ባይፈርስ ሚዲያ በመላው አለም ላይ በርካታ ተመልካቾችን ያተረፈውና አየር ላይ በቆየባቸው ያለፉት ስድስት አመታት ሚንስትሮችን ጨምሮ የሀገሪቱን ከፍተኛ የጸጥታ እና የደህንነት የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ልሂቃንን ወዘተ ከ ስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ እንግዶችን በማስተናገድ እውቅናን ያተረፈው የዋልታ ቴሌቭዥን ነፃ ሐሳብ አዘጋጅ በነበረው ጋዜጠኛ ስሜነህ ባይፈርስ የተቋቋመና አሁንም በጋዜጠኛ ስሜነህ ባይፈርስ ዋና አዘጋጅነት የሚመራ የሚዲያ ተቋም ነው።
በአሰራሩ መፍትሔ ተኮር፣ አሳታፊና የተደራስያንን አቅም እንዲገነባ በማድረግ ላይ ያተኮረ የታሪክ ነገራ ወይም የጋዜጠኝነት አሰራርን የሚከተለውን Constructive Media Model ን መርህ በማድረግ በሚዲያው አለም በጎ ሚና ለመጫወት የተቋቋመው ባይፈርስ ሚዲያ መረጃ ሰጪ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰብ ደህንነትና ለህዝባዊ ተዋስዖው አወንታዊ አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ዘገባዎችንም ለማቅረብ የተደራጀ ተቋም ነው። የባይፈርስ ሚዲያ ስለ ነፃ ሐሳብ ዘገባዎች ችግርን ብቻ ሳይሆን በተቻለ መጠን መፍትሔንም የሚያመላክቱ ሚዛናዊ ዘገባዎች ሲሆኑ፤የሚቀርቡት ዘገባዎች ተደራስያንን በአሉታዊ ነገሮች የሚያጥለቀልቁ ከመሆን ይልቅ፤ አቅም አጎልባች (Empowering audiences) ለፍላጎታቸው ትኩረት የሚሰጡ፣ ህይወታቸውን ለማሻሻል የሚያስችል ክህሎት የሚያስጨብጡ፣ ወደ ህይወት ግባቸው ለመድረስ የሚያስችሉ አማራጮችን የሚያመላክቱና ልምድ የሚቀስሙባቸው ናቸው። በጥቅሉ በሰላም ልማት እና ዴሞክራታይዜሽን ግንባታ ሂደት ላይ እንቅፋት የሆኑ ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥ ለህብረተሰብም ሆነ ለግለሰብ አርአያ አመልካችና መንገድ ጠቋሚ ይዘቶችን ማቅረብ የባይፈርስ ሚዲያ ተልእኮ ነው።
ከቀደመው የዋልታ ቴሌቭዥን ‹‹ነፃ ሐሳብ›› የነበረውን ወረት ይዞ እና አዳዲስ እሴቶችን ጨምሮ በአዲሱ ስለ ነፃ ሐሳብ ፕሮግራሙ የመጣው ባይፈርስ ሚዲያ፦
ተደራስያንን ለውይይትና ግብአት በመጋበዝ፤ በሚዲያና በህዝብ መካከል እምነትን በማጠናከር፤ ንቁ ተሳታፊነትን ማረጋገጥ፤ ሰዎች የገጠማቸውን ችግር ለመፍታት ያደረጉትን ጥረት የሚያመለክት ዘገባ በማቅረብ፤ ለሀሳባዊነት ሳይሆን ለውጤታማነት ትኩረት በመስጠት፤ በምንገኝበት ሁኔታ መተግበር የሚችሉ፤ ‹‹እንዴት እና ለምን›› ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ ነገሮችን ፈትሾ በማቅረብ፤ መፍትሔ ጠቋሚ ጋዜጠኝነትን ማረጋገጥ፤ ዘላቂ ተጽዕኖ ያላቸውንና ለውጥ ለመፍጠር የሚያስችሉ ጉዳዮችን በመለየት፤ ፈጠራንና ወደፊት ተኮር አስተሳሰብን ማበረታታት፤ ጭፍን ተስፈኝነት ወይም ‹‹አወንታዊ ዜና›› ብቻ እያሉ ባለመንጎድ፤ ለጋዜጠኝነት መርሆዎች ብቻ ታማኝ በመሆን፣ ችግርን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በሂሳዊ ዓይን በመፈተሽ ገንቢ ሂስ ማቅረብ የባይፈርስ ሚዲያ ስለነፃ ሐሳብ ዘገባዎች ቁልፍ መርሆዎች ይሆናሉ።
የሐሳብ ነፃነትን በማረጋገጥ ነጣጣይ ትርክቶችን በመድፈቅና አሰባሳቢ ትርክቶችን በማጉላት ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚያስችሉ የልማት የሰላም እና የዴሞክራታይዜሽን ስራዎች ላይ ባይፈርስ ሚዲያ ገንቢ ሚና ለመጫወት የሚችለው በተመልካቾቹ የላቀ ተሳትፎ እና ድጋፍ መሆኑ አያጠያይቅምና በንግድ ማስታወቂያም ሆነ በክብር አጋርነት ከባይፈርስ ሚዲያ ጋር ለመስራት የምትሹ አካላት በተከታዮቹ አድራሻዎች ብቻ ባይፈርስ ሚዲያን ማግኘት ይቻላል።