶ የቡድኑ ወታደራዊ መሪ ሆኖ ቡድኑ ራሱንና እናት ድርጅቱን የማስተዋወቅ ስራ ለመጀመር ክረምት ላይ በህዝቡ መካከል ግልፅ እንቅስቃሴ ጀመረ። የመጀመሪያ ፈጣንና አሳሳች እንቅስቃሴውን ከኢሮብ ወረዳ ወጥቶ፣ በጉለማካዳ፣ ዳሞ፣ ብዘት፣ ሓውዘን፣ ክልተአውላዕሎ፣እስከ እንደርታ ጫፍ በማድረግ ራሱንና እናት ድርጅቱን ከህዝቡና በተለይ በወቅቱ በአከባቢው ዘምተው ከነበሩ የእድገት በህብረት ዘማች ተማሪዎች ጋራ አስተዋውቆ ወደ ኢሮብ ወረዳ ተመለሰ።

ኢህአፓ/ሰ በትግራይ ለሚያካሄደው የትጥቅ ትግል የመጀመሪያ መናገሻ (ቤዙ) በኢሮብ መሆን አለበት ብሎ ስላመነ፣ የመሬቱ አቀማመጥና ህዝቡን በሚገባ ማወቅ ነበረበት። በመሆኑም በወቅቱ የነበረው በሁለት ጋንታ የተደራጀው (ወደ 50 ሰው) ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን በ1968 ጥቅምት መጀመሪያ ላይ ሞላው የኢሮብ ወረዳ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚያዳርስ ዓላማው ከህዝቡና ከመሬቱ ጋራ መተዋወቅ ያደረገ እንቅስቃሴ ተደረገ። በዚህ እንቅስቃሴ ወቅት የመላው የቡድኑ አባላት ከህዝቡ ጋራ የመተዋወቅና ስለ ኢህአፓ ዓላማ ማሳውቅ ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች፣ ችግሮች፣ ሃሳቦች/አስተያየቶች. . . በሚገባ በፅሁፍ ማሰባሰብ፣ በቦታው መመለስ የነበረባቸው ቀላል ጉዳዮች በቦታው ለመመልስ ጓድ ገረይ በዋነነት እኔ ደግሞ በረዳትነት ተመደብን። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ሁለታችን የአከባቢው ተወላጆች ስለሆንና ቋንቋዉን/ሳሆ የምንናገር በተለይ ጓድ ገረይ በአብዛኛው የኢሮብ አከባቢ በሚገባ ይታወቅ ስለነበረም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ጓድ ገረይ የኢሮብ ህዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ ስነልቦና በሚገባ ከሚያውቁና በህዝቡ ተቀባይነት ከነበራቸው በኢህአፓ ውስጥ ከነበሩ የብሄረሰቡ ተወላጆች አንዱ ስለነበረም ነበር። እኔ ቋንቋውን ከመናገር ውጭ ስለ ህዝቡ ባህል፣ስነልቦና፣ ታሪክ በጣም ቁንጹል የሆነ እውቀት የነበረኝ ሲሆን፣ ጓድ ገረይን የመሰለ አስተማሪና አርአያ የሚሆን ጓድ ከፊቴ መኖር ስለ ኢሮብ ህዝብ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህልና ስነልቦና በቀላሉና ቶሎ ለማወቅ ዕድል አገኘሁ። ገና እንቅስቃሴው ከመጀመሩ በፊት ጓድ ገረይ ስለ ኢሮብ ህዝብ ባህል፣ ስነልቦና በሚገባ ትምህርት ሰጥቶኝ፣ እንዴት ወደ ህዝቡ መቅረብ እንዳለብኝ፣ በየቁሸቱ ከነበሩ የዕድሜ ባለፀጎች ጋራ እንዴት መቅረብና ከነሱ ምክር መጠየቅ እንዳለብኝ፣ ዋናዋ የአከባቢው ኢንፎርመሽንና መረጃ ምንጭነት እንዴት እነሱን መጠቀም እንደነበረብኝ፣ እንዴት ምክራቸውን መከተል እንዳለብኝ. . . በዝርዝር ትምህርትና መመሪያ ሰጠኝ። ያኔ ገና በ20 ዓመት ዕድሜ ላይ ለነበርኩና ስለ ኢሮብ ምንም እውቀት ላልነበረኝ ወጣት ጓድ ገረይን የመሰለ እንደ አርአያ ልከተለው የምችል አስተማሪም ጓድም ማግኘት የማላወቅ የነበረ ማንነቴን/ኢሮብነት እንዳውቅ፣ የኢሮብ ህዝብን ይብልጥ እንዳውቅ ትልቅ የረዳኝ ትልቅ ዕድል ስለነበር እሱ የሚሰጠኝ ትምህርት፣ ምክርና መመሪያም በጥብቅ እከተል ነበር፣ የሆነ ጥያቄ/ሃሳብ ሲኖረኝም ወዲያውኑ እያቀረብኩለት ወዲያውኑ መልስ ይሰጠኝ ነበር።

ለቦካለ፟ማኮ ስብሰባ ግብአት የሆነውና በጓድ ገረይ መሪነት የተካሄደው የዳሰሳ ጥናትና ውጤቱ፤

ይህ ኢሮብን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያዳረሰ የመጀመሪያ እንቅስቃሴ በምስራቃዊ ቡክናይቲ ዓረ ኣበ በሚባል ቀበሌ ተጀምሮ በዋርዓትለ በኩል ወደ ካፍና በመውጣት ሞላው አድጋዲ ዓረ ያዳረሰ፣ ከአድጋዲ ዓረ ወደ ቡክናይቲ ዓረ ምዕራባዊ ደጋ በመመለስ ዋና ዋና ቀበሌዎችን በማዳረስ ወደ ቆላው ቡክናይቲ-ዓረ በመቀጠል ከዛ ወደ ምዕራባዊ ኢሮብ ዓጋራለኮማ በመቀጠል ዋናዋና ቀበሌዎችን ያዳረሰ፣ በመቀጠል በዓሰፋት ወደ ሓሳባላ በመግባት የሓሳባላ ዋና ዋና ቀበሌዎችን በማዳረስ የሓሳባላ የመጨረሻ ሰው የሰፈረበት ደቡባዊ ጫፍ የሆነው ጉንዳጉንደ ገዳም ላይ የተጠናቀቀ ነበር።

በዚህ እንቅስቃሴ ጓድ ገረይ እንቅስቃሴው ከመጀመሩ በፊት በሰጠኝ ትምህርትና መመሪያ መሰረት ተልእኮዬን ለመፈፀም ህዝቡን መገናኘት ስጀምር አንድ ነገር ታዘብኩ። በቆየው የኢሮብ ባህል መሰረት በሳሆ “ዋሪስም” (ዜና መለዋወጥ) እና በኢሮብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ኢሮቦች ብቻ በሚተዋወቁበት የራሳቸው ኮድ መሰረት በጥሪ በሚተላለፈው መልእክት ህዝቡ በያረፍንበት ቀበሌ ያልነው፣ የስራነው ቀጥሎ በምንርፍበት ቀበሌ ቀድሞ ደርሶ አውቆ፣ ማንነቴም ገና እኔ ራሴን ከማስተዋውቄ በፊት ብዙዎቹ አውቀው በኢህአፓነቴ ሳይሆን በኢሮብነቴ ቀርበው ስለሁኔታው በግልፅና በዝርዝር ይነገሩኝ ነበር። እኔም በጓድ ገረይ በተሰጠኝ መመሪያ መሰረት እቦታው መፈታት ያለበት ከቀበሌው ሽማግሌዎች ጋራ በመሆን እየፈታን በቦታት መፈታት የማችሉትን ጥያቄዎች፣ ሃሳቦች ሆነ ችግሮች ለይቼ እየመዘገብኩ እስከ እንቅስቃሴው ፍፃሜ ድረስ ቀጠልኩ፣ በጓድ ገረይ በኩልም እንደዚሁ ተደረገ።

ከዚህ መላው ኢሮብን ያዳረሰ እንቅስቃሴ ፍፃሜ በኋላ አጠቃላይ የእንቅስቃሴው ውጤት ገምግመን በየግላችን ያሰባሰብነው አንድ ላይ ለማቀናጀት ማጋዑማ በሚባል ቀበሌ ተገናኘን። ህዝቡ ለኢህአፓ የነበረው ድጋፍ ሆነ ተቃውሞ በተመለከተ የኢሮብ ህዝብ በባህሪዩ ቶሎ ብሎ ድጋፍ ወይ ተቃውሞ የማያሳይ ህዝብ ቢሆንም በአመዛኙ ኢህአፓ ይዞት የነበረው ዓላማና ድርጅቱ ውስጥ ከዋና አመራር እስከ ተራ አባላት በህብረተስቡ የሚከበሩ የራሱ ልጆች ስለነበሩ ለድርጅቱ ድጋፍ እንደነበረው አወቅን፣ ከየአከባቢዉም አብረን ለመታገል እንፈልጋለን የሚሉ ወጣት አርሶ አደሮች ገና ከጅምሩ ለማየት ቻልን። በተለይ ሁለታችን ተመድበንለት የነበረው የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች/ችግሮች ለይቶ የማወቅ ስራ በተመለከተም፣ ጥያቄዎቹ/ችግሮቹ በሁለት ደረጃ ሊታዩ የሚገባቸው መሆኑ ለየን።

ሀ.     አከባቢውን ብቻ የሚመለከቱ አከባቢያዊ መፍትሄ የሚፈልጉ ጥያቄዎች/ችግሮብ በተለያዩ ቀበሌዎች መኖራቸው፣

ለ.     መላው ኢሮብን የሚመለክቱና አስቸኳይ መፍትሄ የሚሹ፣

የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ይዘት ባጭሩ፤

ሪፖርቱ ወደ 30 ወርቀት (60 ገፅ) የነበረው ደብተር ላይ የተፃፈ ሆኖ፣ በመግቢያ ደረጃ ስለ ኢሮብ ህዝብ ታሪክ፣ ማንነት፣ ባህልና ስነልቦና ሰፋ ያለ ዝርዝር የያዘ፣ በመቀጠል የኢሮብ ህዝብ ለብዙ ዘመናት ስለነበረው ራስ ገዝ የኦና ስርዓት የሚገልፅ፣ የኢሮብ ህዝብ በፅሁፍ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም በቃል ደረጃ ለሁሉም ችግሮች ሆነ ወንጀሎች መፍቻ በህዝባዊ ሽንጎ አማካይነት የተደነገጉ ህጎች እንደነበሩት፣ የራስ ገዝ የኦና ስርዓት እንዴት በአፄ ኃ/ስላሴ ስርዓት እንደፈረሰና የኢሮብ ህዝብ አፄ ኃ/ስላሴ ኢትዮጵያን አንድ ማድረጋቸው የሚደግፍ ሆኖ ያ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ራስ ገዝ የኦና ስርዓቱን በሃይል ማፍረሳቸው የሚኮንነው መሆኑ፣ ከኦና ስርዓት መፍረስ እስከ 1966ቱ አቢዮት እንዴት ሲተዳደር እንደቆየ፣ አሁንም ያ ራስ ገዝ የኦና ስርዓቱ እንዲመለስለት የሚፈልግ መሆኑ በሪፖርቱ በዝርዝር ተቀምጦ ነበር። ያ ሪፖርት የኢሮብ ህዝብን ለማያውቅ የውጭ ሰው የኢሮብ ህዝብን ማንነት፣ ባህልና ስነልቦና በትክክል የሚያሳይ ሪፖርት ሆኖ ለሁለታችን በተሰጠው ተልእኮ መሰረት የኢሮብ የወቅቱ መሰረታዊና አስቸኳይ መፍትሄ የሚሹ ጥያቄዎች/ችግሮችም በቀደም ተከተል ከነ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦችም የተቀመጡበት የተሟላ ሪፖርት ነበር።

የየአከባቢው ጥያቄዎች/ችግሮች ህዝባዊ አስተዳደር ሲመሰረት ከአስተዳደሩ ጋራ በመሆን የሚፈቱ መሆናቸው በማመን አጠቃላይ ኢሮብን በሚመለከቱት ላይ ብቻ በማተኮር በድርጅት ደረጃ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኙ ያልናቸው ለይተን አስቀምጠን ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንሰጥ እንዲሁም አመራሩ ስለ ኢሮብ ህዝብ ትክክለኛ ስዕል እንዲያገኝ የሚያስችል ዝርዝር ሪፖርት ማቅረብ አለብን በሚለው ተስማምተን ቀጥለው የተቀመጡ ሶስት ጥያቄዎች/ችግሮች አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኙ በሚል ለይተን አስቀመጥን።

1.      በወቅቱ መሬት አልባ የነበሩ ወጣት አርሶ አደሮች መሬት የማግኘት ጥያቄ፣

2.      የራስ ገዝ (Autonomous) ክልልና የኦና ስርዓት የመመለስ ጥያቄ

3.      ኢህአፓ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝቡን ከከተማ ግኑኝነት የማይነጥል፣ በተለይ ከደርግ ስርዓት የሚያገኘው አገልግሎት በማይቋረጥበት መንገድ በጥንቃቄ እንዲሆን የሚሉት ዋነኞቹ ነበሩ።

ጓድ ገረይ በሙያው አስተማሪ የነበረና የሪፖርት ማዘጋጀት ልምድ የነበረው ስለነበረ፣ ከኔ የሚፈልገውን ሃሳብ/አስተያየት ወስዶ ስለ አጠቃላይ እንቅስቃሴውና በተለይ ለሁለታችን የተሰጠው ተልእኮ በተመለከተ ለአመራሩ የሚቀርብ ዝርዝር ሪፖርት ከነ የመፍትሄ ንድፈሃሳቦች/Proposals በሶስት ቀን ውስጥ በጽሁፍ አዘጋጀ። ጓድ ገረይ በጣም ዴሞክራትና በጋራ ስራ የሚያምን ጓድ ስለነበረ ያዘጋጀው ሪፖርት የጋራችን ለማድረግ እኔም እንዳነበውና ሃሳብ እንድሰጥበት አድርጎ፣ እኔም ብዙ ተምሬበት፣ ሙሉ በሙሉ ተስማምቼበት ሁለታችን ሪፖርቱን ለአመራር ቀረብን።

ከኢህአፓ አስቸኳይ መልስ የሚሹ ተብለው በተቀመጡ ጥያቄዎች/ችግሮችና የቀረቡ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦች፣


እላይ የተጠቀሱት ሶስቱ ዋና ዋና ችግሮች ለመፍታት የቀረቡት የመፍትሄ እርምጃዎች ክዝህ ስር በቅደምተከተል ተቀምጠዋል፡፡


ሀ) መሬት ለወጣት አርሶ አደሮች ማከፋፈልን በተመለከተ፣

የመሬት ጥያቄ ሁሉንም በሚያስማማ መንገደ በአገባቡ ካልተፈታ፣ መሬት አልባ በነበሩ አብዝሃ ወጣት አርሶ አደሮችና የነበረው ጠባብ ለም መሬት በርስት ይዘው በነበሩ ውሁዳን ባለርስቶች መካከል የሚጀመረውና ወደ ጎሳዎች/መላ አድጎ የኢሮብ አናሳ ብሄረስብን አንድነት ሊያናጋ ይችላል የሚል ስጋት በጓድ ገረይ በኩል ነበር። በኢህአፓ በኩል ደግሞ መሬት ለአራሹ ከሚለው አቋሙ በመነሳት መሬቱ ከባለ ርስቶች በሃይልም ቢሆን ተወስዶ ለውጣቶቹ መሰጠት አለበት የሚል የጸና አቋም እንደነበረም ይታወቅ ነበር። ነገሮችን አርቆ ለማየት ልዩ ተስጥኦ የነበረው ጓድ ገረይም በኢሮብ የመሬት አከፋፈል በተመለከተ አቋሙን እንዲቀይር ከአሳማኝ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦች ጋራ መቅረብ እንዳለብን ቀድሞ ተረድቶ ለዚህ በጋራ እንድንገፋ መከረኝ እኔም በሃሳቡ ሙሉ በሙሉ ተስማማሁ። በዚህ መሰረትም ኢህአፓ በኢሮብ የመሬት መከፋፈል በመሬት ለአራሹ መርህ መሰረት መከፋፈሉን ከማረጋገጥ ውጭ በቀጥታ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠብና ለኛ ለብሄረሰቡ ተወላጆች ከህብረተሰቡ (ከባለ ርስቶቹም ከመሬት ፈላጊ ወጣቶችም) ጋራ በኢሮብ ባህል መሰረት ተመካክረን በሁለቱም ስምምነት እንድንፈታው ዕድል እንዲሰጠን የሚጠይቅ ቀጥሎ የተቀመጡ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦች በሪፖርቱ ተካተቱ።


ለ) ራስ ገዝ የኦና ስርዓት እንዲመለስለት ህዝቡ የጠየቀውን በተመለከተ፣


ሐ) ኢህአፓ/ሰ በአከባቢው የሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝቡን ከከተማና ከደርግ ስርዓት የሚያገኘው አገልግሎ ላይ ችግር በማይፈጥር መንገድ እንዲሆን የቀረብ ጥያቄን በተመለከተ፣

ያኔ መላው ምስራቃዊ ትግራይ ገጠርና ራሱ ዛላምበሳ የጉለማክዳ ወረዳ ዋና ከተማ ጨምሮ ከደርግ ስርዓት ቁጥጥር ውጭ ስለነበረ፣ ህዝቡ ከከተማ የሚፈልጋቸው ነገሮች የሚያገኘው በደርግ ቁጥጥር ስር ከነበረው ከዓዲግራት ከተማ ነበር። ስለሆነም ከአከባቢው ወደ ዓዲግራት ለተለያየ ቆሳቁስ ፍለጋ ለሚሄደው ህዝብ በደርግ ካድሬዎች በአከባቢው ይንቀሳቅሱ ስለነበሩ አማጺ ሃይሎች ብዙ ጥያቄ ይቀርብለት ነበር፣ ምርመራም ይደረግበት ነበር። በተለይ የኢሮብ ወረዳ በተመለከተ በወቅቱ በወረዳዋ የነበረው ብቸኛ በካቶሊክ ቤተክርስትያን የሚካሄድ የነበረ የዓሊተና ክልንክና ብቸኛው የልደታ /ቤት በተመለከት የደርግ ካድሬዎች ለህዝቡ ኢህአፓ በነዚህ ተቋማት ላይ ይጠቀም እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ጥያቄ ያቀርቡ ስለነበረ፣ በዓሊተና ከነበሩ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ጋራ ይገናኛል የሚል ጥርጣሬም ስለነበረ፣ በተቋማቱ አከባቢ የኢህአፓ ሰዎች ከመታየት እንዲቆጠቡ፣ ከካህናቱ ጋራ የሚደረግ ማንኛውም ግኑኝነት የተለየ ጥንቃቄ እንዲደረግለት የህዝቡ ፍላጎትና ጥያቄ ነበር። ምክንያቱም በሆነ ምክንያት በክልኒኩ፣ በት/ቤቱ፣ ከካቶሊክ መንኮሳት ጋራ ኢህአፓ ግኑኝነት እያደረገ መሆኑ ከታወቀ፣ ደርግ /ቤቱንም ክልንኩንም ከመንግስት ያገኙት የነበረው ማንኛውም አገልግሎት ሆነ ማተሪያል ሊዘጋው ይችላል የሚል ትልቅ ስጋት ስለነበረ ማንኛው ከተባሉት ተቋማት ጋራ የሚደረግ ግኑኝነት በምስጥርና በተወሰኑ በጣም በሚታመኑ ግለሰቦች ብቻ ቢደረግ።

ከላይ የተቀመጡ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦችን የያዘ ዝርዝር ሪፖርቱ የቀረበለት አመራር ስለ ሁለቱ (ስለ ራስገዝ የኦና ስርዓትና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ስለሚደረገው ግኑኝነት መደረግ ያለበት ጥንቃቄ) በተመለከተ የቀረቡለትን የመፍትሄ ንድፈ ሃሳቦችን ተቀብሎ ስለ መሬት ለወጣቶቹ ማከፋፈል በተመለከተ የቀረቡትን ግን አልቀበልም አለ። ለዚህ የተቀመጠው መከራከሪያ ሃሳብ ደግሞ ኢህአፓ ውግንናው ለጭቁኑ የአርሶ አደር ክፍል እንደሆነ ድርጅት ከባለርስቶቹ ጋራ መነጋገር/መደራደር ሳይሆን እነሱን በሁሉም መንገድ አስገድዶ ማንበርከክና አስተሳሰቡም እንዲጠፋ ማድረግ የሚል ሆኖ በርስት የያዙት መሬት ካስፈለገ በሃይል ተነጥቀው ለመሬት ፈላጊ ወጣቶች በእኩል መካፈል አለበት በማለት ንድፈ ሃሳቡን ውድቅ አደረገ።

ጓድ ገረይ ይህ የአመራር ውሳኔ በመቃወም ይህ ተግባራዊ እናድርግ ማለት የኢሮብ ህዝብ እንዲከፋፈል በር መክፈት ነው፣ ኢህአፓ በርግጥ ጸረ መስፍናዊና ጸረ መሳፍንት ስርዓት የሆነ ድርጅት ቢሆንም ኢሮብ ውስጥ መሳፍንቶች የሉም፣ በአጼው ስርዓት በተደነገገው የመሬት ስሪት/ህግ መሰረት የተወሰነ መሬት በርስት ይዘው የቆዩ የኢሮብ አባቶች መሬቱን በርስት ብይዙትም በኢሮብ በቆየ ባህል መሰረት ከመሬቱ የተገኘውን ከሌሎች ጋራ ተካፍለው እየበሉ የነበሩ ናቸውም፣ አሁን የመሬት ስሪቱ መቀየሩን፣ አሁን በሃገር ደረጃ ያለው ስሪት/ህግ መሬት ለአራሹ የሚል መሆኑን፣ በሚገባ ካስረዳናቸው በኢሮብ የቆየ በውይይትና በሽምግልና ባህል መሰረት ቀርበን ካነጋገርናቸው እነዚህ ባለ ርስቶች በፈቃደኝነት መሬቱን እንደሚያካፍሉ ምንም ጥርጥር የለኝምና እነዚህ ሰዎች ከመጫን/ከማስገደድ በውይይት በማሳመን ችግሩን ለመፍታት አመራሩ ዕድሉን በድርጅቱ ውስጥ ላለን የኢሮብ ተወላጆች ሊሰጠን ይገባል ብሎ አጥብቆ ተከረከረ። ባጋጣሚ በወቅቱ ገና አዲስ ከከተማ መጥቶበኢንተልጅንስስራ ተመድቦ ሲሰራ የነበረ ጓድ ሓዲሽ በየነ/ማጋቢዳጋ በቦታው ስለነበረ፣ እሱም በጉዳዩ ገብቶበት ጓድ ገረይን በመደገፍ አመራሩን ለሁለት በመሆን ሞገቱ። ጓድ ሓዲሽ ሲጀምር፣ ጓድ ገረይ እንዳለው ኢሮብ ውስጥ እናንተ የምትገምቱት ዓይነት መስፍን/መሳፍንት የሉም። የኢሮብ ህዝብ ያለውን አብሮ ተካፍሎ የሚበላ፣ ከጥንት ጀምሮ የውስጥም ሆነ የውጭ ችግሮችን በውይይት የመፍታት የዳበረ ባህል ያለው፣ በሆነ ምክንያት አንድነቱን ሊያናጋ የሚችል ችግር በውስጡ ቢፈጠር እንኳን ይህን በውይይት ሲፈታ የኖረ፣ ይህን ቀላሉን በርስት መሬት የያዙ ጥቂቶች በቀላሉ በማሳመን መሬቱ ለሁሉም በእኩል እንዲካፈል ለማድረግ ስለምቻል የጓዱ የመፍትሄ ንድፈ ሃሳብ ተቀባይነት ማግኘት አለበት በማለት ተከራከረ። ጓዶቹ በህዝባቸው አንድነት መጠበቅ ላይ አጥብቀው የሚያምኑና ለዚህም መከፈል የሚገባውን መስዋእትነት ለመክፈል የቆረጡ ስለነበሩ፣ አመራሩም በመረጃ የተደገፈው የጓዶቹ ሃሳብ ስለተቀበለ ከሰፊ ውይይትና ክርክር በኋላ አመራሩ የጓዶቹን ሃሳብ ተቀብሎ በኢሮብ መሬት በጓድ ገረይ በቀረበው የመፍትሄ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ኣንዲከፋፈል ተወሰነ፣ ይህ ንድፈ ሃሳብም ከኢሮብ ውጭ በመላው ምስራቃዊ ትግራይ ኢህአፓ መሬት ሲያከፋፍል እንደ ግብአት ተጠቀመበት።

አመራሩ ንድፈ ሃሳቦቹን ከተቀበለ በኋላ የመሬት ማከፋፈል ስራ ከመጀመሩ በፊት ጓድ ገረይ ባለ ረስቶቹን የማነጋገርና የማሳመን ስራ ወዲያውኑ ጀመረ። እኔም ከቦታ ወደ ቦታ እየዞርኩ ህዝቡን መሬት እንደሚከፋፈል በማሳወቅ እንዴት መሬት መከፋፈል እንደሚፈልግ የህዝቡን ሃሳብ ማሰባሰብ ጀመርኩ። ይህ ስራ ከሕዳር- ጥር 1968 በነበረው 3 ወር ጊዜ ውስጥ ተካሄደ። እንደተገመተውም ብዙዎቹ ባለ ርስቶች በቀላሉ ለማግባባት ተቻለ፣ በጣት የሚቆጥሩትን ደግሞ በቆየው የኢሮብ የዳበረ የውይይትና የሽምግልና ባህል መሰረት ማሳመን ተችሎ፣ ከህዝቡ መሰብሰብ የነበረበት ሃሳብም በሚገባ ተሰብስቦ የቆየው የመሬት ስሪት በአዲሱ መሬት ለአራሾች ስሪት መሰረት ለማሻሻል ህዝባዊ ስብሰባ መጥራት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደረሰ።

ከላይ በጭሩ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በኢሮብ በርግጥ በጽሁፍ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም በቃል ደረጃ ሁሉም ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለበት ለሁሉም ችግር አፈታት የተቀመጠ ህግ ነበረ። ለመሬት ማከፋፈሉ በቃል ደረጃ የነበረ ህግ የነበረ ቢሆንም ይህ ህግ ከአዲሱ የመሬት ላአራሹ አዋጅና የኢህአፓ በመሬት ጥያቄ ላይ ከነበረው አቋም ጋራ ሊስማማ በምችል ደረጃ መሻሻል ነበረበት። በነገራችን ላይ ኢህአፓ መሬት ጥያቄ ላይ የነበረው አቋም ለማወቅ ለምትፈልጉ በያትልድ ድረ ገፅ www.yatewlid.com በዴሞክራሲያ እትሞች ስር የጥቅምት 05፤1967ቱን ቁ_12 መመልከት ትችላላችሁ።

የቦካለ፟ማኮ ስብሰባ

 በኢሮብ ከጥንት ጀምሮ መላው ኢሮብን የሚመለከቱ ጉዳዮች/ህጎች ማሻሻል ሆነ አዲስ ህግ ማውጣት ሲያስፈልግ በኢሮብ የቆየ ባህልና አሰራር መሰረት በህዝብ በተወከሉ የህዝብ ተወካዮች አማካይነት ነበር የሚሻሻሉት/የሚወጡት። የቦካለ-ማኮ ስብሰባ መጠራት ዋነኛው ምክንያትም በኢሮብ የቆየውን የመሬት ስሪት/ህግ ከመሬት ላራሹ አዋጅና የኢህአፓ የመሬት ጥያቄ አቋም ጋራ በሚያስማማ መንገድ ለማሻሻል የመላው ኢሮብ ተወካዮች መገኘት ያስፈልግ ስለነበረ ነበር። ለዚህ ስብሰባ ከመላው ኢሮብ በየቀበሌው በነበረው ህዝብ ብዛት መሰረት ከሁሉም ዓይነት የህብረተሰብ ክፍሎች 300 በላይ ተወካዮች ተመርጠው የተሳተፉበት፣ ከሶስቱ ኢሮብ (አድጋዲ-ዓረ፣ ቡክናይቲ-ዓረ፣ ሓሳባላ) ከሁሉም የህ/ሰብ ክፍሎች (በዕድሜ የገፉ ሽማግሌዎ፣ ታዋቂና ተሰሚ የነበሩ ግለሰቦች፣ ባለርስቶቹ፣ መሬት ፈላጊ ወጣቶች በሚገባ የተወከሉበት በትክክል መላው ኢሮብ የሚወክል ስብሰባ ነበር። ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት የመላው ኢሮብ ተወካዮች ስብሰባዎች የሚካሄዱ የነበሩት በዓሊተና/አግለ ሓዳ በሚባል ዛፍ ስር የነበረ ቢሆንም የመሬት ስሪት ለማሻሻል ያኔ የተጠራው ስብሰባ ብዙ ሰው የሚሳተፍበት ስብሰባ እንደሚሆን አስቀድሞ ስለታወቀ ስብሰባው ከዓሊተና ወጣ ብሎ በሚገኝ በቦካለ፟ማኮ(ቦካለ-ማኮ) እንዲደረግ ተወሰነ። ቦካለ-ማኮ ለማታውቁት ከዓሊተና ከተማ በስተሰሜን ወደ 15 ደቂቃ የእግር ጉዞ ርቀት ላይ የሚገኝ ትላልቅ በዛ ያሉ የወይራ ዛፎች የነበረበት የወንዝ ዳርቻ ነው።

 

በክፍል ሶስት፣ የስብሰባው አካሄድ እንዴት ነበር፣ውጤቱስ ምን ሆነ በሚለው ዝርዝሩን ይዤላችሁ እቀርባለሁ፣

እስከዛው በቸር ሰንብቱ!


የነገ ሰው ይበለን! 

በየነ ገብራይ/ደንማርክ

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ

ቁጥር ሦስት

የ1968 ዓ.ም. የቦካለ፟ ማኮ/ዓሊተና ታሪካዊ ስብሰባ አካሄድና ውጤቱ፣


ከበየነ ገብራይ/ደንማርክ ሕዳር 2014 ዓ/ም


የስብሰባው አካሄድ፣

ከሶስት ኢሮብ (ኣድጋዲ-ዓረ፣ ቡክናይቲ-ዓረ፣ ሓሳባላ) ከ300 በላይ ተወካዮች የተገኙበት ታሪካዊው የቦካለ ማኮ ስብሰባ የተካሄደው በየካቲት የመጀመሪያ ሰሙን በ1968 ዓ.ም. ነበር። በኦና ስርዓት ወቅት ህዝባዊ ስብሰባዎች የሚመሩት በህዝብ በተመተረጠው ኦና ነበር። የኦና ስርዓት ከጣሊያን የሁለተኛ ወረራ በኋላ፣ በአፄ ኃ/ስላሴ በሃይል ፈርሶ ወረዳው በቀጥታ ከላይ በሚመደብ አስተዳዳሪ መተዳደር ከጀመረ በኋላ ደግሞ በዛው በመንግስት በሚመደብ አስተዳዳሪ ነበር። ይህ በእንዲህ እያለ ከ1966ቱ አቢዮት በኋላ በኢሮብ ከመንግስት የተመደበ አስተዳዳሪ በቦታው ስላልነበር ስብሰባው በቀጥታ ስብሰባውን በጠራው በኢህአፓ ተወካይ በጓድ ገብረስላሰ ተስፋይ/ገረይ መመራት ወይም ተሰብሳቢው የራሱ መሪ እንዲመርጥ ማድረግ  ያስፈልግ ነበር። ጓድ ገረይ የኢሮብ ህዝብ ከዘመኑ እድገት ጋራ መሄድ የምችል የኦና ስርዓት በኢሮብ መቀጠል አለበት የሚል ፅኑ እምነትና አቋም ስለነበረውና ይህ ደግሞ ከዚህ ስበስባ መጀመር አለበት ብሎ ስላመነና ስለወሰነ ስብሰባውን ራሱ መምራት ትቶ ተሰብሳቢው የራሱ ሊቀመንበር እንዲመርጥ ወሰነ። ስለሆነም በዙሪያው በነበሩ ዛፎች በትንንሽ ቡድኖች ተበታትኖ ተቀምጦ የነበረው ተሰብሳቢ ወደ አንድ አክባቢ እንዲሰበሰብ ጠይቆ ማኽል ላይ ቁሞ ለተሰብሳቢው ወደ ሁሉ አቅጣጫ በመዞር ሰላምታ ሰጥቶ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ካስተላለፈ በኋላ ከኦና ስርዓት እስከ የአፄ ኃ/ስላሴ ስርዓት የነበረው የስብሰባ አካሄድ ምን ይመስል እንደነበረ ባጭሩ ጠቅሶ፣ የኦና ስርዓቱ ባህላችን መልሶ መገንባትና መዳበር እንዳለበት በመጥቀስ ለዕለቱ ስብሰባ ተሰብሳቢው የራሱ ሊቀመንበር እንዲመርጥ ጠየቀ። 

በቆየው የኢሮብ ባህል መሰረት የዕድሜ ባለፀጋ፣ አዋቂና ልምድ ያለው ሰው ከሁሉም አስቀድሞ መናገር/ሃሳብ መስጠት የተለመደ አካሄድ ስለነበረ ተሰብሳቢው በዕለቱ በስብሰባው ተገኝተው በአንድ አካባቢ በተሻለ የዛፍ ጥላ ስር ተቀምጠው ወደነበሩት እነ አቤቶ ዓዶዑማር ሓሊቦ ወልደገርጊስ (ዓዶዑማር ጎዒስ) ዓሊተና፣ ኦና ወልደገርጊስ ዎልዱ/ዓይጋ፣ ልጅ ንጉሰ ወልደጊዮርጊስ/ማጋዑማ፣ ልጅ አብራሃ ሓጎስ /አድጋዲ ዓረ፣ አቤቶ ተስፋይ ወልደሓንስ /ኮኮሖ/ሳብዓታ፣ ልጅ ብስራት ገብራይ ዒንዳይ/ሳራይቲ አራሕ. . .ወዘተ. አባቶች በምልክት አመላክቶ ከነሱ ውስጥ አንዳቸው እንዲናገሩ ተጠቆመ። በወቅቱ በቦታው ከነበሩ የዕድሜና የእውቀት ባለፀጎች፣ በዕድሜ፣ በእውቀትና ልምድም የላቁ የነበሩ አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ስለነበሩ አባቶችም እሳቸው እንዲናገሩ/ሃሳብ እንዲሰጡ ጠየቋዋቸው። አቤቶ ዓዶዑማር እርጅና በጣም ተጫጭኖአቸው፣ ዓይናቸው ታውረው ስለነበረ ቆመው መናገር ስላልቻሉ በተቀመጡበት ሆነው መናገር ጀመሩ። 

አቤቶ ዓዶዑማር ወደ ዋናው ነጥብ ከመግባታቸው በፊት፣ በመጀመሪያ ከብዙ ዓመታት በኋላ እንዲህ ዓይነት የሶስቱ ኢሮብ በርካታ ተወካዮች የተገኙበት ስብሰባ ላይ ለመካፈል ለዚች ዕለት ላደረሰኝ ቸሩ መድሃኔዓለም አመስግናለሁ፣ በመቀጠል በዚህ መንገድ እንደ ድሮአችን (የኦና ስርዓት ዘመን) ተሰብስበን በጉዳያችን ለመምከር፣ ይህን ስብሰባ ላዘጋጀልን ለልጃችን መምህር ገረይ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ ካሉ በኋላ፣ አዎ መምህር ገረይ እንዳስቀመጠው አሁን የመረጥነው ኦና የለንም። ነገር ግን በቅርብ ጊዜ የራስችን የመረጥነው ኦና እንደሚኖረን ተስፋ አደርጋለሁ። እስከዛው በርግጥ መምህር ገረይን በባህላችን መሰረት ኦና ብለን ባንመርጠውም አንድ ኦና የሚሰራው የነበረ ስራ እየሰራ ስለሆነ ይህ ስብሰባንም ሆነ ለወደፊት የሚደረጉ ህዝባዊ ስብሰባዎች እሱ ቢመራልን፣ የራሳችን ኦና እስክንመርጥ ድረስም እኛን/ኢሮብን ወክሎ ከሚመለከታቸው ጋራ እንዲገናኝልንና እንዲመራን መስማማት አለብን በማለት ሃሳብ አቀረቡ።

 

የስብሰባው አመራርና ተሳትፎ፣ 

የኢሮብ ህዝብ በስብሰባ ላይ አንድ ተናጋሪ ሲናገር ልብ ብሎ ሊያደምጠው ከፈለገ ሁሉም ነገር ትቶ ሙሉ ቱክረቱን ተናጋሪው ላይ አድርጎ ያደምጣል። ተናጋሪው የሚናገረው ካልጣመው ግን ጠጠሮች በእጁ አስባስቦ ከጠጠሮቹ ጋራ ይጫወታል ወይም በትንንሽ ድንጋዮች መንደቅ ይነድቃል። በመጨረሻም ስብሰባው ካልተመቸው ተቃውሞን ለመግለፅ ጠጠሮቹን ይበትናል፣ ወይም የገነባውን መንደቅ ነገር ያፈርሳል። ይህ የኢሮብ ህዝብ የስብሰባ ባህል ጓድ ገረይ ከስብሰባው በፊት ነግሮኝ በዕለቱም የተሳታፊዎች ሁኔታ በደንብ እንድከታተል ነግሮኝ ስለነበረ፣ እሱም አቤቶ ዓዶዑማርም ሲናገሩ ልብ ብዬ ወደ ሁሉም አቅጣጫ እየተመለከትኩ እከታተል ነበር። ገና ጓድ ገረይ በማኸል ቆሞ መናገር ስጀምር ሆነ አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ሃሳብ ሲሰጡ በነበረት ጊዜ ዙሪያውን ተሰብሳቢውን ስቃኝ አንድም ሰው ከጠጠሮቹ ጋራ የሚጫወት ወይም የሚነድቅ አልነበረም። ሁሉም ሙሉ ቱክረቱን ወደ ተናጋሪዎቹ አድርጎ በፅሞና ያዳምጥ ነበር። ሌላ ጓድ ገረይ ከስብሰባው ዕለት በፊት የኢሮብ ህዝብ በስብሰባ ተሳትፎን በተመለከተ የነገረኝ ኢሮቦች በራሳቸው ስብሰባ አስቀድመው የዕድሜ ባለፀጎችና አዋቂዎች አስቀድመው እንዲናገሩ እንደሚያደርጉ፣ ብዙዉን ጊዜ እነዚህ አዋቂዎችም የህዝቡን ፍላጎት በሚገባ ወክለው ሃሳብ/ውሳኔ ስለሚያስቀምጡ ስብሰባ ባጭሩ ውሱን አባቶች በሰጡት የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ስምምነት እንደሚጠናቀቅ፣ ይህ ካልሆነ ግን የኢሮብ ህዝብ የማያምንበት ነገር በቀላሉ የማይቀበል ህዝብ ስለሆነ ስብሰባው ሊራዘም እንደምችልና ባንድ ቀን ሊያልቅ የማይችልበት ዕድል ሊጋጥመን እንደምችል አስቀድሞ ነገሮኝ ስለነበረ ይህም በቅርበት እከታተል ነበር። ስለሆነም አቤቶ ዓዶዑማር ስብሰባውን ጓድ ገረይ ይምራው ብለው ምክንያታቸውን ዘርዝረው የሰጡት ሃሳብ ተሰብሳቢው በየአከባቢው በጥቅሻም በመነጋገርም ትንሽ ካብላላ በኋላ በአንድ ድምፅ “ኤድ፟ኦሮብና” ሲተረጎም፣ በሃሳብዎ ተስማምተናል ብሎ ማፅደቁ ጓድ ገረይ አስቀድሞ የነገረኝን የኢሮቦች የስብሰባ አካሄድ ባህል አረጋግጦልኝ በጣም ተደሰትኩ፣ የኢሮብ አባቶች አርአያነትና የወጣቱ ለነሱ የነበረው ክብርና አርአያነታቸው መከተልን አደነቅኩ። በዚህ የተሰብሳቢው  በአንድ ድምፅ ኤድ፟ኦሮብና ውሳኔ መሰረትም ጓድ ገረይ ውሳኔውን ተቀብሎ ስብስባውን መምራት ቀጠለ።


የዕለቱ አጀንዳና ለአዲሱ የመሬት ስሪት/ህግ በአቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ የቀረቡ ነጥቦች፣   

የዕለቱ ብቸኛ አጀንዳ የቆየውን የመሬት ስሪት (ርስትና ሰሐና ስሪት) በመሬት ለአራሹ አዋጅ መሰረት፣ በመላው ኢሮብ ወጥ በሆነ መንገድ መሬት እንዴት ይከፋፈል ለሚለው የነበረውን ስሪት የሚተካ አዲስ ስሪት ማውጣት ስለሆነ በአዲሱ ስሪት መካተት ያለባቸው ነጥቦች ምን መሆን አለባቸው በሚለው እያተኮራችሁ ሃሳብ እንድትሰጡ መድረኩ ለውውይት ክፍት ነው በማለት ጓድ ገረይ መድረኩን ከፈተ። ያኔ በነበረው የኢሮብ ባህል ከዕድሜ ባለፀጋ፣ አዋቂ በፊት መናገር/ሃሳብ መስጠት እንደ ነውር ይቆጠር ስለነበረ ወጣቶቹ በሙሉ አሁንም ወደ ትልልቆቹ ቀድመው መንደርደሪያ ሃሳብ እንዲሰጡ ሃሳብ አቀረቡ። በዚህ መሰረትም ኦና ወልደገርጊስ/ዓይጋ ቆመው፣ በአጠቃላይ ኢሮብ የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሁላችን በላቀ ደረጃ ከወጣትነት ዕድሜው እስከ ዛሬ ድረስ እየሰራ ያለ፣ ዛሬ እዚህ ከተገኘነው በዕድሜ፣ በእውቀትና ልምድ የሚበልጥ ስለሆነ፣ ይህ ዛሬ የተሰበሰብንለት ጉዳይ (በርስት ተይዞ ያለው መሬት ጉዳይ) ርስት ቀርቶ መሬት ለሁሉም እኩል እንዲከፋፈል ሲወተውት የነበረ ስለሆነ፣ አሁንም አቤቶ ዓዶዑማር አዲሱ የመሬት ስሪት ማካታተ ያለባቸው ነጥቦች በተመለከተ መንደርደሪያ ቢሰጠንና በሱ መንደርደሪያ መሰረት ውይይቱ ቢቀጥል በማለት ሃሳብ አቀረቡ። ተሰብሳቢውም እንደ ቅድሙ ኤድ፟ኦሮብና (እንስማማለን) በማለት በአንድ ድምፅ በሃሳቡ መስማማቱን አረጋገጠ።

በተሰብሳቢው ውሳኔ መሰረት ጓድ ገረይ ኦና ወልደገርጊስ ያቀረቡት ንድፈ ሃሳብ/Proposal አድንቆና አመስግኖ አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ሃሳብ እንዲሰጡ ጋበዘ። አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ከ1950ዎቹ በፊት የነበረው የኢሮብ ህዝብ ብዛት፣ የነበረው የመሬቱ በደን መሸፈን፣ ከዛ በፊት የነበረው የኢሮብ ህዝብ የኢኮኖሚ መሰረት በዋናነት የእንስሳ ርቢ መኖሩን. . .  ጠቅሰው፣ ከ1960ዎች በኋላ ግን ሁኔታው በጣም መቀየሩ፣ በየቀበሌው ብዙ አዲስ ነዋሪ መጨመሩ፣ ዋና የኢኮኖሚ ምንጭነት ከእንስሳ ሪብነት ወደ እርሻ እየተቀየረ መምጣቱ፣ የሚታረስ ያለው አንስተኛ የእርሻ መሬት በጥቂቶች በርስት ስለተያዘ አዲሶቹ የሚታረስ መሬት ፈላጊ ወጣቶች በየተራራውና ጥጋጥጉ ያለውን ጫካ እየመነጠሩ ለእርሻ እያዋሉት መሆናቸውና የዚህ ውጤት ነገ ምን ሊሆን እንደምችል እየታያቸው እንዳልሆነ . . . በመዘርዘር ለዚህ ለወደፊቱ በስፋት በህዝብም በመንግስትም ደረጃ ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ለጊዜው የጫካ ምንጠራውን ለመቀነስ እንዲረዳ በርስት የተያዘው የእርሻ መሬት ለሁሉም በእኩል መከፋፈል እንዳለበት በአፅንዖት ገለፁ። ሌላውም በኢሮብ አሁን እየተደረገ ያለው የደን ብርሰት እንዲህ ከቀጠለ ባጭር ጊዜ ውስጥ የኢሮብ መሬት እርቃኑን ቀርቶ ምድረበዳ ወደመሆን ሊቀየር እንደምችል በግልፅ ቋንቋ አስቀምጠው እንደ መፍትሄም፣  ዋናው መፍትሄ የሚመጣው ህዝቡን ከሚያስተዳድረው መንግስት ቢሆንም ያ እስከሚገኝ በኛ ደረጃም በሰዓቱ መውሰድ ያለብን እርምጃ መውሰድ አለብን አሉ። አሁን መውሰድ ካለብን እርምጃዎች ዋነኞቹ ደግሞ ለእርሻ መሬት ተብሎ እየወደመ ያለውን ደን ባስቸኳይ ማስቆም፣ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ደግሞ ወጣቶቻችን የሚጠይቁት የእርሻ መሬት ጥያቄ ለመመለስ እስካሁ በርስት የተያዘው መሬት ለሁሉም እኩል እንዲከፋፈል ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ የቆየውን የመሬት ስሪት የሚተካ አዲስ ስሪት አውጥተን በስሪቱ መሰረት መሬት ለሁሉም እንዲከፋፈል ማድረግ ነው። በኔ እምነትና ፍላጎትም አዲሱ የመሬት ስሪታችን ቀጥለው የተቀመጡ ነጥቦች ማካተት አለበት በማለት ወደ ነጥቦቹ አንድ በአንድ መዘርዘር ገቡ።

አቤቶ ዓዶዑማር የመሬት ስሪት ነጥቦቹን ሲያቀርቡ ልክ እንደ አንድ ነጥቦቹን በፅሁፍ ያዘጋጀ አቅራቢ የፃፈውን እንደሚያቅርብ ዓይነት ሆኖ በቃላቸው ነበር ያቀረቡት፣ የአቀራረባቸው ቀደምተከተልና ላዛ እጅግ የሚደነቅና የአድማጭ ጆሮና ልብ ሳቢ ነበር። በመሆኑም ተሰብሳቢዉ ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው በፅሞና አዳኣምጦ እርካታውና በነጥቦቹ ላይ የነበረው ሙሉ ስምምነት በፊቱ ይነበብ ነበር።  

 

ለውሳኔ በቀረቡ ነጥቦች ላይ የቀረቡ ሃሳቦች/አስተያየቶችና ውሳኔ፣  

አቤቶ ዓዶዑማር የአዲሱ የመሬት ስሪት/ህግን በተመለከተ ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች ካስቀመጡ በኋላ ስብሰባውን ሲመራ የነበረው ጓድ ገረይ በነጥቦቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥቶ፣ ጥያቄ፣ ሃሳብ/አስተያየት፣ ተጨማሪ፣ ተቃውሞ ካለ በማለት መድረኩን ለተሰብሳቢው ከፈተ። እንደተለመደው ተሰብሳቢው የመጅመሪያ ሃሳብ ሰጭ ከትልልቆቹ እንዲቀድም “ናባማራኮ ጋሮክ ኡኩማ” (ሲተረጎም ከትልልቆቹ አንዳችሁ ቅደሙ) በማለት ሃሳብ አቀረበ። ልጅ ብስራት ገብራይ (ከጣሊያን 2ኛ ወረራ በፊት በቡክናይቲ ዓረ የተመረጡ የመጨረሻ ኦና ገብራይ ዕንዳይ ልጅ) ተነስተው ስለ አቤቶ ዓዶዑማር  ማንነት፣ ለኢሮብ ህዝብ አንድነትና ህልውና መቀጠል ያበረከቱትን አስተዋፅዖ፣ በኢሮብ በርስት የተያዘው መሬት እንደ ሰሓናው ለሁሉም እኩል መከፋፈል አለበት ብለው ከድሮ ጀምሮ ሲናገሩና ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውን፣ የኢሮብ ህዝብ ህልውና የኢኮኖሚ መሰረት መሆን ያለበት በተራሮች ላይ የበቀለውን ጫካ በመመንጠር የእርሻ መሬት ለማድረግ መሞከር ሳይሆን የእንስሳ ርቢና በዋናነት የተማረ ትውልድ መፍጠር ላይ ያተኮረ መሆን አለበት በምሳሌ ደረጃ  “ኢሮ ሚህሮድ ላኣ፟ ጊርቦድ” (ሲተረጎም፤ ልጆች ወደ ትምህርት ከብትን ወደ አቁማዳ/ከብት ይሸጥ ለማለት) ይሉ እንደነበረ፣ . . . በመዘርዘር፣ እሳቸው ያስቀመጡዋቸው ነጥቦች እንደ ህጋችን ተቀብለን እናፅድቃቸው፣ ይህ ስብሰባም አሁን መሬት እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ያሉ ልጆቻችን ለዘንደሮው (1968ቱ) የአዝመራ ወቅት ከራሳቸው መሬት የመጀመሪያ ምርት እንዲያገኙ መሬቱ መጋቢት ከመጠናቀቁ በፊት በአዲሱ ስሪት መሰረት መከፋፈል እንዳለበት እንወስን በማለት ሃሳባቸውን አጠናቀቁ።

በመቀጠል ልጅ አብራሃ ከአድጋዲ ዓረ፣ የነበረው የርስት ስርዓት እንዳበቃ መንግስት (ደርግ) አውጇል፣ አሁን ኢሮብን እያስተዳደረ ያለው ኢህአፓም መሬት ለአራሹ እንደሚሉና የርስት ስርዓት/የመሳፍንት ስርዓት መቅረት ብሎ እንደሚያምና ለዚህም እንደሚታገል ልጃችን መምህር ገረይ በግልፅ ቋንቋ ወደዚህ ስብሰባ ከመምጣታችን በፊት በማይፂዓ/አድጋዲ ዓረ ባደረግነው ስብሰባ በግልፅ ነግሮናል። አሁን መሬት ከሚፈልጉ ልጆቻችን በፍቅር አንድነታችን ተጠብቆ መኖር ከፈለግን መሬቱን በርስት የያዝን ወላጆች መሬቱን ከልጆቻችን ጋራ እኩል ተካፍለን መኖር የግድ ስለሆነ በአዲሱ ስሪት መሰረት መሬቱ ይከፋፈል የሚለው የጋራ ውሳኔያችን ይሁን። ስለሆነም ወንድሜ ልጅ ብስራት ያቀረቡት ሃሳብ ተቀብለን የዛሬው ስብሰባችን እንጨርስ በማለት የልጅ ብስራት ሃሳብ ደገፉ። ከልጅ አብራሃ/አድጋዲ ዓረ በመቀጠል ኦና ወልደገርጊስ/ዓይጋ በአፄ ኃ/ስላሴ ስርዓት ጊዜ ኢሮብ ወረዳ እንዲያስተዳድሩ የተመደቡት ባሻይ ቢሻኡ በቦታው ሆነው ሊያስተዳድሩን ስላልቻሉ የአስተዳዳሪ ችግር ሲገጥመን ችግሩን የተረዱት ሰለቃ ወልዱ ገብራይ መጥተው ያስተዳደር ችግራችንን ፈተው አንድነታችን አስጠብቀው እስከ ዕለተ ሞታቸው አስተዳደሩን፣ ከሳቸው ሞት በኋላ የአስተዳዳሪ አለመኖር ችግር ቀጥሎ ወደ አንድነታችን ንፋስ መግባት ጀምሮ ነበር። አሁን ኢህአፓ በአከባቢያችን ከመጣ በኋላ ልክ እንደ ሰለቃ ወልዱ ልጃችን መምህር ገረይ መጥቶ የኸው በሱ አስተዳዳሪነት ለዚህ ስብሰባ ደርሰናል። ይህ ስብሰባ የድሮ ኦና ስርዓት ጊዜ “ሓዳሎብቲ” ትርጉም (አጠቃላይ ስብሰባ) ዓይነት ስብሰባ ነው። ዛሬ ራሳችን የመረጥነው ኦና ባይሆንም የመረጥነው ኦና ማሟላት የሚገባውን አካሄድና አሰራር አሟልቶ በልጃችን በመምህር ገርይ የተጠራ ሓዳሎብቲ (አጠቃላይ ስብሰባ) ስለሆነ የቆየውን የርስትና ሰሐና የመሬት ስሪት ወደ አዲሱ በአቤቶ ዓዶዑማር ያስቀመጡት አዲስ ስሪት የምንቀይርበት፣ እንደ ኢሮብ መወሰን ያለብን ጉዳዮች ለወደፊትም በዚህ መልክ ማድረግ እንዳለብን የምንወስንበት ውሳኝና ታሪካዊ ስብሰባ ነው። አዲሱ የመሬት ስሪት ምን መምሰል እንዳለበት አቤቶ ዓዶዑማር በግልፅና በዝርዝር አስቀምጠውልናልና ልክ ወንድሞቼ ልጅ ብስራትና ልጅ አብራሃ እንዳሉት ስሪቱን እንዳለ ተቀብለን፣ መሬቱ ከመጋቢት መጨረሻ በፊት በአዲሱ ስሪት መሰረት በመላው ኢሮብ መከፋፈል እንዳለበት ወስነን ስብሰባችን እንጨርስ በማለት ሃሳብ አቀረቡ። 

የቦካለ ማኮ የ1968 ስብሰባ እዉነተኛ የኢሮብ ህዝብ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣው የዕድሜ ባለፀጎችና አዋቂዎች በወጣቶቹ መከበር፣ መደመጠ፣ አርአያቸውን መከተል በትክክል የታዘብኩበት፣ የዕድሜ ባለፀጎችም ለወጣቶቹ የነበራቸው አሳቢነትና በንግግራቸው ሆነ በተግባራቸው የነሱን አርአያ እንዲከተሉ የማድረግ ችሎታና ዘዴ በተግባር ያየሁበት፣ የኢሮብ ህዝብ ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም በኢሮባዊ ማንነቱ የሚኮራና ፈፅሞ የማይደራደር መሆኑ በግልፅ የተገነዘብኩበት፣ ያ ጓድ ገረይ ሲነግረኝ የነበረ የኢሮብ ህዝብ ማንነት በትክክል በተግባር ያየሁበት እስከ ዛሬ ድረስ የቦታውና የተሰብሳቢው ስዕል በአእምሮዬ ተቀርፅ ያለ ስብሰባ ነበር። ጓድ ገረይ አስቀድሞ እንደነገረኝ የኢሮብ ህዝብ የልቡን የሚናግርለት ሰው ካየ የግድ እኔም ልናገር የሚል ባህል እንደሌለው በዕለቱ ከ300 ሰው በላይ በተሳተፈበት ስብሰባ ተናጋሪዎች ከ5 ሰዎች የማይበልጡ የዕድሜና የእውቀት ባለፀጎች ብቻ ነበሩ። በዚህ መሰረት አቤቶ ዓዶዑማር ያቀረቡት አዲሱ የመሬት ስሪት በሶስቱ ጉምቱ ኢሮቦች ንግግር ተደግፎ፣ 300 በላይ ተሳታፊ ሳይናገር “ኤድ፟፟ ኦሮብና” (ሙሉ በሙሉ በሃሳቡ እንስማማለን) በማለት የጥቂት አዋቂ አባቶች ሃሳብ በመቀበል አዲሱ የመሬት ስሪቱ ፀድቆ፣ በስሪቱ መሰረት መሬቱ ከ1968 የአዝመራ ወቅት በፊት እንዲከፋፈል ተወስኖ በግምት ከቀኑ ወደ 9 ሰዓት አከባቢ ስብሰባው ተጠናቀቀ።

ለዕለቱ የተጠራው ስብሰባ በዚህ መልክ ቢያልቅም ወደ ስብሰባው ማጠቃለያ አከባቢ ወደ ቦታው የመጡ የተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት) ተወካዮች ለተሰብሳቢው ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው፣ ከተወሰነ ክርክር በኋላ በጓድ ገረይ ተሰብሳቢው ላጭር ደቂቃዎች እንዲያደምጣቸው በጠየቀው መሰረት ተሰብሳቢው ተስማምቶ፣ ለመሄድ ተነስቶ የነበረውም መልሶ ተቀምጦ ከተወካዩቹ አንዱ ለተሰብሳቢው በትግርኛ ያደረገ አጭር ገለፃና ለገለፃው ተሰብሳቢው የሰጠው ምላሽ ምን ይመስል እንደነበረ በዝርዝ በቁጥር አራት ይዤላችሁ እቀርባለሁ። 

እስከዛር በቸር ሰንብቱ፣ 


የነገ ሰው ይበለን! በየነ ገብራይ/ደንማርክ

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ

ቁጥር አራት

በ1968ቱ የቦካለማኮ/ዓሊተና ስብሰባ የተሓህት ተወካይ ገለጻና የኢሮብ ተሰብሳቢው መልስ


ከበየነ ገብራይ/ደንማርክ                                                 ሕዳር 2014 ዓ/ም

በ1968ቱ የቦካለማኮ/ዓሊተና ስብሰባ የተሓህት ተወካይ ገለጻና የኢሮብ ተሰብሳቢው መልስ፣

 

በቀጥታ ወደ የህወሓት ተወካይ ድርጅቱን ለማስተዋወቅ ያደረገው ገለጻና ለገለጻው ተስብሳቢው የሰጠው መልስ ከመግባቴ በፊት፣ በወቅቱ ተሓህት በኢሮብ ወረዳ የነበረው ይዘት፣ በወቅቱ የነበረው የኢሮብ ህዝብ  ስነልቦና ምን ይመስል እንደነበረ ባጭሩ መጥቀስ ሃቁን ለማወቅ ለሚፈልጉ ተመራማሪዎች እንደ መነሻ ሊሆን ስለምችል፣ እንዲሁም የአንድ ወገን (የህወሓት) ፕሮፓጋናዳና የነሱን ትርክት ብቻ ከመስማት ውጭ ሌላ አማራጭ ለሌላቸው አንባቢዎቼም በሌላ በኩል ያለውንም አይተው የራሳቸው ፍርድ ለመስጠት ስለሚጠቅም ባጭሩ ጠቅሼ ወደ ዋናው ርእሴ እገባለሁ።

ሀ) በወቅቱ ተሓህት በኢሮብ ወረዳ የነበረው ይዞታ፣

ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት)፤ ከ1972 በኋላ ስሙን ወደ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የቀየረው፤ ትጥቅ ትግሉን የጀመረው በ1967 ዓ.ም. በየካቲት ወር በምዕራብ ትግራይ ሽረ አውራጃ ደደቢት በረሃ ላይ ሲሆን፤ ወደ ምስራቅ ትግራይ (ዓጋመ አውራጃ) የመጣው በ1968 ሕዳር (ከ9 ወር በኋላ) ነበር። ተሓህት ወደ ዓጋመ አውራጃ እንደመጣ ዋና ቤዙን ያደረገው በሱቡሓ ሳዕሲዕ ወረዳ ልዩ ስሙ ማርዋ በሚባል አከባቢ ነበር። ይህ በእንዲህ እያለ ልክ ወደ ዓጋመ እንደመጣ በኢሮብ ወረዳም ልዩ ስሙ ዋርዓትለ በሚባል ቀበሌ “ገሪማት ኢንዳዓርቶ” (የገሪማ ዋርካ) ላይ ሰፈሩን በማድረግ ለአንድ አነስተኛ ቡድን የአጭር ጊዜ ወታደራዊ ስልጠና ሰጥቷል። ከዚህ አጭር በዋርዓትለ ወታደራዊ ስልጠና (ታዕሊም) መስጠት በኋላ ግን የኢሮብ ወረዳን ሙሉ በሙሉ ለቆ በመውጣት እንቅስቃሴውንና የማደራጀት ስራውን ያደርግ የነበረው ትግርኛ ተናጋሪ በሚኖርበት አከባቢ ላይ ብቻ ነበር።

ስለሆነም ከ1968 ሕዳር - 1970 ግንቦት በነበረው ጊዜ ተሓህት በኢሮብ ወረዳ በዋርዓትለ ቀበሌ ላጭር ጊዜ ከሰጠው ስልጠናና በዓይጋ (በዛጋብላ በረሃ ጫፍ) የነበረ አንድ ለረጅም ጊዜ የተለቀቀ ቤት ውስጥ በክፍለ ህክምና ስም ከነበሩት ጥቂት አባላት ውጭ በኢሮብ ወረዳ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሆነ ድርጅታዊ ስራ አልነበረውም። ለምን የሚል ጥያቄ መነሳቱ ስለማይቀር ምክንያቶቹም፣


ለ) የያኔ የኢሮብ ህዝብ ይዘትና ስነልቦና፣ 

በቁጥር ሶስት ዕትም በውሱን እንደተጠቀሰው፤ ያኔ የነበረው የኢሮብ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣው አንድነቱና ኢሮባዊ ማንነቱ ዋና ምሶሶውች የሆኑ እሴቶች ነበሩት፡፡ ለምሳሌ ያህል፤ የራሱን ሚስጥር በውስጡ መጠበቅ፣ አንድን የኢሮብ ተወላጅ የፈለገ ጥፋት ቢያጠፋ ራሱ መቅጣት እንጂ ለውጭ አሳልፎ አለመስጠት፣ ማንኛውም በውስጡ የሚነሱ ችግሮች/ልዩነቶች  በውይይት መፍታት፣ በውይይት ሊፈቱ ለማይችሉ ቅራኔዎች የሚፈታበት በጣም የዳበረ የሽምግልና ባህል የነበረው፣ ታናሽ ታላቁን የማክበር፣ ታላቅም ለታናሹ አርአያ የመሆን፣ . . . ወዘተ. ባህልና ስነልቦና እንደተጠበቀ ነበር። ያኔ የነበረው የኢሮብ ህዝብ በ% ለማስቀመጥ ባልችልም በጣም ውሱን ከትግርኛ ተናጋሪ አጎራባች በሆኑ አከባቢ ከሚኖረው ውጭ አብዝሃ የኢሮብ ህዝብ ትግርኛ መናገር ቀርቶ የማይሰማ ሳሆ ተናጋሪ ህዝብ ነበር። በኢኮኖሚ ደረጃም ከእርሻው በተጨማሪ ሲገለገልበት የነበረው የእንስሳ ርቢ እያሽቆለቆለ የነበረ ቢሆንም፤ ብዙዎች ደህና እንደ ፍየል፣ ከብት፣ የንብ ርቢ ተጠቃሚዎች ስለነበሩ፤ ምንም ስደት የሚባል ነገር የማያውቅ፣ በጣም ውሱን በጣት የሚቆጠሩት በትምህርትና በስራ ምክንያት አከባቢውን ለቀው ከሚኖሩት ውጭ የተቀረው ከሌሎች ጎረቤቶቹ ብዙ ንኪኪና ግኑኝነት ሳይኖረው በወረዳው ተወስኖ የሚኖር ውሁድ ህዝብ ነበር።   


ሐ) የተሓህት ተወካይ ገለጻ፣ ለገለጻው የአቤቶ ዓዶዑማር መልስና የኢሮብ ተሰብሳቢው ግብረመልስ፣


መንደርደሪያ፣

በቁጥር ሶስት ዕትም እንደተገለጸው የቦካለማኮ ስብሰባ የተጠራበት ብቸኛ ምክንያት/አጀንዳ የቆየውን የመሬት ስሪት/ህግ በመሬት ለአራሹ አዋጅ መሰረት ለማሻሻል ነበር። ከዚህ አጀንዳ ውጭ ሌላ አጀንዳ የያዙ ሰዎች ወደ ስብሰባው ይመጣሉ የሚል ግምት ስብሰባን ባዘጋጁ የኢህአፓ ተወካዮዎች (በጓድ ገረይና እኔ) በኩልም በተሰብሳቢውም በኩል አልነበረም። ስለሆነም ከእኩለ ቀን በኋላ በግምት ወደ ሰባት ሰዓት አከባቢ ላይ ሁለት የተሓህት ታጋዮች ወደ ስብሰባው ሲመጡ ማየት ለሁሉም እንግዳ ነገር ነበር። በመሆኑም ሁለቱ ወደ ስብሰባው ቦታ ሲጠጉ የተሰብሳቢው ዓይንና ልብ ወደነሱ ሆነ። ይህ መሆኑ በሚገባ የተመለከቱት በስዓቱ ቆመው በመናገር ላይ የነበሩት ልጅ ብስራት ገብራይ፤ ንግግራቸውን አቁመው እሳቸውም የሁለቱን እንቅስቃሴ መከታተል ጀመሩ። የተሰብሳቢው ቀልብ በሙሉ ወደነሱ መሆኑን የተመለከቱ የተሓህት ታጋዮችም ዝም ብለው ወደ ስብሰባው መቀላቀልን ትተው ተጠግተው ቆሙ። ይህን በመታዘባቸው ልጅ ብስራት ገብራይ “ታይ የመተ ገዳክ ዲፈያ አከያ” (ለመጡ እንግዶች ተቀመጡ በሉዋቸው) አሉና ጓድ ገረይ የሳቸውን ሃሳብ ተቀብሎ የዕድሜ ባለጸጋ አባቶች በተቀመጡበት በኩል እንዲቀመጡ ቦታ ሰጥቶኣቸው እነሱም ተቀምጠው ስብሰባው በልጅ ብስራት ንግግር ቀጠለ።

የቦካለማኮ ስብሰባ ለማዘጋጀት ወደ ሶስት ወር የፈጀ ዝግጅትና ብዙ ጥሪዎችም በተለያየ ጊዜ ይተላለፉ ስለነበረ፤ የተሓህት አባላትም ስለ ስብሰባው የመስማት ዕድል ክፍተኛ መሆኑ ምንም የማያጠራጠር ቢሆንም ለኛ ሳያሳውቁ ለምን በድንገት እኛ በጠራነው ስብሰባ ለመገኘት ፈለጉ የሚል ጥያቄ ግን ለሁላችን (ለኔ፣ ለጓድ ገረይ፣ ለተሰብሳቢውም) እንቆቁልሽ ስለነበረ ራሴን ጠይቄ መልስ ማፈላለግ ጀመርኩ። ወደያውኑ የመጡልኝ መልሶችም፣ አንደኛ በኛ በኩል የምናሳየው ሪአክሽንና (reaction) የምንወስደውን እርምጃ ለማየት/ለመለካት ሊሆን ይችላል፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኢሮብ ህዝብ በዚህ ዓይነት የተሟላ የሶስቱ ኢሮብ (አድጋዲ-ዓረ፣ ቡክናይቲ-ዓረ፣ ሓሳባላ) ውክልና ያለው ስብሰባ ራሳቸው መጥራት ስለማይችሉ ዕድሉን ተጠቅመው ከኢሮብ ህዝብ ለመተዋወቅና የህዝቡን ስሜት ለማወቅ/ለመለካት ይሆናል የሚሉ ነበር። ከስብሰባው በኋላ ለጓድ ገረይ ይህን የኔ ግምቶች አንስቼለት እሱም ተመሳሳይ ግምት እንደነበረው፣ እስከመጡና ልጅ ብስራት እንዲቀመጡ እስከጋበዙዋቸውና ተስብሳቢውም በሃሳቡ እስከተስማማ ድረስ ህዝቡ እንዲወስን መተዉ ነው የሚሻለው በሚል ነው እንዲቀመጡ ያደረግኩት ብሎ ነገረኝ።   

የዕለቱ ብቸኛ አጀንዳ የነበረው (የመሬት ስሪት ማሻሻል) ጉዳይ በግምት ወደ 9 ሰዓት አከባቢ ላይ እንዳለቀ ጓድ ገረይ የዕለቱ ስብሰባ መደምደሚያ ንግግር አደረግ። የመጡለት ጉዳይ ማለቁን ካወቁ ተሰብሳቢዎች የተወስኑትም ለመሄድ ተነሳሱ፡፡ ይህን ጊዜ ከተሓህት ታጋዮች አንዱ ከተቀመጠበት ተንስቶ በትግርኛ ለአጭር ጊዜ የመጣንበት ጉዳይ ለመግለጽ እባካችሁ አንዴ አድምጡን ብሎ ጠየቀ። ትግርኛ ይሰሙ ከነበሩት አንዳንዶቹ አሁን መሽቶብናልና ከፈለጋችሁ የራሳችሁ ስብሰባ ጥሩና ሌላ ጊዜ አነጋግሩን ብሎዋቸው ስሉ፤ ተቀምጠው የነበሩ ቀሪ ተሰብሳቢዎችም ለመሄድ መነሳት ጀመሩ። የህወሓት ተወካይ ለመሄድ የተነሳውን ተሰብሳቢ በራሱ ለማስቆም የምችልበት ዕድል እንደሌለው ሲያውቅ ለጓድ ገረይ ተሰባሳቢውን አንዴ እንዲያደምጠን አግባባልን ብሎ ጠየቀው። ጓድ ገረይም ለተናጋሪው እየመሸ ስለሆነ ንግግሩን እንዲያሳጥር ነግሮት፣ ለተስብሳቢው በሳሆ አንዴ አድምጡኝ ለሚል እንግዳ ዝም ብሎ ጥሎ መሄድ ባህላችን ስላልሆነ፣ ለመሄድ የጀመራችሁም የቆማችሁም አንዴ ቁጭ በሉና ላጭር ደቂቃ አድምጡት ብሎ ተናገረ፡፡ ለመሄድ መንገድ ጀምረው የነበሩ ተመልሰው፣ የቆሙትም ቁጭ ብለው የተሓህት ተወካይ ለተሰብሳቢው በትግርኛ ስለ ድርጅቱ (ተሓህት) የማስተዋወቅ ገለጻ ለመስጠት በተሰብሳቢው ማይኸ (mic) ቆመ።

የተሓህት ተወካይ ስለ ድርጅቱ ገለጻ ሲጀምር ከተሰብሳቢው የሚበዛው ትግርኛ የማይሰማ ስለነበረ አንዳንዶች በሳሆ “ታይ ኣምሓርቲ ኣይም ኪኒ ኣያነም” (ይህ ትግራዋይ ምን ነው እያለ ያለው) ብለው መጠየቅ ጀመሩ፣ ለነዚህ ጠያቂዎች ሌሎች ደግሞ “ኣምሓራ ዲዕታም መልሲ ኣካህ ኣሓየ ለክ ቲዕግስቲ ኣብኖይ” (ትግርኛ የሚችሉ መልስ ይሰጡታልና ትንሽ ትዕግስት እናድርግ) በማለት መለሱ።፣ ብዙዎችም ትግርኛ ስለማይሰሙም ትግርኛ የሚሰሙትም ገለጻው ስላልጣማቸውም በዚያ በተለመደው የኢሮብ ባህል መሰረት የተናጋሪው ሃሳብ ሳይጥማቸው ሲቀር የሚያደርጉት ትንንሽ ጠጠሮችን በመሰብሰብ ካንዱ እጅ ወደ አንዱ በማገላበጥ ከጠጠሮቹ ጋራ መጫወት ጀመሩ፣ ሌሎችም እርስ በርስ መንሾካሸክ ጀመሩ።

የተሓህት ተወካይ ድርጅቱን ለማስተዋወቅ የሰጠው አጭር ገለጻ፣

የተሓህት ተወካይ ተሰብሳቢው ልብ ብሎ እያዳመጠው እንዳልሆነ በተሰብሳቢው መካከል ከነበረው ሽኩሹክታ፣ የኢሮብ ህዝብ የተናጋሪው ንግግር ሳይጥመው ሲቀር በሚያሳየው/በሚሰጠው ግብረመልስ (ከጠጠሮቹ ጋራ መጫወት፣ ዓይኑንም ቀልቡንም ከታናጋሪው ማራቅ. . .ወዘተ) በግልጽ ቢገንዘብም/ብያይም፤ ይዞት የመጣው ድርጅቱን የማስተዋወቅ መልእክቱን ማስተላለፍና የተሰብሳቢው መልስ ማየት/መስማት ስለነበረበት መልእክቱን እንደሚከተለው ባጭሩ ገለጸ።

አንኳር አንኳር የተናጋሪው ነጥቦች፣  

አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ተሰብሳውን በመወከል ለተሓህት ተወካይ የሰጡት መልስ፣

የተሓህት ተወካይ ገለጻውን ከጨረሰ በኋላ ጓድ ገረይ ተናጋሪው በቀጥታ የተናገረው ለናንተ/ለተስብሳቢዎች ስለሆነ፣ በርግጥ ብዙዎች የቋንቋ ችግር እንዳለባችሁ ባውቅም ጥቂት ብትሆኑም ትግርኛ የምትሰሙ ስላላችሁ፤ ወንድሜ በተናገረው ላይ ሃሳብ/አስተያየት ያላችሁ አጠር አጠር እያደረጋችሁ ሃሳብ/አስተያየት ብትሰጡበትና ስብሰባውን ብንጨርስ ብሎ ሃሳብ/አስተያየት ያለው እንዲናገር ጠየቀ። በጥያቄው መሰረት ትግርኛ በሚገባ ያውቁ የነበሩት አቤቶ ዓዶዑማር ጎዒስ በተቀመጡበት ሆነው ዋና ዋና መልስ የሚሰጥባቸው ነጥቦችን በማስታወሻው ጽፎ ነጥብ በነጥብ ከተሓህቱ ተወካይ ንግግር እየጠቀሱ ቀጥሎ የተቀመጠውን መልስ ሰጡ።

እንደ ቆመ ሲያዳምጣቸው የነበረ የተሓህት ታጋይ “ኣቦይ ዓቢዪ እዙይ ናይ ውልቅኹም ሓሳብ ስለዝኾነ ናይ ካሎት ሓሳብ/ርእቶ ንስማዕ” (አባት ይህ የግልዎ ሃሳብ/አስተያየት ስለሆነ የሌሎች ሃሳብ እንስማ) ብሎ እንደተናገረ አቤቶ ዓዶዑማር በሳሆ “ኢኒ ዲኪህ አራዎክ ባቅሊ ዮህ ባሃ” (ቤቴ ልግባ በቅሎየን አምጡልኝ) ብለው ጠየቁ። ልክ ይህ የአቤቶ ዓዶዑማር ወደ ቤተ ልሂድ በቅሎየን አምጡልኝ እንዳሉ ጠጠር ይዞ ከጠጠሮቹ ጋራ ሲጫወት የነበረ ሁሉ ጠጠሮቹን በትኖ፣ ብዙዎችም ደግሞ የኢሮብ ህዝብ ድምጽ አልባ የተቃውሞዉ ማሳያ/መግለጫ ዜዴዎች አንዱ የሆነው ነጠላን ማራገፍ ዘዴን በመጠቀም፤ ነጠላቸውን እያራገፉ፣ “ደህና እደሩ” በመባባል ተሰብሳቢው ወደየ አከባቢው ተበተነ፡፡ የተሓህት 2ቱ ተወካዮች ወደ ሰበያ አቅጣጫ አቀኑ፡፡ ጓድ ገረይና እኔም ለአዳራችን ወደ ጊቢዳዎ ቀበሌ አቀናን።

ስለሆነም ለማጠቃለል ያህል የ1968ቱ የቦካለ-ማኮ ስብሰባ፤

 

ማሳሰቢያ ለአንባቢዎቼ፣

ሀ) ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ በሚል ርእስ በተከታታይ ከቁጥር 1-4 ያቀርብኩዋቸው መጣጥፎቼ በታሪካዊ ጭብቶች/መረጃዎች የተደገፉ ናቸው። እስካሁን ከተለመደው የህወሓት ደጋፊዎች ከሚሰንዝሩት በስድብ የታጀቡ የግል ስሜቶች መግለጽ የዘለሉ በጭብጥ/በመረጃ አስደግፈው የሞገቱኝ የሉም። ለወደፊት አሳማኝ፣ በመረጃ የተደገፈ፣ ትችት ሆነ ነቀፌታ በመጣጥፎቼ ካለ ለመቀበል ሆነ ለማረም ዝግጁ ነኝ። አንድ መታወቅ ያለበት ገን ይህ ታሪክ እንጂ የግሌ ፖለቲካዊ አቋም ለማበልጸግ የማደርገው ፕሮጋንዳ ስላልሆነ ማንኛውም የሚደረግ ትችት ሆነ ነቀፌታ ታሪክን መሰረት አድርጎ መሆን አለበት።

ለ) በኔ እምነት የኢሮብ አናሳ ብሄረሰብ ዛሬ ገብቶበት ላለው የህልውና አደጋና ቀውስ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋናነት ግን በ1968ቱ የቦካለማኮ ስብሰባ ላይ የኢሮብ ህዝብ በማንነት ጥያቄ ላይ የነበረው ግልጽ አቋም በህወሓት አመራር ከታወቀ በኋላ ከዛች ዕለት ጀምሮ የህወሓት አመራር የኢሮብ ህዝብ ኢሮባዊ ማንነትን በሂደት አዳክሞ ከተጋሩ ጋር አስሚለት (Assimilate) ለማድረግ ከዛች ዕለት ጀምሮ በተለያየ ጊዜ በሸረባቸው ሴራዎችና የኢሮብ አናሳ ብሄረሰብ ኢሮባዊ ማንነት ለማጥፋት በየጊዜው በወሰዳቸው እርምጃዎች ነው የሚል ነው። ይህ በተመለከተ ራሱ በቻለ ርእስ ለወደፊቱ በዝርዝር እጽፍበታለሁ።

ሐ)    ለዚህ እምነቴ እንደ ማስረጃ የሚላቸው ማን ያርዳ. . . በሚል ርእስ በተከታታይ የጻፍኩዋቸው መጣጥፎቼ፤ በዮሴፍ ዓዳዩ “ያልተፈለገው የኢሮብ ህዝብ ሕልውናና ረጅሙ ተቃሮኖ” በሚል በተከታታይ የተጻፉ መጣጥፎችና፤ "የኢሮብ ብሄረሰብ ከ19ኛው ክፍለዘመን እስከ 21ኛ ክፍለዘመን መጀመሪያ የቁልቁለት ጉዞ በጨረፍታ" በሚል ርእስ በተቆርቋሪ ኢሮቦች የተጻፈ መጣጥፍ ይመልከቱ፡፡ እንዲሁም በአጠቃላይ ስለ የኢሮብ አናሳ ብሄረሰብ ይበልጥ ማወቅ ለምትፈልጉ፣ የኢሮብ አድቮካሲ አሶሴሽን ድረ-ገጽን እንድትጎበኙ በትህትና አሳስባለሁ።


የነገ ሰው ይበለን! 

በየነ ገብራይ/ደንማርክ

የኢሮብ ብሄረሰብ ከ19ኛው ክፍለዘመን እስከ 21ኛ ክፍለዘመን መጀመሪያ የቁልቁለት ጉዞ በጨረፍታ


ከተቆርቃሪ ኢሮቦች/Concerned Irobs መስከረም 2014 ዓ/ም

የኢሮብ ብሄረሰብ ከ19ኛው ክፍለዘመን እስከ 21ኛ ክፍለዘመን መጀመሪያ የቁልቁለት ጉዞ በጨረፍታ


3ቱ ኢሮብ (ቡክናይቲ ዓረ፣ አድጋዲ ዓረ፣ ሓሳባላ) በማለት ከሚታወቅ የኢሮብ ብሄረሰብ አንድ ኣካል ከሆነው ሓሳባላ የሚወለዱት ደጃዝማች ሱባጋዲስ ትግራይና አሁን ራሷን የቻለች ሀገር ሁና ያለቸው ኤርትራ ያኔ ሲገዙ የነበሩ መሳፍንቶችን አስገብረው ከ1818 እስከ 1831 እንደገዙ የታሪክ መዛግብት ዘግበዉት ያለ ሃቅ ነው። አናሳ ብሄረሰብ ከሆነው ኢሮብ የሚወለዱት ደጃዝማች ሱባጋዲስ መላው የትግራይና የኤርትራ መሳፍንቶችን ለማስገበር ያካሄዱት ብዙ ጦርነት የጀመሩት መጀመሪያ አከባቢያቸው/ዓጋመን ለማስገበር ባካሄዱት ጦርነት ነበር። በዚህ ዓጋመን ለማስገበር ባካሄዱት ጦርነት በሌላው ጦርነቱን በቀላሉ እያሸነፉ የቀጠሉ ሲሆን ኢሮብ ላይ ሲደርሱ ከአድጋዲ ዓረና ሓሳባላ ጎሳዎች ተቃውሞ ባይገጥማቸውም ከቡክናይቲ ዓረ ጎሳና መሪዎቹ (ኦና ፃዕሩና ሓነይታ ኩማኒት) ግን የኢሮብ ራስ ገዝና (Autonomous) የኦና ስርዓታችን ፈርሶ በርስዎ ቀጥተኛ ቁጥጥር ስር መገዛትን አንቀበልም በማለት ተቃውሞ ስለገጠማቸው ተቃውሞዉን በሃይል ወይም በድርድር መፍታት የግድ ይል ነበር። ስለሆነም ደጀዝማች ሱባጋዲስ ለጊዜው ከቡክናይቲ ዓረ መዋጋትን አቁመው በወቅቱ ከሳቸው ጋራ ግኑኝነት ያደርጉ ከነበሩት ኦና ፃዕሩ ጋራ የማዘናጋት ግኑኝነት እያደረጉ ለጦርነቱ በሚገባ መዘጋጀትን መረጡ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሓነይታ ኩማኒት ደጃዝማች ሱባጋዲስን በጥርጣሬ ዓይን ያዩዋቸው ስለነበረ ከሳቸው ጋራ ምንም ዓይነት ግኑኝነት ሳያደርጉ ራሳቸውን አርቀው በመቀመጥ በበኩላቸው ለሚመጣው ሁሉ ተዘጋጅተው ይጠብቁ ነበር።

ደጃዝማች ሱባጋዲስ የኢሮብ ራስ ገዝ ከጥንት ጀምሮ የኢሮብ ህዝብ ሲተዳደርበት የነበረው የኦና ሥርዓት አፍርሰው የኢሮብን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ በነበሩበት ወቅት ከኢሮብ ውጭ በዓጋመ ድርቅና ረሃብ ገብቶ ስለነበረ ለኦና ፃዕሩና ሓነይታ ኩማኒት ሠራዊቴ በረሃብ ተጎድቶብኛልና ቀለብ አግዙኝ፣ ይህን ለማድረግ ባትችሉ እንኳን ለአንድ ጊዜም ቢሆን ጥሩ እራት ሰራዊቴን ጋብዙልኝ ብለው ጠየቁ። ሴራው ያልታያቸው ኦና ፃዕሩ የሰራዊቱን የአንድ ጊዜ እራት የመጋባዝ ጥያቄ ሲቀበሉ ከድሮም የደጃዝማች ሱባጋዲስ እንቅስቃሴ በዓይነ ቁራኛ ሲከታተሉ የነበሩ ሓነይታ ኩማኒት ግን አንተ ከፈለግክ ጋብዛቸው እኔ ግን የለሁበትም በማለት ጥሪውን ባለመቀበል በኦና ፃዕሩ ለደጃዝማች ሱባጋዲስ ሰራዊት በተዘጋጀው የእራት ግብጃ ላይ ሳይገኙ ቀሩ። የእራት ግብጃው የቡክናይቲ-ዓረ መሪዎችን (ኦና ፃዕሩና ሓነይታ ኩማኒት) አፍኖ በመያዝ ህዝብን በቀላሉ ለማስገበር የታቀደ ሴራ ስለነበረም ኦና ፃዕሩ በሴራው መሰረት በግብጃው ጊዜ ተይዘው ታሰሩ። ደጃዝማች ሱባጋዲስም ኦና ፃዕሩ ከታስሩ በኋላ ሓነይታ ኩማኒትና የቡክናይቲ ዓረ ህዝብ የትም አይደርስም በማለት የቡክናይቲ ዓረ ህዝብን በሃይል ለማስገበር ጦራቸውን ወደ አከባቢው ላኩ። ይህ ሊሆን እንደምችል ገምተው ቀድመው ተዘጋጅተው ህዝባቸውን አሰባስበው ሲጠባበቁ የነበሩ ሓነይታ ኩማኒት ከተላከው የደጃዝማች ሱባጋዲስ ጦር ጋራ ገጥመው ጦርነቱ በሓነይታ ኩማኒት አሸናፊነት ተጠናቀቀ። የደጃዝማች ሱባጋዲስ የጦር መሪና የተወሰኑ የሰራዊቱ አባላትም ተማረኩ። የጦራቸው መሪና የተወስኑ የሰራዊቱ አባላት መማረካቸውን የሰሙት ደጃዝማች ሱባጋዲስ የጦር መሪያቸውና አብረው የተማረኩ ወታደሮቻቸውን እንዲለቁ ወደ ሓነይታ ኩማኒት መልእክተኛ ላኩ። ሓነይታ ኩማኒት ምርኮኞቹ እንዲለቀቁ ከፈልግክ መጀመሪያ አንተ ኦና ፃዕሩን ልቀቅ፣ ጦርህንም ይዘህ ወደ ቦታህ ተመለስ፣ ከዛ እኔ የጦር መሪህንና ምርኮኞቹን እለቃለሁ ብለው መለሱላቸው። ደጃዝማች ሱባጋዲስ ሓነይታ ኩማኒትና የቡክናይቲ ዓረ ህዝብ ማምረሩን ተረድተው ኦና ፃዕሩን ለቀቁ፣ ሓነይታ ኩማኒትም የደጃዝማች ሱባጋዲስ የጦር መሪና ምርኮኞችን ለቀቁ።

ከጦርነቱ በኋላ ደጃዝማች ሱባጋዲስ የኢሮብ ህዝብን፤ በተለይ ቡክናቲ ዓረን በኃይል ማንበርከክ እንደማይቻል አውቀው መደራደሩ እንደሚሻል አምነው ወደ ኦና ፃዕሩና ሓነይታ ኩማኒት የእንደራደር መልእክት ላኩ። ሁለቱ መሪዎችም ድርድሩን ተቀብለው ሁለቱ ወገኖች ለድርድር ተቀመጡ። የድርድሩ የስምምነት ነጥቦችም ከሞላ ጎደል የምከተሉ ነበሩ፣

1. ኢሮብ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ራሱ ባቆየው የአስተዳደር ሥርዓት ራስ-ገዝ ሆኖ እንዲቀጥል፣

2. ደጃዝማች ሱባጋዲስም ሆኑ ሌሎች የኣገርቷ የበላይ ሹመኞች በኢሮብ ራስ ገዝ የውስጥ አስተዳደር ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ፣

3. የኢሮብ ህዝብ በራሱ ባህላዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመርጣቸው መሪዎቹ በደጃዝማች ሱባጋዲስ እና በሌሎች የኣገርቷ የበላይ አስተዳደርዎች ሙሉ እውቅና እንዲያገኙ፣

4. የኢሮብ ህዝብ ደጃዝማች ሱባጋዲስ የኣከባቢው የበላይ ገዢ መሆናቸውን እውቅና እንዲሰጥ፤

5. እውቅና ለመስጠታቸውን ማረጋገጫ እንዲሆንም ግብር እንዲክፍል፣ የሚሉ ነበሩ፡፡

ይህ ስምምነትም እስከ 1935 ዓ ም የጣሊያን ወረራ በሁሉም የበላይ መንግስታዊ ወኪሎች ተጠብቆ፣ የኢሮብ ራስ-ገዝም ማንም ጣልቃ የማይገባበት አስተዳደር ሆኖ፣ በዓጋመ በሚሾሙ ሹመኞች አማካይነት ከበላይ ባለስልጣኖች ጋራ እየተገናኘ የኢሮብ ህዝብ የኦና ስርዓቱን ይዞ ቀጠለ።

የጣሊያን የ1935 ዓ ም ወረራ ሊጀመር አከባቢ በኢሮብ ህዝብ በቆየው ባህል መሰረት የተመረጡት ኦናዎች፣ ኦና ገብራይ ዕንዳይና ኦና ደስታ ወልደጊዮርግስ ነበሩ። እነዚህ ወኪሎች እንደተመረጡ ብዙ ሳይቆዩ ጣሊያን ኢትዮጵያን ወሮ ስለተቆጣጠረ፣ በኢሮብ ግዛትም የነዚህ የህዝብ ተመራጮች ውክልና በጣሊያኖች ተሽሮ ጣሊያን የራሱ ወኪል ፊትወራሪ ተሰማ ተስፋይ ሾሙ። የኢሮብ ህዝብም ከብዙ ዘመናት ራሱ በመረጣቸው መሪዎች መተዳደር ወጥቶ በባዕድ በተመደበለት ወኪል እንዲገዛ ተደረገ።

ከ5 ዓመት የጣሊያን ባዕዳዊ አገዛዝ በኋላ ጣሊያን ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ሲወጣ አፄ ኃይለስላሴ ከስደት ተመልሰው ስልጣን እንደያዙ፣ ኢትዮጵያን በ14 ጠቃላይ ግዛት በህግ ተሸንሽኖ በየጠቅላይ ግዛቱ ሥርም አውራጃ፣ ወረዳ የሚባል አስተዳደረ እንደተዋቀረ ተደረገ። የኢሮብ ግዛትም ለመጀመሪያ ጊዜ የሶስት ኢሮብ ወረዳ የሚል ኣስተዳደራዊ ስያሜ ተስጥቶት (የራስ ገዝና የኦና ስርዓቱ ተሽሮ) በቀጥታ የወረዳ ገዢ ከላይ ተመደበለት። ለመጀመሪያ ጊዜ በኢሮብ ወረዳ የተመደቡት ወረዳ ገዢም ፊተውራሪ ግደይ የሚባሉ የነበሩ ሆነው እንደተሾሙ ብዙ ሳይቆዩ በአከባቢው በተፈጠረው ግጭት ተገደሉ።

ከፊተውራሪ ግደይ መገደል በኋላ ቀኝ አዝማች እምባየ የሚባሉ በወረዳው ተሾሙ። ወቅቱ በደቡብ ትግራይ ቀዳማይ ወያኔ እየተባለ የሚታወቀው እንቅስቃሴ በአፄ ኃ/ስላሴ መንግስት ተመቶ መላው ትግራይ የነበረው ብረት የሚገፈፍበት ወቅት ስለነበረ በቀኛዝማች እምባየ አማካይነትም የኢሮብ ህዝብም ብረቱ እንዲገፈፍ ተደረገ። ቀኛዝማች እምባየም ወረዳውን ለ4 ዓመት ያህል ጊዜ ገዙ።

ከቀኛዝማች እምባየ በኋላ ባሻይ ብሻኡ የሚባሉ ለወረዳው ገዢነት ቢመደቡም እሳቸው በአከባቢው ብዙ አይቀመጡም ነበርና ህዝቡ በቅርቡ ሆኖ የሚመራው በማጣት ተቸገረ። ይህን በውል የተገነዘቡ፤ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የኢሮብ ህዝብ ወደ ችግር ሊገባ መሆኑን ያዩት ሰለቃ ወልዱ ገብራይ (የኦና ገብራይ ዕንዳይ ልጅ)፤ በወቅቱ በመቐለ በመንግስት መስሪያቤት በጥሩ ደሞዝ ሲሰሩ የነበሩ ቢሆንም የመቐለ ስራቸውንና ጥሩ ደሞዛቸውን ትተው በዝቅተኛ ደሞዝ በኢሮብ በምክትል ወረዳ ገዢነት ደረጃ ለመስራት ፈቃደኛ እንደሆኑ ለጠቅላይ ግዛቱ ገዢ ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አግኝቶ ሰለቃ ወልዱ የወረዳዋ ምክትል ገዢ ሆነው ተመደቡ። ሰለቃ ወልዱ ከራሱ ከብሄረሰቡ የሚወለዱ፣ ቋንቋና ባህሉን ጠንቅቀው የሚያውቁ በጣም አዋቂና ብልህ ሰው ነበሩ። ለህዝቡ ሁኔታውን በሚገባ አስረድተው ህዝቡን አረጋግተው በቆየው ባህሉ መሰረት ህዝቡን እየመሩ ለማእከላዊ መንግስት መግባት የነበረት ግብር በውቅቱ እያስገቡ እስከ ዕለተ ሞታቸው የኢሮብ ወረዳን አስተዳደሩ። ከሰለቃ ወልዱ ሞት በኋላ ራሱ የቻለ ወረዳነት ተሰርዞ፣ ጉለማክዳ፣ ሱሩኩሶና ኢሮብ አንድ ላይ ተጠቃሎ የዛላምበሳ ወረዳ የሚል ስያሜ ተሰጦት በዚሁ ኣስተዳደር እሰክ የ1966ቱ አቢዮት ቀጠለ።

በ1966ቱ አቢዮት የአጼ ኃይለስላሴ አገዛዝ በህዝባዊ አመጽ ከስልጣ መወገድ በኋላ፤ በ1967 መስከረም 2 ራሱን ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በሚል ስም ወታደራዊ ጁንታ ስልጣን ላይ እንደመጣ የኢሮብ ወረዳ የተለያዩ ደርግን በትጥቅ ትግል ለመፋለም ጠመንጃ ያነገቡ ቡድኖች ዋና መናሀሪያ ሆነ። በ1966 አጋማሽ ላይ ግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ/ግገሓት የኢሮብ ወረዳ አካል የሆነውን ኣድጋዲ-ዓረን/ማካታ መቀመጫ አድርጎ የትጥቅ ትግል በአከባቢው ጀመረ። በ1964 ዓ/ም በርሊን/ጀርመን ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ህዝቦች አርነት ድርጅት (ኢህአድ) በ1967 ራሱን በፓርቲ ደረጃ በማደራጀት ስሙን ወደ የኢትዮጵያ ህዝብ አቢዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ቀይሮ፤ በነዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ፣ ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ ኣበራ ዋቅጂራ፣ ክፍሉ ታደሰ፣ ዘርኡ ክሕሸን. . . ወዘተ. ሲመራ የነበረው ድርጅትም ከ1966 መጀመሪያ ጀምሮ ወደ አከባቢው ከራሱ ከኢሮብ የተወለዱ ካድሬዎቹን ወደ አከባቢው ልኮ ድርጅቱን የማስተዋውቅና አባላት የመመልመል ስራ ጀመረ። በኢሮብ ህዝብ ከፈተኛ ተሰሚነትና ክብር የነበረው ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይም ከአከባቢው ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋራ እየተገናኘ በአከባቢው ኢህአድ/ኢህአፓን በሚገባ አስተዋወቀ። በውጭ ኣገሮች ሰልጥኖ በኤርትራ በኩል የገባው የኢህአፓ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድንም በ1967 ዓ/ም ላይ ኢሮብ ወረዳ ገብቶ ዋና ቤዙን ዓሲምባ ተራራን አደረገ። የኢህአፓ ትጥቅ ትግል ዓሲምባ እንደገባም ገና በአከባቢው መንቀሳቅስ ከመጀመሩ በፊት መንገድ በመምራትና ከህዝቡ ጋራ በቀላሉ ለመግባባት እንዲረዱ ተልከው የነበሩት እነ ጴጥሮስ ሃይለማሪያም፣ ገረይ ተስፋይ፣ ዳባሳይ ካሕሳይ፣ ደበሱ ካሕሳይ፣ ኩማኒት ወልደገርጊስ፣ ንጉሰ ሙሩቅ፣ ወልዱ ገብራይ፣ ቢኒያም ገብራይ፣ አሰፋ ወልዱ ወዘተ. ቡድኑን ተቀላቀሉ። ልክ ቡድኑ እንቅስቃሴ እንደጀመረ ወደ ትጥቅ ትግሉ ተቀላቅለው የማደራጀት ሥራውን እንዲሰሩ የሚችሉ ተማሪዎችም፤ በወቅቱ ዓዲግራትን ማእከል በማድረግ ኢህአፓን የማደራጀት ስራ ሲመራ በነበረው በገብረእግዚኣብሄር ሃይለሚካኤል/ጋይም አማክይነት ተዘጋጁ።

በልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት/ኢዴህ አባላትም ከ1967 መጀመሪያ ጀምሮ በአከባቢው መንቀሳቀስ ጀመሩ።

በ1967 ዓ ም የካቲት ላይ በምዕራብ ትግራይ/ደደቢት በረሃ ትጥቅ ትግል የጀመረው የያኔው ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ/ተሓህት ቡድን በ1968 ሕዳር ላይ ወደ ዓጋመ አውራጃ መጥቶ የማደራጃ ማእከሉን በሱቡሓ ሳዕሲዕ/ማርዋ ላይ በማድረግ፣ በኢሮብ ወረዳም ዋርዓትለ ላይ ማሰልጠኛ ማእከል ነበረው። በመሆኑ፣ በአከባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ቁጥር ወደ 4 አደገ። ተሓህት ወደ አከባቢው እንደመጣ ከግገሓት ጋር በእንዋሃድ ስም ተሰባስበው አብሮ በተኙበት ዛጋብላ በረሃ ተሓህት ሌሊት አባላቱን በመቀስቀስ የግገሓት አባላት ላይ በተኙበት እርምጃ እንዲወስዱ በማዘዝ፣ የሚገደሉትን ገድሎ እጅ የሰጡትን ምርኮኛ በማድረግ ግገሓትን ገና በጨቅላ ዕድሜው ባጭሩ ቀጨው። የኢዴህ አባላትም በኢህአድ/ኢህአፓ ሆነ በተሓህት/ህወሓት ከፍተኛ ክትትል ይደረግባቸው ስለነበረ አከባቢውን ለቀው ወደ ምዕራብ ትግራይ ሄዱ። ስለሆነም ከ1968 መጀመሪያ ጀምሮ በምስራቅ ትግራይ ኢህአፓ/ኢህአሰና ተሓህት ብቻ ቀሩ።

የኢሮብን በተመለከተ በ1968 ተሓህት ላጭር ጊዜ የስልጠና ቦታውን ዋርዓትለ አድርጎ ቢቆይም በኢሮብ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴም ሆነ የማደራጀት ስራ እስከ 1970 ግንቦት አያደርግም ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በ1968 አጋማሽ ላይ የመሬት ማከፋፈል የጋራ ህግ (ሲሪት) ለመንደፍ ኢህአፓ ለኢሮብ ህዝብ በጠራውና ከመላው ኢሮብ ከ300 በላይ ተወካዮች በተገኙበት የቦካለማኮ/ዓሊተና ስብሰባ ላይ የተሓህት ተወካዮችም ተገኝተው ቀጥሎ የተቀመጠውን የዓላማቸው አንኳር ነጥቦች ለተስብሳቢው ከገለፁ በኋላ፤ ኢሮብን በመወከል አበቶ ዓዶዑማር ሓሊቦ/ጎዒስ መልስ የሰጡት መልስና ከመልሱ በኋላ ተሰብሳቢው የወሰደው እርምጃ ሁለቱን (ህዝቡንና ተሓህት) የሚያገናኝ ዓላማ አለመኖሩን በግልፅ ስለተገነዘቡ ነበር። ስለሆነም መላው ኢሮብ በኢህአፓ/ኢህአሰ ቁጥጥር ሥር ነበር የቆየው።

የተሓህት ተወካይ በቦካለማኮ ለተሰብሳቢው ካደረገው ንግግር አንኳር ነጥቦች፣

1. ስማችን ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ ይባላል፣

2. መሰረታዊ ዓላማችን ባህላችን፣ ቋንቋችንና ትግራዋይ ማንነታችን በአማራ ገዢ መደቦች ስለተጨፈለቅ፣ በቋንቋችን መፃፍ፣ ባህላችን ማሳደግ ስለተነፈግን፣ ትግራዋይ ማንነታችን ስለተረገጠ፣ ባህላችንና በቋንቋችን ለመፃፍና መዳኘት መብታችን ለማስከበር፣ ባጭሩ ሲጠቃለል ከአማራ ገዢ መደብ የሚደርስብንን ብሄራዊ ጭቆና ለማስወገድና የራስችን ዕድል በራሳችን ለመወስን በመታገል ላይ ያለን ልጆቻችሁ ነን።

3. ስለሆነም ከአማራ ብሄራዊ ጭቆና ነፃ ወጥተን የራሳችን ዕድል በራሳችን ለመወሰን በምናደርገው ትግል የናንተ ድጋፍና ተሳትፎ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ የትግራይ ህዝብን ከብሄራዊ ጭቆና ለማላቀቅ በምናደርገው ትግል ከጎናችን እንድትቆሙና እንድትቀላቀሉን ለመጠየቅና ራሳችንን ለማስተወቅ ነው ዛሬ እዚህ በመካከላችሁ የተገኘነው ብሎ ጊዜው እየመሸ ስለነበረ ገለፃዉን ባጭሩ ጨረሰ።

አበቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ህዝቡን ወክለው የሰጡት አጭር መልስ፣

1. በመጀመሪያ ስማችሁ ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ ከሚባል ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ኢትዮዽያ ቢሆን ጥሩ ነበር።

2. በሁለተኛ ደረጃ አንተ በግልጽ እንዳስቀመጥከው እናንተ የምትታገሉት የተጋሩ ባህልና ቋንቋ በአማራ ገዢ መደቦች ስለተረገጠ በቋንቋችሁ መፃፍን እንድትችሉ፤ ትግራዋይ ማንነታችሁና ባህላችሁን እንድታስከብሩ እንድምትታገሉ በግልፅ ነግረሀናል።

3. በርግጥ እኛ የኢሮብ ብሄረስብ በትግራይ ጠቅላይ ግዛት የምንኖር ህዝብ ነን። ትግራይ መሬታችን ሆኖ በማንነት፣ በባህልና በቋንቋ ከተመጣ ደግሞ ከተጋሩ የተለየ የራሳችን ማንነት/ኢሮብ፣ የራሳችን ቋንቋ/ሳሆ፣ የራሳችን ባህልና ስነልቦና ያለን ራሳችን የቻልን ብሄረሰብ ነን።

4. በቋንቋ፣ ባህል ጭቆናና ረገጣ ከተመጣ ደግሞ የኛ የኢሮብ ህዝብ ቋንቋ (ሳሆ) የሚረገጠው ገና “ቃላይ በዓንቱራ” እንደተሻገርን ኣንታ ዓኳር ሻሃይ፣ ተብለን የምንሰደበውና በቋንቋችንና በባህላችን የምንቋሸሸውና የምንሰደበው በአማራ ሳይሆን በተጋሩ ነው።

5. ካንተ ንግግር እንደሰማነው በማንነት ደረጃ ከታሰበ እኛ ኢሮቦች ከተጋሩ የተለየን የራሳችን ማንነት/ኢሮብ መሆናችን እንኳን አታውቅም ወይም አትቀበልም። ስለሆነ እኛ የኢሮብ ህዝብ እንድንሰማችሁና እንድንደግፋችሁ ከፈለጋችሁ መጀመሪያ በግልጽ ማንነታችን/ኢሮባዊነት ተቀበሉ፣ አክብሩ።

6. ስለ ማንነት፣ የባህልና ቋንቋ ጭቆና ማስወገድ ትግል ይደረግ ከተባለ እኛ የኢሮብ ህዝብ መጀመሪያ መታገል ያለብን ሩቅ ያሉትን አማራን ሳይሆን እዚህ ከጎረቤታችን ከሆኑትና በማንነታችን ከሚጨቁኑን ከተጋሩ/ከናንተ ጋራ ነው መሆን ያለበትና የናንተ ዓላማ ለኛ ለኢሮብ ህዝብ ካለንበት የባህልም፣ የቋንቋም ከሁሉም በላይ ደግሞ የድህነት ጭቆና ለማላቀቅ የሚጠቅመን አይደለም፣ ብለው ንግግራቸውን እንደጨረሱም ተሰብሳቢው የአበቶ ዓዶዑማር ሃሳብ ሃሳባቸው መሆኑ ለማሳየት የተሓህት ልኡካን ቡድን ለቀረበው ሃሳብ የሚሰጠውን መልስ ሳይጠብቅ ከስብሰባው ተነስቶ በመበተን የኢሮብ ህዝብ በኢሮባዊ ማንነቱ ፈፅሞ የማይደራደር መሆኑን በግልፅ አሳያቸው።

የኢሮብ ህዝብ ከ1968-1970 ዓ ም ግንቦት በኢህአፓ/ሰ ስር ሲተዳደር ከቆየ በኋላ በ1970 ግንቦት ላይ ህወሓት ኢህአፓ/ሰ ላይ ጦርነት ከፈተና በአጭር ቀናት ውጊያ ኢህአፓ/ሰ ትግራይን ለቆ ሲወጣ፣ በርካታ የኢሮብ ተወላጆች በኢህአፓ/ሰ ውስጥ ስለነበሩ የተወስኑት ከድርጅቱ ጋራ አብረው ሲወጡ በርከት ያሉ ደግሞ ህዝባችንና መሬታችን ለቀን አንወጣም ብለው እዛው እንደ ተደራጁ ቀሩ። ተሓህት እነዚህ ወገኖችን ማሳደዱን ቀጠለ። በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ውጊያዎችም ንጉሰ ተስፋይ/ቡሉፅ፣ ደበሱ ካሓሳይ፣ ተስፋይ ሃይሉ. . . ወዘተን ገደለ። የተቀሩትም ምንም መፈናፈኛ ሲያጡና በነሱ ምክንያት ህዝቡ ብዙ መከራ በተሓህት እየወረደበት መሆኑ በመረዳት ለተሓህት እጅ ከመስጠት ለደርግ እጃቸውን መስጠት መርጠው ለደርግ እጃቸውን ሰጡ። የኢሮብ ወረዳ በተሓህት ቁጥጥር ስር እንደወደቀም በኢህአፓ/ሰ ጊዜ ህዝቡ ራሱ የመረጣቸው የስተዳደር መዋቅሮች በሙሉ እንዲፈርሱ ተደረገ። ህዝቡ የመረጣቸው መሪዎች ከቦታቸው ተነስተው ህወሓት በሚፈልጋቸው ሰዎች እንዲተኩ ተደረገ።

ከ1970 ዓ ም እስከ 1983 ዓ ም ለ13 ዓመታት አብዛኛው ገጠራማው ምስራቅ ትግራይ በህወሓት ብቸኛ ቁጥጥር ስር ቆይታ ወቅትም ገና ታሪክ ለወደፊት ሊዘግባቸው የሚችል ብዙ ግፎች፣ ግድያዎች፣ እስራት፣ የንብረት፣ ከቀየ ማፈናቀል (መንቀል) ውርስ ተፈፀመ። በኢሮብ ወረዳ ደግሞ ህዝቡን የኢህአፓ/ሰ አባል ነህ ወይም ነበርክ በማለት በርካቶች ተገደሉ፣ ታሰሩ፣ ተሰደዱ፣ በቦታው የቀሩም አፋቸውን ዘግተው አጎምብሰው እንዲኖሩ ተደረገ። በዚህ መሰረትም የኢሮብ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ያቆየው ኢሮባዊ ማንነት ከ1970 ዓ ም ጀምሮ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረና እየተዳከመ መሄድ ጀመረ።

በ1983 ዓ ም ደርግ ተወግዶ ህወሓት በኢህአዴግ ስም ኢትዮጵያ ወስጥ የመንግስት ስልጣን እንደተቊጣጠረ ትግራይ ክልልን ሲያዋቅር ሌሎች ወደ ኢሮብ መካለል የሚገባቸው ሳሆ ተናጋሪ የኢሮብ ቀበሌዎችን ወደ ትግርኛ ተናጋሪ አካባቢዎች ቢያካልላቸውም የኢሮብ ልዩ ወረዳን አዋቅሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ለዘመናት የኢሮብ ህዝብ ማእከል የሆነችውና፤ ከኢሮብ ህዝብ ታሪክና ማንነት ጋራ ከፍተኛ ትርጉምና ቁርኝት የነበራት ታሪካዊ የዓሊተና ከተማ ርእሰ ከተማነትን የህወሓት መሪዎች የህዝቡን አቤቱታ ወደጎን በማለት ወደ ጻውሃን አዛወሩት። ለምን ከ5 ኪሜ በማይበልጥ ርቀት ውስጥ ርእሰ ከተማውን ከዓሳቦል ግድብ ስር ወደሆነችው ዳውሃን መቀየር እንዳስፈለገ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ እሳቤዎችን ቢያቀርቡም፣ ለጊዜው ከዚህ በላይ ወደ ዝርዝሩ መግባት አስፈላጊ አይሆንም። ከዚህ ሌላ የልዩ ወረዳዋ አስተዳዳሪዎችም በቀጥታ በህወሓት የሚሾሙ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቹም ቋንቋውን የማይናገሩና ከህዝቡ ባህልና ልምድ ጋር ምንም ትውውቅ ያልነበራቸው ነበሩ። ይባስ ብሎም የልዩ ወረዳው ምክርቤትና የሥራ ቋንቋም ትግርኛ እንዲሆን ተደርጓል።

በ1990 ዓ ም የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ሲወር የኤርትራ ወራሪ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ከገባባቸው ግንባሮች አንዱ የኢሮብ ልዩ ወረዳ እንደነበረ ይታወቃል። ጦር ወደ አከባቢው ሲገባ ምንም ዓይነት መከላከያ በአከባቢው ስላልነበረ ወደ 50 የሚሆኑ የኢሮብ አርሶ አደሮች በፊታቸው ያገኙትን ጠብመንጃም ጩቤም ሆነ መጥረብያ በማንሳት መላው ህዝባቸውን ወንድ ሴት ሳይሉ ባንዴ በማደራጀት በዓይጋና በአንዳንድ የኣድጋዲ-ዓረ መንደሮች ላይ ከወራሪ ሰራዊት ጋራ በመግጠም ለሶስት ቀን ከባድ ራስን የመከላከል ጦርነት በማካሄድ ጠላትን ወደ መጣበት ለመመለስ ችሎ ነበር፡፡ ይህ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ሥልጠናም ሆነ ሙያ ያልነበረው በእጁ ያገኘውን በመጠቀም በዕለተ እሁድ ባንዴ ከያለበት ተሰባስቦ የኤርትራን መደበኛ ጦር ገትሮ መያዝ ብቻ ሳይሆን እንደገና ተጠናኽሮና ተደራጅቶ ቢመለስም ሰንዓፈ ድረስ አባርሮት ነበር። ከዚህ በመነሳትም ነበር እነዚህን በጀግንነት የተዋደቁትን ጀግኖች “የሰምበት ታጣቂዎች (ዕጡቃት ሰምበት)” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው፡፡ ታዲያ ምን ዋጋ አለው የኤርትራ ሰራዊት እንደገና ተደራጅቶ ተመልሶ መጣ፤ የኢሮብ ሚሊሺያም በኢትዮጵያ ሰራዊት በኩል ምንም እርዳታ ስለኣላገኘ መላው አድጋዲ-ዓረ እስከ ዓሊተና ድረስ ያለው ቡክናይቲ-ዓረ መሬት በኤርትራ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ወደቀ። በ1992 ዓ ም ሰኔ ወር በኢትዮጵያ ሰራዊት ድባቅ ተመቶ እስከተባረረበት ጊዜ ድረስ ለሁለት ዓመት ያህል የኤርትራ ሰራዊት አከባቢዎችን ተቆጣጥሮት ቆይቷል። በነዚህ የኤርትራ ወራሪ ሰራዊት ሁለት ዓመታት ቆይታ ጊዜም በአከባቢው በመንግስት ሆነ በበጎ አድራጎት ድርጀቶችና በካቶሊክ ቤተክርስትያን ተገንብተው የነበሩና በመገንባት ላይ የነበሩት የልማት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች የብዙ ግለሰብ ገበሬዎች ቤቶችና ንብረቶች ሳይቀሩ የሚዘረፈው ተዘረፈ፣ መውሰድ ያልቻሉትም እንዲወድም ተደረገ፣ ብዙ ሰው ተገደለ፣ 97 ንጹሃን የኢሮብ አርሶ አደሮችም ታግተው ተወስደው እስከ አሁኗ ሰዓት ደብዛቸው እንደጠፋ ቀርቷል። ዜጎች ታግተው ተወሰዱብኝ ብሎ የሚጠይቅ መንግሥት አለመገኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ ቤተ ሰቦቻቸውም ስለታገቱባቸው ቤተ ሰቦቻቸው እንዳያነሱ በመከልከላቸው፣ በውጭ አገር ነዋሪ ኢሮቦች አቤቱታም በመንግሥትም ሆነ በሚመለከታቸው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ተገቢ አትኲሮት ሊሰጣቸው ባለመቻሉ የኸው እስከ ዛሬ ለ23 ዓመት ደብዛቸው እንደጠፋ ነው፣ የኢሮብ ብሄረስብም ለ23 ዓመታት መቋጫ ባጣ ሃዘን ውስጥ ይገኛል።

በ1992 ዓ ም የኤርትራ ሰራዊት በኢትዮጵያ ሰራዊት ተሸንፎ ሙሉ በሙሉ ተጠርጎ ወጥቶ በመሸሽ ላይ በነበረበት ወቅት፣ የኤርትራ መንግስት አድርግ የተባለውን ከማድረግ ውጭ ምንም ሌላ አማራጭ ማቅረብ ይችል ባልነበረበት ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ጦርነቱ እንዲቆም አስደርገው ወደ ድርድር በመግባት አልጀርስ ድረስ በመሄድ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት የሆኑ እንደ ባድመና ወደ ግማሽ የሚጠጋ የኢሮብ መሬት ማለት፣ መላው አድጋዲ-ዓረና የተወሰነ የቡክናይቲ-ዓረ ክፍል በአልጀርስ ስምምነት መሰረት በሄግ በተፈረደው የሁለቱ ሃገራት የድንበር ውሳኔ ለኤርትራ እንዲሰጥ ተደረገ። ስለሆነም ዛሬ የኢሮብ ህዝብና መሬቱ፣

1. አንድም ቀን የኤርትራ አካል ሆኖ የማያውቀው፣ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ አካል የነበረው ወደ ግማሽ የሚጠጋ መሬቱ ለኤርትራ በነአቶ መለስ ተሰጥቶበት፣

2. በአከባቢው ምንም ተስፋ የሚሆን ነገር ስለጠፋ ወጣቱ በስደት ወደ ተለያየ አቅጣጫ የተበተነበት፣

3. ኢሮባዊ ማንነት በ’አስሚለሽን’ ለማጥፋት በህወሓት መሪዎች ከ40 ዓመት በላይ በተሰራው እኩይ ሴራ በኢሮባዊ ማንነቱ የማይተማመን (Identity crisis) ውስጥ የገባ፣ ቋንቋዉንና ባህሉን እያጣ ያለ ወጣት ትውልድ የተፈጠረበት፣

4. በሃገር ቤትና በውጭ ዓለም በስደት የሚኖረው የብሄረስቡ ተውላጅ ቁጥር በወረዳው ከሚኖረው ህዝብ ሊብለጥ የምችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ፤ ዛሬ ኢሮብ የሚባል አናሳ ብሄረሰብ ነበር ወደሚባልበት የመጥፋት አቅጣጫ እየተንደረደረ ያለ አናሳ ብሄረሰብ ሆኗል ቢባል ስህተት አይሆንም።

ይህ አልበቃ ብሎ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንድሉት፤ ከጥቅምት መጨረሻ 2013 ዓ/ም ጀምሮ ትግራይ ላይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የኢሮብ ህዝብ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ የህልውናው አደጋ የባሰ አንጃብቦበት ይገኛል፡፡

ስለዚህ የኢሮብ ህዝብ ራሱን የቻለ ብሄረሰብ ሆኖ የማንነቱ መገለጫዎች የሆኑ ታሪኩ፣ ቋንቋው፣ ስነልቦናው፣ ባህሉና የመሬት ጂኦግራፊያዊ አከላለሉ ተከብሮለት እንዲቀጥል የኢሮብ ተወላጅ በሙሉ የቻለውን ማድረግ የግድ የሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ጠንካራ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ መሰረት ያለው፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ የተሟሉለትና የተጠበቁለት፣ በዴሞክራሲያዊ ኣስተሳሰብ የዳበረ፣ በኢሮባዊ ማንነቱ የሚኮራና የማይደራደር፣ በሚኖርበት አከባቢ ሁሉ ኢሮባዊ ሥነልቦናዉንና አንድነቱን የጠበቀ የኢሮብ ህዝብ ለማየት፤ እያንዳንዱ ኢሮብ በሚችለው ሁሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ይኸው ጥሪ ቀርቧል፡፡

=========//=======