Articles and Views

Home         Mission      Coffee House        Radio & TV        Entertainment        Contact         Photo Gallery

እንኳን ለ2005 ዘመን መለወጫ በሰላም አደረሳችሁ!

ሁሉም ሲያልፍ ቀላል ይመስላል።ዛሬ ኢትዮጵያ የምታሰመዘግበዉ ድርብ ዲጂት እድገቷ፤ አለምን ያስደነቀዉ የዉሃ ሃብት ክእሎቷ፤የአፍሪካ የዲሞክራሲ ዋለታነቷ፤ስንቱ ተብሎ ይዘለቃል።ከየት ተነስተን እዚህ እንደደረስን ከዘመን ወደ ዘመን በምንሸጋገርበት ወቅት ማንሳት አስፈላጊ ይመስለኛልና ጀባ ልበላችሁ።

ዓፄ ሃይለሥላሴ በድምሩ 54 ዓመት ኢትዮጵያን ገዝተዋል።በስዉር ዓመጽ ሥልጣን ከተቀዳጁ በሗላ ኢትዮጵያን በሚያስተዳድሩበት ጊዜ የተወለዱ ባለሥልጣኖቻቸዉ ዛሬ በሕይወት የሉም።ደጋፊዎቻቸዉ ግን እስካሁን ኢሕአዴግን ይታገላሉ።ተራማጁ ሃይለስላሴ አልፈዉ አድሃሪዉ ሃይለስላሴ ሲተኩ ግማሽ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባርነት ባልተሻለ የገባር ሥርዓት ዉስጥ ይማቅቅ ነበር። ታዲያ አይካድምና የአፍሪካ ታላቅ ሰዉ ነበሩ (እንደ መለስ)።መልካም ሥራ፣ በደልም ሠርተዉ አልፈዋል።

መልካምም ሆነ መጥፎ ሥራቸዉን የቀበረዉ ደርግ የዛሬ 48 ዓመት በሕዝብ ዓመጽ ታግዞ ሥልጣን ያዘ። ደርግ ሲጀምር የተማሪዉንና የገባሩን ድምጽ በመስማት መሬት ላራሹ አለ፣ የሺዎች ዘመን የፊዩዳል ሥርዓትም ከኢትዮጵያ ለዘልዓለሙ ተነቀለ። በተቃራኒዉ ሕዝባችን በቀይና በነጭ ሽብር ልጆቹ ሲያልቁ፣ሲበተኑ፣ሲሰደዱ አየ።ደርግም መሳሪያዉን ለኢሕአዴግ አስረክቦ ተበተነ።

ኢሕአዴግ በበኩሉ ሥልጣን በቀጥተኛ ዓመጽ ከተረከበ 31 ዓመት ሲሆነዉ የአምባገነን የደርግ ሥርዓትን በመገርሰሱ ሕዝብ ደግፎት ነበር፣ ታዲያ መልሶ እራሱ አምባገነን ሊሆን!

ከዛሬ አንጻር ወደሗላ ሦስቱንም ሥርዓቶች ስመለከታቸዉ ለሁሉም ጥያቄ መልስ ባይኖረኝም፣ መጠኑና ዓይነቱ ይለያይ እነጂ ሁሉም መልካምም ሆነ መጥፎ ሥራ እንደሰሩ ለማንም ግልጽ ይመስለኛል።ዝርዝር ዉስጥ አልገባም።ነገር ግን ኢሕአዴግ መጨረሻ ላይ የሠራዉ ሥራ አሁን ላለንበት የተረጋጋ የሰላም፣የነጻነትና ከፍተኛ የእድገት ጎዳና ታላቅ አስተዋጽኦ ማድረጉ ማንም አሌ ስለማይለዉ በዚሁ ላይ ማትኮር እፈልጋለሁ።

በ2005 መጀመሪያ ላይ አገራችን ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሳ ነበር። በጊዜዉ የነበሩት ጠ/ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በሕመም ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ከፍተኛ ግራ መጋባት በአገሪቱ ተፈጠረ።የሥልጣን መተካካት/ሽግግር ጉዳይ በራሱ በኢሕአዴግ እንኳ አስቸጋሪ ሆነ።የጠ/ሚኒስትሩ በድንገት መሞት ፈረንጆች እንደሚሉት ‘የፓንዶራ ሳጥን’ ከፈተ።የሥልጣን ሽኩቻ ተጀመረ። በኢሕአዴግ መሐል የትኛዉ ወገን ለምን እንደቆመ  ማወቅ አዳገተ።በተለይ የም/ጠ ሚኒስቴሩ አቶ ሃይለማሪያም ደስአለኝ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስቴር ተብሎ መሰየምና ከጥቂት ቀናት በሗላ ተመልሰዉ ም/ጠ ሚኒስቴር መባላቸዉ በኢሕአዴግ ዉሰጥ ያለዉ የሃይል አሰላለፍ ላይ ብዙ አነጋገረ።ተስፋ፤ስጋሰት ፍርሐትም አመነጨ።

የለዉጥ ዕድል ብልጭታ በመታየቱም በአገር ዉስጥም በዉጭም በተቃዋሚዉ ጎራ የተጀመሩ መሰባሰቦች ተጧጧፉ።ዉይይታቸዉም አዲሱን ሁኔታ እንዴት እንቀበለዉ ሆነ።

በአገር ዉስጥ በተለይ ከ1997 የምርጫ ወቅት ወዲህ የመቃወም መብት፣የሚዲያ ነጻነትና እንዲሁም የሌሎች ነጻነቶች መታፈን፣ የኑሮ ዉድነት፣ ተቃዋሚዎች ላይ የሚሰነዘረዉ ግፍ፣ በሐይማኖትና በብሄረሰቦች ጉዳይ የነበረዉ ጣልቃ ገብነትና ፖሊሲዎች፤ወዘተ.የፈጠረዉ የፖለቲካ ዉጥረት አገሪቱ ወዴት ነዉ የምትሄደዉ- የግብጹ ሁኔታ ወይስ የሊቢያና የሲሪያ ሁኔታ ነዉ እጣ ፋንታችን እያለ ሕዝቡ የሚወያይበት ዘመን ሆኖ ነበር።  

ተቃዎሚዉ በመከራ ያካበተዉ ልምድ ነበረዉና አዲሱን ሁኔታ ለየት ባለመልኩ መያዝ እንዳለበት በመረዳት በረጋና ብልሕነት በተዋሃደዉ መንገድ ለዚህ ሥርዓት እሱ ያልተሰጠዉን ዕድል ለዚሕ አዲስ መሪ ለሚመራዉ የኢሕአዴግ መንግስት ለመስጠት ወሰነ።ተከትሎም የታሰሩ የፖለቲካና የሕሊና እስረኞች እንዲፈቱና የአገሪቱ ዉስብስብ ችግሮች በአንድ ወገን ጥረት ብቻ የማይፈቱ በመሆናቸዉ ተሰባስበን የምንወያይበትና ሁሉንም የሚበጅ፣ ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት፣ ሁሉም ወገን የሚገኝበት ስብሰባ ይጠራ ብሎ ሃሳብ አቀረበ።በርግጥ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ከበፊቱ ባልተሻለ አቋም “ያለበለዚያ እንደሊቢያ ትሆናላችሁ” እያሉ ደጋግመዉ የሚያስፈራሩ አልጠፉም ነበር።እንደ ሊቢያ መሆን ለኢትዮጵአ ሕዝብ የሚመረጥ አልነበረም፣ የሕዝባችንን ደም ማፍሰሱ ብቻም አይደለም፣ አገራችን የተወሳሰበ ችግር ያላት አገር በመሆኗ ልትበታተንም የምትችልበት ሁኔታ ነበረ።

“ሰላማዊ አብዮት ፈጽሞ እንዳይካሄድ የሚያደርጉ፣ አመጽ የተሞላበት አብዮትን የማይቀር ያደርጉታል” (ኬነዲ)

በሰላም ለመሸጋገር የሚጥረዉ ብዙዉ የተቃዋሚ ሃይል ለብሔራዊ ዉይይት የተደረገዉ ጥሪ በሁኔታዉ ግራ የተጋባዉን ኢሕአዴግ በትክክለኛዉ አቅጣጫ እንዲሄድ ያበረታታዋል የሚል እምነት ነበረዉ።ኢሕአዴግም እምቢ፤ አሻፈረኝ ማለት ምን እንደሚያስከትል አሳምሮ ያዉቃል። በማወቁም ነበር በብዙ ዘዴዎች ሲከላከለዉ የቆየዉ።ዉጤቱም  ለማንም የማይበጅ መጠፋፋት ዉስጥ ይከተን ነበር።ለዉጥን መከላከል ለረጅም ጊዜ አይቻልምና ምርጫ ያጣ ተቃዋሚ ሕዝቡን ይዞ ባለ በሌለ አቅሙ ከማመጹ በፊት ለዉጥን ማስተናገድ አስፈላጊ ነበር። እዉነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ከስህተቱ የተማረዉ የተቃዋሚ ሃይል ለዉይይት ጥሪ በሚያደርግበት ጊዜ አመጽን እንደማስፈራሪያ ማንሳት አስፈላጊ አይደለም ብሎ ወደጎን በመተዉ፣ በሃገራችን ጉዳይ ላይ ዜጋዊና ሞራላዊ ሃላፊነትን በጋራ ከመወጣት አንጻር ኢሕአዴግን መቅረብ ወሰነ።

ይህ አቀራረብ በርግጥም ፍሬ አፈራ።የ2005 ዘመን መለወጫ አበረታች በሆነ መንገድ ተጀመረ። የፖለቲካና የሕሊና እስረኞችም ተፈቱ። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተቃዋሚ ሃይሎች ግር የዉይይት ፈቃደኝነት አሳዩ፣ ዉይይትም ተጀመረ። ከጊዜ ጋር ጥላቻና ጥርጥር እየቀነሰ መቻቻል እየጠነከረና አንዳንድ የመብት ጥያቄዎች መልስ እያገኙ መጡ። በዉጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን እንደልባቸዉ ያለስጋት ወደሃገር የሚገቡበትና የሚወጡበት ሁኔታ ተፈጠረ። አጫዳፊ የአገሪቱ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ችግሮች ላይ በዉጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን በመተባባር መፍትሔ ለማምጣት የሚያቀርቡት ሃሳብ በቀናነት መታየት ጀመረ። የተቃዋሚዉ ሃይል ተቃዉሞ የሚያስነሳዉ መንግስትን ለመክሰስ ወይም ተጠያቂ ለማድረግ ካለ ፍላጎት ሳይሆን፣ ሰፋ ካለ የሃገርንና የሕዝብን መብት ከማስከበር አንጻር መሆኑን መንግስት ሲቀበል፤ በተቃዋሚዉ ዘንድ ደግሞ ፣ በመንግስት ዘንድ ሁሉ ነገር በሥልጣን ለመቆየት ካለ ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ አለመሆኑንና አገሪቱን ለማሻሻል፣ሕዝቡን ለመጥቀም አሁንም ፍላጎት እንዳለ ሲቀበል፣ ከመፈራራት፣ከመጠላላት ይልቅ የሁሉም ወገን ጥቅም ላይ ዉይይት አድርጎ እንደ ደቡብ አፍሪቃ ሰላምን አዉርዶ ወደ እድገት አንድ ላይ መሄዱ ይበጃል የሚል አመለካከት በሁሉም ዘንድ እያየለ ሄደ። ቀናነት ስር እየሰደደ መፍትሔዉም አገር አቀፍ ዕርቅ ማድረግ መሆኑን መግባባት ላይ ተደረሰ።ተፈጸመም። በዚህም መሰረት የሁሉም ወገን የተወከለበት የምርጫ አስመራጭ ድርጅት ተቋቁሞ ታሪካዊዉ የ2007 ምርጫ ተካሂዶ፣ ሊቢያ ትሆናለች ሲሪያ የተባለችዉ ኢትዮጵያ በሰላም ዴሞክራሲያዊ ሸግግር አድርጋ ይሄዉ ዛሬ የምናየዉን መረጋጋትና እድገት ኢትዮጵያ ልታሰመዘግብ ችላለች።

ኢሕአዴግ በ2005 በወሰደዉ ቀና እርምጃ ከፍተኛ ድጋፍ በማፍራት የ2007 ምርጫዉን ሲያሸንፍ የዛሬ ሦስት አመት ደግሞ ማለትም በ2012 ተቃዋሚዉ የነዶ/ር ቢዘገይ አልቀረም ፓርቲ አሸንፎ እስከአሁን በመምራት ላይ ይገኛል።ዛሬ ኢትዮጵያ ሕዝቧ የረሃብ ማስታወቂያና የአለም መሳለቂያ መሆኗ ተረስቶ፤በአፍሪካ የዴሞክራሲ ዋልታ፤የለዉጥ ሞዴል ሆና፤ ሕዝቧም መሰደድ ቀርቶለት ዛሬ የሌሎች አገሮች ስደተኞችን የምታስተናግድ፤ከራሷ ተርፎ ለሌሎች ምግብና የኢንዱስትሪ ዕቃዎች አቅራቢ አገር ሆናለች።

ጊዜዉ ቢረዝምም መርሳት የሌለብን፣ እዚህ መድረስ የቻልነዉ ኢሕአዴግ በ2005 ያችን አንዲት ግን አስቸጋሪ የብሔራዊ ዕርቅ ስምምነት ለማድረግ በመወሰኑ ነዉ። ይህ ዉሳኔ ሀ ብለዉ በረሃ ሲገቡ የነበራቸዉ የዓላማ እዉነተኝነትን በሗላ ላይ ያከብሩ እንደሆነ የተመሰከረበት፤አዲስ ሁኔታን ለማስተናገድ የቀረ ወኔ እንዳላቸዉ የታየበት፤የኢትዮጵያን ሕዝብ ከማንም ባላነሰ የሚያስቡለትና የባሰ ክፉ ቀን እነዳያይ መስዋዕት የሚሆኑለት መሆኑን ከመቸዉም ጊዜ በበለጠ ያስመሰከሩበት እርምጃ ነበር። በሦስት ስርዓት የተፈጠሩ ሰዎች በሁለቱ ጎራ ፣ማለትም በመንግስትም ሆነ በተቃዋሚ በኩል፤ተከፍለዉ ለአራት አሰርት ዓመታት የተፋለጡበት ጊዜ ያብቃ በማለት የሦስት ስርዓት ሰዎች፣የአንድ ብሩሕ ተስፋ ልጆች እንዲሆኑ የተስማሙበት ዉሳኔ ነበር።

የኢሕአዴግ መስማማት ወሳኝነት የነበረዉ ያህል የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግስትም ወገን ለቆሙት ሆነ በተቃዋሚ ወገን ለቆሙት ይቅር ባይነቱ የበለጠ ወሳኝነት ነበረዉ። ለዚህም ነዉ 2005 በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ዉሰጥ ልዩ ቦታ ያላት። ከ2005 በሗላ የተከተሉት ዘመን መለወጫዎች እንደበፊቶቹ ክረምትን አልፈን የፀሐይ ብርሃንን የምንቀበልበት፤በአደይ አበባና አዲስ ልብስ የምናጌጥበት፤የቀን መቁጠሪያችን አንድ ዓመት የሚጨምርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ነጻነት፣እኩልነትና አንድነት መጎናጸፍ የጀመረበት፤እዉነተኛ ብሩህ ተስፋ ያገኘበት ጊዜ በመሆኑ ነዉ።

እንኳን ለ2015 ዘምን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ! እንደተለመደዉ ይህ አዲስ ዓመት ጥጋብን የምንቆጣጠርበትና የበለጠ እድገት የምናሳይበት ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።

ኢትዮጵያን አምላክ ይባርካት! ኢትዮጵያ ለዘልዓለም ትኑር!

ከልቦና አምላኩ

መስከረም 1 2005
Comments